ባንኮች የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመከላከል ከዚህ ቀደም ሲተገብሩት የነበረውን መደበኛ አሰራር በመቀየር ቫይረሱ በሰዎች የዕለት ተዕለት የገንዘብ እንቅስቃሴ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለመቀነስ እየሰሩ መሆኑን አስታወቁ፡፡
ዳሽን ባንክ እና ሕብረት ባንክ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እና ጥንቃቄ ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ደምበኞች ከብዙ ሰዎች ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት ለመቀነስ በኤቲኢም ሲጠቀሙ ይከፍሉ የነበረው ክፍያ እንዲቀር ማድረጉን ዳሽን ባንክ ገልጿል፡፡ ከውጭ አገር ምርት ለሚያስገቡ ደንበኞች ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ የንግድ ሒደት መስተጓጎልን ለማስቀረት ታስቦ ከዚህ ቀደም ለሰነድ ብድር ወይም ኤልሲ ማራዘሚያ ይከፍሉ የነበረው ኮሚሽን ተነስቶ ነጻ መሆኑን ዳሽን ገልጿል፡፡
በቀጥታ የገንዘብ ክፍያ ወይም ሲኤዲ ከውጭ አገር ምርት ለሚስገቡ ደንበኞቻችን ለጊዜ ማራዘሚያ ይከፈል የነበረው ኮሚሽን በ 50 ፐርሰንት እንዲቀንስ ማድረግም ሌላኛው የባንኩ እርምጃ ነው፡፡ ደንበኞች ከኤቲኤም በየቀኑ የሚያወጡት የወጪ ገንዘብ ገደብ ወደ 10‚000.00 (አስር ሺኅ) ብር ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዳሽን የተበዳሪ ደንበኞች የንግድ እንቅስቃሴያቸው ወረርሽኙ በሚፈጥረው ተጽዕኖ ምክንያት እንደሚቀዛቀዝ በመገመት የብድር ተመላሻቻው የመክፈያ ጊዜ እንዲራዘምላቸው ለሚያቀርቡት ጥያቄ ይከፈል የነበረው ኮሚሽን ተነስቶ ነጻ እንዲሆን አድርጓል፡፡
ሕብረት ባንክ በበኩሉ ደምበኞች ወደ ቅርንጫፎች ለመስተናገድ በሚመጡበት ጊዜ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት አስፈላጊ ጥንቃቄዎች በባንኩ ሠራተኞች እና ደምበኞች መከናወናቸውን የሚከታተል በባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሚመራ ኮሚቴ ተዋቅሮ ግብረ ኃይል መቋቋሙን ገልጿል፡፡
ቅጽ 2 ቁጥር 72 መጋቢት 12 2012



