የደራርቱ ፍልሚያ ለሰብዓዊነት ነው!!

0
1296

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከታጎሉ እቅዶች መካከል የ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ ይገኝበታል። ከዓመት በፊት ዝግጅት የጀመረችው አዘጋጇ ቶኪዮ፣ ውድድሩ ከነአካቴው እንዳይቀርና ዝግጅቷ ሁሉ ኪሳራ ላይ እንዳይወድቅ ከወዲሁ ሰግታለች። ይሁንና ለጊዜው ውድድሩ ለአንድ ዓመት መራዘሙ አልቀረም። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና ኦሎምፒክ ኮሚቴ በዚህ ላይ የተወሰነ ውዝግብ ውስጥ መግባታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ለቫይረሱ ክብደት ያልሰጡ አትሌቶችና የኦሎምፒክ ኮሚቴ አመራሮች፣ ‹ልምምድ አይቋረጥም› ብለው ተሟግተው ነበር። ግዛቸው አበበ ይህን በማንሳትና በፌዴሬሽኑ በኩል የአትሌት ደራርቱ ቱሉን የ‹ሰብአዊነት ይቅደም› መልእክት በመጥቀስ ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል።

ፊፋ በዚህ ዓመት ግንቦት መጨረሻ ላይ ለጥቂት ቀናት አዲስ አበባ ላይ ሊያካሂድ የነበረውን ስብሰባ ወደ ሌላ ጊዜ አስተላልፏል። በአሜሪካና በአውሮፓ ሊካሄዱ የታሰቡ በርካታ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችና አውደ-ርዕዮች ተሰርዘዋል። ኮሮና ቫይረስ በዓለም ዙሪያ ሕይወትን፣ ሥራንና እንቅስቃሴን እያዘበራረቀ ነው። ኃያላን መንግሥታትና ታላላቅ ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች የሕዝብ መሰባሰቦች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የተከሰተውን ችግር እንደሚያባብሱ በማመን ብዙ ፕሮግራሞቻቸውን ወደ ሌላ ጊዜ አሸጋግረዋል ወይም ሰርዘዋል።

ብዙ አገራት በብዙ መቶዎች ወይም በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችን የሚያሳትፉ፣ ነገር ግን ከወቅቱ ችግር ጋር ሲነጻጸሩ አንገብጋቢነት የሌላቸውን፣ አገራዊ ብሎም ዓለም አቀፋዊ እልቂትን ለማስከተል የሰፋ ዕድል አላቸው ያሏቸውን በርካታ የሥራ መስኮች ዘግተዋል። ኮሮና ቫይረስን በሰፊው ለማሰራጨት ያጋልጣሉ ካሏቸውና ከዘጓቸው የሥራ መስኮች ውስጥ ፋብሪካዎች ይገኙበታል።

ኮሮና ቫይረስ ያስከተለውን ችግር አቅልሎ መመልከትና ችላ ማለት የሥልጣኔ ምጥቀት፣ የሀብት መጠን፣ ወታደራዊ ይሁን ሌላ ዓይነት ኃያልነት የማይገታው እልቂት እንደሚስከትል ዓለም ከጣሊያን እየተማረ ነው። ጣሊያን በየሕክምና ጣቢያዎችና በየቤቱ ዜጎቿ በገፍ ሲሞቱባት ምንም ማድረግ ባለመቻልዋ እያነባች ነው። አንዳንዶች መዳን እየቻሉ በሕሙማን መርጃ መሣሪያዎች እጥረት በተለይም ሐኪሞች ቬንቲሌተር በሚሏቸው የአተነፋፈስ ችግርን የሚያስተካክሉ መሣሪያዎች በበቂ መጠን አለመኖር ብቻ፣ ለሞት ሲዳረጉ ለመታደግ ጣሊያን አቅም አልባ ሆናለች።

ጣሊያን በበሽታው ጥንካሬ ሳይሆን የጊዜ መጠን፣ የመሣሪያና የባለሙያዎች ብዛት ከታመሙ ዜጎቿ ብዛት ጋር ስላልተመጣጠኑ ችግር ውስጥ ተዘፍቃለች። ሌላው ዓለም ዜጎቹ በስፋት ለጥቃት እንዳይጋለጡ ማድረጉ ላይ ተግቶ ይሠራ ዘንድ እያሳሰበችና ከእኔ ተማሩ እያለችም ነው።

ይህን እየሰማን ባለንበት በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በአሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) የተለመደ የማን አለብኝነት መውረግረግ፣ ‹‹ሳንዘጋጅ የቶኪዮ ኦሎምፒክ ወቅቱን ጠብቆ ቢካሄድ ውጤት እናጣና ይቆጨናል›› በሚል የኃይሌ ገብረሥላሴ ውትወታ፣ ‹‹በዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ልምምድ አቁም ሳትባል ለምን ታቆማለህ… ማን ልምምድ አቁም አለህ›› በሚል የአባዱላ ገመዳ ግፊት፣ አትሌቶችንና አሠልጣኞቻቸውን ሰብስቦ ወደ ሆቴል አስገብቶ ልምምድ ለማድረግ ያዙኝ ልቀቁኝ እያለ መሰንበቱን ታዝበናል።

