የከተሞች መስፋት ያፈናቀላቸው አርሶ አደሮች ካሣ – መልሶ ማቋቋም – ስጋት

0
1191

ከከተሞች መስፋፋት ጋር በተያያዘ የአርሶ/አርብቶ አደሮች መፈናቀል የውዝግብ መንስዔ ከሆነ ሰነባብቷል። ይሁን እንጂ ከመንግሥት ዘላቂ ምላሽ አላገኘም። ከሰሞኑ ደግሞ የአጀንዳውን በድጋሚ መነሳት አስመልክቶ ስንታየሁ አባተ የችግሩን መንስዔዎች እና የመፍትሔ ሐሳቦች የሚለከታቸውን ባለሙያዎች፣ ባለጉዳዮች እና ሰነዶች በማገላበጥ ለሐተታ ዘ ማለዳ አቅርቦታል።

ሰሙ ሁንዴ የ103 ዓመት አዛውንት ናቸው። ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ መሪ ሎቄ አካባቢ ነው። ከዓመታት በፊት በአርሶ አደርነት ኑሯቸውን ይመሩ የነበሩት የስድስት ልጆች አባት ዕድሜያቸውም ገፍቶ ኑሯቸውም እንደቀደመው አልሆን ብሏቸዋል። እስከ 1990ዎቹ መጀመሪያ ዓመታት ድረስ ለእርሻ ይገለገሉበት የነበሩበት መሬት ለልማት በሚል በመወሰዱ ዛሬ ኑሯቸው ከግብርና ወደ ሰነድ አልባ (ካርታ የሌለው) ቤት አከራይነት ተለውጧል። ከሚያከራዩዋቸው ደሳሳ ቤቶች በወር እስከ ሁለት ሺሕ ብር የሚያገኙ ሲሆን ኑሯቸውን ልጆቻቸው እና መንግሥት በሚሰጣቸው ገንዘብ ይደጉማሉ።
በልማት ሥም ወደ ከተማ አስተዳደሩ የመሬት ባንክ የገባው የእርሻ ቦታ 30 ጥማድ (10 ሔክታር አካባቢ እንደማለት ነው) እንደሆነ የሚገልጹት አዛውንቱ የእርሻ ቦታው በካሬ ሦስት ብር ከ35 ሳንቲም እንዲሁም የግጦሽ መሬቱ ደግሞ በአንድ ብር ከ35 ሳንቲም አካባቢ መገመቱንም ያስታውሳሉ። በአጠቃላይ 70 ሺሕ ብር አካባቢ ካሳ የተከፈላቸው አዛውንቱ በአርሶ አደርነት ሕይወታቸው ሙሉ የነበረው ቤት ዛሬ ላይ መጉደሉን በመጥቀስ በመንግሥት ቅሬታ እንዳላቸው ይናገራሉ። እዚያው ማሳቸው ላይ ሁለት ቦታ የመኖሪያ ቤት ቦታ የነበራቸው ቢሆንም ሁለት አይቻልም ተብለው አንዱን እንዲለቁ መደረጉን በመግለጽም ዛሬ ላይ ሕጋዊ ካርታ በሌለው ቤት እየኖሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ከተሜነትና የከተሞች መስፋፋት በኢትዮጵያ
የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል “የከተሞች የጎንዮሽ መስፋፋት፡ ምክንያቶች፣ ተፅዕኖዎች የመፍትሔ አቅጣጫዎች” በሚል ሚያዝያ 2009 ይፋ ያደረገው ጥናት እንደሚያስረዳው በኢትዮጵያ የከተሞች ዕድገት ምጣኔ በጣም ከፍተኛ የሚባለው ደረጃ ውስጥ የገባ ሲሆን ይህም ከአምስት በመቶ በላይ ደርሷል።
የኢትዮጵያ የክትመት መጠን (Urbanization Level) በ1976 ከነበረበት 11 በመቶ አሁን ወደ 20 በመቶ ከፍ ማለቱን የሚጠቅሰው ጥናቱ በ2017 ደግሞ 30 በመቶ እንደሚደርስም ግምቱን አስቀምጧል። በከተሞች መስፋፋትና የነዋሪዎች ቁጥር በፍጥነት መጨመር በአንድ በኩል የመኖሪያ ቤቶችና ሌሎች አገልግሎቶችን ለማሰተናገድ የመሬት ፍላጎት እንዲጨምር ሲያደርጉ በሌላ መልኩ የመሬት ፍላጎቱን ለማሟላት የአርሶ/አርብቶ አደር ይዞታን ወደ ከተማ የመሬት አጠቃቀም እንዲቀየር ስለማስገደዳቸውም ያትታል።
አምራች ኢንዳስትሪዎችን የከተሞች የምጣኔ ሀብት መሠረት እንዲሆኑ ማድረግ የተጀመረው በቅርቡ ቢሆንም፥ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለከተሞች መስፋፋት አንድ ምክንያት እየሆኑ ስለመምጣቸውም ያነሳል። ከተሞች በቀጣይም በስፋት እያደጉ የሚሔዱ መሆኑን በማስታወስም ለዕድገታቸው ምክንያት የሚሆኑትም የሕዝብና የምጣኔ ሀብት ዕድገቱ በከፍተኛ ፍጥነት የሚቀጥል መሆኑ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት፣ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርኮች እንዲሁም ትላልቅ (ሜጋ) ፕሮጀክቶች እየሰፉ መሔድን ነው።
“The State of Addis Ababa 2017 Report” በሚል ርዕስ የወጣው የ“ዩኤን ሃቢታት” ጥናት በኢትዮጵያ ከተሞች የሚኖሩ ሕዝቦች ቁጥር በአውሮፓዊያኑ 1984 ከነበረበት 4 ነጥብ 87 ሚሊዮን በ2007 ወደ 11 ነጥብ 86 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን ያመለክታል። እንደ ዓለም ባንክ የ2015 ግምት ከሆነም በኢትዮጵያ በ2037 የከተማ ሕዝብ ዕድገት በሦስት እጥፍ ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል።
በኢትዮጵያ ከተሞች ምን ሲካሔድ ነበር?
የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል የጥናት ውጤት እንደሚያመለክተው ከሆነ በከተሞች የማስፋፊያ አከባቢዎች የሚኖሩ አርሶ ወይም አርብቶ አደሮች አያያዝ የከፉ ችግሮች የሚስተዋሉበትና የተዘበራራቁ አሠራሮች የተስተናገዱበት ነው።
በ1987 የፀደቀው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 40 ላይ የመሬት ባለቤትነትን ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሰጠ ሲሆን፥ አርሶ አደሮች መሬት በነጻ የማግኘትና ከመሬታቸው ያለመነቀል መብታቸው የተከበረ ስለመሆኑ እንዲሁም በዚህ ላይ ዝርዝር ሕግ እንደሚወጣ ይደነግጋል። በተያያዘም የግል ንብረት ባለቤትነት እንደተጠበቀ ሆኖ መንግሥት ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ተመጣጣኝ ካሣን በቅድሚያ ከፍሎ የግል ንብረት ሊወስድ እንደሚችልም ተቀምጧል።
ሕገ መንግሥቱ ይህን ቢልም አሠራሮቹ ከችግር ያልተለዩ እንደነበር ነው ጥናቱ የሚስረዳው። ለማስፈፀሚያ ሲወጡ ከነበሩ የሕግ ማዕቀፎች መካከል የከተማ ወይም ወረዳ አስተዳደሮች “አቅም በፈቀደ መጠን” የማቋቋሚያ ድጋፍ ያደርጋሉ የሚልና አስገዳጅነት የሌላቸው ድንጋጌዎችን ማካተታቸውን ጥናቱ አመልክቷል። በዚህም ከተሞች ተነሺዎችን በዘላቂነት የማቋቋም ግዴታ እንደሌለባቸው አድርገው እንዲያስቡ አድርጓቸዋልም ይላል።
ሌለው ችግር ደግሞ “አርሶ/አርብቶ አደሮችን የማፈናቀል ሥራ በእርግጥ የተሻለ ልማት የሚያመጣ መሆኑ ሳይረጋገጥ በመንግሥት ኃላፊዎች አስተዳደራዊ ውሳኔዎች፣ በባለሙያዎች ፍላጎት ቴክኒካዊ ውሳኔዎች እንዲሁም በባለሀብቶች የግል ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ይዞታ የማስለቀቅና የማፈናቀል” ሥራዎች እንዲሠሩ መደረጉ እንደሆነ ያትታል።
አዲስ አበባ ላይስ ምን የተለየ ነገር ነበር?
