ጥበብ – በኮቪድ19 ቫይረስ ወረርሽን መካከል

0
558

ኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ በዓለም ላይ ከፈጠራው ስጋትና ጭንቀት በተጨማሪ፣ የዓለምን የክዋኔ እቅዶች አዛብቷቸዋል። በስፖርቱ የ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ እንዲራዘም ግድ ከማለቱ በተጨማሪ፣ ስለስፖርት የሚነገር ወሬ ጠፍቷል። አሁን የእግር ኳሽ ቡድኖችና ተጫዋቾቻቸው ሥማቸው የሚነሳው ባስቆጠሩት ነጥብና ባሳዩት ብቃት አይደል። ይልቁንም ‹ተጠንቀቁ! ራሳችሁን ጠብቁ› ብለው ሲናገሩ አልያም የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ ነው። ሲከፋ ደግሞ በቫይረሱ ሲያዙ።

ይህን አነሳን እንጂ ነገራችን ከሌላኛው መዝናኛ፣ ከጥበቡ መስክ ነው። አሁን ሲኒማና ቴአትር ቤቶች ተዘግተዋል። የሙዚቃ ድግሶች ተራዝመዋል። ቴአትሮች አይታዩም። ቀን ጠብቀው በሳምንትና በቀናት ልዩነት ይቀርቡ የነበሩ የቴሌቭዥን ዝግጅቶች ቀርተዋል። ይህ ደግሞ ለሳምንት ብቻ አይደለም፣ ለወራት ይዘልቃል ተብሎ የሚጠበቅ ነው።

ከቀናት በፊት ዘጋርድያን ባወጣው ዘገባ፣ በሆሊውድ 12 ሺሕ በላይ ሰዎች ከሥራ ውጪ ሲሆኑ፣ በኢንግሊዝ ደግሞ 50 ሺሕ የትርፍ ሰዓት ተቀጣሪዎች ሥራቸውን ሊያጡ ይችላሉ ተብሎ ነበር። በዓለም አቀፍ ደረጃ በጉጉት ይታዩ የነበሩ ተከታታይ ፊልሞች ሳይቀሩ ታጉለዋል። በኤቢሲ ፊልም ፕሮዳክሽን ተዘጋጅቶ ይቀርብ የነበረው ‹ግሬይ አናቶሚ› የተሰኘውና 16ኛ ምዕራፍ ላይ የሚገኘው ሕክምና ላይ ያተኮረው የፊልም ፕሮዳክሽን ተቋርጧል።

ይህም ሁሉ ዘርፉን አደጋ ላይ የጣለና በገንዘብ ደረጃም ቀውስን የሚያስከትል ነው ተብሏል። የፊልም ባለሞያዎችም ‹ተጠንቀቁ› ከሚል መልዕክታቸው በተጓዳኝ፣ ኑሯቸውን በዚህ ላይ ያደረጉና ከሥራቸው የተፈናቀሉ በዘርፉ ለሚሠሩ ባለሞያዎች ድጋፍ እንዲደረግላቸው ቅስቀሳ እያደረጉ ነው።

የተቀናጀ አሠራር ባለው የሆሊውድ የፊልም ኢንደስትሪ ውስጥ ለዘመናት የኖረው ትስስር አሁን በተዘጉ በሮች ተቋርጧል። አዳዲስ ፊልሞች ከታዩና ከተመረቁ ሰንብተዋል። የጥበቡ ዘርፍ በፊልሙም ሆነ በሙዚቃ፣ በቴአትርም ሆነ በሥነ ጥበቡ፣ ሁሉም ከኪሳራ አልዳነም።

ኢንግሊዛዊቷ የባፍታ ሽልማት አሸናፊ ሬቤካ ብራያን ለዘጋርድያን በሰጠችው አስተያየት፣ የቫይረሱ ወረርሽኝ አሁን በመዝናኛው ዘርፍ እያስከተለ ካለው ተጽእኖ ባሻገር ለነገም አሻራው አይጠፋም ብላለች። በተለይም የፊልም ታሪኮች ጭብጥን ሊቀይር ይችላል የሚል እይታ አላት። ‹‹አሁን ላይ የበለጠ የሚየሳስበኝ ሰዎች በቫይረሱ እንዳይያዙ መከተል የሚገባቸውን መመሪያ እንዲከተሉ ነው። ልቤ ደግሞ በፊልም ዘርፍ በኮንትራት ሲሠሩ የቆዩና ውላቸው የተቋረጠ የፊልም ባለሞያዎች ጋር ነው›› ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች።

