በዘውዲቱ ሆስፒታል ባጋጠመ የሕክምና ስህተት በአንዲት ታዳጊ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደረሰ

0
1060

በዘውዲቱ ሆስፒታል በተፈጠረ የሕክምና ስሕተት ምክንያት ነኢማ ሻሚል በተባለች የሰባት ዓመት ታዳጊ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደረሰ።
ከስድስት ወራት በፊት ትርፍ አንጀት ታማ ወደ ሆስፒታሉ የገባችው ታዳጊዋ ነኢማ፣ ቀዶ ጥገና ቢሠራላትም ግራ ትከሻዋ ላይ፣ ቀኝ እጇ ላይ፣ ቀኝ እግሯ ላይ እንዲሁም ጭንቅላቷ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በመድረሱ ከአልጋ መንቀሳቀስ፣ መናገር እንዲሁም በሥነ ስርዓት መመገብ እንደማትችል አዲስ ማለዳ በስፍራው ተገኝታ ለማረጋገጥ ችላለች።

የታዳጊዋ አባት ሻሚል እንጎይታ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ታዳጊዋ መስከረም 14/2012 አዲስ አበባ በከተማ አስተዳደሩ የተለገሰውን የተማሪዎች የደንብ ልብስ ለመውሰድ ከሄደችበት ስትመለስ ሆዴን አመመኝ በማለቷ ምክንያት ወደ ጤና ጣቢያ ትሄዳለች።

ሕክምና አግኝታ መድኃኒት እንደታዘዘላትም ወላጅ አባቷ በማስታወስ፣ ነገር ግን እሱም መፍትሄ ባለማምጣቱ እና ስላልተሻላት በማግስቱ ወደ ፖሊ ክሊኒክ እንደሄደች እና አልትራሳውንድ እንድትነሳ ተደርጎ ትርፍ አንጀት ተብሎ እንደተነገራት ተናግረዋል።

በዚህም ምክንያት ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል ለከፍተኛ ሕክምና እንደተላከችና እዛም ድጋሚ አልትራሳውንድ ተነስታ ትርፍ አንጀት ተብሎ መስከረም 17/2012 ከሰዓት እስከ ምሽት አራት ሰአት የቆየ ቀዶ ጥገና ተደርጎላታል፤ የታዳጊዋ ወላጅ አባት እንደተናገሩት። ከቀዶ ጥገናው በኋላ ወደ የፅኑ ሕሙማን ከፍል መግባቷንም ከሕክምና ባለሞያዎች እንደተነገራቸው ገልጸዋል።

ለ15 ቀናት ልጃቸውን እንዳያዩ የተከለከሉት የነኢማ ወላጆች፣ ጥቅምት 2/ 2012 እንዲያዩዋት በተደረጉ ጊዜ ኹለቱም እግሮቿ የማይታዘዙላት ሆና እንዳገኟት ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

በነኢማ ላይ የተፈጠረውን እንግዳ ነገር በተመለከተ ለዶክተሮች ጥያቄ ሲያቀርቡ አጥጋቢ ምላሽ የሚሰጣቸው ሰው እንዳላገኙ ሻሚል ያስረዳሉ። ‹‹አንድ ጊዜ መብራት ጠፍቶብን ነው፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ኤሌከትሪክ ሰውነቷ ላይ ተረስቶ ነው እያሉ ነው ምላሽ የሚሰጡኝ።›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ የተባሉትን ጠቅሰዋል። ከመስከረም 17/2012 በትርፍ አንጀት ምክንያት ዘውዲቱ ሆስፒታል የገባቸው ነኢማ፣ ከቀናት በኋላ ሰባተኛ ዓመቷን በሆስፒታሉ ውስጥ የአልጋ ቁራኛ እንደሆነች ታከብራለች።
ጉዳዩን በሚመለከት ወደ ሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አቤት ለማለት የሄዱት ሻሚል፣ ሄጄ ‹‹ከሜዲካል ዳይሬክተሩ ይህን የሚያረጋግጥ ደብዳቤ ካላመጣህ እኛ ልናየው አንችልም” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው አንስተዋል። የታዳጊዋን የሕክምና ክትትል የሚያደርጉ ናቸው የተባሉትን የሕክምና ባለሙያ አዲስ ማለዳ አግኝታ ስለ ጉዳዩ ለማነጋገር ብትሞክርም፣ ሳይሳካላት ቀርቷል።

