የአበባ አምራቾች በኮቪድ19 ምክንያት ሠራተኞቻቸውን ሊቀንሱ ነው

0
589

ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ 90 በመቶ ቀንሷል

የዓለም ዐቀፍ ስጋት በሆነው በኮቪድ19 ምክንያት በተፈጠረ የገበያ መቀዛቀዝ ምክንያት የአበባ አምራቾች ሠራተኞቻቸውን ከሥራ ሊቀነሱ መሆኑን የኢትዮጵያ አበባ ላኪዎች ማኅበር ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

ድርጅቶች ሠራተኛ ላለመቀነስ ጥረት እያደረጉ መሆኑ የተናገሩት የማኅበሩ ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ዘውዱ፣ ሥራ ባይኖርም ሠራተኞች እንኳን በሥራ ላይ እንዲቆዩ ለማድረግ ሰፊ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አስታውቀዋል።

በገቢ ደረጃም 90 በመቶ ቅናሽ እንዳሳየ ነው ቴዎድሮስ የሚገልጹት። እንዴት እና መቼ ይለወጣል የሚለውን ነገር ለማወቅ የጊዜ ጉዳይ ቢሆንም፣ በእኛ በኩል የቻልነውን ያህል መፍትሔ ለመስጠት ሠራተኞችን ደሞዝ ለመክፈል፣ ለማዳበሪያ እና እጽዋቶቹ እንዳይሞቱ ለማድረግ የሚረዱ አስፈላጊ ግብዓቶችን እየተሟላ ይገኛል በማለት ጠቅሰዋል።

‹‹ምንም እንኳን ኤክስፖቱም ባይኖር ሰብሎቹ መመገብና በሕይወት መኖር አለባቸው። ይህ ካልሆነ ግን እጽዋቱም ይሞታሉ፤ ኢንዱስትሪውም ከባድ ኪሳራ እንደሚገጥመው ግልጽ ነው›› ሲሉም አክለዋል።

በአሁኑ ወቅትም በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች እስከ መቼ ችግሩ እንደሚያበቃ ባይታወቅም የዓመት እረፍት የወሰዱ መሆናቸውን በመግለጽ፣ የዓመት እረፍት የሌላቸውን እንኳን እየከፈሉ መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። በዚህ ከቀጠለ ግን ኢንደስትሪው ሠራተኞችን ለመቀነስና ችግሩን ለመቋቋም እንደ አማራጭ እንደሚወስደው ለመረዳት ተችሏል።

‹‹ነገሮች በዚህ ብቻ ይቀጥላሉ ብለን ተስፋ አናደርግም። በመጪዎቹ ወራቶች ችግሮች ይቃለላሉ ብለን እናምናለን›› ያሉት ቴዎድሮስ፣ ድርጅቶቹ ሥራዎቻቸውን ለማስቀጠል ለሥራ የሚሆን ገንዘብ ከባንኮች ለማግኘት ጥረት ላይ እንደሆኑም ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ኩባንያዎችንም እየተቀዛቀዘ ከመጣው ገቢያቸው አንጻር ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሠራተኛ ሊቀንሱ ይችላሉ። ቢሆንም ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እየተንቀሳቀሱ በመሆናቸው እስከ አሁን ለሠራተኞች እየከፈሉ እንደቆዩ ለማወቅ ተችሏል። አሁን ባለው ችግር ሠራተኛው ለኢንደስትሪው የጀርባ አጥንት ነው። ‹‹ሠራተኛ መበተን አዋጭ መፍትሔ አይደለም።›› ያሉት ቴዎድሮስ፣ በአበባ፣ በአትክልት እና ፍራፍሬ የተሰማሩ ድርጅቶች አሉ። ከእነዚህም ተቋማት ይህ ነው ተብሎ የሚነገር የሠራተኛ ቅነሳ ባያርግም በተለይም መደበኛ ሠራተኛ የቀነሰ ድርጅት የለም ሲሉ ጠቁመዋል።

እስከ አሁን ኹለት ድርጅቶች ብቻ ሠራተኞቻቸውን ለመክፈል ባለመቻላቸው ብቻ ሊቀንሱ እንደተገደዱ እና በቀጣይም ሌሎች ሊከተሉ እንደሚችሉ ታውቋል።
እንደ ችግር የገጠማቸውም ለአብነት ያህል ወደ አውሮፓ የሚላኩት አበቦች ወደ ተለያዩ አገሮች እንዳይደርሱ አብዛኛዎቹ አገራቶች በረራ ማቋረጣቸው እና ድንበሮቻቸውም በመዘጋቱ፣ በዚህም ወደ ውጪ የሚላከው የምርት መጠን 80 በመቶ ቀንሷል። በዋጋ ደረጃም የ60 በመቶ ቅናሽ እንዳሳየ ገልጸዋል።

በአሁን ወቅት ኩባንያዎቹ የአውሮፕላን ዋጋ እንኳን መክፈል እንዳልቻሉ እና በዚህም ችግር ምክንያት የደረሱ አበባዎች ተቆርጠው እየተጣሉ ነው። ሥራውም ፈተና ውስጥ ገብቷል ሲሉ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል። አበባን በመጋዘን ማስቀመጥ አይቻልም። በዚህም ምክንያት ከባድ ኪሳራ ላይ እንደጣላቸው ሳይጠቅሱ አላለፉም።
በተያያዘ የተወሰኑት ኩባንያዎች ከባንክ ተበድረው የሚንቀሳቀሱ ሲሆን፣ የወጪ ንግዱ በማሽቆልቆሉ ለዚህም የብድር አከፋፈሉ እንዲስተካከል የወለድ መጠኑን እና የእፎይታ ጊዜያቸው እንዲራዘም ለማድረግ ሙከራ ላይ መሆኑ ተጠቅሷል።

ከ185 ሺሕ በላይ ሠራተኞችን የያዙት የአበባ እና ፍራፍሬ አምራቾች፣ ከተጋረጠባቸው የገበያ መቀዛቀዝ እንዲያገግሙ ከዚህ ቀደም በብሔራዊ ባንክ በኩል ለዓለም ዐቀፍ ገበያ እንዲያቀርቡ የተተመነላቸው መነሻ ዋጋ በጊዜያዊነት መነሳቱ ታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 73 መጋቢት 19 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here