በእርግጥ የአባ ዱላ ገመዳ ‹ማን ልምምድ አቁም ብሎህ ታቆማለህ› የሚል ማፋጠጥ፣ ‹አሜሪካ ውሃ ሙላ ሳትልህ እንዴት የአባይን ግድቡን በውኃ ትሞላለህ?› ብሎ እንደመሟገት ሊቆጠር የሚገባው ነው።

ተወዳጅዋና የወቅቱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተጠሪ፣ አትሌት ደራርቱ ቱሉ ይህን ጭፍንና ማስተዋል የጎደለው አካሄድ በመቃወም ከኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ጋር በሐሳብ ግብግብ ውስጥ ገብታለች። መግባትም ይገባት ነበር። ለአትሌቶቹና ለአሠልጣኞቻቸው ብቻ ሳይሆን ለቤተሰቦቻቸውና ለቀሪው ሕዝብ ስትል ሽንጧን ገትራ መሟገት ነበረባት። ተሟግታለችም። የወቅቱን ችግር ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊነትን አሳንሶ በሚያየው በዚህ የኦሎምፒክ ኮሚቴው ባለሥልጣናት ሙግት በአትሌቶች ላይ አደጋ ተጋርጦ ነበርና።

አንዳንድ ጋዜጠኞች እንደሚሉት ይህ ተራ የቃላት ጦርነት አልነበረም። በሰብዓዊትና በኢ-ሰብዓዊ አመለካከቶች መካከል የተካሄደ ፍልሚያ ነበር። አዎ! ነበረ የሚባለው ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴው ሁሉም ስፖርተኛና አሠልጣኝ ከመሰባሰብ ተቆጥበው የወቅቱን ችግር ያሳልፍ ዘንድ ውሳኔ ስለሰጠ ነው። የአሸብርና የአባዱላ ገመዳ ቡድንም አርፎ እንዲቀመጥ አድርጎታል። ሰብዓዊነት አምባገነንነትንና ማን አለብኝነትን ዘርሮታል።

ከአሸብር (ዶ/ር) እና ከአባዱላ ገመዳ አዛዥ ነን የሚል ማስተዋል የጎደለው አካሄድ በተጨማሪ፣ በጣም አሳፋሪና ሊያነጋግር የሚገባው ሌላ ጉዳይም አለ። ኦሎምፒክ ኮሚቴው የቀጠራቸውና ‹‹አሉ የተባሉ የሕክምና ዶክተሮችና የሥነ-ምግብ ባለሙያዎች›› እየተባሉ የሚወደሱት ምሁራንን እንመልከት። የእነሱ ዓይነት ወይም ከእነሱ የተሻሉ ምሁራንና አዋቂዎች የተባሉ የሰሜን አሜሪካና የአውሮፓ አገራት አትሌቶችን ማሰባሰብ ተገቢ እንዳልሆነ አምነው አርፈው በተቀመጡበት፣ እነ አባዱላ አትሌት ተሰብስቦ ሆቴል ይግባ ሲሉ ለምን ዝምታን መረጡ?

የእነ አሸብር ወልደጊዮርጊስ ኮሚቴ እነሱን ተማምኖ ወይም እነሱን የተማመነ መስሎና እነሱን እንደ ሽፋን ተጠቅሞ አትሌቶችን ሰብስቦ ወደ ሆቴል ለማስገባት ውዝግብ ሲፈጥር ለምን በዝምታ ተመለከቱት? እነዚህ ሰዎች ሌላው ዓለም በተለይም የሰሜን አሜሪካና የአውሮፓ አገራት የእነሱን ያህል የሕክምናና የሥነ ምግብ አዋቂዎችን ስላጡ ልምምድ እንዳቋረጡ አድረግው ለማሰብ የበቁ ትምክህተኞች ሆኑ ወይስ ኦሎምፒክ ኮሚቴው ለሚከፍላቸው ገንዘብ ሳስተውና ኦሎምፒኩ ሲጀመር ወደ ቶኪዮ ከሚሄዱት ሰዎች ዝርዝር ውስጥ እንዳይሰረዙ ፈርተው አትሌቱን ብሎም አገሪቱን የራሷ ጉዳይ ባይ ሆኑ?

ለመሆኑ ስለ 22ኛው ኦሎምፒያድ (ቶኪዮ-202) በወቅቱ ስለ መካሄዱና ለኦሎምፒኩ ስለ መዘጋጀት ከሌሎች አገራት ምን ሲሰማ ሰነበተ? አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) የኬንያና የኡጋንዳ እትሌቶች ተሰባስበው ሥልጠና መግባታቸውን በእርግጠኛነት ተናግረዋል። አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴም ሌሎች አገራት ዝግጅት ጀምረዋል ሲሉ ተደምጠዋል። ከዓለማችን ብዙ አገራት ውስጥ ተለይተው ኬንያና ኡጋንዳ የተጠቀሱት ኹለቱ አገራት በአትሌቲክስ ዘርፍ የኢትዮጵያ ተፎካካሪዎች ስለሆኑ አትሌቶችን ወይም ኢትዮጵያውያንን እልክ በማጋባት የሐሳባቸው ደጋፊ ለማድረግ በማሰብ መሆኑን መጠርጠር አይከፋም።