በ“ዩኤን ሃቢታት” ጥናት መሠረት 80 በመቶ የአዲስ አበባ መሐል ከተማ አካባቢዎች ያልለሙና የቆሸሹ ናቸው። ይህም የመልሶ ማልማት ሥራዎች እንዲካሔዱና ከተማዋ እንድትሰፋ አድርጓል። አዲስ አበባ እንደሌሎች ከተሞች ሁሉ በጊዜ ሒደት ስትሰፋ የኖረች፣ በመልሶ ማልማት ሥራዎችም ውስጥ ያለፈችና እያለፈች ያለች ነች። ቀድመን የጠቀስነው የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ጥናት እንደሚለው የኢትዮጵያ ከተሞች በፍጥነት እየሰፉ የመጡ መሆናቸው ሐቅ ነው። የከተሞቹን የመስፋት መጠን ሲገልጽም ለአብነት የሐዋሳ ከተማ የመስፋት ዕድገት ምጣኔ (10 ነጥብ 31 በመቶ) ከሕዝብ ቁጥር ዕድገት ምጣኔው (6 ነጥብ 3 በመቶ) ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ በከተማዋ ባለፉት ዓመታት የታየው ዕድገት የተስተናገደው በመንግሥት እርሻ ላይ በመሆኑ ብዙ አርሶ አደሮችን እንዳላስነሳ ያትታል። ከአሁን በኋላ የሚኖረው የከተማዋ ዕድገት ግን በዙሪያዋ የሚኖሩ አርሶ አደሮችን የማፈናቀል ዕድሉ ከፍተኛ እንደሆነ ያስቀምጣል። “በአንፃሩ እንደ መቀሌ ያሉ ከተሞች ደግሞ ዕድገታቸው ወደ አርሶ አደሮች ይዞታ ስለነበር ብዙ አርሶ አደሮችን አፈናቅለዋል” ይላል።
ቦታን ከማስለቀቅ ጋር በተያያዘም ባለይዞታዎችን በወጉ አስረድቶና አሳምኖ እንዳልነበር የሚጠቅሰው ጥናቱ መሬት እንዲለቀቅ ሲወስን ባለይዞታው መሬቱን የሚለቅበትን ጊዜ በመጥቀስ እና የሚከፈለውን የካሳ መጠን በመግለጽ የማስለቀቂያ ትዕዛዝ በጽሑፍ ሊደርሰው የሚገባ ቢሆንም በተግባር ሲታይ ግን ከመሬት ይዞታቸው የሚነሱ ተነሽዎች በሒደቱ ላይ በተገቢው ሁኔታ እንዲሳተፉ እንደማይደረግ፣ ይዞታቸውን የሚለቁበትን ጊዜ የሚያውቁት በጽሑፍ ሳይሆን በቀበሌ ወይም በወረዳ አስተዳደር በሚጠራ አጠቃላይ ስብሰባ እንዲሁም በቀበሌ ተሿሚዎች በኩል በሚነገር ቃል እንደሆነ ጥናቱ ስለማረጋገጡ ይገልጻል።
ለገሰ ሰሙ እንደሚሉትም ከሆነ መሬቱን ሲለቁ በወጉ አልመከሩም። የአዲስ አበባ የልማት ተነሽ አርሶ አደሮች መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤትም በዚህ ሐሳብ ይስማማል። የጽሕፈት ቤቱ የኮሙዩኒኬሽን ሥራ ክፍል ኃላፊው የወንድወሰን አካሌ መሬቱ ለላቀ ልማት ስለሚፈለግ ብቻ አርሶ አደሮቹ የት እንደሚሔዱ እንኳን ሳያውቁ የማስነሳት አካሔድ እንደነበር ያነሳሉ። “አርሶ አደሮቹ ከተነሱ በኋላ እዚህ ቦታ ያርፋሉ ተብሎ የሚቀመጥ ነገር አልነበረም” ነው የሚሉት። የአዲስ አበባ መሬት ልማት ማኔጅንት ቢሮ ግን በዚህ አይስማማም። የቢሮው የኮሙዩኒኬሽ ዳይሬክተር ንጉሡ ተሾመ “የምንሔድበትን ቦታ ሳናውቅ ነው ስንነሳ የነበረው የሚለው ተቀባይነትም ሕጋዊነትም የለውም” ይላሉ። ቦታው ጥናት ተደርጎበት ለላቀ ልማት ከተፈለገ ከባለይዞታዎች ጋር ውይይት ተደርጎና መግባባት ላይ ተደርሶ እንደሚነሱ በመጥቀስም ሁሉም ተነሽ ላይግባባ እንደሚችል፥ ይሁንና አብዛኛው ተነሽ ከተግባባ መንግሥት ካሳ ከፍሎ ቦታውን እንደሚያስለቅቅም ንጉሡ ያስረዳሉ።
ከተነሱ በኋላስ?
