ዘመነ ዐቢይ የፖለቲካዊ ማሻሻጥ ዘመን?

0
711

በምዕራቡ ዓለም የፖለቲካ ማሻሻጥ ሥራ በወጉ ተጠንቶ መተግበር ከጀመረ መሰነባበቱን የምትነግረን ቤተልሔም ነጋሽ፥ የፖለቲካ ማሻሻጥን ምንነት እና በአገራችን እያቆጠቆጠ ይሆን የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የተለያዩ ምሳሌዎችን በመጥቀስ የሚከተለውን ታስነብበናለች።

ባለፈው ሰሞን ጠዋት ላይ በማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛዎች (በፌስቡክና ትዊተር) የተለቀው “ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ እንደምን አደራችሁ?” የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትራችን ያማረ ፎቶ ያለበትን መልዕክት ተመልክታችሁታል? ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ አሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ሲጓዙ የለበሷቸው፣ በባሕላዊ ጨርቆች የተሠሩ ዘመናዊ ኮቶችንስ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ቦታዎች ያደረጓቸውን ንግግሮችስ? ለደሀ ተማሪዎች ቦርሳዎችን ማደላቸውስ? በመቄዶንያ ተገኝተው ከወደቁበት በበጎ አድራጊዎች የተነሱትን አዛውንት እና የአዕምሮ ሕሙማን ሲጎበኙስ? ከሳኡዲ ዐረቢያ ከእስር የተፈቱ ኢትዮጵያውያንን በጫነ አውሮፕላን አብረው ሲመጡ የነበረውስ? ሌላውም ሌላውም ሲታወስ የምርጫ ዘመቻ ላይ ያሉ ፖለቲከኛ እንጂ አዲስ መሪ አይመስሉም። የሚያከነውኑት ተግባር ትክክልና ከጥሩ መሪ የሚጠበቅ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፥ ምናልባት አቀራረባቸውና ሁኔታቸው ከአንድ አንግል ብቻ እንድናያቸው ለማድረግ ታስቦ የሚከናወን ቢሆንስ? ባጭሩ – የማሻሻጥ (‘ማርኬቲንግ’) ሥራ ቢሆንስ?
ከዓመታት በፊት ለትምህርት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ሊቨርፑል ሳቀና በከተማዋ ከተቀበሉኝ መካከል በየቀኑ ወደ ክፍል ስገባ በአጠገቡ የማልፈው ትልቅ ቢልቦርድ ይገኝበታል። በጣም ትልቅና የሚያምሩ ቀለማት የሞሉበት የሕፃን ፊት የሞላው ፖስተር። ከሥሩ በትንሹ እንዲህ የሚል ተጽፏል “የእማማ ዓይን፣ የአባባ ፀጉር የጎርደን ብራውን ዕዳ”። ነገሩ የፖለቲካ ማስታወቂያ መሆኑ ከኮንዘርቫቲቭ ፓርቲ ተቀናቃኙን ሌበርን ለማሳጣት የተጠቀመበት መሆኑ ሲገባኝ የፈጠራ ችሎታቸውን ማድነቄን አስታውሳለሁ።
