ወቅታዊው የዓለም አጀንዳ

0
935

ኮቪድ19 የተሰኘው የኮሮና ቫይረስ ዓለምን እያሸበረ ይገኛል። ቻይና አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች መመዝገብ ማቆሟንና በቫይረሱ የመያዝ ሁኔታ እንደቆመ በመግለጽ፣ ወደ መደበኛው ሕይወት ለመግባት እየተንደረደረች ትገኛለች። በአንጻሩ እንደ ጣልያን ያሉ አገራት ደግሞ በቫይረሱ የተያዙ ዜጎቿ ቁጥር ከእለት እለት እየጨመረ በሞት መጠንም ከቻይና በልጣ ተቀምጣለች። የቫይረሱን መሰራጨት ተከትሎ በዓለም ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ አለመረጋጋቶች ሲፈጠሩ፣ ፖለቲካው ደግሞ በአንጻሩ እረፍት ያገኘ ይመስላል። አገራትም ዜጎች እጃቸውን ደጋግመውና በጥንቃቄ እንዲታጠቡ ሲሉ ደጋግመው እያሳሰቡ ይገኛሉ።

የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ፣ ኮቪድ 19 በፈጠረው ተጽእኖ፣ ቀድሞ ዓለማችን ስላስተናገደቻቸው ወረርሽኝኖችና ያደረሱት ጥፋት እንዲሁም ለወደፊቱ ምን መደረግ አለበት የሚለውን ጉዳይ የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጋዋለች።

‹‹ያለው ሁኔታ ያስፈራል። ሬድዮም ቲቪም፣ ሁሉም የሚያወራው ስለበሽታው ነው። ለመጠንቀቅና ቤት ለመቆየት ብፈልግም፣ ከቤት አለመውጣት አልችልም፤ ኑሮዬ አይፈቅድልኝም›› ስትል ግራ በመጋባት ስሜት ውስጥ ሆና ነው። ‹‹ወጣቶች ላይ ብዙ ጉዳት እንደማያመጣና በተለይ የሚያጠቃው እድሜያቸው ገፋ ያለውን እንደሆነ ይነገራል። ስለዚህ ቢይዘኝም ብዙ ላይቆይብኝ ይችላል ብዬ አስባለሁ።›› ስትልም ስሜቷን ታስረዳለች።

ሥሟን መጥቀስ ያልፈለገችውና ለአዲስ ማለዳ አስተያየቷን የሰጠችው ይህቺ ሴት፣ በአዲስ አበባ ከሚገኙ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች በአንዱ ተቀጥራ ትሠራለች። በሰዓታት ልዩነት ከወትሮው በተለየ እጃቸውን ከመታጠባቸው ውጪ ከጓደኞቿ ጋር የተለመደው አኗኗራቸው እንደቀጠለ ነው የምትናገረው።

‹‹ፍርሃቱ ሁላችንም ጋር አለ። ግን ያው ፈጣሪ ይጠብቀናል መቼስ!›› ስትልም ያለውን ሁኔታና እምነቷን ታረዳለች። ነገር ግን ጣልያንና ሌሎች አገራት በሚሰማው ልክ በኢትዮጵያም የሚከሰት ከሆነ ከቫይረሱ አመልጣለሁ የሚል ግምት የላትም።

‹‹በአንበሳ አውቶብስ ነው የምጠቀመው። እንደ ሁልጊዜው ባስ ሞልቶ ነው እኛ ሰፈር የሚደርሰው። ወደ መሥሪያ ቤት ስሄድ በተጨናነቀ ባስ ነው። ለእጅ ማጽጃ አልኮል ይሰጣሉ እየተባለ ቢነገርና በቲቪ ሲሰጡ ቢታይም፣ እኔ በአካል ሲሰጡ አይቼ አላውቅም። እናም በሽታው ጨክኖ ከተስፋፋ የማመልጥ አይመስለኝም።›› ፍርሀቷን አልደበቀችም። ከራሷም በላይ በየአስራ አምስት ቀኑ የምትጠይቃቸውን በእድሜ የገፉ እናቷን ለመጨረሻ ጊዜ ከሳምንት በፊት እንደጠየቀቻቸውና፣ ከዚህ በኋላ ግን ወደእርሳቸው ከመሄድ መታቀቧን ገልጻለች። ከራሷ በላይ ለእናቷ እንደተጨነቀች ለአዲስ ማለዳ ነግራታለች።

ኮቪድ-19 የተባለው የኮሮና ቫይረስ ዓለምን ማስጨነቅ ከጀመረ ኹለት ሳምንት አልፎታል። ከቻይና ዉሀን ግዛት የተነሳው ይህ ቫይረስ፣ አሁን በዓለም አገራት ሁሉ ቤተኛ ሆኗል።

ይህንን ተከትሎ ዓለም አቀፍ ጉዞዎችና ክዋኔዎች ከወትሮው ታጉለዋል። የሰማይ ላይ በራሪ አውሮፕላኖች ቀንሰው ሰማዩን ጭር አድርገውታል፣ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፣ የጉብኚ መዳረሻዎች የሚጎበኛቸው ለዐይን ጎድሏል።

ከምንም በላይ ማኅበራዊ መስተጋብሮች በማኅበራዊ ፈቀቅታ (Social Distancing) ምክንያት እንዲሁም በፍርሃት ሰበብ ተቀዛቅዘዋል። መጨባበጥን የለመዱ ልማዳቸውን ለማስቀረት በብዙ ቢቸገሩም፣ መገናኛ ብዙኀን፣ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎችና የጤና ባለሞያዎችን ‹አትጨባበጡ…አንዳችሁ ከሌላችሁ ፈቀቅ ብላችሁ ቁሙ› ከማለት አልተቆጠቡም።

በኢትዮጵያም መጋቢት 3/2012 የመጀመሪያው የቫይረሱ ተጠቂ መገኘቱን ተከትሎ፣ መነቃቃትና ስጋት፣ በፍርሃትና በቸልታ እየተመሩ ሲሄድ ተስተውለዋል። ትውልድ አዲስ ይሆናል እንጂ፣ ዓለም ግን እንዲህ ላለው ወረርሽኝ እንግዳ አይደለችም። ከዚህም በላይ የከፉትን እንዳስተናገደች የዘመኗ ታሪክ ይነግረናል።

ወረርሽኝና ታሪኩ
ዓለም በተለያየ ጊዜ በተነሱ የተለያዩ በሽታዎች ተጎብኝታለች። ሰዎችን አንዳንዴም እንስሳትን የሚያጠቁና ጥፋት የሚያደርሱ ተዋህስያን አልያም በዝርዝር ባክቴሪያና ቫይረሶች ለብዙዎች ሞት ምክንያት ሆነው፣ የማይሽር ጠባሳ አኑረው፣ ነገር ግን ዓለምን የበለጠ ጠንቃቃ፣ አዳዲስ መንገድ ፈላጊና ባለ ብልሃት አድርገው ለዛሬ አድርሰዋታል። ዛሬ ደግሞ ኮቪድ-19 የተሰኘው የኮሮና ቫይረስ በአዲስ ምዕራፍ የሰፈረ ታሪክ ሆኗል።