የሕግ ባለሙያ የሆኑት አበበ ዘነበ የተፈጠረውን ጉዳይ በማስመልከት ሙያዊ አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ ሲሰጡ፣ ኹለት ዓይነት የሕግ ስርአት አለ ብለዋል። አንደኛ የሚያያዘው የሙያ ሥነ ምግባርን ካለመወጣት ጋር እንደሆነም ተናግረዋል።

በዋነናነት በዓለማችን ላይ በሙያ ቸልተኝነት ከ20 ሺሕ ሰው በላይ በዓመት እንደሚሞትበት የጠቀሱት ባለሞያው፣ በተጨማሪም ሕጉ ምን ይላል የሚለውን ሲያመላክቱ፣ በጠቅላላ ድንጋጌ መደበኛ የሕክምና ስህተቶች ሲሆኑ ከእነርሱም መካከል ውጤቶችን አሳስቶ ማንበብ፣ የታካሚን ሁኔታ በተገቢው መንገድ አለመመርመር፣ የተሳሳተ መድኃኒት ማዘዝ፣ የሕክምና ክትትል አለማድረግ፣ የሕክምና ውጤትን በግልጽ አለመንገር፣ ሌላው የታካሚው ፈቃድ ሳይገኝ አገልግሎት መስጠትንም እንደሚያጠቃልል ይናገራሉ።

በነኢማ ላይ የተፈጠረው ችግር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንዲህ አይነት ውጤት የማያስከትል በመሆኑ፣ ከሕክምና ስህተት ውስጥ የሚካተት መሆኑ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ እና የፍትሐ ብሔር ሕግ፣ የወንጀል ሕግ 548 ሙያን በአግባቡ ባለመጠቀም በሚደርሱ ጥፋቶች፣ እንደተቀመጠው ማስረጃ የየራሳቸው ቅጣት እርከን እንዳላቸው አበበ ይናገራሉ።

የፍትሐ ብሔር ሕግ በግል ሁኔታዎች የሚከሰቱ ጥፋቶችን ደግሞ በ2639 ላይ የሚያስቀምጥ ሲሆን ፤ 2650 ላይ ደግሞ ካሳን በተመለከተ ምን ምን ይመስላል የሚለውን እንደሚያብራራ ባለሙያው ያስረዳሉ። በተጓዳኝ 2651 ስለ ሆስፒታሉ ግዴታዎችና ካሳ እስከምን መክፈል ይጠበቅበታል የሚለውን እንደሚደነግግም አበበ ተናግረዋል።

ነገር ግን እንደ ሕግ ባለሞያው ገለጻ፣ ከተጎጂው አካል የሚጠበቁ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ማስረጃዎች መሰብሰብን ዋነኛው ሲሆን፤ የመጀመሪያው ሕመም ምን እንደነበር ያላቸውን ማስረጃ (በወረቀት ላይ የተጠቀሰበትን ሁኔታ)፣ የሕክምና ተቋም ሲገቡ የነበሩ ምስክሮችን በመያዝ፣ በፍተሐ ብሔር እነዚህን አንቀፅ ጠቅሶ ክስ መመስረት እንደሚቻል ያስረዳሉ።

በሆስፒታሉ ማስረጃ የመደበቅ ችግር ቢኖር እንኳን፣ ለሕክምና ሥነ ምግባር ኮሚቴ ቀርቦ እንዲጠና ማድረግና በእነሱ በኩል ማስረጃዎች እንዲወጡ ማድረግ እንደሚቻል አበበ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 72 መጋቢት 12 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here