አንጋፋው ሙዚቀኛ ኬኒ ሮጀርስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

0
430

ልክ የዛሬ ሳምንት ማለዳ ላይ ነበር የአንጋፋው ሙዚቀኛና የሙዚቃ ባለሞያ ኬኒ ሮጀርስ እረፍት የተነገረው። የሞቱ ምክንያትም ተፈጥሮአዊ እንጂ በሰሞነኛው ኮሮና ቫይረስ እንዳልሆነ ቤተሰቦቹ ገልጸዋል።

ሆስተን ቴክሳስ ውስጥ ከደሃ ቤተሰብ የተወለደው ኬኒ ሮጀርስ፣ ከቤተሰቡና ከስድስት እህት ወንድሞቹ ጋር ልጅነቱን አሳልፏል። በልጅነት እድሜውም ሙዚቃ መጫወትን ይወድ የነበረ ሲሆን፣ ለራሱ በገዛው ጊታርም ‹ስኮላርስ› የተሰኘ የሙዚቃ ቡድን ከጓደኞቹ ጋር መሥርተው ሙዚቃዎችን እንዳቀረቡ በሙዚቀኛው ዙሪያ የተጻፉ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ከቡድን ውጪ ለመጀመሪያ ጊዜ ‹‹That Crazy Feeling›› የተሰኘ በግሉ የመጀመሪያ የሆነውን ነጠላ ሙዚቃው በ1958 ለአድማጭ አድርሷል። ከዚህም በኋላ በርካታ የሙዚቃ ሥራዎችን ማቅረብ የቀጠለ ሲሆን በርካታ ሽልማቶችንና ክብሮችን አግኝቷል።

ኬኒ ሮጀርስ በ1975 ትኩረቱን በአገረሰብ ሙዚቃ (country music) በማድረግ፣ ‹‹Love Lifted Me›› የተሰኘ ሙዚቃን ለአድማጮች አድርሷል። ይህን ሙዚቃ አስከትሎ ባወጣው ‹‹Lucille›› በተሰኘ አሳዛኝ ታሪክ ያለው ሙዚቃ ምክንያት፣ በጊዜው ተወዳጅ በሆኑ ሙዚቃዎች ዝርዝር ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሥሙ ተቀምጦ ቆይቷል።

በግሉ ከሠራቸው ሥራዎች ጎን ለጎን ከሌሎች ጋር በመጣመር የሠራቸው ሥራዎችም ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝተዋል። ከአሜሪካዊቷ ዶቲ ዌስት እንዲሁም ዶሊ ፓርተን ጋር የሠሯቸው ሙዚቃዎችም በበርካታ ሙዚቃ አፍቃሪያን የሚዘነጉ አይደሉም። በኢትዮጵያም የመዝናኛ ሙዚቃ ግብዣዎች ላይ ከዶሊ ፓርተን ጋር በጋራ የሚጫወቱት ‹Islands In the Stream› የተሰኘው ሙዚቃ ብዙ ጊዜ የሚጋበዝና ተወዳጅ የሆነ ሥራ ነው።

ከሙዚቃ ጎን ለጎን ለፎቶግራፍ ሥራ ፍላጎት የነበረው ኬኒ ሮጀርስ፣ በዓለም ዙሪያ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ ያነሳቸውን ፎቶዎች በመጽሐፍ መልክ አሳትሟቸዋል። የልጆች መጽሐፍም ለንባብ ያበቃ ሲሆን ግለታኩን ጨምሮ ለሙዚቀኛች ልምዱን ያካፈለባቸውና ሌሎችም መጽሐፍትን ለአንባብያን አድርሷል።

በአውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር 2004 ላይ 66ኛ ዓመቱ በያዘ ጊዜ፣ ከአምስተኛ ሚስቱ መንታ ልጆችን ታቅፎ የነበረው ኬኒ ሮጀርስ፣ ቀድሞ ከነበሩት ልጆች ጋር በድምሩ የአምስት ልጆች አባት ነበር። በሥራው ኹለት የግራሚ አዋርድን ጨምሮ በርካታ ሽልማቶችን ያገኘ ሲሆን፣ ሥራዎቹ በዓለም ዙሪያ ተወዳጅነት ያተረፉ ነበሩ። ይህ የማይረሳው ዝነኛና ተወዳጅ የሙዚቃ ሰው በ81 ዓመቱ ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው።

ቅጽ 2 ቁጥር 73 መጋቢት 19 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here