ዩቫል ኖህ ሐራሪ የተባለ እስራኤላዊ የታሪክ ተመራማሪና በኢየሩሳሌም ሂብሪው ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ፕሮፌሰር፣ ካስነበባቸው መጻሕፍት መካከል፣ የሰው ልጅ ታሪክን ያስቃኘበት መጽሐፍ ተጠቃሽ ነው። በዚህ ‹‹Homo Deus: A Brief History of Tomorrow›› በተሰኘ መጽሐፉም፣ የሰው ልጆችን የጎበኙ ከባባድ የተባሉ ወረርሽኞችን ‹የማይታዩት ጦረኞች› የሚል ርዕስ በሰጠው የመጽሐፉ ምዕራፍ አስቃኝቷል።

በዚህ ላይ ታድያ በቀደመው ዘመን የዓለም ታሪክ ወረርሽኝና ብዙ ጥፋት ያደረሱ በሽታዎችን ከአገር አገር በማዳርስ ተጠቃሽ የሚባሉት ነጋዴዎች እንዲሁም መንፈሳዊ ተጓዦች እንደነበሩ ይጠቅሳል። በመጀመሪያም ‹ጥቁር ሞት› ተብሎ የሚጠራውና በ1330 የተቀሰቀሰውን ወረርሽኝ ያነሳ ሲሆን፣ ይህም ከመካከለኛ እስያ የተነሳ ነው ይለናል።

ይህም በቁንጫ ውስጥ የሚገኝ ባክቴሪያ ያመጣው በሽታ ሲሆን፣ በተጨማሪ አይጦችና በራሪ ነፍሳትን በመያዙ፣ ወረርሽኙ በአጭር ጊዜ መላው እስያን አዳረሰ። ጊዜው ዘመናዊ የትራንስፖርት መስመር ያልነበረበት በመሆኑ፣ እንደ አሁኑ በሳምንታት ልዩነት ወይም በአንድና ኹለት ወራት መካከል ሳይሆን፣ ሃያ ዓመት ዘልቆ፣ በዓመታም አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ ተገኘ።

በዚህ ወረርሽኝ ከ75 እስከ 200 ሚሊዮን ሕዝብ በሞት ተወስዷል። በኢንግሊዝ ሳይቀር የሕዝብ ብዛት ከነበረበት 3.7 ሚሊዮን ወደ 2.2 ሚሊዮን ወርዷል።
በጊዜው የተወሰደ የመፍትሔ እርምጃ ሕዝባዊ ጸሎት ብቻ ነበር፤ ከዛ ባለፈ ወረርሽኙን እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል ያወቀ አልነበረም። ለምን ቢባል፣ በዘመኑ እንዲህ ያሉ በሽታዎች ምክንያት የአየር ጸባይ ለውጥ፣ ክፉ መናፍስት አልያም የፈጣሪ ቁጣ ነው ተብሎ ይታመናል። እንጂ የቫይረስና ባክቴሪያ መኖርን ማን ጠርጥሮ?!
የዩቫል መጽሐፍ እንዲህ ሲል ነገሩን ያስቀምጠዋል፤ ‹‹ያኔ ሰዎች በመላዕክት ያምናሉ። ነገር ግን ሚጢጢ የሆነች ቁንጫ ወይም አንዲት ጠብታ ውሃ ገዳይ የሆነ መርዝ ሊይዝ እንደሚችል አይገምቱም ነበር።››

በ1520 ደግሞ እንዲህ ሆነ። በርከት ያሉ እያንዳንዳቸው አነስተኛ የሚባሉ የጦር መርከቦች ከኩባ ተነስተው ወደ ሜክሲኮ አቀኑ። መርከቦቹ 900 የሚጠጉ የስፔን ወታደሮችንና ጥቂት በባርነት የተሸጡ አፍሪካውያንን ይዘው ነበር። ታድያ ከመርከቡ ከተሳፈሩ ሰዎች መካከል አንደኛው ለራሱ የያዘውን ባያውቅም፣ ከባድ የሚባለውን በሽታ ተሸክሞ ነበር፣ ፈንጣጣ (Smallpox)
ይህ ግለሰብ በሜክሲኮ፣ በዘመኑ ኬምፖላ ተብላ በምትጠራና አሁን የቱሪስት መስህብ በሆነች አካባቢ አረፈ። በዛ እንደደረሰ ነበር በሽታው በሰውነቱ ላይ ጎልቶ ምልክት ማሳየት የጀመረው፣ ትኩሳቱም ከፍተኛ ሆነ። በአካባቢው የነበሩ አሜሪካውያን ቤተሰቦችም ሊያስታምሙና ሊንከባከቡ ቤታቸው ወሰዱት። በዛች ቅጽበት በሽታው መጀመሪያ ወደእነዚህ ቤተሰቦች ሲተላለፍ፣ እነሱ ለጎረቤቶቻቸው፣ ጎረቤቶቻቸው ለሌላ ጎረቤቶቻቸው እያስተላለፉ፣ ሰውየው መጀመሪያ ያረፈበት የኬምፖላ ግዛት በዐስር ቀናት ውስጥ የመቃብር ስፍራ ሆነች።

በዛ አላባራም፤ ጊዜው የሰዎች እንቅስቃሴ ከፍ ያለበት ስለነበር፣ ፈንጣጣ ሜክሲኮን ከዳር እስከ ዳር አዳረሰ። በጊዜው በሽታው የደረሰባቸው በየግዛቱ የሚገኙ ሕዝቦች አማልክትን በየሥማቸው እየጠሩ ይወቅሱ ጀመር። ቀሳውስትና የሕክምና ባለሞያዎችም ምን ይደረግ ሲባሉ፣ ከጸሎት በተጓዳኝ ሰውነትን በቀዝቃዛ ውሃ መታጠብና ቆዳን በቅጠላ ቅጠል ማሸት መድኃኒት ይሆናል አሉ። ግን አልሆነም። እልፎች በወረርሽኙ አለቁ።

በሽታው የተነሳባትና የጸናባት ሜክሲኮ፣ ከበሽታው መከሰት በፊት ከነበራት 22 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ በአሳዛኝ ሁኔታ የተረፏት 14 ሚሊዮን ብቻ ነበሩ።
ከዓለም ጦርነት ማብቂያ ወራት በኋላ በ1981፣ ዐስር ሚሊዮንና ከዛ በላይ ሰዎችን የገደለ ሌላ ወረርሽኝ ደግሞ ተከሰተ። በዚህ ወረርሽኝ የመጀመሪያ ሟቾች ከሰሜን ፈረንሳይ የተነሱ ወታደሮች ነበሩ። ይህንንም ኢትዮጵያውያን የማይዘነጉትና በኅዳር ሲታጠን የሚነሳው የስፓኒሽ ፍሉ ነው።

