የከፍተኛ ትምህርት ጥራት እና አግባብነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጄነራል የሆኑት አንዱዓለም አድማሴ (ዶ/ር) አሁን ላይ የሚገኙበትን የሥራ ኃላፊነት ከመያዘቸው በፊት ኢትዮ ቴሌኮምን ከ2005 እስከ 2010 ድረስ መርተዋል። እንዲሁም በተቋሙ የኦዲት እና የሰው ሀብት መኮንን በመሆንም አገልግለዋል።
አንዱዓለም የመጀመሪያ እና ኹለተኛ ዲግሪያቸውን በቢዝነስ እንዲሁም በትምህርት አመራር እና በማኔጅመንት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል። ሦስተኛ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ ከፊሊፒንሱ ቡላካን ስቴት ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን አግኝተዋል።
በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያስተማሩት አንዱዓለም፣ በዓለም ዐቀፉ ሥራ አመራር ኢንስቲቲዩት፣ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩንቨርሲቲ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ካስተማሩባቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል ተጠቃሽ ናቸው። ከዚህም ባሻገር ለገቢዎች ሚኒስቴር እና ለጉምሩክ ላሉ መሥሪያ ቤቶች እና የሥራ ኃላፊዎች በአማካሪነት አገልግለዋል። በአማካሪነትም ካገለገሏቸው ተቋማት መካከልም የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩንቨርሲቲ ይገኝበታል።
የአዲስ ማለዳዋ ኪያ አሊ የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ስርዓት ያለበትን ሁኔታ እንዲሁም ተያያዥ ጥያቄዎችን በማንሳት፣ ከአንዱዓለም አድማሴ (ዶ/ር) ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።
እውቅና ያላገኙ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደሆነ እየተነገረ ነው። ይህን ችግር ለመፍታት ምን እያደረጋችሁ ነው?
ከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን የግልና የመንግሥት እያለ አይከፋፍልም። ኹለቱንም እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ነው የምናውቃቸው፣ የምናያቸውም በተመሳሳይ መንገድ ነው። ለዚህ ቃለመጠይቅ እንዲያመቸን ግን ኹለቱን ለያይተን እንመልከት።
አሁን ላይ 238 የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይገኛሉ። ለእነዚህም ኤጀንሲያችን እውቅና የመስጠትና ያንንም የማደስ ሥልጣን አለው። እነዚህ ተቋማት እውቅና ካገኙ በኋላ፣ ሕጉን በማክበር መሥራት አለባቸው፣ ይጠበቅባቸዋልም።
ለምሳሌ አንድ ተቋም ሽሮ ሜዳ አካባቢ እንዲያስተምር ፈቃድ ካገኘ፣ አዲስ ከተማ ላይ አገልግሎት መስጠት አይችልም። ይህ እውቅና ከመሰጠቱ በፊት ግን፣ ኤጀንሲው የሚያያቸው ነገሮች አሉ። አንደኛው የካምፓሱ አቅም ነው። ይህም ቤተመጻሕፍት፣ ላብራቶሪ፣ እንዲሁም የመምህራን ልምድን የሚመለከት ነው። ከዛም የማስተማሪያ ዘዴያቸውም ይታያል።
ስለዚህ የኤጀንሲያችን ዋና ኃላፊነት አግባብነት እና የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥና ተቋማት የሚፈለግባቸውን መስፈርት የሚያሟሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ ነው።
አግባብነት ስንል ኢኮኖሚው ተመራቂ ተማሪዎችን ከሚቀበልበት አቅም አንጻር ነው። በተጓዳኝ ተመራቂ የሆኑ ሥራ አጥ እንዳይኖሩ ከማድረግ አንጻር የሚታይ ነው። ይህም ማለት የኢኮኖሚውን ፍላጎት ያጤናል ነው። ለምሳሌ የ70/30 የትምህርት ፖሊሲን ስንመለከት፣ ችግር ፈጥሯል። አሁን ላይ ብዙ ሥራ የሌላቸው መሃንዲሶችና ዶክተሮች አሉ።