በተለይም በአዲስ አበባ

የልማት ተነሽ አርሶ አደሮች መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት መረጃ እንደሚያሳየው በአዲስ አበባ በተለይም በማስፋፊያ ቦታ ላይ የነበሩ 7327 የልማት ተነሽ አባ/እማወራ አርሶ አደሮች (ቤተሰቦቻቸውን ሲጨምር ቁጥሩ 35 ሺሕ 410 ይሆናል) ተለይተዋል።
ለገሰ ሰሙ፣ ከሰሙ ሁንዴ ልጆች አንዱ ሲሆኑ አሁን ላይ የ61 ዓመት አዛውንት ናቸው። እሳቸውም እስከ 1996 ድረስ በግብርና ሥራ ይተዳደሩ የነበረ ሲሆን በልማቱ ምክንያት 25 ጥማድ ያውል የነበረው የእርሻ ማሳቸው በካሬ ሦስት ብር ከ35 ሳንቲም ተገምቶ በአጠቃላይ 50 ሺሕ ብር ካሣ ተሰጥቷቸው ኑሯቸው ዛሬ ሌላ መልክ እንዲይዝ ሆኗል። ለገሰ እንደሚሉት ከሆነ የእርሻ ማሳቸውን እንዲለቁ ካሣ ሲገመትላቸው በካሬ ሦስት ብር አካባቢ የነበረ ቢሆንም በዚያው ወቅት መንግሥት ግን ለጨረታ ባቀረበው መሬት የመነሻ ዋጋ በካሬ 165 ብር ማስታወቂያ ሲያስነግር ነበር።
የሕግ ባለሙያው አበበ አሳመረ እንደሚሉት ካሣ ግምቱ አናሳ ከመሆኑም ባሻገር ከወቅቱ ገበያ ጋር እየተገናዘበ አለመሰላቱ ችግር ነበር። ለካሳ ማነሱ ምክንያት የሚሆነውም “ምን ያመጣሉ መሬት የመንግሥት ነው” የሚለው የተሳሳተ እሳቤ ላይ የተመሠረተ አካሔድ ነውም ብለው ያምናሉ። በዚህም አርሶ አደሩ ብቻ ሳይሆን ከመሐል ከተማ ሲነሳ የነበረው የልማት ተፈናቃይም ተጎድቷል ይላሉ።
ቀድመን የጠቀስናቸው ጥናቶችም የሚሰጡ የካሣ ክፍያዎች በቂ እንዳልነበሩ የሚያመለክቱ ናቸው። የአምስት ልጆች አባት የሆኑት ለገሰ ለቤት መሥሪያ የከለሉትን ከሁለት ሺሕ ካሬ በላይ ቦታ ለእሳቸውም ጨምሮ ለስድስት ከፍለው ጎጆ የቀለሱ ሲሆን ካርታ ለማውጣት ግን አልቻሉም። ምክንያቱ ደግሞ የሚፈቀደው 500 ካሬ ብቻ ስለሆነ ካርታ ለማውጣት ሲለካ የሚተርፈው ወደ መሬት ባንክ ገቢ ይደረጋል ስለሚባል እንደሆነ ያነሳሉ። የልማት ተነሽ አርሶ አደሮቹ ጥያቄ ደግሞ በያዝነው ቦታ ልክ ካርታው ተሠርቶ ይሰጠን የሚል ስለሆነ በዚህ አለመግባባት እስካሁን ቤታቸው ሰነድ አልባ ነው። ንጉሡ ስለዚህ ሲያስረዱ ሰዎች ሰፊ ቦታ ይዘው ካርታ እንዲሠራላቸው ሊፈልጉ ይችላሉ፤ ይሁንና ከመሬት ውስን ሀብትነት አኳያ መንግሥት ለመኖሪያ ቤት በቂ ነው የሚለውን ለባለይዞታዎቹ ሰጥቶ የተረፈውን ለሌላ ልማት እንደሚወስድ፣ መሬትም የሕዝብና የመንግሥት የጋራ ሀብት መሆኑ መዘንጋት እንደሌለበት ያስገነዝባሉ።
መሬቱ ለልማት ይፈለጋል ተብሎ መኃንዲስ መጥቶ ሲለካ ከአንድም ሁለት ጊዜ መኃንዲሱን አባርሬ ነበር የሚሉት ለገሰ፣ ኋላ ላይ የመንግሥት ውሳኔ ነው በመባሉና የቀበሌው አስተዳዳሪም መጥቶ ስላነጋገራቸው “የመንግሥት ውሳኔ ከሆነማ ምን አደርጋለሁ” ብለው እንደተስማሙ ያስታውሳሉ። ይሁንና በወቅቱ (1996 አካባቢ) የከተማ አስተዳደሩ አርሶ አደሩን ሲያወያይ መሬቱ ሳይወሰድ በፊት አርሶ አደሩን አደራጅቶና አሠልጥኖ ወደ ሥራ በማስገባት በአርሶ አደርነት ከሚያገኘው ገቢ በተሻለ ሕይወቱን መለወጥ እንደሚቻል አሳዩን የሚል ጥያቄን ሲያነሱ፥ አዳራሽ ሙሉ ጭብጨባ እንደተቀበላቸው የሚስታውሱት ለገሰ ያ ባለለመደረጉ ግን ዛሬ ላይ ከአርሶ አደርነት ሕይወታቸው ጋር ‹ሰማይና ምድር› የሆነ የሕይወት ልዩነትን እያስተናገዱ ስለመሆኑ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በተሰጣቸው ካሣ ምን ምን መሥራት እንደሚቻል ሥልጠና ከመስጠት ይልቅ አንድ ቀን ጠዋት ድንገት የካሣ ብር ውሰዱ ተብለው ገንዘቡን እንደተቀበሉም ያስታውሳሉ፤ ይህም እንዳልጠቀማቸው ነው የሚናገሩት። አርሶ አደር እያሉ በሚያመርቱት ጤፍ፣ ስንዴ፣ ምስርና ጓያ ከራሳቸው አልፈው ለሸማቹ ማኅበረሰብ ለመሸጥ ገበያ ያወጡ እንደነበር በማስታወስ ዛሬ ያ ሁሉ አልፎ በሚያገኟት ሁለት ሺሕ ብር የቤት ኪራይ ላይ መንግሥት ከሐምሌ 2009 ጀምሮ ለምግብ ፍጆታ በሚል በየሦስት ወሩ ከሚሰጣቸው 5175 ብር ጋር እያዳመሩ ኑሮን በመግፋት ላይ እንደሚገኙ ያስረዳሉ።
