የግል ድርጅቶች የሠራተኞችን ጡረታ በተገቢው መንገድ እያስገቡ አይደለም

0
628

የግል ድርጅቶች የሠራተኞቻቸውን የማኅበራዊ ዋስትና ገንዘብ በተገቢው መንገድ እየከፈሉ እንዳልሆነ የግል ድርጅቶች የማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ። ከዚህ ቀደም ይህን መሰል ችግሮች በተደጋጋሚ ይስተዋሉ የነበረ ሲሆን፣ ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን ኤጀንሲው ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።
ተገቢውን ክፍያ የማይፈጽሙ ድርጅቶች አሁን በከፍተኛ ሁኔታ መበራከታቸውን ገልፀው እንደተቋም ተገቢውን ሂደት እየተከተልን ነው በማለት የኤጀንሲው የምዝገባና የአበል ክፍያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ቅዱስ ሐጎስ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። እንደዚህ ዓይነት ተግባር ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችን ከሠራተኞቻቸው በሚመጣ ጥቆማ መሰረት ኤጀንሲው ለመያዝ እና ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚንቀሳቀስ ቅዱስ አስረድተዋል።

ኤጀንሲው በሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሰረት ጥቆማዎቹ ከመጡ በኋላ ደርጅቱ እስከ አሁን ያሉትን የክፍያ ማስረጃ በመጠየቅ እንዲያቀርብ የሚጠይቅ ከፍ ሲልም የሚያስገድድ ሲሆን፣ በመቀጠል ትክክል መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ በቅድምያ የክፍያ ማሳወቂያ ጊዜ አምስት ቀናት የሚሰጡት እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል።

ከዚህም ባለፈ ለሁሉም ባንኮች ደብዳቤዎችን በመጻፍ እና በማሳወቅ ድርጅቱ ያለውን እዳ ተቀማጭ ካደረገው ገንዘብ ላይ እንዲቀንስ ይደረጋል ሲሉ ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። ነገር ግን ይህም ካልሆነ እና ተገቢውን ክፍያ መፈጸም ካልቻሉ፣ ኤጀንሲው የተቋሙን ንብረት ወደ ማጣራት እንደሚገባ አስታውቀዋል።

የሠራተኞች የማኅበራዊ ዋስትና ጋር በተያያዘም ይህ የማኅበራዊ ጡረታ ተፈፃሚነት እንዲኖረው በመጀመሪያ መዋጋት ያለበት ሠራተኛው ሲሆን፣ ከዛ መለስ መንግሥት እየተከታተለ ተፈፃሚነቱን ማረጋገጥ አለበት ሲሉ የሕግ ባለሙያው አመሃ ጌታቸው ይናገራሉ። አሠሪዎች ይህን አለማድረጋቸው በወንጀል የሚስቀጣ አይደለም ያሉት የሕግ ባለሙያው፣ የሠራተኞቹን የጡረታ ዋስትና ተጠራቅሞ ከቅጣት ጋር እንዲከፍሉ እንደሚደረግ ይናገራሉ።

እንደ ኤጀንሲው ገለጻ፣ የማኅበራዊ ዋስትና ክፍያዎችን በማይከፍሉ ድርጅቶች ላይ በየወሩ መክፈል የሚገባቸውን የገንዘብ ጨምሮ የገንዘቡን 5 በመቶ ተጨማሪ ቅጣት እንደሚኖርባቸው ለማወቅ ተችሏል።

በተጨማም የሕግ ባለሙያው እና አማካሪው ወንድወሰን አሰግደው ለአዲስ ማለዳ በሰጡት አስተያየት፣ የግል ድርጅቶች ይሄን አለማድረጋቸው በፍትሐ ብሔርም በወንጀልም ሊጠየቁባቸው እንደሚገባ ይጠቁማሉ።

የግል ሠራተኞችን ማኅበራዊ ዋስትና በተመለከተ በአዋጅ ቁጥር 715/2003 ላይ ከሠራተኛው ሰባት በመቶ፣ ከአሠሪው ደግሞ 11 በመቶ ተቆርጦ በየወሩ ለኤጀንሲው ገቢ እንዲደረግ ያስገድዳል የሚሉት ወንድወሰን፣ አንቀፅ 11 ንዑስ ቁጥር 3 ላይ ከሠራተኞች ላይ ተቀናሽ ተደርጎ ነገር ግን ለኤጀንሲው ገቢ ካልተደረገ ራሱ ድርጅቱ እንዲከፍል ይደረጋል። በመቀጠል ገቢ ሳይደርግ 3 ወር ያለፈ ከሆነ ደግሞ ኤጀንሲው ከግል ድርጅቱ የባንክ ሂሳብ ላይ ተቀናሽ እንዲሆን ማድረግ ይችላል ብለዋል።
ይህ ካልሆነና እና የባንክ ሂሳባቸው ቢቀየር እና ገንዘብ ሳይኖረው ቢቀር .፣ ሳያሳውቁ ቢቀሩ በአንቀፅ 11 ንዑስ ቁጥር 9 ላይ ንብረታቸው በጨረታ ተሸጦ ገቢ እንዲሆን ሕጉ ይደነግጋል ሲሉ ይናገራሉ።

ከዛ በተጨማሪም የግል ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች ደግሞ በሥማቸው ከደሞዛቸው ላይ እየተቆረጠ የሚቀመጥ (ገቢ የሚደረግ) ስለመሆኑ በማንኛውም ሰዓት የማረጋገጥ እና የመጠየቅ መብት አላቸው።

በዚሁ አዋጅ ስር የተቀመጠው ድንጋጌ በአንቀፅ 59 ላይ የአዋጁን ድንጋጌዎች ያሰናከለ ሰው በ1997 በወጣው የወንጀል ሕጉ መሰረት እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ ፅኑ አስራት እና ከእስራቱ በተጨማሪ ደግሞ እስከ 10 ሺሕ ብር የሚደርስ የገንዘብ መቀጮም እንደሚጠብቀው የሕግ ባለሙያ እና አማካሪው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 73 መጋቢት 19 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here