በሌላ በኩል ግን ከአገራቱም ሆነ ከሌላው ዓለም የዜና ምንጮች የዚህን አባባል ሃቀኝነት ለማጣራት ጉግል ማድረግ የዶክተሩና የአትሌት ኃይሌ አባባል ከየት እንደመጣ ማሰብን ግራ አጋቢ ያደርገዋል። ኬንያ ከማንም ቀድሞ አትሌቶቿ ወደ ውጭ ለውድድር እንዳይሄዱ ዕገዳ የጣለች አገር ናትና በዚህ ረገድ ትዘናጋለች ተብሎ አይጠበቅም። ዶክተሩ የኹለቱን አገራት ጉዳይ ከአንድ የቪዲዮ ኮንፈረንስ እንደሰሙት ነው የሚናገሩት። ነገር ግን ከዚህ ከእሳቸው አባባል ውጭ የኹለቱ አገራት አትሌቶቹ ተሳባስበው ወደ ሥልጠና ለመግባታቸው ማረጋገጫ የለም።

የዓለምና የጃፓን ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች የውድድሩን ጊዜ በማራዘምና ባለማራዘም መካከል ከፍተኛ ግራ ማጋባትና ውዝግብ ውስጥ የሚገኙ ቢሆኑም፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ውድድር በፍጹም አይራዘምም የሚል ማረጋገጫ እንዳገኘ ሆኖ ውሳኔ ላይ መድረሱ ትዝብት ውስጥ የሚጥለው ብቻ ሳይሆን በእልክና በማን አለብኝነት ኃላፊነት የጎደለው ውሳኔ እየወሰነ መሆኑንም የሚያጋልጥ ነው። ይህን በሚመለከት ያለው ሃቅ የዓለም ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከችግሩ ጋር የተያያዙ ነገሮችን አጢኖ ከሳምንታት በኋላ እንደሚወስን እያሳሰበ መቆየቱ ነው። የዓለም ኦሎምፒክ ኮሚቴ ለውሳኔ ዘገየ እየተባለ ባለበት ጊዜ፣ በሳምንታት የሚዘገይ ቀጠሮ በመያዙ ብዙ ወቀሳዎችን ስላስከተለበት መጋቢት 15/2012 ላይ አስቸኳይ ስብሰባ አካሂዶ ቶኪዮ-2020ን በአንድ ዓመት አራዝሞታል።

እነ አሸብር ወልደጊዮርጊስና የእነ ኃይሌ ገብረሥላሴ በትክክለኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ ክርክር ማካሄዱን የፈለጉት ለምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ የግድ መልስ ማግኘት ያለበት ጉዳይ ነው። ነገሩ በውሸት መረጃ እልክ በማጋባት ሕይወትን ለእልቂት የመዳረግ ጉዳይ ነውና በቸልታ ሊታለፍ አይገባውም። ‘የኬንያና የኡጋንዳ አትሌቶች ለሥልጠና ሆቴል/ካምፕ ገቡ እንዴ?’ ተብሎ ለጉግል ጥያቄ ሲቀርብ የሚገኘው መልስ የኬንያ ብሔራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴና (NOCK) አትሌቲክስ ኬንያን (AK) ጥቅምት 2012 ላይ በጋራ በሰጡት መግለጫ ኬንያ አትሌቶቿን ወደ ጃፓን በመላክ፣ ከቶኪዮ ወደ አንድ ሺሕ አንድ መቶ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ከሚገኙት የካይሹ-ሆንሹ ደሴቶች በአንደኛዋ ላይ በምትገኘው ኩሩሜ ከተማ ሰፍረው በዚያ ልምምዳቸወን እንዲደርጉ መታሰቡን ነው።

ይህን መግለጫ የሰጡት የኬንያ ብሔራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዘደንት የሆኑት አትሌት ፖል ቴርጋት ሲሆኑ፣ የአትሌቲክስ ኬንያም ተጠሪም በዚያው ነበሩ። ነገር ግን ዓለምን ባጋጠመው ችግር ምክንያት ይህ ዕቅድ ሊተገበር አልቻለም።

ወደ አሜሪካና ወደ አውሮፓ አገራት ስንመለከት ግን ነገሩ ሌላ ነው። ብዙዎቹ ሙሉ ትኩረታቸውን የወቅቱን በሽታ ወደ መከላከልና ወገንን ወደ ማዳኑ ሥራ ስላተኮረ እንደ ኢትዮጵያው ኦሎምፒክ ኮሚቴ ለውዝግብም ሆነ ለንግግር የሚጋብዝ እንቅስቃሴ ውስጥ አልገቡም። ለዚህ ዓይነት ኋላፊነት የጎደለው ዘመቻ ጊዜአቸውን ሲባክኑ አልታዩም። አሜሪካና እንግሊዝ የቶኪዮው ኦሎምፒክ የሚካሄድበት ጊዜ እንዲተላለፍ ጥያቄ ማቅረባቸው በየመገናኛ ብዙኀኑ እየተሰማ ነው የቆየው።