በንጽጽር ስንመለከት፣ በኢትዮጵያ ሥራ የሌላቸው የሕክምና ምሩቆች አሉ፣ ነገር ግን የሕክምና ባለሞያዎች እጥረት አለ። በተመሳሳይ አገሪቱ መሃንዲሶችን ትፈልጋለች። ነገር ግን ሥራ የሌላቸው በርካታ በምሕንድስና የተመረቁ ተማሪዎች አሉ።
ኢትዮጵያ ብረትን እንኳ በአግባቡ እያመረተች አይደለም። ይልቁንም በከፍተኛ ወጪ ከውጪ እያስገባች ነው። ስለዚህ የግንባታ ግብዓት የሆነውን ብረት የማምረት አቅምን ሳያጠናክሩ፣ ብዙ መሐንዲሶችን ማስመረቅ ችግር ነው የሚፈጥረው። በተመሳሳይ በቂ መሠረተ ልማት ሳይሟላና ሆስፒታሎች ሳይገነቡ ብዙ የሕክምና ባለሞያዎችን ማፍራት ምንም ዋጋ የለውም።
እነዚህን የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከብዛታቸው አንጻር ኤጀንሲው ባለበት አሁናዊ መዋቅርና አሠራር ለመከታተል ከባድ ነው። እያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ ዐስር ካምፓስና የትምህርት ክፍል አለው ብንል እንኳ፣ በድምሩ ሃያ ሺሕ አሉ ማለት ነው። ይህን ያህል ብዛት ያለውን በተለመደው አሠራር መከታተል ደግሞ ከባድ ነው።
ስርዓቱ ዘመናዊ ካልተደረገ በቀር፣ ያሉትን ሁሉ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አሁን ኤጀንሲው ባለው አቅም ለመከታተል ይከብደዋል። ይህም ችግር የተለያዩ ጥፋቶችን አስከትሏል። የመጀመሪውን ስናይ በኤጀንሲው የተቀመጠውን የማለፊያ ነጥብ ችላ በማለት፣ የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ወይም ሲኦሲ እንኳ ሳይጠይቁ፣ የ10ኛ ክፍል ተማሪን ለዲግሪ መርሃ ግብር የሚቀበሉ አሉ።
ሌላው ዝቅተኛ ነጥብ ያመጡ ተማሪዎችን አይጥሉም። ተማሪዎችን እንደ ገቢ ምንጭ ብቻ ነው የሚቆጥሩት። የመምህራን ማኅደር እና የቤተ ሙከራ እንዲሁም የቤተ መጻሕፍት ግብዓት ጉዳይም በዚህ ላይ የሚደመር ችግር ነው።
ሌላው 50 የሚደርሱ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አሉ። በእነዚህም ከግሎቹ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ችግሮችን እናገኛለን። በክልል የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ በአዲስ አበባ በሚገኙ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ቅርንጫፍ ይከፍታሉ። ለዚህ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል።
በዳግማዊ ምኒልክ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ኮምፕዩተር ሳይንስ ይማራሉ። እንዴት ነው በቂ ቤተ ሙከራና ቤተ መጻሕፍት በሌለበት ትምህርት ቤት፣ ከቴክኖሎጂ ጋር የተገናኙ ትምህርቶችን መስጠት የሚቻለው? በአንጻሩ በመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመደቡ መደበኛ ተማሪዎች፣ተገቢውን ትምህርት አያገኙም። ምክንያቱም መምህራን በአግባቡና በሰዓቱ አይገኙላቸውም። መምህራኑ በክልል በመደበኛነት በሚሠሩበት የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያስተምራሉ፣ እንዲሁም በተመሳሳይ አዲስ አበባ እየተመላለሱም ያስተምራሉ።
ስለዚህ በግልም ሆነ በመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለውን ሁኔታ የተሻለ ለማድረግ ወሳኝ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው። ሁሉም ለዚህ ለውጥ ዝግጁ ከሆነ፣ አሁን ያለውን ሁኔታ መቀየር ይቻላል። ይህን የመለወጥ ተግባርም በመንግሥት ላይ ብቻ መተው የለበትም። ማኅበረሰቡም ኃላፊነቱን ተጋርቶ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ነገ ራሳቸው አልያም ልጆቻቸው ገብተው የሚማሩባቸው እንደሆኑ በማሰብ፣ ሊገቡበት የሚፈልጉትና ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ሚናቸውን መጫወት አለባቸው።
