አራት መቶ ሚሊዮን ብር የተመደበለት የበቆጂ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት መጓተቱ ተገለፀ

0
763

በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን የበቆጂ የውሃ ሥራ ፕሮጀክት መጀመር ከነበረበት ጊዜ በአምስት ወራት መጓተቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለፁ። የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮው ከኹለት ዓመታት በፊት ተጀምሮ የተተወ ቢሆንም በ2012 መጀመሪያ ላይ ግን 400 ሚሊዮን ብር ተመድቦለት መስከረም ላይ ወደ ሥራ እንደሚገባ መግባባት ላይ መደረሱን የአካባቢው ነዋሪዎች አስታውቀው በጥር ወር ላይ እንቅስቃሴ መጀመሩን ጨምረው ገለጸዋል።

ለበቆጂ ከተማ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ለማቅረብ ታስቦ የተጀመረው የውሃ ፕሮጀክቱ በዋናነት የኦሮሚያ ውሃ ቢሮ የሚያስተዳድረው ሲሆን፣ የኦሮሚያ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን በግንባታው እንደሚሳተፍና የክልሉ የውሃ ሥራዎች አማካሪ ቢሮም በአማካሪነት ተሳትፏል።

የግንባታውን መዘግየት በተመለከተ የውሃ ፕሮጀክቱን በግንባታ የሚመራው የኦሮሚያ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ዳይሬክተር ብርሃኑ በቀለ (ኢ/ር) ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ቢሮው ሥራውን ከተረከበበት ጊዜ አንስቶ በተያዘለት ቀነ ገደብ እያከናወነ መሆኑን በመግለጽ ይጀምራሉ። አያይዘውም ከነዋሪው የመጣው የኹለት ጉድጓዶች ቁፋሮ ከኹለት ዓመታት በፊት መጠናቀቁን እና እስከ 2012 ዓመት መጀመሪያ ድረስም ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳልተደረገባቸው አረጋግጠዋል።
ይሁን እንጂ ጥር ላይ ተጀመረ የተባለው መረጃ ሐሰት እንደሆነ እና ግንባታው መስከረም ላይ ተጀምሮ በተገቢው ሁኔታ እየተካሔደ እንደሚገኝ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ሠርቶ ለማጠናቀቅ የአንድ ዓመት ጊዜ ገደብ የተሰጠው የበቆጂ ንጹሕ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት፤ ኹለት የውሃ ማጠራቀሚያ ሲኖሩት ባለ 3 መቶ እና ባለ 5 መቶ ሚትር ኪዮብ ውሃ የመያዝ አቅም እንዳላቸውም ብርሃኑ አስታውቀዋል። ብርሃኑ አያይዘውም በአሁኑ ሰዓት ግንባታው እየተካሔደ እና የማስተላለፊያ ቱቦዎች ዝርጋታም በተገቢው ሁኔታ እየተከናወነ እንደሆነ ጨምረው ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ ከአካባቢው ያገኘችው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ግንባታው ከተያዘለት ጊዜ በላይ ከመዘግየቱ ጋር ተያይዞ በመጪዎቹ ኹለት ዓመታት ይጠናቀቃል ብለው እንደማይገምቱ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ይህን በሚመለከት ብርሃኑ ምላሽ ሲሰጡ፤ ተገቢውን የዕቃ አቅርቦት እና አስፈላጊ ግብዓቶችን ፕሮጀክቱን በባለቤትነት ከሚያስተዳድረው መሥሪያ ቤት የሚቀርብላቸው ከሆነ ከተያዘለት ቀነ ገደብ አስቀድመው እንደሚጨርሱም አስታውቀዋል።

የኦሮሚያ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ቢሮ ከንጹሕ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ባለፈ በፌዴራል መንግሥት በጀት የሚገነቡ ታላላቅ ግድቦችን እና የመስኖ ፕሮጀክቶችን እንደሚሠራ እና ከእነዚህም ውስጥ የአርጆ ዴዴሳ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት ተጠቃሽ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

ክልሉ ባሳለፍነው ዓመት ብቻ የበቆጂ ውሃ ፕሮጀክትን ሳይጨምር ስድስት ፕሮጀክቶችን ይፋ ያደረገ ሲሆን በጠቅላላው የ9 መቶ ሚሊዮን ብር ፕሮጀክቶች እንደሆኑም ታውቋል።

ስድሰቱንም ፕሮጀክት ግንባታ የኦሮሚያ ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን የሚያከናውን ሲሆን ድርጅቱ ባለፈው ዓመት ብቻ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ገቢ ማስመዝገቡም ተገልጿል። በተገነቡት የውሃ ፕሮጀክቶችም በስድስት ሳይቶች ለኹለት መቶ ሰዎች የስራ እድል መፍጠራቸውም ታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 73 መጋቢት 19 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here