አጋጣሚ ሆኖ ጊዜው ዓለም አቀፍ ንግድ የተጧጧፈበት በመሆኑ፣ ይህ ወረርሽኝ በጥቂት ወራት ውስጥ አንድ ሦስተኛ ወይም ግማሽ ቢሊዮን የሚጠጋ የዓለም ሕዝብ ጋር መድረስ ችሎ ነበር። ለምሳሌ በሕንድ 15 ሚሊዮን ሕዝብ ወይም 5 በመቶው ሕዝብ በዚህ በሽታ ምክንያት ሞቷል። በየአገሩ የነበረው እልቂት ሲደመርም፣ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ፣ ከ50 ሚሊዮን እስከ 100 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ተመዝግቧል።

በተለያዩ ዓመታትም ተመሳሳይ ወረርሽኞች ተከስተዋል። ለዚህም በ2002/03 ሳርስ፣ በ2005 በርድ ፍሉ፣ 2009/10 ስዋይን ፍሉ እንዲሁም በ2014 ኢቦላ ተጠቃሽ ናቸው። ተያይዞም ኤች.አይ.ቪ. ኤድስ ይነሳል። ቫይረሱ በ1980 ከተቀሰቀሰ በኋላ በተከታታይ 30 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ ለሞት እንደዳረገ የሚረሳ አይደለም።

ዓለም ታድያ ከእነዚህ ወረርሽኞች ብዙ የተማረችው እንዳለ ምሁራንና የጤና ባለሞያዎች ይናገራሉ። በዚህ እርምጃዋም የቀደሙትን በሽታዎች ተበቅላቸዋለች ማለት ይቻላል።

ኢትዮጵያና ወረርሽኝ – እስከ ኮሮና
ኢትዮጵያ የብዙ አውሮፓውያን መዳረሻ እንደመሆኗ መጠን ጥቂት የማይባሉ በሽተዎችን እንደሌላው የዓለም አገር ተቀብላ፣ ብዙ ዜጎቿንም ሰውታ አልፋለች። ለዚህም ከላይ ለምቀስ እንደተሞከረው የኅዳር በሽታ ተብሎ የሚጠራው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስፓኒሽ ፍሉ ተብሎ የሚታወቀው ወረርሽኝ ሊጠቀስ ይችላል።

ከዛም ባለፈ ግን ዛሬ ድረስ ከከተማ ወጣ ባሉ አካባቢዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ወረርሽኞች ሕይወታቸው ያልፋል። ኮሌራ እንኳ በቅርቡ በተለያዩ አካባቢዎች ሕይወት እየነጠቀ እንደሆነ ጤና ሚኒስቴር ሲያስታውቅ ነበር። ከኹለት ሳምንት ባልዘለለ የዜና ሽፋን ትውስታም፣ ወረርሽ በስፋት በታየባቸው አካባቢዎች ክትባት መስጠት ቢጀመርም፣ በቂ አለመሆኑ ተገልጿል።

የኩፍኝ በሽታም በተመሳሳይ በወረርሽኝ መልክ ተነስቷል ተብሏል። ይህም የኮሮና ጉዳይ እንዲህ መነጋገሪያ ሳይሆን በፊት ነው። በኩፍኝም ከ1200 በላይ ሰዎች መያዛቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም በ30 ወረዳዎች ውስጥ የተመዘገበ መሆኑን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መግለጫዎች ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ በእነዚህ ይልቁንም በሠለጠኑ አገራት መኖራቸው እስኪዘነጋ ከሆኑ በሽታዎች አልተላቀቀችም። ይህ የኮሮና ቫይረስም ቀድሞ ከተማይቱን አዲስ አበባን ይጎብኝ እንጂ፣ አልፎ ከተሻገረ ሊያደርስ የሚችለውን ጥፋት መገመት ያስፈራል።

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ ኢትዮጵያ ባላት አቅም ሕክምና መስጫ ተቋማትን ከማስፋት አኳያና ግብዓት ከማማሏት አንጻር፣ በእርዳታም በመታገዝ ጠንካራ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። ታድያ የአቅም ጉዳይ ከተነሳ፣ የሕክምና መስጫ ቁሳቁስና መመርመሪያ መሣሪያ ላይ ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰብ ላይ የሚሠሩ ሥረዎችም ትልልቅ ናቸው ብለዋል። በተለይም የግል ንጽህናን ከመጠበቅ አንጻር፣ እንዲሁም በመንገድና በትራንስፖርት የሚታየውን መጨናነቅ በመቀነስ፣ ብዙ አገራት ቻይና ጨምሮ በሽታውን እንደተቆጣጠሩት፣ ኢትዮጵያም ሳይበረታ በጊዜ እንድትቆጣጠረው ያስችላታል ብለዋል።

ፌጦ መድኃኒት ቢሆንም…
የኮሮና ቫይረስን ወደ ኢትዮጵያ መግባት ተከትሎ፣ የባህል መድኃኒት ጉዳይም መነጋጋሪያ ሆኗል። በተለይም ከየት እንደሆነ ያልታወቀ መረጃ በማኅበራዊ ሚድያ ተሰራጭቶ፣ ፌጦና ገበያ ላይ እንዲታሰስ አድርጓል። በኢትዮጵያውያን ብሂል ‹‹…ፌጦ መድኃኒት ነው›› ቢባልም፣ እንዲህ ባለ የወረርሽኝ ጊዜ ግን አድርጉ የተባለውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ባለሞያዎች ደጋግመው ሲያሳስቡ ከርመዋል።

በኢትዮጵያ የስፓኒሽ ፍሉን ወይም የኅዳር በሽታን ለመከላከል ኢትዮጵያውያን የተጠቀሙት የባህል መድኃኒትን ነበር ይላሉ። በእርግጥም በወቅቱ በባህል መድኃኒትነት ተቀባይነት ያገኘው የአበሻ አረቄ መጠጣትና የተላጠ ቀይ ሽንኩርት በገመድ አስሮ በየደጅ አፍ ላይ ማንጠልጠል፣ ውጤታማም የነበረ የባህል መድኃኒት እንደሆነ ተነግሮለታል።