አንዳንዴ በመንግሥት የሚተዳደሩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተለያዩ ትምህርቶችን ለመስጠት በሚል ከግሎች ጋር በመሻረክ ፋይናንስ ሕግን ሲጥሱም ታይቷል። ይህ ወንጀል ነው። በምዝገባ፣ በወርሃዊ ክፍያ ወዘተ ሥም የሚያስከፍሉት ገንዘብ ወደ ግለሰቦች ኪስ የሚገባ ነው። በዛም ላይ መደበኛ ተማሪዎቻቸውን ትተው አዲስ አበባ ይመጣሉ።
ይህ በመደበኛው የመማር ማስተማር ሂደት ላይ እንዲሁም በትምህርት ጥራትም ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ይፈጥራል። በዚህም ምክንያት በፊት በኢትዮጵያ የተመረቁ ተማሪዎች ባህር ማዶ ሄደው ሥራ ያገኙ ነበር። አሁን ግን ያ ቀርቶ፣ በውጪ አገራት የሚገኙ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ትምህርታቸውን ተከታትለው የጨረሱ ምሩቃንን ለመቅጠር ፈቃደኛ አልሆኑም።
ለዚህ ችግር ታድያ መፍትሔው ምንድን ነው?
ሕዝብ በፈቃዱ ተጎጂ መሆን የለበትም። አንድ ሰው አንድ ተቋም ሄዶ ለትምህርት ከመመዝገቡ በፊት ማጣራት አለበት። በተለይም ተቋሙ እውቅና ያለው መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። መገናኛ ብዙኀንም በዚህ ላይ ግንዛቤ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል። አሁን ላይ ለፖሊስም ጭምር ኃላፊነት እየሰጠን ነው ያለው።
ሕገወጥ የሆኑ ተቋማት ሕጋዊ እንዲሆኑ እያበረታታን ነው። አንዳንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አግባብ የሆነ ፈቃድ እንኳ የላቸውም። የአስመጪና ላኪ ፈቃድ ነው የያዙት። ምንም እንኳ ሙስና በሁሉም ዘርፍ ችግር እንደሆነ የሚታወቅ ቢሆንም፣ በትምህርት ጉዳይ ላይ ሲሆን፣ ትውልድና አገር ከማጥፋት እኩል የሚቆጠር መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል።
ስለዚህ በትምህትር ዘርፍ ላይ የሚገኙ ባለሀብቶች በኃላፊነትና በጥንቃቄ ሊንቀሳቀሱ ይገባል። ከዛም ባለፈ መንግሥት መዋቅሩን መቀየር አለበት። በዓለም ላይ የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ እኛ አገር ያለውን ዓይነት አደረጃጀት የትም የለውም።
የእኛ ኤጀንሲ ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተጠሪ ነው። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሃምሳ የሚሆኑትን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሲያስተዳድር፣ የእኛ ኤጀንሲ ደግሞ ሪፖርቶችን ለሚኒስትሩ ከማቅረቡ በተጓዳኝ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱን የመቆጣጠርና በዛም ላይ ሪፖርቶችን አሰናድቶ የማቅረብ ኃላፊነት አለበት።
ይህ የሚጻረር ከመሆኑ በተጨማሪ የኤጀንሲውን ነጻነት የሚጋፋ ነው። ሪፖርት የምናቀርበው ለምንቆጣጠረው ተቋም ነው። ይህንን ለመንግሥት አሳውቀን ምላሽ እየጠበቅን ነው። ኤጀንሲው ለፓርላማ አልያም ካልሆነ ደግሞ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው ሪፖርት ማቅረብ ያለበት፣ ይህ ዓለማቀፍ አሠራርም ነው።