አሜሪካ ኦሎምፒኩ ቢያንስ በአንድ ዓመት ካልተራዘመ በውድድሩ እንደማትካፈል አሳውቃለች። ሲኤንኤን በዕለተ አርብ መጋቢት 11/2012 በለቀቀው ዜና፣ የመጨረሻው ውሳኔ ባይታወቅም፣ የአሜሪካው ፕሬዘደንት ዶናልድ ትራምፕ የቡድን-7 (G7) መሪዎች ቶኪዮ ኦሎምፒክ እንዲሰረዝ ወይም እንዲራዘም መወያየታቸውን ይፋ አድርጓል። አውስትራሊያና ካናዳ ከወዲሁ ከውድድሩ ራሳቸውን ማግለላቸውን አሳውቀዋል።

እንግሊዝም ከውድድሩ ራሷን ለማግለል እያሰበችበት መሆኑን ተናግራለች። አውስትራሊያ ዘንድሮ ስፖርተኞችን ሰብስቦ ልምምድ ማካሄድ አደገኛ መሆኑን በመጥቀስ ራሷን ማግለሏንና ስፖርተኞችን ለልምምድ መሰብሰብ የሚታሰብ ከሆነም በሚቀጥለው ዓመት ሊሆን እንደሚችል ስታሳውቅ፣ ካናዳ ደግሞ በኦሎምፒኩ መሳተፍ ለኮሮና ተጋላጭነት ያሰፋል ብላለች። የፈረንሳይ የስፖርት ባለሥልጣናት ደግሞ ካለው አሳሳቢ ችግር አንጻር ኦሎምፒኩ የግድ መተላለፍ እንዳለበት ተናግረዋል።
ቶኪዮ-2020ን ያዘጋጀችው ጃፓን ምን አለች?

ጃፓን እስካለፈው ታኅሳስ ወር ለግንባታዎችና ለሌሎች ዝግጅቶች 1.35 ትሪሊዮን የን (12.35 ቢሊዮን ዶላር) መከስከሷን አዘጋጆቹን ጠቅሶ ሲኤንኤን ዘግቧል። የሲኤንኤን ዘገባ ይህ ወጭ በአስቸጋሪ አየር ጸባይ ምክንያት መወዳደሪያ ስፍራቸው ወደ ሌላ ቦታ ለተዛወረው ማራቶንን እና እርምጃ ውድድሮች በሚመለከት በመውጣት ላይ ያለውን ተጨማሪ ወጭ አይጨምርም ብሏል። በኦሎምፒኩና በተያያዥ ጉብኝቶች በ2020 እስከ 90 ሚሊዮን ጎብኝዎችን እንደሚያስተናግዱ ተስፋ አድርገው ደፋ ቀና ሲሉ የከረሙት የጃፓን ባለሥልጣናት፣ ላለፉት ዐስር ዓመታት ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጋቸውን ይናገራሉ። እናም የኦሎምፒኩ በወቅቱ መካሄድና አመለካሄዱ ብቻ ሳይሆን የተከሰተው ችግር በቀላና በቅርቡ እንደሚወገድ የሚያሳይ የተስፋ ጭላንጭል አለመኖሩ፣ ችግሩ ዓመታትን ከወሰደ የቀጣዩ የፓሪስ ኦሎምፒክ መካሄጃ ጊዜ ስለሚደርስ የቶኪዮው ውድድር እንዳይሰረዝ በመፍራት ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ገብተዋል።

እኤአ በ1916፣ በ1940 እና በ1944 በአንደኛውና በኹለተኛው የዓለም ጦርነቶች ምክንያት ኦሎምፒኮች መሰረዛቸውን እያስታወሱም እንቅልፍ አጥተዋል። ሲኤንኤን በዚሁ ዜናው ላይ የጃፓኑ ሽንዞ አቤ ኦሎምፒኩ አንዳችም ጉድለት ሳይኖርበት (የተሳታፊ አገራትና የውድድር ዓይነቶች ሳይጎድሉበት) እንደሚካሄድ የቡድን ሰባትን ድጋፍ አግኝቻለሁ ቢሉም፣ ውድድሩ ከታለመለት ጊዜ ይሸጋገር እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ ግን መልስ ሳይሰጡ ማለፋቸውን ገልጿል። የጃፓን ኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል የሆኑት ኮሪ ያማጉች ኦሎምፒኩ የሚካሄድበት ጊዜ መተላለፍ እንዳለበት ተናግረው፣ ብዙ አትሌቶች ልምምድ ማድረግ የማይችሉበት ሁኔታ ባለበት ጊዜ ኦሎምፒኩን በተቀመጠለት ጊዜ ማካሄዱ የማይታሰብ ነው ብለዋል።