በምዕራቡ ዓለም ለዘመናት ፖለቲከኞች ባሉበት ሳይገኙ ቀርተው ፖለቲካ በሰዎች ተአማኒ ለመሆን፣ ሐሳባቸውን ከሚሰርቁ ከቢራ ማስታውቂያ እስከ የቲቪ ድራማና ቅናሽ ምርቶች ግዙ ውትወታ፣ ብዙ ተቀናቃኝ ጉዳዮችና ተፎካካሪ ፖለቲከኞች ልቆ ለመገኘት የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። ደረቅ ፕሮፖጋንዳ የመሰማት ዕድሉ ካከተመ ቆየ። ቀለል ያለ ቋንቋ፣ በርካታ እነሱ “ስፒን ዶክተሮች” የሚሏቸው ሳተና ጸሐፊዎች የሚያዘጋጁት የሰውን ትኩረት የሚስብ ማስታወቂያና ማግባቢያ ይጠቀማሉ። ፖለቲከኛውን ሲያሻሽጡ፣ እንደምርት ሁሉ ‘በምን ተጠቅሎ ቢቀርብ፣ እንዴት ቢለብስ፣ የት ቢሔድ፣ ምን ቢያወራ፣ እንዴት ቢራመድ፣ ምን ቢያደርግ በሕዝብ ዘንድ አመኔታና ተቀባይነት ያገኛል?’ የሚለው ታስቦበት ታቅዶ መሠራቱ ሳይንስም ሆኗል። የፖለቲካ ማሻሻጥ የሚል ሥያሜ ተሰጥቶታል።
የፖለቲካ ማሻሻጥ ከአንድ ዐሥርት ዓመታት በፊት የመጣ፣ በፖለቲካ ሳይንስ ውስጥ እንደ ንዑስ ክፍል ተደርጎ የሚታይ፣ በአንፃራዊ መልኩ አዲስ የሚባል ሥነ ጥናት ነው። ሐሳቡም የማሻሻጥን ቴክኒኮችንና ፅንሰ ሐሳቦችን ለፖለቲካ ተግባር ማዋል ነው። የፖለቲካ ምኅዳሩን አንድ ምርት ገበያውን ሰብሮ እንዲገባ ለማድረግ ከሚተገበሩ የማሻሻጥ ሥራዎች ጋር በሚመሳሰል መልኩ ሰንጥቆ እንደመግባት ነው። ይህ ዓይነቱ ፖለቲካ ከፓርቲ እስከ መሪውና ቤተሰቡ አሽሞንሞኖ ለብዙኃኑ በመሸጥ የረባ ሐሳብ የላቸውም ወይም ፅንፈኛ ሐሳብ ያራምዳሉ የሚባሉ ፖለቲከኞች ሳይቀር ተቀባይነት እንዲያገኙ ለማድረግ የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው። ይሔ ገጸ መለያ መፍጠር (‘ብራንድ’ ማድረግ) ወይም እንደ ምርት ሁሉ የተጠና ቀለምና መለያ ተመርጦ ተከታታይ መልዕክቶችን ማስተላለፍና የአንድን ፖለቲከኛ አባባልና መልካም ምሳሌነት በማጉላት በሕዝብ ዘንድ ያለው ሁሉ እንዲታመን የሚቻል ባለግርማ ሞገስ መሪ (‘ካሪዝማቲክ ሊደር’) እንዲሆን ማድረግ ነው።
ይህንን ስል ባለፉት ሰባት ወራት፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት ከላይ በመግቢዬ የዘረዘርኩትን ጨምሮ የሴት ሚኒስትሮች በተመሳሳይ የባሕል ልብሶች የታጀበ ፎቶ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የራሳቸው ባማረ ፎቶግራፍ የታጀበና ንግግራቸው በትዕምርተ ጥቅስ ያለበት ፎቶ፣ ተመሳሳይ ፓርቲና ስርዓት መኖሩን እስክንዘነጋ ድረስ እንደገና ‘በአዲስ መጠቅለያ እና አቀራረብ እየተጠቀለለልን ነውን?’ የሚል ሐሳብ የሚያጭሩ፥ ‘የፖለቲካ ማሻሻጥ ነገር አገራችን ገባ እንዴ?’ የሚለውን ጥያቄ የሚያስከትሉ ክስተቶች መከናወናቸውን ደግሜ ለማስታወስ እወዳለሁ።
የፖለቲካ ማሻሻጥ ፅንሰ ሐሳብን በትንሹ ለማፍታታት፣ በአገራችን እያየን ያለነው ከዚህ ጋር ይያያዛል የሚለውን ለመፍረድም እንዲመች የፖለቲካ ማርኬቲንግ በውስጡ የሚይዛቸውን ተግባራት በኦክላንድ ዩኒቨርሲቲ ይህንኑ ለማብራራት ከወረበው ጽሑፍ እንደሚከተለው ቀንጭቤ ለማየት ሞክሬያለሁ።
የፖለቲካ ማሻሻጥ የሚከናወንበትን ስልት ማውጣት (‘አጠቃላይ ሥራው እንዴት ይመራል? ማን ምን ይሠራል?’ የሚለውን የሚዘረዝርና አጠቃላይ ሥራው የሚመራበት)፣ የፖለቲካ ገበያውን በሚመለከት የዳሰሳ ጥናት ማካሔድ (ሰዎች ማለትም ደጋፊዎችና ሌሎች የፖለቲካ አቋማቸው ምን ይመስላል? ምን ይወዳሉ? ምን ይጠላሉ? የሚለውን ለማወቅና በዚያ ላይ ተመሥርቶ ውሳኔ ላይ ለመድረስ)፣ የፖለቲካ ገጸ መለያ ማውጣት (ከቀለም ጀምሮ አንድ ፓርቲና መሪው/ዎቹ የሚጠቀሙባቸውን ቃላት አገላለጾች፣ ተናጋሪዎች የሚተዋውቅባቸውን መንገዶች፣ ወዘተ. የሚያካትት)፣ የውስጥ ፖለቲካ ማሻሻጥ የሚካሔድበትን ዘዴ መወሰን፣ የፖለቲካ ማሻሻጥ ተግባቦት ሥራዎችን ማከናወን (የመንግሥት በኽዝብ ዘንድ ያለውን ገጽታ ማሻሻል/መገንባት፣ አዲስ የገጸ መለያ ቀለማትን ማውጣት፣ ወጥነት ያላቸው ተከታታይ መልዕክቶችን፣ የተለያዩ ብዙኃ መገናኛዎችን በመጠቀም ለሕዝብ ማጋራት፣ ከተፎካካዎችም ሆነ ከሌሎች በመንግሥት ላይ የሚሰነዘሩ አሉታዊ አስተያየቶችን የሚያፈርሱ መልዕክቶችን መላክ፣ ወዘተ.) ናቸው።
ይሄ መሪን አድምቆና አጉልቶ፣ መልካም ሰው፣ ሩህሩህ፣ ለአገር የሚያስብ፣ የተጎዱትን የሚረዳ፣ ከራሱ ይልቅ ሌሎችን የሚያስቀድም፣ ሳምራዊ አድርጎ የመሳሉ ነገር፥ ሰውየው ሰው መሆኑን እና የሚያደርገውም ነገር የሚጠበቅበትን መሆኑን ረስተን ገንቢ ትችት ለመስጠት እስኪያዳግተን ስሜታዊና በፍቅሩ የወደቅን እስካላደረገን ድረስ ምንም አይደል ልንል እንችላለን። ነገር ግን ፉክክሩና የንግድና ማሻሻጥን ሐሳብ በቀጥታ ፖለቲካ ላይ መተግበሩ በበዛ ቁጥር የሚታየው ላይ እያተኮሩ ፖሊሲውና ሐሳቡ ላይ መወያየትና የተሻለ ሐሳብ ያለውን የመምረጡ ነገር ላይ ተፅዕኖ ሊያመጣ ይችላል።
በእንግሊዝ የኬንትና የሌክስተር ዩኒቨርሲቲዎች የፖለቲካ አጥኝዎች በእንግሊዝ የአካባቢ ምርጫዎች ሚመረጡት መካከል በተሻለ ሁኔታ የቀረቡት፣ ሰው የወደዳቸው፣ አለባበስና አቋማቸውን አይቶ ‘ተአማኒ ናቸው’ ብሎ የመረጣቸው ፖለቲከኞች ሥራቸውን በአግባቡ የማይወጡ ሆነው ተገኝተዋል ይላሉ። ይህ ሁኔታ ከተደጋገመ ፖለቲከኞቻችን ውጤታማ ያልሆኑና ለተራው ሕዝብ ጠብ የሚል ነገር የማያመጡ ሆነው ቢቀጥሉ አይገርምም ይላል።
በተጨማሪም ዘጋርዲያን የተሰኘው የእንግሊዝ ጋዜጣ እ.አ.አ. በጁን 2012 ባወጣው አንድ እትሙ “መራጮች ማመን በሚያቅታቸው መጠን የዕጩ ተመራጩ መልክ በምርጫ ውጤት ላይ ትልቅ ተፅዕኖ አለው” በሚል ርዕስ ባሳተመው ጽሑፍ እንደሚለው፥ ባራክ ኦባማን በአሜሪካ ምርጫ፣ ሚት ሮምኒ፣ በ2008 ተቀናቃኛቸው ከነበሩት ጆን ማኬይን ይልቅ ጠንካራ ተፎካካሪ የሆኑት የተሻለ መልክና አቋም ስለነበራቸው ነው። ይኸው ዘገባ የእንግሊዙ ሌበር ፓርቲ የአንድ ወቅት ሊቀመንበር የነበሩት ወጣቱ ኤድ ሚልባንድ ይህንኑ አስተሳሰብ የሚያንፀባርቅ ንግግር ማድረጋቸውን ጠቅሶ፥ “እኔ የምርጫ ዘመቻ አዘጋጆች ፖለቲከኛ ፍጠሩ ቢባሉ የሚያስቡት ዓይነት ሰው አይደለሁም” ማለታቸውን ጠቅሶ አምነው አስደነቁን ብሏል። ለፖለቲካ የሚሆኑ አለመሆናቸውን በመልካቸውና በቁመናቸው ምክንያት እንዳሉት እንዴት እንዳረጋገጠ ግን ዘገባው አላተተም።
