የሁለቱ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች አድማ ላይ ናቸው

0
617
የአዲስ አበባ እና የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች ጥያቄዎቻችን እስካልተመለሱ ድረስ በትምህርት ገበታችን አንገኝም ብለው አድማ ከመቱ ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡ የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ሴኔት ለተማሪዎች ከለጠፈው ማስታወቂያ ላይ ለመረዳት እንደሚቻለው ዩኒቨርሲቲው በውጪ ዜጎች በሚተዳደርበት ወቅት ለተማሪዎቹ ቃል የተገቡላቸው ስምንት ጉዳዮች እስካልተመለሱ ድረስ ትምህርት እንደማይቀጥሉ ኅዳር 15/2011 በፅሁፍ እና በቃል ገልፀው ከዐሥር ቀናት በላይ በትምህርት ገበታቸው ላይ ሳይገኙ ቀርተዋል፡፡ በተመሳሳይም የአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኅዳር 24 ከዩኒቨርሲቲው ጋር በተደረገ ውይይት ዝርዝር ጥያቄዎቻቸውን ለዩኒቨርሲቲው አስተዳደር አቅርበው ምላሽ እስካላገኙ ድረስ ትምህርት እንደማይጀምሩ አስታውቀው እንደነበር ከዪኒቨርሲቲው ድረ ገፅ ላይ የተገኘ መረጃ ጠቁሟል፡፡ የሁለቱም ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች ያነሷቸው ጥያቄዎች ተመሳሳነት ያላቸው ሲሆኑ በዋናነት ከ 97 – 100 በመቶ የሚሆኑ ተመራቂ ተማሪዎች ከተመረቁ በኋላ የሥራ ዕድል እንዲመቻችላቸው፤ ከ 90 – 100 በመቶ የሚሆኑ ተመራቂ ተማሪዎች በውጪ አገራት እና በአገር ውስጥ የድኅረ ምረቃ ትምህርት እንዲመቻችላቸው፤ 54 በመቶ የሚሆኑ ደግሞ የሦስተኛ ዲግሪ ትምህረት እንዲመቻችላቸው፤ የ ኢ-ለርኒንግ (የበይነ መረብ ትምህርት) ተግባራዊ እንዲደረግ እና ተማሪዎች ከዶመኝታ ክፍላቸው ሆነው ትምህርታቸውን መከታተል እንዲችሉ፤ ለተማሪዎች የኢንተርንሺፕ ፕሮግራም የሚሰጠው ክፍያ መሻሻያ እንዲደረግበት እንዲሁም የዩኒቨርሲቲዎቹ ተጠሪነት ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ወደ ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተዛወረው ለምንድነው የሚሉት ይገኙበታል፡፡ ከዚህ ባለፈም የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ ለተፈፀሙ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች የሞራል ካሳ እና ተገቢው ሕክምና እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በበኩላቸው ለእያንዳንዱ ተማሪ በነፍስ ወከፍ ላፕቶፕ እንዲሰጥ እንዲሁም ለሁሉም ተማሪዎች ዓለም ዐቀፍ ‹ኦነር› ዲግሪ እንዲሰጥ ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ሁለቱም ዩኒቨርሲቲዎች በተማሪዎች ለቀረቡት ጥያቄዎች በፅሑፍ ምላሽ የሰጡ ሲሆን በዋናነትም የተማሪዎቹ ጥያቄዎች የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታን ያላገናዘበ መሆኑን ጠቅሰው አቅም በፈቀደ መጠን ጥያቄዎቹን ለመመለስ እየተደረጉ ያሉ እና ከዚህ በፊት የተከናወኑ ሥራዎችን አስታውሰዋል፡፡ ለተግባር ልምምድ የሚከፈለው ክፍያ ማሻሻያን በተመለከተ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጉዳዩን ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ኅዳር 12/ 2011 ጀምሮ እንዳሳወቀና ምላሹን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ የገለፀ ሲሆን በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ ተፈፀሙ የተባሉት የሰብኣዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ በዝርዝር ቀርበው ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሊቀርቡ እንደሚችሉ ዩኒቨርሲቲው ምላሽ ሰጥቷል፡፡ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ ለእያንዳንዱ ተማሪ በነፍስ ወከፍ ላፕቶፕ እንዲሰጠው የቀረበው ጥያቄ የአገሪቱ ሁኔታ ከግምት ያላገናዘበ መሆኑን ጠቅሶ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በተለያዩ መዋቅሮች ውስጥ የተደራጁ ዴስክ ቶፕ ኮምፒውተሮችን በአግባቡ መጠቀም ይቻላል ሲል መልስ ሰጥቷል፡፡ የተቋማማን ተጠሪነት በተመለከተም ሁለቱም ዩኒቨርሲቲዎች ከተጠሪ መስሪያ ቤት ለውጥ ውጪ ተቋማቸው የራዕይና የተለኮ ለውጥ አለማደረጉን እና ለተማሪዎች በሰጡት ምላሽ ገልጸዋል፡፡ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲዎቹ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በተለየ መልኩ የተዋቀሩ እና ስርዓተ ትምህርታቸው የተለየ ነው፡፡ ዮሴፍ የተባለ የተማሪዎች ኅብረት አመራር ‹‹ወደ ዩኒቨርሲቲው በገባንበት ወቅት›› ይላል ‹የዩኒቨርሲቲው ተልዕኮ እና ዓላማ ተብሎ የቀረበልን ከአገሪቷ ውስጥ ምርጥ ውጤት ያላቸው ተማሪዎች ብቻ የሚማሩበት፤ የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውንም እስከ ፒኤችዲ ድረስ እንዲቀጥሉ ልዩ ድጋፍ የሚደረግበት፤ ከሥራ ዕድል አኳያም ዩኒቨርሲቲው ከአምራች ተቋማት ጋር ትስስር አድርጎ የተማሪዎችን የሥራ ዕድል የሚያስገኝ እንደሚሆን ተገልፆአል››፡፡ ነገር ግን ባለፈው ዓመት ከየትምህርት ክፍሉ የድህረ ምረቃ ትምህርት ዕድል የተሰጣቸው ጥቂት ተማሪዎች ብቻ መሆናቸውን ዮሴፍ ተናሯል፡፡ ከሥራ ዕድል አንፃርም ዩኒቨርሲቲዎቹ የተለየ፣ ከባድ እና አዲስ ካሪኩለም ከመከተላቸው አንፃር ተማሪዎች በሚፈለገው ደረጃ ውጤት አለማምጣታቸውን ተከትሎ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች አንፃር ተወዳዳሪ ሊሆኑ አንዳልቻሉ ጠቅሷል፡፡ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ኅዳር 25 ለተማሪዎች በተለጠፈ ማስታወቂያ እንደተገለፀው ዩኒቨርሲቲው የተማሪዎቹ ጥያቄዎችን በተመለከተ በቀጣይነት የሚሰራ መሆኑ ታውቆ ተማሪዎቹ ከኅዳር 26 ጀምሮ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ተገልፆአል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ኅዳር 28 በማስታወቂያ ሠሌዳው ከለጠፈው መልዕክት ለመረዳት እንደሚቻለው ተማሪዎቹ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር ውይይት ለማድረግ ጠይቀው ውይይቱ የተደረገ ቢሆንም ከፌደራሉ መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ከተጀመረ በኋላ ተማሪዎቹ አቋርጠው መውጣታቸው ተገልፆአል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ኅዳር 28 አስቸኳይ ስብሰባ ካደረገ በኋላ ተማሪዎቹ የሚጠይቋቸውን ጥያቄዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ በሠላማዊ መንገድ እንዲያቀርቡና እስከ ታኅሣሥ ሁለት ቀን ድረስ ተመዝግቦ ትምህርቱን የማይቀጥል ተማሪ ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አሳስቧል፡፡ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ታህሣሥ 2 ለተማሪዎች ማስታወቂያ የለጠፈ ሲሆን እስከዚሁ ዕለት ድረስ ያልተመዘገቡ ተማሪዎች በገዛ ፍቃዳቸው ትምህርታቸውን ያቋረጡ ተደርገው እንደሚወሰዱ ገልፆአል፡፡ ሆኖም አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው ተማሪዎቸ ለመረዳት እንደተቻለው እስከተጠቀሰው ቀን ድረስ ከተወሰኑ ተመረቂ ተማሪዎች ውጪ ትምህርት እየተሰጠ አልነበረም፡፡ ዩኒቨርሲቲው ታኅሣሥ 4 ቀን በድጋሜ በለጠፈው ማስታወቂያ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጌታሁን መኩሪያ (ዶ.ር ኢ/ር) በተነሱት ጥያቄዎች ዙሪያ ተማሪዎቹ ለማነጋገር እንደሚመጡ ገልፆ ምዝገባ ላካሄዱ ተማሪዎች የስብሰባ ጥሪ ያደረገ ሲሆን ሚኒስትሩ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪቀዎች በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የትምህርት እና የሥራ ዕድል እንደሚሰጣቸው ቃል ገብተዋል፡፡ አንድ ሥሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ የዩኒቨርሲቲው ተማሪ ‹‹ከዚህ በፊት በነበሩት ዓመታትም ይህ የተለመደ ጉዳይ ሆኖ ሳለ ተማሪዎች በካሪኩለሙ እና ቃል በተገባውን መሰረት ይፈፀሙልን ብለው ላቀረቧቸው ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ አይደለም ሲል›› ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል፡፡ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው አንዳንድ የዩኒቨርሰሲቲዎቹ ተማሪዎች እንደገለፁት የትምህርት ማቆም አድማው አስተባባሪ የሆኑ ግለሰቦች ትምህርት የመጀመር ፍላጎት ባላቸው ተማሪዎች ላይ ዛቻ እና ማስፈራሪያ እያደረሱ ሲሆን ተመዝግበው ትምህርታቸውን መቀጠል እየፈለጉ ባለው ሁኔታ ምክንያት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ሴኔት ለተማሪዎች መልስ በሰጠበት ማስታወቂያ ጥያቄዎቹ ተገቢ ቢሆኑም ዩኒቨርሲቲው አጥጋቢ መልስ ስለሰጠበት ትምህርት አቁሞ ጥያቄ የሚቀርብበት አግባብ ትክክለኛ አካሄድ እንዳልሆነ ገልፆ እስከ ታህሳስ 1 ድረስ ትምህርት የማይጀምሩ ተማሪዎች በገዛ ፍቃዳቸው ትምህርታቸውን ያቋረጡ ተደርጎ እንደሚታሰብ እና የዩኒቨርሲቲውን ግቢ ለቀው መውጣት እንደሚኖርባቸው አሳስቧል፡፡ በተጨማሪም ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ የሚፈልጉ ተማሪዎችን ለመጠበቅ አስፈላጊው የጥበቃ ኃይል እንደሚሠማራ እና ከለላ እንደሚደረግላቸው እንዲሁም በእነዚህ ተማሪዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ለማሳደር የሚፈልጉ ተማሪዎች ላይ የዲሲፕሊ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡ ይህንን ዘገባ እስከተዘጋጀበት አርብ ከሰአት በኋላ ድረስ በሁለቱም ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት በተሟላ መልኩ ያልተጀመረ ሲሆን በሚቀጥሉት ሳምንታትም ተማሪዎቹ ለጥያቄዎቹ አጥጋቢ መልስ ካላገኙ በአቋማቸው እንደሚፀኑ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ተማሪዎች አስታውቀዋል፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 5 ታኅሣሥ 6 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here