የጃፓኑ የዜና ምንጭ ‘ካዮዶ ኒውስ’ ያካሄደው ጥናት 70 ከመቶ ጃፓናውያን ኦሎምፒኩ በታለመለት ጊዜ አይካሄድም ብለው እንደደመደሙ ያሳያል። አጃንስ ፍራንስ ፕሬስም የአስተናጋጇ የቶኪዮ ነዋሪዎች ከሌሎቹ ጃፓናውያን የተለየ አመለካከት እንደሌላቸው ያሳያል። የብዙዎች የጃፓን የስፖርትና የፖለቲካ ባለሥልጣናት ጸሎት ወቅቱ እንዲራዘም ነገር ግን እንዳይሰረዝ የሆነ ይመስላል። ለዚህም ይመስላል ሽንዞ አቤን ጨምሮ ሌሎች የጃፓን ባለሥልጣናት ስለ ኦሎምፒኩ ዛሬ አንድ ነገር፣ ነገ ደግሞ ሌላ ነገር ሲናገሩ የሚደመጡት። እነዚህ ከወደ ጃፓን የሚታዩ አዝማሚያዎች አትሌቶችን ሰብስቦ ወደ ሥልጠና ለማስገባት የሚገፋፉ አይደሉም።

ስለ ኦሎምፒክ-2020 በውጭ የሚሆነውንና የሚታሰበውን ነገር የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ካወጣው ዕቅድ ጋር በማነጻጸር አንድን ሃቅ ፍንትው አድርጎ ማሳየት ይቻላል። በአሁኑ ወቅት፣ በዚህ ዓለም ላይ በኮሮና ቫይረስ አማካኝነት የተጋረጠውን አደጋ፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ባለሥልጣናትን ያህል አቅልሎ የሚያይና ያየ ማንም የለም።

በዕለተ ሰኞ መጋቢት 14/2012 የአደይ አበባ ስቴዲዮም ግንባታን በሚመለከት በተካሄደ የፊርማ ሥነ-ስርኣት ላይ በተገኙበት ጊዜ፣ የነበረን ሁኔታ በማጤን የጥርስ ሐኪም የሆኑት አሸብር ወልደጊዮርጊስ ችግሩን ከሚገበው በላይ አቃልለው ከሚያዩ ሰዎች መካከል አንዱ መሆናቸውን መረዳት ይቻላል። በዚህ የፊርማ ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት ቻይናውያን ሁሉ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ያደረጉ ሲሆን፣ በቦታው ከነበሩት በርካታ ኢትዮጵያዊ ባለሥልጣናት ውስጥ አንዱ ብቻ ነበሩ ይህን ማስክ ያደረጉት።

አሸብር ወልደጊዮርጊስን ጨምሮ ሌሎቹ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ማስክ አለማድረግ ብቻ ሳይሆን ትከሸ ለትከሸ እየተነካኩና ተቀራርበው ነበር ሥነ ስርኣቱን የሚከታተሉት። ኦሎምፒክ ኮሚቴው በነዚህ ሰዎች እየተመራ ነው፤ የአትሌቶችን ደኅንነት ለመጠበቅ ከፍተኛ ዝግጅት አድርጌአለሁ ሲል የነበረው።
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በሰጠው መግለጫ ላይ ስፖርተኞች የማስተናገዱን ጨረታ ወዳሸነፈው ወደ አምባሳደር ሆቴል ገብተው ለብቻቸው በተወሰኑ የሆቴሉ ክፍሎች ውስጥ እንደሚቆዩ፣ የተለየ ሊፍት እንደሚጠቀሙ ወዘተ… በመግለጽ ስፖርተኞቹ ከሌላው ኅብረተሰብ ርቀው እንደሚቆዩ ይገልጻል። ስፖርተኞቹ ለልምምድና ለሥልጠና ወደ ጎዳናዎች፣ ወደ ስቴዲዮሞችና ሌሎች የአካል ጥንካሬ ሥልጠና መውሰጃ ቦታዎች አይሄዱምን?

እነዚህና እነዚህን መሰል አስፈላጊ ቦታዎችና ሁሉም የሚገለገሉባቸው ቁሳቁሶች እንደ ሆቴሉ ክፍሎች ለእነሱ ብቻ ተለይተው ተዘጋጅተዋል? በሆቴሉ ውስጥም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ለስፖርተኞቹ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡና ገባ ወጣ የሚሉ ሌሎች ብዙ ሰዎችስ አይኖሩምን? ለመሆኑ አሜሪካና አውሮፓ ከአምባሳደር ሆቴል የተሻለ ሆቴልና ካምፕ ስለሌላቸው ይሆን እንደ አሸብር ወልደጊዮርጊስና እንደ አባዱላ ገመዳ ስፖርተኞችን ሰብስበው ማለማመዱን ያልደፈሩት?