አሁን ባለንበት ጊዜም ታድያ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የሕክምና ባለሞያዎች ከሚያስተላልፉት የ‹ተጠንቀቁ› መልእክት ውጪ የተለያዩ ምክረ ሐሳቦች ሲሰጡ ይሰማል። ከዚህም አንዱ ነጭ ሽንኩርት፣ ፌጦ፣ ጤና አዳምና ማር ቀላቅሎ መውሰድ መድኃኒት ይሆናል እንዲሁም ላለመያዝም ይረዳል የሚል ይገኝበታል። ሰዉም ከስጋቱ የተነሳ ማድረግ ካለበት ጥንቃቄ ይልቅ ሊያድንና ሊከላከል የሚችልን መድኃኒት መርጦ ሞክሮታል፤ እንደማይሆንና ሐሰተኛ ወሬ እንደሆነ እስኪረዳ ድረስ።

ነጭ ሽንኩርትና ቃርያም ገበያ ላይ ውድና ተፈላጊ የሆኑት በዚሁ ምክንያት ነው። የዓለም ጤና ድርጅት በዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ቴዎድሮስ አድኀኖም በኩል ባስተላለፈው መልእክትም፣ ነጭ ሽንኩርት ለሰውነት አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ያሉት በመሆኑ መጠቀሙ መልካም ነው። ነገር ግን ኮቪድ19ን ሊከላከል ይችላል የሚል ጥናት ባለመኖሩ፣ ከቫይረሱ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም ብሏል።

ይህ ታድያ ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተላፈ መልእክት አይደለም። በተለያዩ የዓለም አገራትም ነጭ ሽንኩርት መድኃኒት እንደሚሆን አምነው የሞከሩ ነበሩ። ነገር ግን ኮቪድ-19 የተሰኘውን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል፣ አሁንም በብዙኀኑ እጅ ያለው አማራጭ እጅን በአግባቡ መታጠብና እርስ በእርስ ንክኪን በመቀነስ መጠንቀቅ ብቻ ነው።

በተጓዳኝ ሰዎች በየሃይማኖታቸውና እንደየእምነታቸው ፈጣሪ እንደሚጠብቃቸው ደጋግመው ሲናገሩ ይሰማል። ይህ እምነት ከመቶ መቶ የሚጠጋ ሃይማኖተኛ በሚገኝባት እንደ ኢትዮጵያ ባለች አገር የሚጠበቅ ሆኖ ሳለ፣ ይህን ተከትሎ መዘናጋትና ‹‹ይጠብቀናል›› እያሉ ጥኝቃቄ አለማድረግ ብዙዎችን ያስወቀሰ ተግባር ሆኖ ሰንብቷል።

በአንጻሩ አምልኮ የሚደረግባቸው ሁኔታዎች ተቀይረዋል። ምእመናን በአንድ ቦታ እንዳይሰባሰቡና እንዲራራቁ፣ ለተወሰኑ ቀናትም ምስጋናና ጸሎታቸውን ለየግል እንዲያደርሱ በብዙ አገራት ተነግሯቸዋል።

ለምሳሌ በእስልምናው ለወትሮው በታላቁ የመካ መስጂድ የሚታዩ ሰዎች ቁጥር መቀነሱ ተዘግቧል። የጉብኝት ክልከላና ገደም መኖሩም ለዚህ ተጨማሪ አስተዋጽኦ አበርክቷል። እንደውም ይህ ክልከላ እስከ ረመዳን እና የሃድ ጉዞ የሚቀጥል እንዳይሆን ነው ስጋቱ ያየለው፣ እንደ ዓለም መገናኛ ብዙኀን ዘገባ።

በክርስትናውም ተመሳሳይ ነው። ወረርሽኙ በበረታባት ጣልያን ፖፕ ፍራንሲስ ወደ አደባባይ ብቅ ብለው ቡራኬ ለመስጠት እንዳልደፈሩና፣ ያንንም ያላደረጉት የሚፈጠረውን መጨናነቅ በመፍራት እንደሆነ ሲዘገብ ሰንብቷል።

በኢትዮጵያም ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ባስተላለፉት መልእክት፣ ነጋዴዎችና ባለሀብቶች ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ እንዲያደርጉ አሳስበዋል። ሆኖም ሙስሊሙ ለአምልኮ የሚሰበሰብባቸው ሃይማኖታዊ ስርዓቶችን በተመለከተ የተወሰነ ነገር እንደሌለ ጠቅሰው፣ ሕዝቡ ግን የተባለውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አደራ ብለዋል።

የኢትትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ፓትሪያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስም፣ ማዕመናን የተባሉትን ጥንቃቄዎች በማድረግ የባለሞያ ምክረ ሐሳቦችን እንዲሰሙ አሳስበዋል። በተመሳሳይ የካቶላካዊት ቤተክርስትያንን የሃይማኖት ተቋማት በየግላቸውና በኅብረት ባወጡት መግለጫ፣ ምዕመናኑ እንዲጠነቀቁ ሲሉ አሳስበዋል። በሽታውን ለመግታት ለጊዜው ያለው አማራጭ መተጋገዝና በጥንቃቄም ራስን መጠበቅ ብቻ ስለሆነ፣ የሃይማኖት አባቶች መልእክትም ከዚህ የዘለለ አልነበረም።

ገበያና ኮሮና
ደንበኞቹን ሜትር በማይሞላ የቅርብ ርቀት የሚያስተናግደው ጠበብ ያለው ካፌ እንደ ወትሮው በሰው አልተጨናነቀም። ለምሳ እንዲሁም ሻይ ቡና ለማለት ወደ ካፌው የሚገቡ ደንበኞችም የመጀመሪያ ሥራቸው ከክፍሉ ጠርዝ ላይ ወደሚገኘው የእጅ መታጠቢያ ማምራት ነው። ቀጥሎም እጃቸውን እያረጋገፉ ወንበራቸውን ይይዛሉ።

ሙሉጌታ አወቀ ከካፌው በርካታ ደንበኞች መካከል አንዱ ነው። ካፌው ከነዳጅ ማደያ ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ፣ መኪናውን ለማሳጠብ አልያም ነዳጅ ለመሙላት ወደዛ አዘውትሮ ስለሚያቀና፣ ለካፌው እንግዳ እንዳልሆነ ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል። ታድያ ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ፣ ወደኢትዮጵያ መግባቱ ከተሰማበትና ጥንቃቄ እንዲደረግ ብዙ መልእክትና ማሳሰቢ ከተሰጠበት ጊዜ አንስቶ፣ ጥንቃቄ የተሞላበት እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ ነው የጠቀሰው።

ካፌው ውስጥ በቁጥር መጠነኛ የሚባሉ ሰዎች መኖራቸውን ቃኘት አድርጎ ከተመለከተ በኋላ ያስረዳል። ‹‹እንደ ስጋቱና እንደ ተባለው ቢሆን አንዳችንም በዚህ መገኘት አልነበረብንም። ግን በየቀኑ በሚደረግ እንቅስቃሴ ገቢ እያገኘ ኑሮውን የሚገፋ በበዛበት ከተማ፣ ያንን ማድረግ ስለማይቻል መቆጣጠር ከባድ ሊሆን ይችላል።›› ሲል አስተያየትና ስጋቱን ለአዲስ ማለዳ አካፍሏል።

