ኢትዮጵያ ከ3 ዓመታት በኋላ በስንዴ ምርት ራሷን ትችላለች ተባለ

0
439

ኢትዮጵያ ከሦስት ዓመታት በኋላ የስንዴ ፍጆታዋን በአገር ውስጥ በማምረት ራሷን እንደምትችል እና ከውጭ ስንዴ ማስገባት እንደምታቆም የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ኢትዮጵያ ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚያስፈልጋት ስንዴ ከ65 እስከ 70 ሚሊዮን ኩንታል ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት እየተመረተ ያለው ከ50 እስከ 55 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ መሆኑን እና ኢትዮጵያ ካለፉት 50 ዓመታት ጀምሮ ስንዴ ከውጭ ስታስገባ እንደቆየችም ሚኒስቴር መ/ቤቱ ገልጿል።

እስካሁን ድረስ አጠቃላይ የኢትዮጵያ የስንዴ ምርት በደጋው እና በወይናደጋው አካባቢ ተወስኖ የቆየ ሲሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት በዋቢ ሸበሌ፣ በሱማሌ ክልል፣ በአፋር እና አዋሽ ተፋሰስ ባሉ ቆላማ አካባቢዎች የሰርቶ ማሳያ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል። ሙከራ በተሠራባቸው በሁሉም ቦታዎች ማምረት እንደሚቻል በመረጋገጡ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ማምረት ይጀመራል ተብሏል። ለቆላማ አካባቢ የሚሆኑ የስንዴ ዝርያዎች ተባዝተው ለአርሶ አደሩ እንሚሰራጩም ይጠበቃል።

በኢትዮጵያ በስንዴ ምርት የሚለማው መሬት ወደ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሔክታር የሚጠጋ ሲሆን ከዚህም የሚገኘው ምርት 5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ነው፤ የምርት መጠኑም በሔክታር 27 ኩንታል ነው። ይህም አገሪቱን በአፍሪካ በስንዴ ምርት ልማት በሦስተኛ ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ አድርጓታል።

ሆኖም አገሪቱ ለዜጎቿ የዕለት ተዕለት ፍጆታ የሚውል ስንዴን ከውጭ በማስገባት ታቀርባለች። ይህም ከአገሪቱ ዓመታዊ የስንዴ ፍጆታ 25 በመቶ ያህሉን የሚሸፍን ሲሆን፣ በዓመት ስንዴ ከሌሎች አገራት ለመግዛት የምታወጣው ወጪ በአማካኝ 600 ሚሊዮን ዶላር ያህል ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 72 መጋቢት 12 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here