ሰዎች አንድ መሆናቸውንና የዘር፣ የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የቀለምና የማንነት ወዘተ ልዩነቶች፣ ልዩነት ብቻ እንጂ የሚያበላልጣቸው እንዳይደለ የሚረዱበት አጋጣሚ ጥቂት ነው። አንድ ሆኖ ለመቆም ከሰላሙ ጊዜ ይልቅ የመከራውን ዘመን መርጠዋል፤ መርጠናል። እናም አሁን ይኸው ኮቪድ19 የተባለ የኮሮና ቫይረስ፣ ለዐይን ፈጽሞ የማይታይ ደቃቅ ሕዋስ፣ በአንድ ጀንበር ዓለምን አንድ አድርጎት ተመልክተናል።
ይህ በመተሳሰብና በመተጋገዝ የታየ የዓለም አገራት አንድነት፣ እድሜው እንዲያጥር ባንፈልግም፣ ቫይረሱ ግን ቶሎ እንዲጠፋ የሁላችን ምኞትና ተስፋ ነው። ጉዳቱን ለመቀነስም ከወዲሁ ሁሉም ሰው ጥንቃቄ በማድረግ፣ እርስ በእርስ በመተጋገዝና በመረዳዳት መያያዝ ይኖርበታል።
‹‹የበሽታ እንኪ እንካ የለውም›› የሚል ብሂል አለ። የቤተሰብ አባላት የሆኑ የቅርብ ሰዎቻችንን፣ ጓደኛችንን፣ የትዳር አጋራችንን፣ ልጆቻችንን ምንም ያህል ብንወዳቸው፣ ከክፉ ይጠብቀንና፣ ቢታመሙ እንኳ በሽታውን ተቀብለን ልንታመምላቸው አንችልም። እኛ ብንታመምም እነርሱ ተቀብለው ሊታመሙልን አይችሉም። ከመጣና ካልተጠነቀቅን ሁላችን በቫይረሱ ከመያዝ የማንተርፍ መሆኑ ግልጽ ነው።
በጣልያንና በሌሎች የአውሮፓ አገራት የሆነው ተመሳሳይ ነው። መዘናጋት ከፍተኛ ዋጋ እንዳስከፈለ ጣልያናውያን ባለሥልጣናት ሳይቀሩ ሲናገሩ ነበር። የመረጃ አሰጣጥ ክፍተትና መዛባት ያደረገው አስተዋጽኦ ቀላል ባይሆንም፣ ‹እኛ ጋር አይደርስም…አይነካንም› የሚል መታበይ አገሪቱን እንደጎዳት ግን ከማንም የተሸሸገ አይደለም።
በአገራችን ኢትዮጵያም ቫይረሱ ከታየ ከራርሟል። መንግሥትም ይህን ተከትሎ ተቋማት እንዲዘጉ፣ ትምህርት ቤቶች እንይከፈቱና በተቻለ መጠን ሰዎች በቤታው እንዲቆዩ አዟል። ካልተቻለም በሙሉና ከፍተኛ በሆነ ጥንቃቄ እንድትንቀሳቀሱ ሲል አሳስቧል። ይህ ደግሞ የተወሰነ ይሆናል ብለን ብናስብም፣ ላልተወሰነ ጊዜ በቤታችን እንድንሰበሰብ የሚያደርገን ነው። እናም በቤት ውስጥም ቢሆን ታድያ ጥንቃቄው ሊለየን እንደማይገባ ነው ባለሞያዎች እያሳሰቡ የሚገኙት።
ታድያ የሕክምና ባለሞያዎች የሚናገሩትን መስማትና መተግበር ቀዳሚው ነው። ቤት ውስጥ ሳል ያለበት፣ የሚየስነጥስና ጉንፋን የያዘውን ሰው በተቻለ ርቀት ማስተናገድ ተገቢ ነው። በሽታውን ቀላል አድርጎ ማየትም ትክክል አይደለም። በተለይ በማስታመምና በመንከባከብ የሚያገለግሉ ሰዎች፣ የበለጠውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይጠበቃል።
ከወንዶች በበለጠ ደግሞ እንክብካቤ በመስጠት እንዲሁም በነርሲንግ ሥራ ላይ የሚገኙት ሴቶች እንደመሆናቸው፣ ከሴቶች ያንን ጥንቃቄ መጠየቃችን አይቀርም። አሁን ላይ በአገራችን ያለው የቫይረሱ ስርጭት ስጋት ላይ አይጥልም ብለን ብናስብ እንኳ፣ ያለንበት ሁኔታ የእነ ጣልያን ዋዜማ ነውና፣ የሚሆነው እንደማይታወቅ ማስታወስ አስፈላጊ ነው።
መንግሥት በየዘርፉና በየቦታው እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች የሚያሳዩት፣ ቫይረሱ ከኹለት አሃዝ ልቆ ሊዳረስ እንደሚችል ነው። ይህ ለጥንቃቄ የሚወሰድ እርምጃ ብዙ ኪሳራዎችን የሚያስከትልና ብዙ ወጪ የሚያስወጣ መሆኑም ግልጽ ነው። ይህ ሁሉ ድካም ለከንቱ እንዳይሆን ደግሞ፣ ከዜጎች የሚጠበቀውን ሳይሰስቱና ሳይዘናጉ ማድረግ ያስፈልጋል።
ሴቶች በዚህ ላይ ድረሻቸው ቀላል አይደለም። ይህን ክፉ ቀን እስኪያልፍ ድረስ፣ በመረዳዳት፣ በመተጋገዝና ሐሳብ በመለዋወጥ፣ የሚገባውን ጥንቃቄ ሁሉ በመተሳሰብ በማከናወን መጠበቅ ጠቃሚ ነው። የጤና አገልግሎትና ሽፋን ከፍተኛ ደረጃ ደርሶባታል በምትባል ጣልያን ቫይረሱ ያስከተለው ጥፋት፣ ኮሌራን እንኳ በቅጡ መቆጣጠር ላልቻለች ኢትዮጵያ የሚዲርሰውን ጉዳት መገመት አስፈሪ ነው።
ለዚህም ነው ተባብሮና ተጋግዞ፣ ተሳስቦም ጥንቃቄን ማስቀደም የሚገባው። የሕይወት ጉዳይ ነውና፣ መስነፍም መዘናጋትም ያስጠይቃል። ሁላችን እያንዳንዳችን ስለየራሳችን ብቻ ሳይሆን፣ አንዳችን ስለሌላችንም ጭምር ስለሆነ፣ ከማስተዋል አንታቀብ። መድኃኒቱ እስኪገኝ ለጊዜው ያለው መድኃኒት የእኛ ጥንቃቄ መሆኑን አንዘንጋ!
መቅደስ /ቹቹ/