በካፌው አስተናጋጅ የሆነውና ሥሙ እንዳይጠቀስ የፈለገው ወጣት፣ በጣም ተፈላጊው የቤቱ አገልግሎት ‹ሻይ በሎሚ› መሆኑን ይናገራል። ‹‹በፈት ብዙም ጠያቂ አልነበረውም። አሁን ግን ሻይ ብቻውን ከሚየዘው ይልቅ ሻይ በሎሚ የሚጠይቀው ይበዛል። የቆዩ ደንበኞቻችንም የሚያዙት ሻይ በሎሚ ነው›› ሲል ያስረዳል። ገበያውና እንቅስቃሴው ከወትሮው በመጠኑ መቀነሱንም አያይዞ አንስቷል።

የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ፣ ገበያው አሳዛኝም አስቂኝም ገጽታዎች ታይተውበታል። ይልቁንም ፌጦ ሳይቀር በፕላስቲክ ውሃ መያዣ ክዳን 10 ብር ሲሸጥ እንደነበር በተለያዩ መደበኛ ባልሆኑ መገናኛ ብዙኀን ሲዘገብ ከርሟል። መንገድ ላይ ሎሚ አምስት ብር ሲሸጥ የተነበረው፣ እስከ ሃያ እና ሃምሳ ብር ድረስ ዋጋ ተተምኖለትም ሰንብቷል።

ደረጃውን ያልጠበቀ የአፍ መሸፈኛ ማስክ እጅግ ከፍተኛ በሆነ ዋጋ መሸጡንም መደበኛ መገናኛ ብዙኀን ሳይቀሩ ዘግበውታል። ይህ ሁሉ ከበሽታው ራሱን ለመከላከል ነዋሪው ይጠቀመዋል ተብሎ የታሰበ ሆኖ ሳለ፣ ከዚህ ጋር የማይገናኙ ምርቶችም በተመሳሳይ ዋጋቸው ንሮ ነበር።

በመድኃኒት መሸጫ መደብሮች 5 ብር የነበረውን የአፍ መሸፈኛ እስከ 200 መቶ ብር፣ ነጭ ሽንኩርት ከ100 – 110 ብር የነበረው ከ250 – 290 ብር፤ ሙዝ በኪሎ 25 ብር የነበረውን 60 ብር፤ በርበሬ 90 ብር የነበረውን 130 ብር ሲሸጡ የተገኙም ነበሩ። እርምጃ የተወሰደባቸውም ጥቂት አይደሉም።

ብዙ የአዲስ አበባ ነዋሪ፣ እጅግ ጥቂት ከሚባሉ በቀር፣ የእጅ ማጽጃ ፈሳሽ ወይም ሳኒታይዘር የመጠቀም ልምድ አይታይም። ይኸው ኮቪድ19 ግን የሳኒታይዘር ተጠቃሚና ፈላጊውን ቁጥር ከፍ አድርጎ፣ ሳኒታይዘር ከገበያ እስኪጠፋ ድረስ ተሟጦ አልቆ ነበር።

ኮቪድ-19 በቸልታ መካከል
ኮቪድ-19 የሚል ሥያሜ የተሰጠው ቫይረስ መስፋፋት በጀመረበትና አውሮፓን በጎበኘ ማግስት፣ የየአገራቱ መንግሥታት በየድርሻቸው መደረግ አለባቸው ያሉትን ጥንቃቄዎች ለሕዝባቸው ሲነግሩና ሲያስነግሩ ከርመዋል። ዓለም ሌላ ችግርና አለመረጋጋት ያልነበረባት ይመስል፣ ሁሉም አጀንዳ ተዘግቶ ትኩረት ሁሉ ቫይረሱ ላይ ሆኗል። ለጦርነት አንድ ሐሙስ የቀራው የሚመስሉ አገራትም ጠባቸውን በይደር አቆይተው፣ ውጊያቸውን ከማይታየው ተዋህሲ ኮቪድ 19 ጋር ውጊያ ገጥመዋል። የጦር መሣሪያ ብዛት፣ የባለጸግነት ጥግ፣ የኒኩሌር ባለቤትነትም ሆነ አምጣቂነት፣ አሁን ከዚህ በዐይን ከማይታይ ቫይረስ የሚያድን አልሆነም።

የአሸባሪው ኢስላሚክ ስቴት (አይ.ኤስ.) ሳይቀር በመሪው በኩል፣ ከሽብር ጥቃቱ ቆም ብሎ፣ ‹ከፈጣሪ የተላከ ቁጣ ነውና፣ በዚህ ቁጣ ውስጥ ከተገኙ የአውሮፓ አገራት ድርሽ እንዳትሉ› የሚል መልእክት ማስተላለፉን የውጭ መገናኛ ብዙኀን ዘግበዋል።

የቡድኑ መሪ ወረርሽኙ ከተሰራጨባቸው አካባቢዎች እንዲርቁ ሲልም ለአባላቱ አሳስቧል። ያም ብቻ ሳይሆን በቫይረሱ የተያዙ እንደሆነ ካሉበት እንዳይንቀሳቀሱና ስርጭቱን እንዳያባብሱም በመልእክቱ አክሏል። በተረፈም ለጥንቃቄ እጅ መጣጠብ፣ ሲያስሉና ሲያስነጥሱ የአፍ መሸፈኛ ማድረግን እንዳይዘነጉ ለአባላቱ ምክሩን ለግሷል።

አሸባሪ ቡድንን ሳይቀር ያሰጋው ወረርሽኙ፣ በኢትዮጵያ ግን አቀባበል የተደረገለት በቸልታ ነው። ይህም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ይደረጋል ከተባለውና ነገር ግን በትኩረት እንደማይደረግ ከተገለጸው ምርመራ የሚጀምር ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከውጪ የሚገቡ ሰዎችን በሚገባና አጥጋቢ በሆነ ሁኔታ ምርመራ እያደረገ እንዳልሆነ አዲስ ማለዳ ተረድታለች።

በቦሌ ዓለማቀፍ አየር ማረፊያ የሚደረገው ምርመራ አጥጋቢ አይደለም፣ ከውጪ የገቡ ኢትዮጵያውያን እንደሚያስረዱት ነው። ‹ከየት ነው የመጣችሁት?› ብሎ በመጠየቅና የመጡበት አገር ቫይረሱ ያልተስፋፋበት ከሆነ በቀላል ምርመራ ማሳለፍ ተስተውሏል።