ሌላው ነጥብ፣ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከእኛ ፈቃድ ውጪ አዳዲስ ትምህርት ክፍሎችን ወይም የትምህርት ዘርፎችን ይከፍታሉ። የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ኦዲት የማድረግ ሥልጣን አለን። በፕሮፌሰሮች ይሁንታ አንድ አዲስ ትምህርት ክፍል ይከፍታሉ። በዛ የትምህርት ዘፍር ተማሪዎች ከተመረቁ በኋላ ግን ሥራ ለማግኘት ይቸገራሉ። ምክንያቱም አግባብነት ላይ መጀመሪያ ጥናት አለመደረጉ ነው።
በአርባ ምንጭ እንዲህ ያለ ነገር አጋጥሞ ነበር። በዛ ላይ ቀጣሪዎች የተመራቂ ተማሪዎችን የትምህርት መረጃዎችና ማኅደር አጥብቀው ነው የሚመረምሩት። አንዳንድ ክልሎች ላይ ያለውን ብንመለከት፣ ሳጥኖቻቸው በኤጀንሲው እውቅና ካላገኘ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የተመረቁ ተማሪዎች መረጃ ሞልተውባቸው ይገኛሉ።
እነዚህን እውቅና የሌላቸውን የትምህርት ማስረጃዎች ሰብስበን አገልግሎት እንዳይሰጥባቸው ብናደረግ፣ ሙሉ ለሙሉ የሚዘጉ የመንግሥት ቢሮዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ዘመናዊ እና ቴክኖሎጂን የሚጠቀም አሠራር እንዲህ ያሉ ችግሮችን አስቀድሞም ለመከላከል ያስችላል።
የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ ብቁ ነው ብለው ያምናሉ?
ብቁ ነው ለማለት ከባድ ነው። ለምሳሌ በመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ እውቅና ያልተሰጠው ትምህርት ክፍልን የማዘጋት ኃይል የለውም፣ መፍትሔው ያ እንደሆነ ቢታወቅም። እንደዛ ያለው ሥልጣን በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ብቻ ነው ያለን።
ኤጀንሲውን ብቁ ነው ለማለት መጀመሪያ በኃላፊነቱ ልክ፣ የሚጠበቅበትን ለመወጣት የሚያስችል ኃይልና አቅም ሊኖረው ይገባል። ሌላው በክልል ደረጃ ቢሮዎችና አደረጃጀቶች ሊኖሩት ያስፈልጋል። በተጨማሪም ያለው የሰው ኃይል በቂና ብቁ አይደለም። ከሌላው መስክና ዘርፍ የተረፈው እንጂ ዋናው ክሬም አይደለም ለኤጀንሲው የሚደርሰው። ይህም በጣም የሚያሳዝን ነው።
ታድያ በኤጀንሲው የሰው ኃይል ብቃትን ከፍ ለማድረግ ምን እየተሠራ ነው?
ዘመናዊና ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ ስርዓት ለመተግበር በሂዳት ላይ ነን። ላለፉት 11 ወራትም ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በጋራ ስንሠራበት ቆይተናል። ከኹለተኛ ዲግሪ በላይ ያላቸው 40 አዳዲስ ሠራተኞችንም ቀጥረናል። በክልል ቢሮዎችን የመክፈት ሐሳብ ስላለንም መንግሥት የኤጀንሲውን መዋቅርና አደረጃጀት እንዲቀይር ጠይቀናል።
የሠራተኞቻችንን አቅም ለማሳደግም፣ ከአማካሪዎች ጋር በመምከር እንዲሁም ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት በመሥራት፣ ሥልጠና የሚሰጥበትን መንገድ በየጊዜው እያመጫጨን፣ ሥልጠና እንዲሰጥም እያደረግን ነው።
አሁን በተግባር ላይ ያለውና ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለመክፈት የሚጠየቀው መስፈርት ነባራዊውን/አሁናዊ ሁኔታ ያገናዘበ እንዲሁም የወደፊቱንም የሚያመዛዝን ነው ማለት ይቻላል?
ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለመክፈት የሚጠየቀው መስፈርት የተዘጋጀና ነባራዊ ሁኔታንም የሚያገናዝብ ነው። ነገር ግን የተሟላ ነው ማለት አንችልም። አሁን እየሠራንበት ካለው ነገርም አንዱ ይህ ነው። ኦንላይን እንዲሁም የሦስተኛ ዲግሪ መርሃ ግብርን እንዲሁም መሰል የትምህርት አሰጣጥን የሚያካትት መስፈርት ማውጣት ላይ እየሠራን ነው።
ከግል ተቋማት ጋር በሽክርና የሚሠሩ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሕጋዊ ናቸው?