የኦሎምፒክ ኮሚቴው ያልተረጋገጠ ሰበብ ደርድሮ ብቻ ሳይሆን ኬንያና ኡጋዳን ካልተረጋገጠ መረጃ ጋር ጠቅሶ፣ የበለጸጉና የሠለጠኑ አገራት የሚያደርጓቸውን የጥቃቄ እርምጃዎች ያላናዩ ያልሰሙ መስለው፣ ስፖርተኞችንና አሠልጣኞቻቸውን ሰብስበን ካላሠለጠንን ሞተን እንገኛለን ባይ የሆኑት ለምን ይሆን? ስለ ወቅቱ በሽታ አስከፊነትና ስለ ‘ኦሎሚፒክ-2020’ ወይም ‘ቶኪዮ 2020’ መጻኢ ዕድል ተቀባይነት ያለው ምክንያታዊ ግምት (Logical Guess) ታሳቢ አድርገው ለተወሰነ ጊዜ፣ ቢያንስ ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ውሳኔውን እስኪያሳውቅ ቆም ብለው መጠበቁን ያፈለጉት ለምንድን ነው?

ስለ አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር)፣አባ ዱላ ገመዳና ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ
በእነዚህ ግለሰቦች የሚመራው ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከአንዴም ኹለት ጊዜ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን ሥልጣን ብቻ ሳይሆን ሕልውናውንም ጭምር ዕውቅና የነፈገ አካሄድ ታይቶበታል። አገራችን በኦሎምፒክም ሆነ በሌሎች አሕጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች የጎላ ተሳትፎ የምታደርገውና ስኬትም የምታገኘው በአትሌቲክስ መሆኑ እየታወቀ፣ የኦሎምፒክ ኮሚቴው አጉራ ዘለል አካሄድ እንደ ቀላል ችግር መታየት የለበትም።

በተለይም የኦሎምፒክ ኮሚቴው መሪ አሸብር ወልደጊዮርጊስ የማን አለብኝነት አካሄድ መላ ሊበጅለት ይገባል። ኦሎምፒክ ኮሚቴው የአገሪቱን አትሌቲክሰ ፌዴሬሽን በምድር ላይ እንደሌለ ቆጥሮ በቀጥታ ከአትሌቶችና ከአሠልጣኞቻቸው ጋር ለመገናኘት መሞከሩ አምባገነናዊ አካሄድ መሆኑ ግልጽ ነው። እናም ይህን መሰሉን አምባገነንነት ሊያራምዱ የሚሞክሩት የኦሎምፒክ ኮሚቴው ባለሥልጣናት ለስፖርቱ ሰላምና ስኬት ሲባል ተገቢ ካልሆነ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ መደረግ አለበት።
ለዚህ ሁሉ የማን አለብኝነት መበረታታት ‘መንግሥት በስፖርት ጣልቃ አይገባም’ የሚለው ዓለም ዐቀፍ መመሪያ ሽፋን ሆኖ እያገለገለ ሊሆን ይችላል። የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ድክመትና ንዝህላልነት መነሻም ይህ ሊሆን ይችላል። ይህ አካሄድ ደግሞ አገሪቱንና ስፖርቱን ወደ ችግር ውስጥ እንዲገቡ እያደረገ ነው። ከስፖርት ጋር በተያያዘ ከተሞችና ስፖርት አፍቃሪዎች ሰላም ያጡባቸው አጋጣሚዎችና በዓለም ዐቀፍ መድረኮች የሚገኙ ድሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆሉ መምጣታቸው፣ የዚህ ማን አለብኝነት የመጀመሪያ ውጤቶች መሆናቸው ሊሰመርበት ይገባል። ማንኛውም ግለሰብ በግሉ ይሁን በኮሚቴ ሽፋን በስፖርቱና በስፖርተኞች ላይ ያሻውን እያደረገ እንዲኖር ሊፈቀድለት አይገባም።

ማንም ይሁን ማን ከአገርና ከሕዝብ በላይ አይደለምና መንግሥት ዝምታውን መስበር ይገባዋል። መንግሥትም ቢሆን ገደብ የሌለው ዝምታው ራሱን ለችግር እንደሚዳርገው መረዳት ይገባዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ዓመት፣ ችግሮች ሲበዙና ነውጦች ከስቴዲዮሞች አልፈው አገርንና ሕዝብን ወደ መበጥበጥ ሲቃረቡ ስፖርቱስ (እግር ኳሱን) አስቆመዋለሁ ሲሉ መዛታቸው አይረሳም።

ይህ ድንገተኛ ዛቻ ‘ሳይቃጠል በቅጠል’ የሚለውን ብሂል ልብ ሳይል የቆየው የመንግሥት ዝምታ ተገቢ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው። በአገሪቱ ውስጥ የሚከሰትን ትንሽ ይሁን ትልቅ ችግር በዝምታ ማየት ራስን ለከፋ አደጋ ከማመቻቸት ተለይቶ አይታይም። ባለው ዓመት በእግር ኳስ ሜዳዎች የጎሉ ችግሮች በተከሰቱባቸው አጋጣሚዎች፣ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ከፍተኛ ባላሥልጣናት ባሉበት የተፈጸሙንና ባለሥልጣናቱ እርምጃ ለመውሰድ ባለመፈለጋቸው የተበረታቱ እንደሆኑ መካድ አይቻልም።

አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) የሚመሩት የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴርሽን ጋር ዐይንና አፍንጫ የሆኑት ለምን ይሆን? ኦሎምፒክ ኮሚቴው ባለፈው ነሐሴ ወር ደብረ ብርሐን ላይ የኹለት ቀን ኮንግረስ ጠርቶ ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ዋና ተጠሪ ብቻ ሳትሆን የራሱ የኦሎምፒክ ኮሚቴው ሥራ አስፈጻሚና የኮሚቴው አባል የሆነችው አትሌት ደራርቱ ቱሉ አለመጋባዟ ይታወሳል።

የስፖርቱ ጉዳይ በግለሰቦች እልከኝነትና ማን አለብኝነት እንዳይጎዳ የፈለገቸው አትሌት ደራርቱ፣ ሳትጠራ በኮንግረሱ መገኘቷም የሚረሳ አይደለም። ይህ ሁኔታ የኦሎምፒክ ኮሚቴውን መሪ የአሸብር ወልደጊዮርጊስን ብቻ ሳይሆን የዚያ ኮሚቴ አባላት የሆኑ ግለሰቦችንም ጭምር ለትዝብት የዳረገ ነበር። በዚህ ኮሚቴ ውስጥ መሰሪነት ያለበት ጨዋታ ሊኖር እንደሚችልም ያሳየ ነው። አትሌት ደራርቱ በስብሰባው ላይ ሳትጠራ ተገኝታ ለምን እንዳልተጠራች ስትጠይቅ፣ ከኦሎምፒክ ኮሚቴው ዋና እና ትንንሽ ባለሥልጣናት መካከል የረባ መልስ መስጠት የቻለ ማንም አልነበረም።

ይህን ደግሞ ሕዝብ በሚገባ ታዝቧል። ሕሊና ላለው ሰው ይህ ትልቅ ቅጣት ነው። በእርግጥ ዕርባና ቢስ ተንኮል ሲፈጸም ለጊዜው ተንኮለኞችን የሚያረካ ቢሆንም ተጠያቂነት ሲመጣ ነገሩ አሸማቃቂና አሳፋሪ ነውና፣ የኮሚቴው አባላት የዘሩትን አጭደዋል። ከሁሉም በላይ ሕዝብ ታዝቧቸዋል፣ ማንነታቸውንም በደንብ አውቋል። ነገር ግን ይህ በቂ አይደለም። ሕጋዊ ተጠያቂነት እንዳለባቸው ማሳየት ተገቢ ነው።

የአሸብር ወልደጊዮርጊስ ቡድን ያሳተመው የኮሚቴው መጽሔትም በወቅቱ ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። የኦሎምፒክ ኮሚቴው አባላት ፎቶ በመጽሔቱ ላይ ሲታተም የደራርቱ ምስል ተቆርጦ ወጥቶ ነበር። ለምን? ጥቃት በመፈጸም ላይ ያለው በደራርቱ ላይ ነው ወይስ እሷ በምትመራው የአትሌቲክ ፌዴሬሽን ላይ? ነገሩ የማጥቃት ጉዳይ ከሆነ፣ ጥቃቱ ያነጣጠረውም በደራርቱ ላይም ሆነ በፌዴሬሽኑ ላይ፣ ችግር የሚፈጠረው በአትሌቶች፣ በአገሪቱና በስፖርት ወዳዱ ኅብረተሰብ ስሜት ላይም ጭምር ነውና ነገሩ መላ ሊበጅለት ይገባል።

አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዘደንት እንደነበሩና በዚህ ጊዜም በፌዴሬሽኑ ውስጥ ትርምስ ሰፍኖ እንደኖረ የሚረሳ አይደለም። ይህ ትርምስ እግር ኳሱን ከመበጥበጥ አልፎ ፊፋንና ካፍን (የዓለምን እግር ኳስ ፌዴሬሽንና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን) ጎትቶ እስከ ማስገባት ደርሶ፣ ፊፋ በአሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) ላይ እርምጃ የወሰደበት ሁኔታ መፈጠሩም አይረሳም።

የፊፋ እርምጃ ግለሰቡን በመቅጣት ሳያቆም የኢትዮጵያን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከፊፋ አባልነት አግዶት ስለነበረ ኢትዮጵያ ከ2010 የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ማጣሪያ ውድድሮች ተሰርዛ ነበረ። ይህ እገዳ የተነሳው እነ አሸብር ወልደጊዮርጊስ ከኃላፊነታቸው ገለል ብለው በእግራቸው ሌላ አመራር መተካቱን ተከትሎ መሆኑን በወቅቱ ነገሩን ይከታሉ ከነበሩ መገናኛ ብዙኀንን መለስ ብሎ በማየት መረዳት ይቻላል። ይህን መሰሉ የአሸብር ወልደጊዮርጊስ የትርምስ ሥራ አሁንም እያገረሸ ሊሆን ስለሚችል፣ መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት በአትሌቶች፣ በአትሌቶቹ አሠልጣኞችና በአገሪቱ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ችግሮች ከወዲሁ ለማስቀረት ሊረባረቡ ይገባል።