በቫይረሱ የተያዘ ሰው መኖሩ ይፋ ከተደረገ በኋላ በዋለው እሁድ የተከተለው የአደባባይ የሴቶች ሩጫ፣ በሚሊንየም አዳራሽ በሜቄዶንያ የተዘጋጀው የምስጋና እና የገቢ ማሰባሰቢ መርሃ ግብር፣ የፖለቲካ ፓርቲ ስብሰባዎች ወዘተ ተጠቃሽ የመዘናጋት ማሳያዎች ናቸው።

ሆኖም ሰኞ መጋቢት 10/2012 አንደኛና ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ዝግ ሆነው ለኹለት ሳምንታት እንደሚቆዩ ከጠቅላይ ሚኒስር ጽሕፈት ቤት የወጣ መግለጫ አስታወቀ። ይህን ተከትሎ ስብሰባዎች፣ ጥበባዊ ክዋኔዎችና የውይይት መድረኮች ሁሉ በይደር እንዲቆዩ ተወሰነ። ይህም ለወረርሽኙና ቢስፋፋሊያመጣ ስለሚችለው ጦስ አንዳች መረዳት ላይ እንደተደረሰ ማሳያ ይሆናል።

ፍርድ ቤቶች ከመጋቢት 10 እስከ 24 ቀን 2012 ድረስ ይዘጋሉ ተባለ። የኢትዮጵያ ብሐየራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ ተቋማት ለተወሰኑ ቀና በሮቻቸው ዝግ እንደሚሆኑ አስታወቁ። የመንግሥት ሲኒማና ቴአትር ቤቶችም ተመልካች እንደማያስተናግዱ አስታወቁ።
በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን አዲስ አበባ በመላው ጭር አላለችም። እንቅስቃሴዎች ኮሮናን አልሰማንም አላየንም ያሉ ይመስላሉ። አውቶብሶች እንደ ወትሮው ሞልተው፣ ታክሲዎች ትርፍ ጭነውና በአቋራጭ እየገሰገሱ፣ ረጃጅም የትራንስፖርት ሰልፎች በሰዎች መቀራረብ ተሰምረው፣ አንዳንድ ስብሰባዎች መካሄዳቸውን ቀጥለው፣ ካፌዎችም እንግዶች ማስተናገድ እንደቀጠሉ ይታያሉ።

ሌላው ቀርቶ የእጅ ንጽህና መጠበቂያ ፈሳሽ (ሳኒታይዘር) በከነማ ፋርማሲዎች መሰራጨቱንና በተመጣኝ ዋጋ መቅረቡን ተከትሎ፣ ያልቅብናል በሚል ስጋት ይመስላ የአዲስ አበባ ነዋሪ ፋርማሲዎቹን በእጅጉ አጨናንቆ ይታይ ነበር። የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደርም ‹‹ከቀናት በኃላም ተጨማሪ ስለሚሰራጭ፣ የከተማችን ነዋሪዎች ያለምንም ስጋት ተረጋግታችሁ እንድትገዙ እና ለመግዛት በሚደረጉ ሰልፎችም ለጥንቃቄ በመሀከላችሁ የሚኖረውን ተገቢውን ርቀት እንድትጠብቁ እናሳስባለን።›› የሚል መልእክት አስተላልፏል፤ ሰሚ አልተገኘም እንጂ።

ከዛም አልፎ ቫይረሱ አፍሪካውያንን የሚይዝ አይደለም፣ ኢትዮጵያውያንን አይነካም የሚል አመለካከት ተንሰራፍቶ ይታያል። ነገር ግን ቫይረሱ እስካልተጠነቀቁ ድረስ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ቀለምና ዜግነት የማይጠይቅና ሁሉን የሚያጠቃ መሆኑን የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዲሁም የጤና ሚኒስቴር በሰጡት መግለጫ ሲያሳስቡ ተደምጠዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትም ተከታዩን መልእክተ አስተላልፏል።

‹‹የኮቪድ-19 ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ በአገር ደረጃ እየተከናወነ ነው። ቫይረሱ ከየትኛውም አገር ወይም ዜግነት ጋር የተያያዘ ያለመሆኑን ልንገነዘብ ያስፈልጋል። ሰው የሆነ ሁሉ ለቫይረሱ ተጋላጭ ነው። መፍትሔው የጤና ሚኒስቴር ያወጣውን የመከላከል እና ጥንቃቄ መመሪያ መከተል ነው። ቫይረሱን የመከላከል ጥረታችን ሰብአዊነታችንን የሚጋርድ እና ርኅራሄን የሚያስጥል መሆን አይኖርበትም። የዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ አካል እንደመሆናችን፣ አንዳችን የአንዳችን ጠባቂዎች ነን። የበሽታ ፍርሃት ሰብአዊነታችንን እንዲነጥቀን አንፍቀድ።››

ፍርሀትና ከሰብአዊነት
ዘረኝነት እንዲህ ባለ መልኩ ይጀምራል የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም። ይህም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራንፕ ‹የቻይና ቫይረስ› እያሉ በመግለጫቸው ደጋግመው በመጥቀሳቸው ውስጥ ይታያል። ይህን የቃል አጠቃቀምም በቫይረሱና ወረርሽኙ ዙሪያ በሚሰጡት መግለጫ አብዝተው መጠቀማቸውን የታዘቡ የአገሩ መገናኛ ብዙኀን፣ በአሜሪካ የሚገኙና የቻይና ዘር ያላቸው ዜጎች ላይ መገለል እንዳያደርስ ሲሉ ቅሬታቸውን በግልጽ ሲያቀርቡ ተሰምተዋል። ትራንፕ ግን ‹ከቻይና ስለመጣ ነው ይህንን አባባል የተጠቀምኩት። በዚህ ደግሞ አሜሪካዊ የሆኑ ኤሽያውያንም በሚገባ ይስማማሉ።› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ነገር ግን መገለሉ እንዳለ የተለያ የዓለም መገናኛ ብዙኀን ገጠመኞችን ጠቅሰው በማሳያ አስቀምጠዋል። በኢትዮጵያም በዛ ልክ ባይሆንም ተመሳሳይ ትዕይንቶች ግን መስተዋላቸው አልቀረም። በተለይም ከባህር ማዶ የመጡ ነጮችን እና ቻይናውያንን መሸሽና መራቅ የሚስተዋል ጉዳይ ሆኗል። ጥንቃቄው መደረግ ያለበት ሆኖ፣ የማግለል ስሜትና የውጪ ዜጎችን ‹ኮሮና› እያሉ መጥራት ግን የዘረኝነት መገለጫ መሆኑን ተገልጿል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ በበኩላቸው፣ ‹‹ቫይረሱን መቆጣጠር የምንችለው በጋራ ነው።›› ብለዋል። የሚሰጡ ማሳሰቢያዎችን ከመከተልና ከመታዘዝ በተጓዳኝ፣ ፍርሃት ሳይኖር በመረጋጋት እንደማኅበረሰብ ተደጋግፈን መሥራት አለብን ሲሉ አሳስበዋል። በአዲስ አበባም የውጪ ዜጎች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች ሪፖርት መደረጋቸውን ያነሱት ሚኒስትሯ፣ ‹‹ችግሩ የአንድ ሰው አይደለም፤ በሽታው ቀለም ዘር አይለይም። ሁላችንም በጋራ ልንዋጋው የሚገባ ዓለምአቀፍ ፈተና ነው። ብዙ አገራትም እያገዙን ስለሆነ በጋራ ነው መሥራት ያለብን›› በማለት በአደራ መልክ መልእክታቸውን አስተላፈዋል።

