በኮቪድ19 ምክንያት የሚደርስ ጉዳትን እንደማይሸፍኑ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች አረጋገጡ

0
1047

በመላው ዓለም ከ10 ሺሕ በላይ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው ኮሮና ቫይረስ ምክንያት የሚከሰቱ ማንኛውም ዓይነት ኪሳራዎችንም ሆነ አደጋዎችን በኢትዮጵያ የሚገኙ 17ቱም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች እንደማይሸፍኑት አዲስ ማለዳ አረጋገጠች።

ለባለፉት ኹለት ሳምንታት ጉዳዩ ላይ እልባት ለመስጠት ኩባንያዎቹ የጠለፋ ዋስትና አገልግሎት ከሚሰጧቸው ተቋማት ጋር የተመካከሩ ሲሆን፣ ተቋማቱ ከደንበኞቻቸው ጋር ያደረጉት ውል መሰረት እንደ ኮኖና ቫይረስ ላሉ ወረርሽኞች ለሚያስከትሉት ኪሳራ ምንም አይነት ሽፋን መስጠት እንደማይጠበቅባቸው ማወቅ ተችሏል።

ይህም ማለት የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ በጉዞ ላይ ለሚደርሱ ማንኛውም አደጋዎች እንዲሁም የተለያዩ የጤና መድኅን ኢንሹራንስ አገልግሎት እየሰጡ ቢሆንም፣ ደንበኞቻቸው በኮኖና ቫይረስ የተነሳ ሕይወታቸው ቢያልፍ ወይም ጉዳት ቢደርስባቸው ምንም አይነት ካሳ እንደማይከፍሉ ታውቋል።

በተጨማሪ፤ የኮሮና ቫይረስ ስርጭቱ በኢትዮጵያ ተስፋፍቶ ድርጅቶች እንዲዘጉ እንዲሁም አገልግሎት ምርት እንዲያቆሙ የሚያስገድድ አጋጣሚ ቢከሰት እንኳን፣ በአገሪቷ የሚሰጡ የኢንሹራንስ ፖሊሲዎች ይህ አይነቱን በወረርሽኝ የተነሳ ሊከሰት የሚችል ኪሳራን እንደማያካትቱ አዲስ ማለዳ ማረጋገጥ ችላለች።

ቀዳሚ ከሚባሉት የግል ኢንሹራንስ ተቋማት ተርታ የሚመደበው አፍሪካ ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኪሮስ ጂራኔ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ በኢትዮጵያ የሚሰጡ የሕይወት ነክ እና የአጠቃላይ ኢንሹራንስ አገልግሎቶች ወረርሽኞችን ስለማያካትት ኮኖና ቫይረስን ተከትሎ ለሚመጡም ኪሳራ እና ካሳ ሊከፍሉ እንደማይችሉ አስረድተዋል።

‹‹በተለይም እንደ ኮሮና ቫይረስ ያሉ ወረርሽኞች ሊያደርሱ የሚችሉ ኪሳራዎች ለመገመት ከባድ በመሆናቸው ቀድሞ ከደንበኞች ጋር ውል በሚገባበት ወቅት ከግምት ውስጥ ሊገቡ የሚችሉበት መንገድ ስላልነበር፤ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ካሳ ሊከፍሉ አይገባም።›› ሲሉ ኪሮስ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የፀሐይ ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ካሳ ልሳነወርቅ እንደተናገሩት፣ ድርጅታቸው በኮኖና ቫይረስ ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ ኪሳራዎችንም የማይሸፍን ሲሆን ውድመታቸው ከፍ ያሉ እንደ ወረርሽኝ ያሉ አደጋዎች መሸፈን የሚያስችል ውል ያለው የኢንሹራንስ ተቋም በኢትዮጵያ ውስጥ እንደሌለ አስታውሰዋል።
ይህንን ሐሳብ ያጠናከሩት የናይል ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ንጉሥ አንተነህ በበኩላቸው፣ ምንም እንኳን በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ካሳ ማግኘት መብት ያላቸው የሕይወት መድን የገዙ ደንበኞች ቢኖራቸውም፣ በኮሮና ቫይረስ ሕይወታቸው ቢያልፍ ካሳ ሊያገኙ የሚችሉበት አግባብ እንደሌለ ተናግረዋል።