የወንድወሰን እንደሚሉት የልማት ተነሽ አርሶ አደሮቹ ካሣ ከተከፈላቸው በኋላ በገንዘቡ እንዴት ሠርቶ መለወጥ እንደሚቻል የሚያስገነዝብ ምንም ዓይነት ሥልጠና እንዲወስዱ አለመደረጉ ዛሬ ላይ ለችግር እንዲጋለጡ አድርጓል። ንጉሡም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፤ የልማት ተነሽዎች የካሣ መተመኛ መመሪያን መሠረት ተደርጎ ካሣ ይሰላ እንጂ መጀመሪያውኑ በካሬ ይከፈል የነበረው ገንዘብ አነስተኛ እንደሆነ (በቂ ነው የሚል እምነት እንደሌላቸው) ያነሳሉ። ይሁንና ከፍተኛ ካሣ ቢከፈለውም እንኳን በአርሶ አደርነት ሕይወታቸው ሲያገኙ ከነበረው ገቢ አንፃር ዝቅተኛ የሚሆንባቸው እንዳሉ፣ እንዲሁም ከተነሱ በኋላ ሥልጠናና በቂ ክትትል ባለመደረጉ ዛሬ ላይ ገንዘቡን ጨርሰው ሌላ ቅሬታ እንዲያነሱ ስለማድረጉም ይገልጻሉ። የወንድወሰንም ቢሆኑ እስከ 700 ሺሕ ብር ካሣ የተከፈለው ተነሽ በገንዘቡ ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝ ሥራ ባለመሥራቱ ገንዘቡን ጨርሶ ዛሬ ላይ ክፍያው ትንሽ ነበር ሊል እንደሚችል ይጠቅሳሉ። የገንዘብ አጠቃቀም ግንዛቤን በማስረዳትና ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረጉ የጎላው እጥረት በመንግሥት በኩል የነበረ መሆኑን በመጥቀስም፥ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ የተቋቋመው ይህን ዓይነት ችግር ይቀርፍ ዘንድ መሆኑን ያስረዳሉ። እዚህ ላይ ግን ሙሉ በሙሉ ጥፋቱ የመንግሥት ብቻ ነው ተብሎ እንደማይወሰድ አስተያየት ሰጭዎች ያሠምሩበታል።
ለገሰ በቀለ ወጣት ሲሆን በመሪ ሎቄ አካባቢ የሚኖር የአርሶ አደር ልጅ ነው። የእሱም ቤተሰብ ተመሳሳይ ሒደት ውስጥ እንዳለፈ በመጥቀስ ለልጅ 105 ካሬ ለቤተሰብ ደግሞ 300 ካሬ የቤት መሥሪያ ተሰጥቷቸው ሌላው ለልማት በሚል መወሰዱን ያስታውሳል። አብዛኞቹ የልማት ተፈናቃዮች በምጣኔ ሀብት በኩል በከባድ ችግር ውስጥ እየኖሩ ነው ብሎ የሚያምነው ወጣት ለገሰ የወጣቱ ጥያቄም ዘላቂ ገቢ በሚያስገኝ ዘርፍ ተደራጅቶ ሕይወቱን መለወጥና የመኖሪያ ቤት የማግኘት ቢሆንም ይህ ባለመሆኑ ለችግር ተጋልጧል፤ ለፖለቲካ ትኩሳትና ፍጆታ ሰለባም ሆኗል ይላል።
የወንድወሰን እንደሚሉት ከ1986 ጀምሮ በልማት የተነሱ አርሶ አደሮችን በአምስት ክፍል ለይተው በዘላቂነት የሚደገፉበትንና በመንግሥትና በራሳቸው ጥረት ሀብት የሚያፈሩበትን መንገድ ለማግኘት ጽሕፈት ቤቱ እየሠራ ይገኛል። ምንም ገቢ ለሌላቸውና መሥራት ለማይችሉት በዘላቂነት እንደየቤተሰባቸው ለምግብ ፍጆታ የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው። በዚህም 5563 የልማት ተነሽ አርሶ አደሮችንና ቤተሰቦቻቸው ዘላቂ የቀጥታ ድጋፍ አገልግሎት እያገኙ ነው የተባለ ሲሆን፣ የገንዘበ ድጋፉ እስከ ሕይወት ፍፃሜ አይቋረጥም። ከእነዚህ ውስጥም የመኖሪያ ቤት ችግር ያለባቸው ከ60 በላይ ተነሽዎች በየወሩ ለቤት ኪራይ በሚል ተጨማሪ ሦስት ሺሕ ብር እንደሚሰጣቸው ታውቋል። ሁለተኛው ክፍል ደግሞ ምንም ገቢ የሌላቸው ግን መሥራት የሚችሉ በሚል የተለዩ ሲሆን በጊዜያዊነት የገንዘብ ድጋፍ ይደረግላቸዋል። በዚህም 3029 ተነሽ አርሶ አደሮችና ቤተሰቦቻቸው በገንዘብ እየተደገፉ ነው። ለዚህም (በሁለቱ ክፍል ለተለዩ ተነሽዎች) ጽሕፈት ቤቱ በ2011 በጀት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ11 ሚሊዮን በላይ ገንዘብን ማውጣቱም ታውቋል።