አባ ዱላ ገመዳ የሕወሐቱ ኦሕዴድ አባልና ባለሥልጣን ነበሩ። የሕወሐቱ-ኦሕዴድም የእነ አባዱላ ገመዳ ድርጅት ነበር። የእነ አባዱላ ገመዳ ታሪክ ደግሞ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። የበደልና የአፈና፣ የእስራትና የማሳደድ ታሪክ ነው ያላቸው። የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑን ሰበብ እየደረደሩ ለመጫን (ለማፈን) መሞከርም ሆነ የአትሌቶችን ጤንነትና ሕይወት አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ጉዳይን እንደ ቀላል በማየት ጫና ለመፍጠር መሞከር፣ ተቀባይነት ያለው ነገር አይደለም ሊባሉ ይገባል። በዘመነ ሕወሐት/ኢሕአዴግ በእነ አባዱላው ኦሕዴድና ኢሕአዴግ የደረሰው በደልና ግፍ ከበቂ በላይ ነው።

ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ዝግጅት ሳናደርግ ቀርተን ውጤት ብናጣ ይቆጨናል፣ ኦሎምፒክ ኮሚቴውን ወደ መውቀስም ልታመሩ ትችላላችሁ ወዘተ… እያሉ አትሌቶችና አሠልጣኞቻው ያለ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እውቅናና ፈቃድ ወደ ሆቴል እንዲገቡ ለማድረግ ተከራክረዋል። በእርግጥ አትሌት ኃይሌ ለአትሌቲክስና ለአትሌቶች ተቆርቋሪ ሆነው መታየታቸው ከልባቸው ነውን? በአንድ ወቅት አትሌቲክሱ ውጤት አልባ የሆነውና በደሎች በዝተው የአትሌቶች እሮሮ ሰሚ የታጣው፣ የአትሌቲክስ ውጤታችንም እያሽቆለቆለ የመጣው አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከስፖርቱ ጋር ጥሩ ትውውቅ በሌላቸው ሰዎች ስለሚመራ ነው የሚል ጩኸት በርክቶ ነበር።

ይህ ጩኸት ትኩረት ከሳበ በኋላ በተካሄደው ምርጫ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ የፌዴሬሽኑ ፕሬዘደንት ሆነው ተመረጡ። ነገር ግን ብዙም ሳይቆዩ ‹ሥሜ በከንቱ እየተነሳ ነው› በሚል ሰበብ ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ጥለው ወጡ። ጠንካራና እልከኛ አትሌት እንደነበሩ ያስታወሱ፣ የእግር ቁስል ስቃይና የደም መንዠቅዠቅ ሳይበግራቸው ውድድሮችን ጥርሳቸውን ነክሰው ሲያሸንፉ የሚያውቋቸው ብዙዎች ኢትዮጵያውያን፣ አትሌቱ ለሐሜትና ለዘለፋ እጅ ሰጥተው የፌዴሬሽኑን መሪነታቸውን ወዲያ ጥለው ሄዱ መባሉ ስላልተዋጠላቸው ሌላ ምክንያት ማፈላለግ ጀመሩ።

እናም በአዲስ አበባ፣ በደቡብ ኢትዮጵያና በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ከተሞች የሚያስፋፉት ዘርፈ ብዙ ኢንቨስትመንት ጊዜና ፋታ ስለማይሰጣቸው አትሌቲክሱን ገሸሽ አድርገውት ይሆን ሲሉ ለመጠየቅ ተገደዱ። የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከአንዴም ኹለት ጊዜ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን እንዲሁም የፌዴሬሽኑን ተጠሪ አትሌት ደራርቱ ቱሉን ገሸሽ ማድረጉ አሳዛኝና የማይጠበቅ ነገር ቢሆንም፣ የዚህ ኮሚቴ ምክትል አለቃ የሆኑት አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴና ሌላውን ታዋቂ አትሌት ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም የዚህ ስፖርተኞች ባልሆኑ ሰዎች የተሞላ ኮሚቴ ተባባሪዎች ሆነው መገኘታቸው አሳፋሪ ነገር ነው።

የእንጀራ በር በከፈተላቸው፣ ባለ ጸጋ ለመሆን ባበቃቸው፣ የአገር ኩራት አድርጎአቸው ሥማቸውን ባስጠራላቸውና በአትሌቲክስ ስፖርት ላይ በጠላትነት የተሰለፉ የሚያስመስላቸውን አቋም የያዙት ለምን ይሆን?

እነኃይሌ ከማንም በላይ ለአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ፣ ለደራርቱ ቱሉ፣ አትሌቶቻችንና ለአሠልጣኞቻቸው በጣም የሚቀርቡ ቢሆንም፣ ከአሸብር ወልደጊዮርጊስ እና ከአባ ዱላ ገመዳ ጋር ግንባር ፈጥረው ለአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑና ለባለሙያዎቹ ጀርባ መስጠታቸው ክህደት ነው ወይስ አድር ባይነት? ጊዜ መልስ ይሰጠን ይሆናል። ከኮሮና ጋር የተጀመረው ግብግብ በድል ሲጠናቀቅ!!

ግዛቸው አበበ / gizachewabe@gmail.com

ቅጽ 2 ቁጥር 73 መጋቢት 19 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here