አዲሱ የሥራና ሠራተኛ አገናኝ መመሪያ ተግባራዊ አልተደረገም

0
972

የኢትዮጵያ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከታኅሳስ 22/2012 ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን ለክልሎችና ለከተማ አስተዳደሮች ያስተላለፈው አዲሱ የሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ መመሪያ በአገናኝ ኤጀንሲዎች እየተተገበረ እንዳልሆነ ተገለጸ።

የኢፌዴሪ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጄንሲዎች በአገር ውስጥ የሥራ ስምሪት አገልግሎት ስለሚሰጡበት ሁኔታ ለመወሰን ያወጣውን አዋጅ፣ ክልሎች ተግባራዊ እንዲያደርጉ መመሪያውን ቢያስተላልፍም፣ በኤጀንሲዎች ዘንድ ቅሬታ በመፈጠሩ መመሪያውን ተግባራዊ እያደረጉት አለመሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

ከዚህ በፊት የነበረው የአገር ውስጥ የግል ሥራና ሠራተኛ ስምሪት መመሪያ፣ የአሠሪ አገናኝ ኤጀንሲዎች ድርሻ 30 በመቶ እና የሠራተኛ 70 በመቶ ነበር። ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ አዲስ ያወጣው መመሪያ ደግሞ የአሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ኤጄንሲዎች ድርሻ ከ30 በመቶ ወደ 20 በመቶ እንዲሆን እና በተመሳሳይ የሠራተኞች ድርሻም ወደ 80 በመቶ ከፍ እንዲል ማድረጉ ታውቋል።

የኢፌዴሪ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደረጀ ታዩ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ አዲስ መመሪያ የተዘጋጀው በአሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በኩል ወደ ሥራ የሚገቡ ሠራተኞች ‹ከምናገኘዉ ገቢ ለአገናኝ ኤጀንሲዎች የሚገባው 30 በመቶ እየጎዳን ነው› በሚል ያቀረቡትን ቅሬታ ለማስታረቅ ነበር።

ይሁን እንጅ የአገር ውስጥ የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች አዲስ የተሻሻለው መመሪያ ይጎዳናል በማለታቸው ቅሬታ አስነስቶ እንደሚገኝ እና አንዳንድ ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ሠራተኞችን እንበትናለን ማለታቸውን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክትሩ ጠቁመዋል። አገናኝ ኤጄንሲዎች ጥቅማችን ተነካ በማለት ባነሱት ቅሬታ ምክንያት፣ በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ እና በአገር ውስጥ ሥራና አሠሪ አገናኝ ኤጀንሲዎች መካከል አሁንም ድረስ አለመግባባት ፈጥሮ እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 በአንቀጽ 171/1/1 እና በአንቀጽ 174 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት፣ መመሪያውን እንዳወጣ ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሰው ኃይል ጥናትና ሥራ ስምሪት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አበበ ኃይሌ ናቸው። አበበ ኤጀንሲዎች ያቀረቡት ቅሬታ ከዚህ ቀደም ሲያገኙት የነበረው ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ስለቀረባቸው ነው ሲሉ ተናግረዋል።

አክለዉም ኤጀንሲዎች እስከ አሁን ሲሠሩበት የነበረው አሰራር የሠራተኞችን ጉልበት ያለአግባብ ከመበዝበዝ ተግባር የሚተናነስ እንዳልነበር ጠቅሰው፣ የሚያቀርቡት ቅሬታ ተገቢ ያልሆነና መመሪያውን ሊቀይር እንደማይችል ተናግረዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያወጣውን እና ተግባራዊ እንዲሆን ለክልሎች የተላለፈው አዋጅ የማይስማማቸው ኤጄንሲዎች ካሉ፣ የሚኖራቸዉ የመጨረሻ አማራጭ የሥራ ፈቃዳቸዉን ለሰጣቸው አካል መመለስ እና ሥራ ማቆም እንደሚሆንም አበበ ጠቁመዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይሄን ይበል እንጂ ኤጀንሲዎች አዲሱን አዋጅ ተግባራዊ እያደረጉ እንዳልሆነ አዲስ ማለዳ ያናገረቻቸዉ ኤጀንሲዎች ተናግረዋል። ስብሐትና ልጆቹ የአገር ውስጥ ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ያወጣውን መመሪያ ተግባራዊ እንዲያደርግና በአምስት ቀናት ውስጥ በሥራ ላይ እንዲያውል ትዕዛዝ ቢሰጠውም፣ ተግባራዊ እያደረገ እንዳልሆነ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

ሌላኛው የኤጀንሲ ሥራ የሚሠራ ሥሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ግለሰብ ኤጀንሲዎች አሁንም በበፊቱ አዋጅ እየሠሩ መሆኑን ለአዲሰ ማለዳ ጠቁሟል።
እንዲህ ዓይነቱ ችግር ሁሌም እንዳለ እና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም የሚደርሱት መረጃዎች እንዳሉ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ጠቅሰዋል። የችግሩ ተጋላጭ የሆኑት ግለሰቦች በአዋጁ መሰረት የሚደርስባቸውን ችግር ማጋለጥ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

ኃላፊዉ አክለውም ኤጀንሲዎችን የመከታተል የመንግሥት ክፍተት እንዳለ እና የኤጀንሲዎችን ሕገ ወጥነት ለመከላከል ግለሰብ ሊዋጋቸዉ የማይችላቸው እና ጥቅማቸው ሲነካ በግለሰብ ሕይወት ላይ አደጋ የሚያደርሱ ናቸው ብለዋል። ኃላፊው አክለውም አንዳንድ ኤጀንሲዎች በባለሥልጣኖች በእጅ አዙር የተቋቋሙ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ለመቆጣጠር ያለውን አስቸጋሪነት ጠቁመዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 73 መጋቢት 19 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here