ከዚህ የማግለልና ጥቃት የመፈጸም ድርጊት ባሻገር ደግሞ ሰብአዊነትን ያላቁ ሰዎችን መታዘብ ይቻላል። ብዙ ሕዝብ በሚንቀሳቀስባቸው መንገዶችና አካባቢዎች፣ በተቋማት መግቢያ በሮችና መሰል እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው ስፍራዎች፣ ውሃና ሳሙና ይዘው እጅ የሚስታጥቡ በጎ ፈቃደኞች ይታያሉ። እነዚህም ምስጋና የሚገባቸው ሆኖ ሳለ፣ በአገልግሎቱና በሕዝብ አጠቃቀም ዙሪያ ግን አሁንም የሚነሱ ቅሬታዎች እንዳሉ አዲስ ማለዳ ታዝባለች።

መስፍን አበራ (ሥሙ የተቀየረ) ብዙ የአዲስ አበባ ሕዝብ በሚንቀሳቀስበት መገናኛ አካባቢ እጅ በማታጠብ የበጎ ፈቃድ ሥራ ከተሰማሩ ወጣቶች መካከል ይገኛል። በበኩሉ በጎ ፈቃድ ሥራውን ደስ ብሎት እንደሚያከናውንና ነገር ግን ሰዉ ቫይረሱ በመጨባበጥ ብቻ የሚተላለፍ እየመሰለው መነካካትና መጠጋጋትን እየዘነጋ መሆኑን ማስተዋሉን ይናገራል።

‹‹ለመታጠብ ወደዚህ የሚመጡ ሰዎች ከሚወርዱበት ትራንስፖርት ግር ብለው ስለሚሆነ የሚወጡት፣ እየተጋፉና በጣም ተጠጋግተው ነው። እጅ በመታጠብ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ጥንቃቄዎችንም ማድረግ እንደሚገባ ማሳወቅ ያስፈልጋል›› ሲልም ሐሳቡንና ስጋቱን አካፍሏል።

በእርግጥም የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ፣ ሳኒታይዘርን ጨምሮ ስርጭት ከተደረገና በተመጣጣኝ ዋጋ ነዋሪ ማግኘት እንደሚችል ይፋ ከተደረገ ጊዜ ጀምሮ፣ አዲስ ማለዳ ይህን ሐተታ እስካሰናዳችበት ቀን መጨረሻ ድረስ፣ የመድኃኒት ቤቶች ይልቁንም ከነማ ብዙ የተጨናነቀ ሰልፍ ይታይባቸው ነበር።

ቸልታው በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይደለም። ጤና ተቋማት መግቢያ በር ላይ የትኩሳት መለኪያ አገልግሎት እየተሰጠ በሚታለፍበት፣ ብዙዎች ሰው በሰው ላይ ተደራርበው ሲጋፉ ይታያል። አውቶቢስና ታክሲ እንደ ወትሯቸው ጥቅጥቅ ብለው ሞልተው ይስተዋላል። ከጥቂት ኃላፊነት ከሚሰማቸውና ‹ከዚህ በላይ አንጭንም› ከሚሉ ትራንስፖርት ሰጪዎች ውጪ፣ ብዙዎቹ በዚህ ቸልታ ውስጥ የሚገኙ ናቸው።

የኮቪድ-19 ነባራዊ እውነቶች
በኮቪድ-19 ቫይረስ የተያዘ ሰው የመሞት እድሉን አንድም የእድሜው ሁኔታ እንደሚወስነው፣ በቨይረሱ ላይ አዳዲስ መረጃዎችን በየሰከንዱ የሚያቀብለው ወርልዶሜትር የተሰኘው የመረጃ ምንጭ ያትታል። ይህም እስከ አሁን ካከተለው የሞት መጠንና ሁኔታ አንጻር የቀረበ ነው።

በዚህ መሠረት ታድያ ከተመዘገቡ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ብዛት አንጻር፣ እድሜያቸው ከሰማንያ በላይ የሆነ ሰዎች በቫይረሱ የመሞት እድላቸው 14.8 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል። በአንጻሩ ግን የተረጋገጡና በዛ እድሜ ክልል የተመዘገበ ሞት 21.9 በመቶ መድረሱን ተያይዞ ተቀምጧል። በተጓዳኝ እድሜያቸው 70-79 የሆኑ ሰዎች ስምንት በመቶ፣ ከ60-69 የሆኑ 3.6 በመቶ፣ ከ50-59 መካከል ያሉ 1.3 በመቶ ሲሆኑ፣ ከ49 እድሜ በታች የሚገኙ ከ0.4 እስከ 0.2 በመቶ ሆኖ እንደተመዘገበ ተገልጿል።

እድሜያቸው ከ0-9 በሆኑ ሕጻናት ላይ ግን የተመዘገበ ሞት የለም። በጾታ ደረጃ ሲታይም፣ ወንዶች የበለጠ ለሞት ተጋላጭ ሆነው ተመዝግበዋል። ይህም እንደ ዘገባው ከሆነ፣ በተለይ የመጀመሪያው ብዙ ሞት በተስተናገደባት ቻይና ሲጋራ የሚያጨሱ ወንዶች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ እንደሆነ ተቀምጧል።

አዲስ ማለዳ ይህን መረጃ አጠናቅራ ለሕትመት እስከገባችበት ሰዓት ድረስ በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ብዛት 9 ደርሷል። በጥቅሉም 255 ሺሕ በላይ ሰዎች በዓለም ደረጃ ቫይረሱ እንዳለባቸው የተረጋገጠ ሲሆን፣ 88 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ሰዎች ከበሽታው ሲያገግሙ፣ 10 ሺሕ የሚልቁ ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከዚህም ውስጥ ከፍተኛው ድርሻ የጣልያን ሆኗል።