በተጨማሪ፤ በኮኖና ቫይረስ መስፋፋት የተነሳ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው ካሉ ተቋማት አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ወደተለያዩ አገራት የሚያደርገው በረራ በወረርሽኙ ምክንያት በማቋረጡ ኪሳራ እየደረሰበት ቢሆንም የኢንሹራንስ ካሳ እንደማያገኝ ማወቅ ተችሏል።

ወረርሽኙ በተከሰተ ኹለት ሳምንታት ውስጥ ብቻ የአየር መንገዱ የበረራ አገልግሎት ተጠቃሚዎቹ በ20 በመቶ የወረደ ሲሆን፣ በያዝነው በጀት ኹለተኛ አጋማሽ ላይ ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ሊያጣ እንደሚችል የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ።

ከአየር መንገዱ ባሻገር፤ የቫይረሱ መስፋፋት በቱሪዝም ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ሆቴሎች እና ሌሎች ተቋማት ላይ ጉዳት ያሳደረ ሲሆን፣ የኢንሹራንስ ተጠቃሚ ቢሆንም እንኳ አንዳቸውም ካሳ ሊያገኙበት የሚችል መንገድ እንደሌለ መረጃዎች አመላክተዋል።

ሌሎች ዋነኛ የኢንሹራንስ አገልግሎት የሚያገኙ እንደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ፋብሪካዎች፣ የንግድ ተቋማት እና የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ቫይረሱ እንደ ሌሎች አገራት በኢትዮጵያ ከተስፋፋ ሥራ ሊቋረጥ የሚችልበት ዕድል ሰፊ እንደመሆኑ መጠን፣ ከፍተኛ ኪሳራ ሊደርስባቸው እንደሚችል ከወዲሁ ተሰግቷል። ይሁን እንጂ ተቋማቱ በዚህ የተነሳ የሚያገኙት ካሳ አይኖርም።

በኢትዮጵያ ሕይወት ነክ እና አጠቃላይ የኢንሹራንስ አገልግሎቶች ጠለፋ አገልግሎት የሚሰጠው አፍሪካን ሪ፣ ከወዲሁ ኮኖና ቫይረስን ተከትሎ ለሚከሰቱ ቀውሶችም ሆነ ኪሳራዎች ካሳ እንዲከፍል የሚያስገድደው ውል ከኢንሹራንስ ኩባንያዎች እንደሌለው አሳውቋል።

በኢትዮጵያ የአፍሪካን ሪ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሃብታሙ ደበላ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ድርጅታቸው ወረርሽኝ (pandemic) የሚያስከትለውን ኪሳራም ሆነ የሕይወት መጥፋት ካሳ ለመክፈል የሚያስችል ውል ከኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጋር እንደሌላቸው ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል። በሌላውም የዓለም ክፍል ይህን አይነት ችግሮች ሽፋን እንደማይሰጣቸው ተናግረዋል።

ኢንሹራንስ ኩባንያዎችም ከደንበኞቻቸው ጋር በገቡት ውል መሰረት ወረርሽኞችን ከግምት ውስጥ አላስገቡም፤ ተመጣጣኝ ክፍያም አላገኙበትም ያሉት ሃብታሙ፣ በዚህም መሰረት ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በኮኖና ቫይረስ ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ ኪሳራዎችን ለመክፈል አይገደዱም ብለዋል።

በተመሳሳይ የኢንሹራንስ ባለሙያ የሆኑት ፍቅሩ ፀጋዬ እንደተናገሩት፣ ኮሮና ቫይረስ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የአደጋ ስጋት ዝርዝር ውስጥ ቀድሞ ያልተካተተ ስለሆነ፣ ለሚያመጣው ኪሳራ ካሳ መክፈል የሚቻልበት የሕግ አግባብ የለም። ይህም ማለት ኩባንያዎቹ የጉዞ፣ የሕክምና የሌሎች ሕይወት-ነክ ፖሊሲዎችን ሲሸጡ ከግምት ውስጥ ስላላስገቡት የተቀበሉት ክፍያ የለም ሲሉ ፍቅሩ ተናግረዋል።

ስለዚህ፤ ጉዳዩ በመንግሥት ሊፈታ ይገባል ያሉት ፍቅሩ፣ ቫይረሱ ከወዲሁ ሊያመጣ ለሚችለው ኪሳራ በመንግሥት በኩል ቅድመ ዝግጅት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል። በዚህ ሐሳብ የሚስማሙት ሃብታሙ፣ ድርጅቶች ሊወጡት የማይችሉት ኪሳራ ውስጥ እንዳይዘፈቁ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ለጉዳዩ እልባት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 72 መጋቢት 12 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here