ሕጋዊ ናቸው። የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት አዋጅ አለ። ትግበራውን የመቆጣጠር ኃላፊነትም የፋይናንስ ሚኒስቴር ነው። አጋርነት ይሳካል አይሳካም በሚለው ላይ ጥናት ከተካሄደ በኋላ የተወሰነ ሂደቶችን እንዲያልፍ ይጠበቃል። አልፎም ጨረታ ተከፍቶ አሸናፊ የሚሆን የግል ተቋም ለቦርዱ ይቀርባል። ይህንን ሁሉ አልፎ ነው የሚጸድቀው።
ነገር ግን አንድም እንኳ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በዚህ ሂደት አላለፈም። ይህም ሕግን መጣስ ነው። እንዲህ ያሉ አሠራሮችም ሕገ ወጥ ናቸው። በእርግጥ የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት ጠቃሚ ነው። ነገር ግን በትክክለኛው የሕግ ሂደት ውስጥ ማለፍ አለበት።
አስቀድሞ እንደጠቀሱት፣ አሠራራችሁን ስታዘምኑ እውቅና ካላቸው ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የወጡ ምሩቃን ለማቆየት ያስችላችኋል። የሌሎቹ በተለይም እውቅና በሌላው አጋርነት መሠረት የተመረቁት እጣ ምንድን ነው የሚሆነው?
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት ትግበራን በሚመለከት አዳዲስ መመሪያ፣ ሕግና ደንብ እያዘጋጀ ነው። ስለዚህ አጋርነቱ ይቀጥላል። እውቅና ከሌላቸው ተቋማት የወጡ ምሩቃን ነገር ግን ለእኛም ራስ ምታት ሆኖብናል። ችግሩ በአጋርነት ስምምነት መሠረት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከተመረቁት ጋር ብቻ የሚያያዝ አይደለም።
ውጤታቸው ማለፊያ ነጥብ ጋር ያልደረሰ ነገር ግን ዲግሪና ማስተርስ ዲግሪ ይዘው በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ተቀጥረው በሥራ ላይ የሚገኙ ሰዎች አሉ። አንዳንዶቹ የሥራ እድገት ሳይቀር አግኝተዋል። እንዲህ ያሉ ኹነቶችን ለመንግሥት አካላት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ጭምር የምናቀርብና በሚሰጠን ውሳኔና ምክረ ሐሳብ መሠረት የምንቀጥል ይሆናል።
ሌሎች አገራት ተመሳሳይ ጉዳዮችን እንዴት እንዳስተናገዱም እያጠናን ነው። ጉዳዩ በጥንቃቄ ነው መያዝ ያለበት። በአንጻሩ አሁኑኑ ወደ ተግባር ከገባን፣ አንዳንድ ክልሎች ሥራቸውን ሊያቆሙ ይችላሉ። በዚህ አግባብ ያልሆነ ድርጊት ላይ የተሰማሩትን ለመክሰስና ለሕግ ለማቅረብም አቅደናል፣ ግን በቂ ፍርድ ቤትና ማረሚያ ቤት አይኖርም።
ምክንያቱም በዚህ ላይ ተሳታፊ ያልሆነ አካ ማግኘት ከባድ ነው። ምንአልባት ከዚህ ጉዳይ ነጻ ሊሆኑ የሚችሉት በቅርቡ የተቋቋሙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብቻ ናቸው ሊሆኑ የሚችሉት።
በተያያዘ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምዝገባ ስርዓታቸውን በኹለት ከፍለውታል። አንደኛው ለሁሉም ክፍት የሆነው ሲሆን እኛም ለማጣራት ስንጠጋ በግልጽ የሚያሳዩንና ንጹህ የክፍያ ስርዓት የሚታይበት ነው። በሌላኛውና ግልጽ በማያደርጉት ምዝገባ ደግሞ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለመግባት ነጥብ የማያሟሉ ተማሪዎች የሚገኙበት ነው።
ባለፈው ጊዜ ይፈጸም የነበረው የሚያሳስበን ቢሆንም፣ አሁን ላይ ግን እንዲህ ያለ አሠራር ብናገኝ፣ የተገኘበትን ተቋም በፍጥነት የምንዘጋ ይሆናል።
እርምጃዎችን በመውሰድ ወደፊት ሊደርሱ የሚሉ ጥፋቶችን መከላከል ይቻላል። ከባዱ ነገር ያለፈ ስህተትን መቆጣጠር የሚቻልበንትን ዘዴ ማወቅ ነው። ባለፉት በርካታ ዓመታት የነበሩ ጥፋትና ስህተቶችን በዚህ በአጭር ጊዜ ማረም ከባድ የቤት ሥራ ነው።
ለምሳሌ በጋምቤላ 12 ኮሌጆች ይገኛሉ። ግን አንዳቸውም እውቅና የላቸውም። የክልሉ ካቢኔ አባላት እነዛ ኮሌጆች ውስጥ ተምረው የተመረቁ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ በጋምቤላ ብቻ የሆነ አይደለም፤ በሌሎች ክልሎች ያለውም ተመሳሳይ ነገር ነው።
መንግሥት ለነዚህ ሁሉ ችግሮች ተጠየቂ አይደለም?