እንደጋርዲያኑ ዘገባም ሆነ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ትንታኔ የሰውነት አቋምና መልክ የምርጫ ቅስቀሳ ላይ ተፅዕኖ ማሳረፍ የታየው በ1960ዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ የምርጫ ክርክር በቴሌቪዥን መቅረብ በጀመረበት ወቅት ነበር። በዚሁ ወቅት በሪቻርድ ኒክሰንና በጆን ኤፍ ኬኔዲ መካከል የተካሔደው የምረጡኝ ክርክር ኒክሰን ደከም ብሎ፣ በአነጋገሩም ትንሽ ራሱን በደንብ ያለመቆጣጠር ሁኔታ ታይቶበት በአንፃሩ ኬኔዲ በወቅቱ በጠባብ ልዩነት፣ ካንድ በመቶ ባነሰ ብልጫ ሲያሸንፍ መልከ መልካምነቱ ነው የረዳው ተብሎ ነበር። ቆይቶ የካፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ጥናት ይህንኑ አረጋገጠ። ጥናቱ እንደሚለው የሰውነት አቋምና አቀራረብ በራስ መተማመንን የሚያሳይ ሳቢ ሆኖ ሲገኝ፥ ሰዎች ሥራውን በብቃት ይወጣዋል ወይም ለቦታው ይገባል የሚል እምነት እንዲያድርባቸውና በዚህ መመዘኛ የተሻለውን እንዲመርጡት ያደርጋል።
ይህም ፖለቲከኞችንና ፓርቲዎቻችን ሰው ምን ይፈልጋል የሚለውን በትክክል ለማወቅ ከጥናትና ግምት ውጪ በፉክክር አሸንፎ ለመውጣት እንደ ፌስ ቡክ ያሉ የግለሰቦችን መረጃዎችን የሚሰበስቡ ተቋማትን ተጠቅሞ፥ በትክክል የሚያስቡት እንዴት ነው የሚለውን ዳታ መግዛት ድረስ ይኬዳል። ‘ካምብሪጅ አናሊቲካ’ የተሰኘው የእንግሊዝ ውሒብ (‘ዳታ’) አሰባሳቢ ተቋም የፌስቡክ ውሒብን ገዝቶ ለትራምፕ ቅስቀሳ አውሎታል የሚለው ቅሌት በፖለቲካ የሕዝብ ድጋፍና ድምፅ ለማግኘት እየተሔደ ያለውን ርቀት ለማሳየት በምሳሌ ሊጠቀስ የሚችል ነው።
ምናልባት በብዙ ማስታወቂያ በመታጀብ ለመቅረብ ፖለቲካችን ገና ቢመስልም፥ በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ፖለቲከኞችን አሰማምሮ የማቅረቡ ነገር በዚሁ ከቀጠለ ምናልባት የሚመጣው ምርጫ የፖለቲካ ማሻሻጥ እንደ አንድ ዘርፍ አብቦ የምናይበት ሊሆን ይችላል።

ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው bethlehemne@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 5 ታኅሣሥ 6 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here