የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ውሃ ለሌላቸው አካባቢዎች በቦቴ ተሽከርካሪዎች ውሃ መሰራጨት ተጀመረ

0
512

የሐረሪ ውሃና እና ፍሳሽ ባለሥልጣን አገልግሎት የኅብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ ተቋማዊ ግብረ ኃይል በማቋቋምና ስትራቴጂ በመንደፍ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል መጠነ ሰፊ ርብርብ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ።

የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ተወለዳ አብዶሽ እንደተናገሩት፣ የውሃ አቅርቦት የኮሮና ቫይረስ እንዳይከሰት፤ ከተከሰተም ደግሞ ስርጭቱን ለመግታት ዋነኛ ጠቃሚ ነው ሲሉ ገልጸዋል። በክልሉ የውሃ አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ግብረ ኃይል በማቋቋም በክልሉ (በገጠርና በከተማ) የሚስተዋለውን የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና የፍላጎት ክፍተት ለማጥበብ የተቀናጁ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

ከዛም በተጨማሪ ውሃ ለሌላቸው እና በፈረቃ የሚካሄደውን ከፍላጎት ጋር ያልተጣጣመ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ተጨማሪ የውሃ መገኛ ሥፍራዎችን በማበልፀግና በመደበኛ የቧንቧ ውሃ ስርጭት ተደራሽ ላልሆኑ አካባቢዎች በቦቴ ተሸከርካሪዎች ውሃ በመሰራጨት መጀመሩን የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ለተተከሉ ከ40 በላይ የውሃ ታንከሮች በቦቴ ውሃ በነፃ በማቅረብ ለኅብረተሰቡ በጀሪካን አንድ ብር እንዲሸጡ መደረጉን ገልፀዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ፣ የሕፃናት ማሳደጊያዎች፣ ማረሚያ ቤት፣ ፖሊስ ማሠልጠኛ አካባቢ ለሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪዎች እና አረጋውያን ማእከል እንዲሁም ለመታጠቢያ አገልግሎት ውሃ ለሚያስፈልጋቸው ተቋማት ሁሉ በቦቴና በተሸከርካሪ ውሃ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ባለ ሥልጣን መሥርያ ቤቱ አስራ አምስት ሮቶዎችን በመግዛት አስራ ኹለት በከተማ እና ሦስት በገጠር ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች በመትከል ሁሉም ወደ ሥራ ገብተዋል ብለዋል።

ሥራ አስኪያጁ እንደገለፁት በክልሉ የገጠር መስተዳድሮች ተበላሽተውና አገልግሎት አቋርጠው የነበሩ የውሃ አቅርቦት መስጫዎች ግብረ ኃይል በማቋቋም የመጠገንና ወደ አገልግሎት የማስገባት ሥራም ተሠርቷል በማለት ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 73 መጋቢት 19 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here