አዎን! ለደረሱት ጉዳቶች በሙሉ መንግሥት ተጠያቂ ነው። ማኅበረሰቡ ለመንግሥት ግብር እንደሚከፍለው አንድም በምላሹ ከመንግሥት ጥበቃን ስለሚሻ ነው። መንግሥት በበኩሉ ቢያንስ ግንዛቤ በመፍጠር የአደጋ ስጋቱን ሊቀንስ ይችላል። በዛ ላይ ኃፊነቱን በአግባቡ ማውረድ ይጠበቅበት ነበር።
እንደምናየው የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ፕሬዘደንት የሆኑ፣ ነገር ግን በንግድ ሥራዎች ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦች አሉ። ይህ እንዴት ሊሆን እንደሚችል አላውቅም። የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ጥራት እና አግባብነት ኤጀንሲም ራሱ ተጠያቂ ነው።
እንዲሁም ደካማ በሆነው የትምህርት ፖሊሲ ምክንያት የወጡ፣ ሙያውን የማይመጥኑ ዶክተሮች እና ነርሶችም አሉ። ይህ ደግሞ በጣም አደገኛ የሆነ ነገር ነው። የትምህርትን ጥራት ጥያቄ ውስጥ መክተት አገርን ሊያፈራርስ የሚችል ተግባር ነው። በዚህ ላይ ሙስና ሲታከል ደግሞ፣ ችግሩን የሚያባበስ ድርጊት ነው።
እኛ እንደውም በሙስና ውስጥ ተሳትፊ ሆነው የተገኙ በእኛ መሥሪያ ቤት ይሠሩ የነበሩ የኮሌጅ ባለቤት የሆኑ ሰዎችን ሳይቀር ከሥራ አባረናል። መገመት እንደሚቻለው፣ በከፍተኛ ትምህርተ ተቋም ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ እየሠሩ፣ የራሳቸውን ኮሌጅ በጥራትና አግባብነት መጉደልና ደካማነት ምክንያት ሊዘጉት አይችሉም።
በአብዛኛው የኦዲት ዘዴው ትኩረት የሚያደርገው ከገንዘብ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ነው። ሆኖም በሰው ሃበት እና በቤተ ሙከራ እቃዎች በተለይ ከሕክመና ጋር በተያያዙ የትምህርት ክፍሎች ላይ ይስተዋላል። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ምን አቅዳችኋል?
ሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የግልም ሆኑ የመንግሥት፣ በየአምስት ዓመቱ ኦዲት ይደረጋሉ። የኢዶት ዘገባ ውጤቱም ታትሞ በመጽሐፍ ይቀርባል። ይህ የኦዲት ሂደት ቢያንስ 10 መስፈርቶችን ያካተተ ነው።
በሁሉም የመንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የትምህርት ጥራትን የሚከታተሉ ዳይሬክቶሬቶች አሉ። በግሉ ዘርፍ ግን እነዚህን ዳይሬክቶሬቶች በቋሚነት ማቋቋም ላይ ገባ ወጣ ማለት ይስተዋላል። ስለዚህ የኦዲት ሥራውን በሚገባና በስርዓት እናከናውናለን።
ከፍተኛ ትምህርት ጥራት እና አግባብነት ኤጀንሲ የኦዲቱን ውጤት መሰረት ባደረገ መልኩ እርምጃዎችን እስካልወሰደ ድረስ ግን፣ ይህ አሠራር ፍሬያማ ነው ለማለት አልችልም።
ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በ2.75 እና ከዛ በላይ በሆነ ነጥብ የሚመረቁ ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አስተማሪዎች መሆን እንደሚችሉ ይታወቃል።
ይሁን እንጂ እነዚሁ አስተማሪዎች የትምህርት ጥራት ችግር ተጠቂዎች ናቸው። እንዴትስ ጥራት ያለው ትምህርት መስጠት ይችላሉ ብለው ያስባሉ? ይህን ተያያዥነት ያለውን ችግር ለመፍታት ምን ታስቧል?
ስለሚያስተምሩት ትምህርት በቂ እውቀት የሌላቸው አስተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል። ዐስር ሺሕ በሚሆኑ እና በ3.75 የመመረቂያ ነጥብ በጨረሱ የኹለተኛ ደረጃ መምህራን ላይ ጥናት ተካሒዶ ነበር። እነዚህ መምህራንም የሚያስተምሩትን የትምህርት ዓይነት እንዲፈተኑ ተደርጎ ነበር።
ለምሳሌ የፊዚክስ መምህራን የሚያስተምሩትን ትምህርት ተፈትነው ውጤታቸው እጅግ አስደንጋጭ ነበር የሆነው። 0.5 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ማምጣት የቻሉት።
ችግሩ በትምህርት ክፍል ኃላፊዎችም ላይ ይስተዋላል። ይህም ደግሞ በሙሉ ስርዓቱ ላይ ችግር እንዳለ ያሳያል፤ ይህን ችግር ለመፍታት ታዲያ የጠራ ፍኖተ ካርታ አላችሁ ወይም አዘጋጅታችሁ ይሆን?
ረጅም ዓመታትን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያስተማሩ ፕሮፌሰሮችን ማግኘት ይቻላል። ነገር ግን ጥናታዊ ጽሑፎችን ከሠሩ እና ካሳተሙ ረጅም ጊዜያት ተቆጥረዋል። በሌሎች አገራት ግን በየኹለት ዓመታት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ጥናታዊ ጽሑፎችን መሥራትና ማሳተም ግዴታቸው ነው። ካልሆነ ግን የሚሠሩበትን ተቋም ሊለቁ ግዴታ ይሆንባቸዋል።
ሌላው አሳዛኙ ጉዳይ በአገራችን መምህራን ከአንድ በላይ የትምህርት ዓይነቶችን ደርበው ማስተማራቸው ነው። ይህን ችግር ለመቅረፍ የመምህራንን የግል ማኅደር በኮምፕዩተር በመመዝገብ እየሠራንበት ያለው ጉዳይ ነው።
ከዚህ ባለፈም የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ቁጥጥር በሚያደርግበት ወቅት፣ የትምህርት ማስረጃዎቻቸውን ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚያከራዩ ባለሙያዎች መታዘብ ተችሏል። ይህን ለመቆጣጠር ጠንካራ የባለሙያዎች ማኅበር መገንባት ያስፈልጋል።
እንዲህ ዓይነት ማኅበራት ጠንካራ መምህራንን በየሚያስተምሩበት ዘርፍ አወዳድሮ በመሸለምና እውቅና በመስጠት ብቃት ያላቸው ተለይተው እንዲወጡ ያደርጋሉ። መምህራንን በሠሩት ሥራ መዝኖ የሚሸልም ማኅበር ቢኖር ኖሮ፣ እስከ አሁን የሚታዩት ችግሮች ይቀንሱ ነበር። ነገር ግን ችግሩን ጨርሶ ከማጥፋታችን በፊት፣ አንድ ትውልድ ልንሰዋ ግድ ሊለን ይችላል።
ጠቅላላ ትውልዱን መስዋዕት ሳያስፈልግ፣ ችግሩን በራሱ መቅረፍ አይቻልም?
