የ430 ተሽከርካሪዎች የግዢ ጨረታ ታገደ

0
904

የመንግሥት ግዢ እና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ለተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚውሉ 430 ተሽከርካሪዎችን ለመግዛት ወጥቶ የነበረው ጨረታ፣ በላይ አብ ሞተርስ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ታገደ።

በጨረታው ሰነድ ላይ የሰፈረው የውጪ አገር ተጫራቾች ጂቡቲ ወደብ ድረስ ተሽከርካሪዎቹን ለሚያጓጉዙበት የትራንፖርት ወጪ የሚቀርበው የገንዘብ ጭማሪ ለቅሬታው መነሻ መሆኑም ተገልጿል። በላይ አብ ሞተርስ የአገር ውስጥ ተወዳዳሪዎችን የሚጎዳ መስፈርት ነው የሚለው ሌላው የቅሬታው መነሻ ነው ተብሏል።

ድርጅቱ ቅሬታውን ለአገልግሎቱ ቅሬታ ሰሚ ቦርድ አቅርቦ ጉዳዩ በቦርዱ እየታየ ይገኛል ያሉት የመንግሥት ግዢ እና ንብረት ማስወገድ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አሰፋ ሰሎሞን፤ የአገር ውስጥ አቅራቢዎች ተሽከርካሪዎቹን እዚሁ የሚገጣጥሙ በመሆኑ የትራንስፖርት እና ማጓጓዣን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ እኩል አይስተናገዱም ብለዋል።

አሁን ተግባራዊ በሚሆነው አሰራር መሰረት፣ የውጪ አገራት አቅራቢዎች ወደብ ድረስ በራሳቸው ወጪ ካደረሱ በኋላ ከወደብ ወደ አገር ውስጥ በኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ድርጅት የሚገባ ሲሆን፣ የማስጫኛ እና የማጓጓዣ ወጪዎች በገዢው እንዲሸፈኑ የሚያደርግ ነው።

በላይ አብ ሞተርስ ለአገልግሎቱ ቅሬታውን ካስገባ በኋላ፣ በአገር ውስጥ አቅራቢዎች ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር እንዲወያዩ መደረጉን የገለፁት አሰፋ፣ ቦርዱ የደረሰበትን ውሳኔ እስኪያሳውቅ ጨረታው ታግዶ እንደሚቆይ ተናግረዋል።

አክለውም ጥያቄውን በላይ አብ ያቅርበው እንጂ በጨረታው ላይ ለመሳተፍ ጥያቄ ያቀረቡ ሌሎች የአገር ውስጥ ተጫራጮች በዚህ ጥያቄ መሰረት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጠቅሰዋል።

‹‹ጨረታው እኛ ባቀረብነው ጥያቄ መሰረት እንዲቆም ተደርጓል›› ያሉት የበላይ አብ ሞተርስ የጨረታ ጉዳዮች ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሰጥቷል ታረቀኝ ‹‹ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግረን በጉዳዩ ላይ ከስምምነት ላይ ደረሰናል። ከስምምት ላይ የተደረሰባቸውን ጉዳዮች ግን አሁን መግለጽ አልችልም›› ብለዋል።
ታኅሳስ 10/2012 አገር በቀል እና ዓለም ዐቀፍ አቅራቢዎች እንዲሳተፉበት የተከፈተው ጨረታው፣ ጥር 20/2012 እስከታገደበት ቀን ድረስ 28 ተጫራቾች በጨረታው ላይ ለመሳተፍ ሰነድ ገዝተዋል።

የጨረታው ሰነድ በስድስት ክፍሎች የተከፋፈለ ሲሆን፣ ሦስት ዓይነት አውቶቢሶች፣ አነስተኛ የጭነት ተሽከርካሪዎች የግዢ ጨረታው ከወጣባቸው መካከል ይገኙበታል። ለተሽከርካሪዎቹ የግዢ ወጪ በገንዘብ ሚኒስቴር አማካኝነት የሚፈፀም ሲሆን፣ የጨረታው አሸናፊ ከመታወቁ በፊት ይፋ እንደማይደረግ አገልግሎቱ አስታውቋል።

ከዚህ ቀደም መጋቢት 2010 በተደረገው የተሽከርካሪ ግዢ ላይ፣ በላይ አብ ሞተርስ 400 ተሽከርካሪዎችን ለማቅረብ 352 ሚሊዮን ብር የጨረታ ዋጋ በማቅረብ ከመንግሥት ግዢና ንብረት ማስወገድ ጋር ውል በመፈፀም ማቅረቡ የሚታወስ ነው።

የመንግሥት ግዢ እና ንብረት ማስወገድ አገልግሎቱ በ2011 በጀት ዓመት ለተሽከርካሪ ግዥ 9 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ገደማ ወጪ አድርጓል።
ማናቸውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ወይም አቅራቢ፣ ሕግ ከሚያዘው ውጪ ስለመፈፀሙ፤ ግዥ በትክክል ስላለማከናወኑ፣ የግዥውን አሰራር በትክክል ስላለመፈፀሙ ወይም ስለመመሳጠሩ ጥቆማ የቀረበ እንደሆነ፣ ከግዥው አፈፃፀም ጋር የተያያዙ መረጃዎች፤ ሰነዶች፤ መዝገቦች እና ሪፖርቶች እንዲቀርቡለት የማዘዝ እና ምስክሮችን የመጥራት፤ ምስክሮችና ግዥውን የሚመለከታቸው ወገኖች ቃላቸውን በመሃላ እንዲሰጡ የማድረግ፤ የሂሳብ መዝገብ፤ ፕላን፤ ሰነድ እንዲቀርብለት የማድረግ ተግባራትን ያከናውናል።

እንዲሁም ከገበያ ጋር የማይጣጣም ዋጋ በሚያቀርቡ እና ሌሎችም በገንዘብ ሚኒስቴር የሚወጡ መመሪያና ድንጋጌዎች፤ አቅራቢዎች ወይም በመንግሥት ንብረት ማስወገድ ሂደት ተሳታፊዎች ላይ በቀረበ አቤቱታ መነሻነት፣ ማስጠንቀቂያ የመስጠት ወይም የንብረት ማስወገድ ሂደት እንዳይሳተፍ የማገድ ሥልጣኖችም ተሰጥተውታል።

ቅጽ 2 ቁጥር 72 መጋቢት 12 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here