ተደጋጋሚ ግጭት እያጋጠማት በሚገኘው ሞያሌ ከተማ በተነሳ ሰሞነኛ የፀጥታ ችግር የ13 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ገለጸ፡፡
የክልሉ መግለጫ እንዳመለከተው መቶ የሚሆኑ ሰዎች ላይም ከባድና ቀላል የመቁሰል አደጋ አጋጥሟል። የተጎጂዎች ቁጥር እስካሁን በተገኘው መረጃ ላይ የተመሠረተ መሆኑን የጠቀሰው መገግለጫው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር በፀጥታ አካላት እየተጣራ መሆኑንም በመጠቆም የተጎጂዎች ቁጥር ከፍ ሊል እደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል፡፡
ባጋጠመው የፀጥታ ችግር እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለማስቆም መንግሥት ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥ የሚጠይቁ ሰልፎች በቦረና ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ተካሒደዋል፡፡ ሕዝቡ ስሜታዊ በመሆን ራሱን ለተጨማሪ ችግር ከማጋለጥ በመቆጠብ በመንግሥት እርምጃዎች ላይ ንቁ ተሳታፊ ሆኖ የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚደረገው እንቅስቃሴ አጋዥ እንዲሆን የክልሉ መንግሥት ጠይቋል፡፡
በፀጥታ ችግሩ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደርስ እየተሠራ ሲሆን፥ ምግብና የተለያዩ ቁሳቁሶችን ማድረስ ስለመጀመሩም አመልክቷል፡፡ ሰሞነኛው ግጭት በምን ምክንያት እንደተቀሰቀሰ በክልሉ በኩል የተገለጸ ነገር የለም፡፡
በመንግሥት በሁሉም አቅጣጫዎች እያጋጠሙት የሚገኙትን ችግሮች ለመቅረፍ እየሠራ ቢሆንም እርምጃዎቹ ገና ጅምር በመሆናቸው በተለያዩ አካባቢዎች የሚያጋጥሙ ችግሮችን ሙሉ በሙሉ ማቆም እንዳልተቻለ ቢሮው በመግለጫው አትቷል፡፡
በኅዳር የመጀመሪያዎቹ ሦስት ቀናት በሞያሌ ከተማ በተቀሰቀሰ ግጭት የ19 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ይታወሳል። በወቅቱም የፌደራል ፀጥታ ኃይል ጣልቃ ገብቶ የማረጋጋት ሥራ ያከናውን እንጂ ሞያሌ ከተደጋሚ ግጭት መላቀቅ አልቻለችም፡፡ ከወር በፊት ያጋጠመው ግጭት በመሬት ይገባኛል ቅራኔ መነሳቱ የተገለጸ ሲሆን የይገባኛል ጥያቄው በሱማሌና ኦሮሚያ ክልል በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን መካከል በተደጋጋሚ እየተነሳ ለግጭትና የሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑ ተገልጿል፡፡
ኅዳር 18 በኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዋሳኝ በሆነው የምሥራቅ ወለጋ ዞን ሊሙ ወረዳ ልዩ ሥሙ አርቁምቤ አካባቢ ባጋጠመውና በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት እንደቀጠፈ በተነገረለት ግጭት ምክንያት ኅዳር 25 ስብሰባ ያካሔደው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ካቢኔ መንግሥት በተለያዩ አካባቢዎች እያጋጠሙ ያሉ የፀጥታ ችግሮችን ለማስቆም በትኩረት እንደሚሠራ ማሳወቁ ይታወሳል።
በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ 14 የፖተለቲካ ማኅበራት በተሳተፉበት የኅዳር 27/2011 ምክክር በኋላ የኦዴፓ፣ ኦነግና ኦፌኮ አመራሮች በሰጡት የጋራ መግለጫ የፖለቲካ ማኅበራቱ ለክልሉ ነዋሪዎች ደኅንነት ቅድሚያ ሰጥተው በጋራ እንደሚሠሩና ለሠላም እንደሚተባበሩ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡ ኦፌኮ መዋሐድ የሚችሉት ፓርቲዎች እንዲዋሐዱ፣ የማይችሉትም በጋራ ተደጋግፈው እንዲሠሩ ሲጠይቅ ኦነግ በበኩሉ የሚፈጠሩ ግጭቶችን ምክንያት ውጪያዊ ከማድረግ ይልቅ መንግሥት ለዜጎች ደኅንነት በትኩረት እንዲሠራ መጠየቁ ይታወሳል፡፡
በተያያዘ ዜና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ለማ መገርሳ ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 4/2011 ከሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ምሁራን ጋር በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፣ አገሪቱ የሠላም ችግር ውስጥ መሆኗ እንደማይሸሸግ አስገንዝበዋል። በመሆኑም የሠላምን ጉዳይ ከዳቦና እንጀራ በላይ አድርጎ መመልከት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል፡፡
ቅጽ 1 ቁጥር 5 ታኅሣሥ 6 ቀን 2011