እንደ የወንደወሰን ገለጻ መሥራት ለሚችሉት የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ (ጊዜያዊ የቀጥታ ድጋፍ) ለአንድ ዓመት ብቻ ሰጥቶ ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚገባ መመሪያ አለ። ይሁንና ወደ ሥራ የሚገቡበት ሁኔታ ባለመመቻቸቱ ተረጂዎቹ ከአንድ ዓመት በላይ ገንዘብ እየተከፈላቸው ዛሬም ቀጥለዋል። ወደ ሥራ ለማስገባት ካልተቻለባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ የመሥሪያ ቦታን ከመሬት ልማት ማግኘት አዳጋችና ረጅም ቢሮክራሲን የሚፈልግ በመሆኑ ነው። ጽሕፈት ቤቱ አሁን ላይ 64 የተለያዩ ፕሮጀክቶችን (የትምህርት ቤት፣ የዶሮና እንስሳት እርባታ፣ የመሥሪያና መሸጫ ሼድ፣ ወዘተ) ግንባታዎችን በማቀድ ለተነሽዎቹ ዘላቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየሠራ መሆኑን በመጥቀስ ቦታው ግን ቶሎ እንደማይገኝ ይጠቅሳሉ። ንጉሡ ግን በዚህ ሐሳብ አይስማሙም። ምክንያታቸውን ሲያስረዱም “ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ የሚዘጋጁ ቦታዎችን የሚወስነው ካቢኔው ቢሆንም ቢሮው የተጠየቀውን ቦታ ማዘጋጀት እየቻለ ያልሠራበት መንገድ የለም። ግን የተጠየቁ ጥያቄዎች ሁሉ መቶ በመቶ ይመለሳሉ ባይባልም ቅድሚያ የሚሰጠው ለአርሶ አደር መልሶ ማቋቋም ነው፤ ጽሕፈት ቤቱ ፕሮጀክቶችን ነድፌ ቦታ አላገኘሁም ማለቱ ተገቢ አይደለም” ይላሉ።
ሥጋትስ የለም?
ከተነሽዎች ጋር በተያያዘ “የልማት ተነሽ ሳይሆኑ ተነሽ ነን ብለው የሚመጡ” መኖራቸውን የወንድወሰን ይጠቅሳሉ። ይህም ሌላ ፈተና ሆኗል። የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደሚሉት ደግሞ አቅሙ ያላቸውና የገንዘብ ቀጥታ ድጋፍ የማይገባቸው ሰዎች “ለእኛም” ገንዘብ ካልተሰጠን የሚል ጥያቄን ይዘው በተደጋጋሚ ወደ ቢሮ ይመላለሳሉ፤ ይህም ለመንግሥት ሌላው ስጋት ሆኗል። ይህን ጥያቄ የሚያቀርቡ ሰዎች የበረከቱት አንድም የተለዩ አቅመ ደካሞች ገንዘብ ሲረዱ ማየታቸው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ተቋቁሞ ወደ ሥራ በገባበት 2009 ወቅት ለሁሉም ተነሾች ገንዘብ ይሰጣል የሚል የተሳሳተ መረጃ መሰራጨቱ እደሆነ ይነሳል። ተጨማሪው ፈተና ደግሞ በሕይወት ከሌሉ አውራሾች ጋር የተያያዘ ውጣ ውረድ ነው፤ አሁን ላይም በሕይወት ከሌሉ 570 “አውራሾች” ወራሽ እንደሆኑ የሚጠይቁ 2135 “ወራሾች” በፍርድ ሒደት ውስጥ ስለመሆናቸው መረጃዎች ያሳያሉ። እነዚህ ጉዳዮችም ሌላ የስጋት ምንጭ ሆነው የሚታዩበት ሒደት አለ የሚሉ ወገኖች አሉ።
አዲስ ማለዳ ለጉዳዩ እጅግ ቅርብ ከሆኑ ምንጮቿ እንዳገኘችው መረጃ ከሆነም በልማት ተነሽ አርሶ አደሮች መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት (አንድ ማዕከልና አምስት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች አሉት) አንድን ብሔር ብቻ መሠረት ያደረገ የሥራ ኃላፊዎች ሹመት ተፈፅሟል። ምንጮቻችን ይህ አካሔድም ጤናማ ነው ብለው አያምኑም። በቅርቡም በአቃቂ ከአርሶ አደሮች ለልማት የተወሰደን ቦታ ለመለካት ወደ ሥፍራዎቹ ያቀኑ የመሬት ልማት ባለሙያዎች በነዋሪዎች ማባረርና ማስፈራራት እንዲደርስባቸው በቅርንጫፍ ኃላፊዎች ሳይቀር የማነሳሳትና አርሶ አደር የነበሩ ሰዎች ወደ አመፅ እንዲገቡ የማድረግ ሙከራ ተስተውሎ እንደነበር ምንጮቻችን ጠቁመዋል።