ችግሩን መቅረፍና ትውልዱንም መቀየር ይቻላል፤ ነገር ግን እጅግ ውድ ነው።
ስለዚህ የዚህ ትውልድ ዕጣ ፋንታ ምንድነው፤ በኢትዮጵያ ካለው ሕዝብ ቁጥር ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው ወጣቱ ነውና?
አሁን ባለው ትውልድ ላይ መሥራት ይቻላል። ነገር ግን በሚቀጥለው እና በአዲሱ ትውልድ ላይ ከአምስት እጥፍ በላይ ኃይል እና ወጪ ይጠበቅብናል ማለት ነው። የትውልዱን እውቀት በአቅም ግንባታ ልምምዶች ማጎልበት ይቻላል። ነገር ግን ልምምዶች አጭር ጊዜ ችግር መፍቻዎች እንጂ የረጅም ጊዜ አይሆኑም። ለረጅም ጊዜ ለውጥና ልማት ደግሞ ፖሊሲ እና ተቋማት ያስፈልጉናል።
ፖሊሲ ለማውጣትና ተቋማትን መገንባት የማን ኃላፊነት ነው ብለው ያስባሉ?
ከኹሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ሊሠራ የሚችል ነው። ይህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲንም ያካተተ መሆን ይኖርበታል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የቆይታ ጊዜ በአንድ ዓመት ማራዘም ተገቢ ነው ብለው ያስባሉ? ከሆነስ እንዴት?
በጣም ጠቃሚ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ አራት ዓመታት የነበረውን ወደ ሦስት ማሳጠሩ ትክክል አልነበረም። አለመግባባቶች በትምህርት ዓይነቶች አሉ። ከእነዚህም መካከል የታሪክ ትምህርት አንደኛው ነው። ይሁን እንጂ በቅርበት በመወያየት መፍታትና መግባባት ላይ ልንደርስ የምንችልበት ነው።
የታሪክ ትምህርትን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከማተማር በፊት፣ በታሪካችን ላይ መግባባቱ አይቀድምም ነበር?
በታሪካችን ላይ ሁላችንም የምንስማማባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ። ችግሩ ግን የፖለቲካ አመራሮች አንድ የተወሰነ ነገር መዝዘው በማውጣት ሕዝብን ለመቀስቀስ ስለሚጠቀሙበት ነው። ችግሩም እሱ ነው። ነገር ግን በርካታ አስደሳችና የጋራ ታሪኮች ስላሉን እነዛን ማስተማር እንችላለን።
ታሪክ እውነታ ነው። መልካም ሆነ መጥፎ ታሪክ መነገር ይኖርበታል። ካልሆነ ግን መልካሙን ብቻ ማስተማር ወገንተኝነትን አይፈጥርም?
የኹለቱንም ወገን ታሪኮች የመዘገቡ መጽሐፍት አሉ። እነሱም እንደ ማጣቀሻ መጽሐፍት መጠቀም ይቻላል። ነገር ግን ታሪክን በስርዓተ ትምህርት ውስጥ ሲካተት የማኅበረሰቡን አንድነት በሚያጠናክሩ ነገሮች ላይ ማተኮር ይኖርበታል። ቀሪው ከማጣቀሻ መጽሐፍት ውስጥ ማግኘት ይቻላል።
ዋነኛው የትምህርት ጥራቱ ችግር ምንጩ ምንድነው ይላሉ?
የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ብንመጣ ዋነኛው ችግር በዋና ጉዳያቸው ላይ አለማተኮራቸው ነው። በግንባታዎች እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ነው የሚያተኩሩት። በሌላ በኩል ደግሞ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትርፋቸውን እንዴት አድርገው ማሳደግ እንደሚችሉና ወጪያቸውን እንዴት መቀነስ እንዳለባቸው ለማሰብ ነው ቅድሚያ የሚሰጡት። ኤፍ ኤክ የተሰኘውና ተማሪዎች ዳግም ፈተና እንዲወስዱ የሚያደርገው የነጥብ አሰጣጥ ስርዓትም ጥራቱ ላይ የራሱ አሉታዊ ተጽእኖ አለው። እናም በጠቅላላው የትምህርት ጥራቱ ጉዳይ ከተቋማት አፈጻጸም ጋር የሚያያዝ ነው።
ቅጽ 2 ቁጥር 72 መጋቢት 12 2012