አረአያ የሚሆን ተግባርና የሚቀሰም ልምድ
ታይዋን 23 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎቿን ይዛ ከቻይና በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ አገር ናት። ኮቪድ19 የተባለው የኮሮና ቫይረስ ቻይናን ካጥለቀለቀ በኋላ፣ ቻይና እየተመላለሱ የሚንቀሳቀሱ ብዙ ዜጎች ያሏት እንደመሆኗ ለታይዋን ተፈርቶላት ነበር። መረጃዎች እንደሚያመላክቱትም፣ ለምሳሌ ባለው ዓመት ብቻ ታይዋንን 2.7 ሚሊዮን ቻይናውያን ጎብኝተዋታል።

ሆኖም አዲስ ማለዳ ይህን ጥንቅር ይዛ ለሕትመት እስከገባችበት ሰዓት ድረስ፣ በታይዋን በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር 135 ብቻ ሲሆን፣ ሃያ ስምንቱ አገግመው ሲወጡ ኹለት ሞት ብቻ ተመዝግቧል።ታይዋን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ይፋ ሳታደርግ ቆየታ እንዳልሆነ ባለሞያዎች ይስማማሉ። ከቻይና ብዙ የሚባል ቀጥታ በረራ የሌላቸው እንደ ኔዘርላንድ ያሉ አገራት እንኳ ከታይና ሦስትና አራት እጥፍ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ተገኝተውባቸዋል።

ታይዋን ለዚህ አረአያ የሚሆን ውጤት ያበቃት፣ ቅድመ ጥንቃቄ ላይ በደንብ በመዘጋጀቷ ነው። 124 የሚደርሱ ተግባራትንም ቀድማ መከወን የጀመረች ሲሆን፣ እንቅስቃሴን መገደብ፣ ማቆያዎችን ማጋጀት፣ ማኅበራዊ ፈቀቅታ ወዘተ የመሳሰሉትን ሕዝቧ ቀድሞ የተዘጋጀበት ጉዳይ ነው።

ቮክስ የተባለው የዜና አውታር በዚህ ዘገባው፣ እንዲህ ያሉ ክስተቶች በሚሆኑበት ጊዜ ትክክለኛ አመራር የሚያደርገው ለባሰው መዘጋጀት ነው ይላል። ታይዋንም ስታደርግ የነበረው ያንን ነው። ከዛም አስቀድሞ በቻይና ገና የመጀመሪያዎቹ የቫይረሱ ተጠቂዎች ስለመኖራቸው ይፋ ከመደረጉ፣ ታይዋን ካቻይና ይልቁንም ከዉሃን ግዛት ወደ አገሯ የመጣውን አውሮፕላንና ተሳፋሪውን መመርመር ጀምራለች።

የታይዋን ተግባር አረአያነት ያለው ሆኖ እንደነ ፈረንሳይና አሜሪካ ሁሉን ዘግቶና፣ ያንንም በሕግ እንዲከበር ተጽእኖ ፈጥሮ ማቆየት ተከታዩ አማራጭ ነው። ከእነዚህ በጎ ተሞክሮዎችም ኢትዮጵያ ልትወስዳቸው የሚገቡ ብዙ ነጥቦች እንዳሉ ባለሞያዎች ይናገራሉ። በመጀመሪያ ደረጃ የቫይረሱን መስፋፋት ለመከላከል ግልፅ የሆኑ በወረርሽኙ ደረጃ እየጠነከሩ የሚሔዱ ተግባራትን ያካተተ እቅድ ማውጣት ያስፈልጋል። ይህም ሁሉም ባለድርሻ አካላትን ያካተተ የሚወሰዱ የሕክምና፣ የአገር ደኅንነት እና ሌሎች እርምጃዎችን በግልፅ ለይቶ የሚያስቀምጥ እቅድ ማዘጋጀት ነው።

እቅዱ ወረርሽኙ አሁን ያለበትን ብቻ ሳይሆን ቀጥሎ የሚደርስበትን ደረጃ ያገናዘበ ሊሆን ይገባል። ይህንን እቅድ የሚተገብር ግብረ ኃይል ሳይሆን ከዚያ ከፍ ያለ የኮማንድ ማእከል እንደሚያስፈልግም የአገሮች ተሞክሮ የሚያሳይ ሲሆን በክልሎች፣ ዞኖች እና ወረዳዎች ከሚኖሩ አካላት ጋር ትስስር ሊኖረው ይገባል።
ሌላው ቫይረሱ ከውጭ አገር በሚመጡ ሰዎች ላይ እና ከእነሱ ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎች ላይ ብቻ የሚገኝበትን የመጀመሪያውን የስርጭት ደረጃ አልፎ በኅብረተሰብ ውስጥ ሳይሰራጭ በዚሁ ላይ ወስኖ ለማስቀረት መጣር ነው። እያንዳንዱ የቫይረስ ተጠቂ ከየት እንደያዘው ማወቅ የሚቻልበት ደረጃ እንዳያልፍ ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ሙሉ በሙሉ መለየት መቻል እንደ ታይዋን ላሉ አገሮች የመከላከል ስኬት ቁልፍ ቦታ አለው።

ቫይረሱ በኅብረተሰብ ውስጥ መሰራጨት ከጀመረ በኋላ ከፍተኛ ቁጥር ላለው ሰው ምርመራ ማድረግ እና እርዳታ መስጠት ኢትዮጵያ ካላት አቅም በላይ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ከዚህ ደረጃ እንዳይወጣ ባለው ሙሉ አቅም መረባረብ የግድ ይላል። ይህንን ዕውን ለማድረግ የጉዞ እገዳዎችንም ሆኑ የሰዎችን የሥራ እና የግል እንቅስቃሴዎችን እስከ ማገድ የሚደርሱ እርምጃዎችን ለመውሰድ ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል።

በተጨማሪ የቫይረሱን ስርጭትም ሆነ የበሽታውን አስፈሪነት እና የአገሪቷን የመከላከል አቅም አስመልክቶ ግልጽ በሆነ መንገድ ለዜጎች ማሳወቅ ተገቢ ነው። ይህ ችግር አለባብሰው የሚያልፉት እና የአንድ ጊዜ መጠነኛ ችግር ሳይሆን ከፍተኛ አደጋ የሚጋብዝ በመሆኑ ሕዝብ ስለቫይረሱ ያለው ግንዛቤ እያደገ መሔድ አለበት። በኢትዮ ቴሌኮም የተጀመረው የስልክ ጥሪ መልዕክት ጥሩ ጅምር ቢሆንም፣ ስርጭቱ የሚበዛባቸው አካባቢዎችን (ሆት-ስፓትስ) ለይቶ ማሳወቅ እና አዳዲስ የስርጭት አካሔዶችን በመልዕክት ለሕዝብ ማሳወቅ የተሻለ ጥቅም ይኖረዋል። በዚህ ረገድ ቫይረሱ የተገኘባቸውን ማንነት መደበቁ ጉዳቱ የሚያመዝን በመሆኑ ማሳወቅ ይገባል።

ቅጽ 2 ቁጥር 72 መጋቢት 12 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here