አበበ በአዲስ አበባ አስተዳደር ውስጥ ሲሠሩ በነበረበት ወቅት እንደሚያስታውሱት አርሶ አደሮቹ ለልማት ሲነሱ ለቤት መሥሪያ ቦታ ይሰጡ ነበር። ግን ልጆቻቸው እያደጉ ሲመጡ የቤት መሥሪያ ቦታ ስለሚፈልጉ ጥያቄዎቹ የፖለቲካ መልክ እንዲይዙ እየሆኑ መጥተዋል። ተነሽዎች በተሰጣቸው ቦታ ላይ ደስተኛ አለመሆንም ሌላው ችግር ፈጣሪ ምክንያት ሆኗል ብለው ያምናሉ። በተጨማሪም ለማቋቋሚያ የሚቀረፁ ፕሮጀክቶች ያለበቂ የአዋጭነትና ዘላቂነት ጥናት በስሜት የተጀመሩ ስለነበሩም ፕሮጀክቶቹ ብዙም ሳይጠቅሙ ውድቀት አጋጥሟቸዋል።
ወጣቱ በዘላቂ ሥራ ዘርፍ ተደራጅቶ መሥራት ቢችል መጥፎ ነገር ለማሰብም ጊዜ ስለማያገኝ የፀጥታም ሆነ የሌላ ስጋት እንደማይሆን የሚያምነው ወጣት ለገሰ “ወጣቱ ሥራ በማጣቱ ነው ችግር የሚፈጥረው” ይላል። ይሁንና መንግሥት ለተገቢ ጥያቄዎች መልስ ከመስጠት ይልቅ ማዋከብ ውስጥ ገብቶ እንደነበር ይጠቅሳል። ለአብነት በሚልም ራሱ (ለገሰ) ከተፈናቃዮች ተጠቃሚነት ጋር በተያየዘ ጥያቄ በማንሳቱ ለተደጋጋሚ እስር እንደተዳረገ ይናገራል። ይሁን እንጂ አሁን ላይ በአስተዳደሩ በኩል በተጀመሩ አዳዲስ የልማት ዕቅዶች ተስፋ እንዳለውም አልሸሸገም። ስለሆነም መንግሥት እቅዶቹን ፈጥኖ በመተግበር ወጣቱን ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚጠበቅበትም ይመክራል።
በቀጣይ ምን ይሁን?
ከዚህ በፊት በድንጋይ ፈለጣ (ካባ) ሥራ ተደራጅተው የነበረ ቢሆንም ድንጋዩ ሲያልቅ መበተናቸውን በመጥቀስ አሁን ላይ በዘላቂነት ሊሠሩት በሚችሉት ዘርፍ ተደራጅተው ወደ ሥራ ለመግባት መንግሥትን በመጠየቅና በመጠባበቅ ላይ እንዳሉ ወጣት ለገሰ ይናገራል። የወንድወሰን በበኩላቸው የተነሽ አርሶ አደር ልጆች ከዚህ በፊትም በተፈጥሮ ሀብቶች ላይ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ሲፈጠርላቸው የነበረ ቢሆንም የተፈጥሮ ፀጋዎቹ ሲያልቁ እንደሚበተኑ ያስረዳሉ። በመሆኑም የጽሕፈት ቤቱ ዓላማ ጊዜያዊውን ወደ ቋሚ የሥራ ዕድል መቀየር በመሆኑ 6014 ተነሽዎችን በ515 ማኅበራት በማደራጀት (እስካሁን 186ቱ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ አሟልተው ሕጋዊ ሆነዋል) የተቀረፁ ፕሮጀክቶች ላይ በቋሚነት እንዲሠማሩ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ ነውም ብለዋል።
ተነሽዎቹ ለዓመታት የዘለቀ የማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ እንዳላቸው የሚጠቁሙት የወንድወሰን ጥያቄዎቹን “መልክ፣ መልክ አስይዞ መፍታት ይገባል”ም ይላሉ። ሌላው የልማት ሥራ የሚቀጥል በመሆኑ በልማት ምክንያትም የሚነሳ ሰው ስለሚኖር ከካሣና መልሶ ማቋቋም ባሻገርም ትኩረት ፈላጊው ጉዳይ ያልተጣጣሙ ሕጎችን ማስታረቅ ነው ተብሏል። ለምሳሌም በፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ መመሪያ አንድ ባለይዞታ ከመሬቱ የሚነሳው እንደሚነሳ በተነገረው በዓመቱ ሲሆን፥ በመሬት ልማት ማኔጅመነት ቢሮ መመሪያ ግን በተነገረው ሦስት ወራት ውስጥ መሆኑን የሚጠቅሱት የወንድወሰን እንዲህ ዓይነቶቹ ልዩነቶች መታረቅ እንዳለባቸው ይመክራሉ።
በቅርቡ ከተነሽ አርሶ አደሮች ጋር መክረው የነበሩት የከተማው ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ አስተዳደሩ አርሶ አደሮችን የመጉዳት ፍላጎት እንደሌለው ገልጸው በልማት የሚነሱ ወገኖች የተሻለ ሕይወትን እንዲኖሩ ለማድረግ እንደሚሠራም ጠቅሰው ነበር። አክለውም አሁን ላይ እየተሠራ ያለበት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ጥያቄዎችን የመመለስ አቅሙ አናሳ በመሆኑ ወደ ከተማ ግብርና ቢሮነት አድጎ ተነሽዎችን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሠራ መሆኑን መገለጻቸውም ይታወሳል።
“ተነሺ አርሶ አደሮች ንብረቶቻቸውን በአግባቡ ሳይሰበስቡና በበቂ ሁኔታ ሳይዘጋጁ በድንገት እንዲነሱ ይደረጋል” የሚለው የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ጥናት ከተሞች መሬቱን ለልማት ማስለቀቅ እንጂ ባለ ይዞታውን በዘላቂነት ለማቋቋም ዓላማ ይዘው እንደማይነሱ በመጥቀስ አካሔዱ በቀጣይ መታረም እንዳለበት ይመክራል። “የከተማ መስፋፋት የመጨረሻ ግብ ለከተማ እና ለኢንዳስትሪ ልማት የሚሆን መሬት ማግኘት ሳይሆን በየአከባቢው የሚገኙ ዜጎች ሕይወት በዘላቂነት መቀየር ነው” የሚለው ጥናቱ የማቋቋም ሥራው መጀመር ያለበት ወደ ከተማ ከተካለሉበት ጊዜ ጀምሮ ሊሆን እንደሚገባም ያነሳል።
የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር “የከተማ መልሶ ማልማት በኢትዮጵያ፤ ነባራዊ ሁኔታዎች፣ ተግዳሮቶችና ቀጣይ ስልቶች” በሚል ያዘጋጀው ሰነድ በከተሞች “መልሶ ማልማቱ ያፈናቀላቸው ሳይቀሩ የልማቱን ተገቢነት ሁለንም ይደግፉታል” ይላል። ይሁንና በቦታው የነበሩ ዜጎች ከልማቱ በወጉ ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ያነሳል። በኢትዮጵያ ከተሞች በሚካሔዱ መልሶ ማልማትና ከተማ ማስፋፋት ሥራዎች መሬት መቆጠብና የተመጣጠነ ጥግግት መፍጠር እንደሚያስፈልግም ይመክራል። ከመስፋት ይልቅ ያሉ ቦታዎችን መጀመሪያ በአግባቡ መጠቀም እንደሚሻልም ያክላል። ንጉሱ እንደሚሉት ከሆነ ከዚሀ በኋለ ተነሽውን ለዘላቂ ሮሮ የሚዳርግ አሰራር አይተገበርም። “ቅሬታ እየፈጠርን አንሔድም ተነሽዎችና ከተማው በጋራ የሚለሙበት ስልት ነው የሚቀመጠው” ይላሉ።
የሕግ ባለሙያው አበበ የሚመክሩት በልማት ወቅት ገበያውን ያገናዘበ የካሣ ዋጋ እንዲወጣ ወይም ባለይዞታው ራሱ ቦታው ለልማት እንደሚፈለግ ከተረዳ በኋላ ራሱ እንዲሸጥ ማድረግን ነው። እንዴት ግለሰብ ደረቅ መሬት ሊሸጥ ይችላል የሚለው ጥያቄ እንደሚነሳ በመጥቀስም መሸጥ አይቻልም ይባል እንጂ፥ አርሶ አደሩ በሕገወጥ መንገድ በሸጣቸው ቦታዎች ላይ የሚገነቡ “ጨረቃ ቤቶች” ሕጋዊ እየተደረጉ ስለሆነ የሚሻለው አርሶ አደሩ ቢፈልግ በካሣ ካልሆነም በራሱ እንዲሸጥ ሕጋዊ ከለላ መስጠት እንደሆነ ያነሳሉ።
ሌላው እየተነሳ ካለው ጥያቄ ጋር በተያያዘ ምላሽ ሲሰጥ ጥንቃቄ እንደሚፈልግ ይመክራሉ። ሌሎች በተለያየ ምክንያት የተፈናቀሉ ኢትዮጵያዊያንም ነገ ጠዋት “እኛስ?” የሚል ጥያቄ ይዘው ሲመጡ ሊያስተናግድ የሚችል አካታች የሕግ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልግ ነው የሚያስገነዝቡት። ይህ ካልሆነ እነሱ ከእከሌ ብሔር ስለሆኑ ነው የሚል ሌላ ትኩሳት ይዞ እንዳይመጣም ስጋት አላቸው።

ቅጽ 1 ቁጥር 5 ታኅሣሥ 6 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here