የፊልም ዳይሬክተርና የኦስካር አሸናፊ ኬቨን ማክዶናልድ፣ እድለኛ ነኝ ይላል። ይህን ያለው ዓለም በሮቻችሁን ዝጉ ብላ ለነዋሪዋቿ ልታሳስብ ኹለት ሳምንት ሲቀራት ጀምሮት የነበረውን ፊልም ቀረጻ በማጠናቀቁ ነው። ምንም እንኳ ሁኔታዎች ፊልሞችን ለማሳየት የሚፈቅዱ ባይሆንም፣ እስኪስተካከል ድረስ ጊዜ ሰጥቶ፣ ፊልሙን ከካሜራው ዐይን ወደ ተመልካች የሚወጣበትን መልክ ለማስያዝ ሰፊ ጊዜ አግኝቷል።

ሆኖም ከእርሱም ዘንድ ስጋቶች አሉ። የቫይረሱ ስርጭት ቀንሶ ወይም ጠፍቶ ጉዳዮች ወደ ቀደመ ነገራቸው ሲገቡ፣ አሠራሮች አብረው ቢቀየሩስ? ሰዎች ፊልም የማየት ፍላጎታቸው ምን መልክ ይኖረዋል? ምን ማየት ይፈልጋሉ? የነበረው አሠራር ያገለግል ይሆን? የፊልሞች ጭብጥስ ምን መልክ እንዲኖራቸው ይጠበቃል? ብዙ ጥያቄዎች አሉ።

‹ክራከን ፊልምስ› የተባለ ኩባንያ ኃላፊ ጆ ሬይ ያስተላለፈው ተቀማጭነቱ በለንደን ነው። ‹‹ቤት ውስጥ በመገለል የተቀመጣችሁ የኔትፍሊክስ ፊልሞችን ተመልከቱ። በመካከል ግን ያንን የሠሩትን ባለሞያዎች ለአፍታ አስቧቸው›› ብሏል። በእርሱ ስር ይሠሩ የነበሩ የፊልም ፕሮዳክሽኖች መቆማቸውን በመጥቀስና ብዙዎች ሥራ ማጣታቸውን በማንሳት ነው ይህን ያለው።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት የፊልምና ሙዚቃ ሰንጠረዥ የሚያወጣው ‹ቦክስ ኦፊስ› በወረርሽኙ ምክንያት አምስት ቢሊዮን ዶላር ያጣል። በተለያዩ አገራት እንዲሰረዙ የተገደዱ ጥበብ ላይ ያተኮሩ የሽልማት ዝግጅቶችም አሉ። በዚህም የፈረንሳይ፣ የጃፓን፣ የህንድ፣ የጣልያን አገርና ዓለም ዐቀፍ የፊልም ሽልማቶች ተራዝመዋል። ጥቂት የማይባሉ የፊልም ፌስቲቫሎችም ቀርተዋል።

የሙዚቃ ድግሶችም በዓለም መድረክ በተመሳሳይ ተራዝመዋል። ድምጻዊ ጀስቲን ቢበራ፣ በትዊተር ገጹ ‹‹የአድናቂዎቼ፣ የቡድን አባላቶቻችንና በሥራው የተሳተፉ ሰዎች ሁሉ ለእኔ ትልቅ ቦታ ያላቸው ናቸው። አሁን ዓለም አስፈሪ ቦታ የሆነች ቢሆንም አብረን መላ እንፈልጋለን። ይህ ጊዜ አልፎ ደኅና ሆነን በአካል እስክንተያይ በጉጉት እጠብቃለሁ። ራሳችሁን ጠብቁ› ብሏል፤ የነበረውን ሙዚቃ ድግስም አራዝሟል።

በተመሳሳይ ዘ ሮሊንግ ስቶንስ፣ ኤልተን ጆን፣ ኬሊ ክላርክሰን፣ ጆናስ ብራዘርስ፣ ማሪያ ኬሪ፣ አሊሽያ ኪስና ሌሎችም የሙዚቃ ድግሶቻቸውን አራዝመዋል። የሚብሰው የሰዎች ጤና ነውና ለዛ ቅድሚያ ሰጥተዋል። ሁሉም የተሻለው ቀን እንዲመጣ ጥንቃቄ እንዲያደርግና እንዲበረታ መልዕክትና ማጽናኛ ቃል ማስተላለፍ ላይ አተኩረዋል።

ኢትዮጵያና ጥበባዊ ክዋኔዎች – በኮቪድ19
አዲስ አበባ በየሳምንቱ አልያም ኹለት ሳምንት እየቆጠረች፣ ጥበባዊ ክዋኔዎችን ታስተናግድ ነበር። አሁን ግን ራስ ሆቴል፣ ኢትዮጵያ ሆቴል፣ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ ወመዘክር አዳራሽና ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ጭር ብለዋል። ጦብያ ግጥምን በጃዝ፣ ሰምና ወርቅ፣ ብራና ወዘተ የወግና ዲስኩር ምሽቶች ሊናፈቁ ነው።
አዳዲስ ፊልሞች በሳምንት ልዩነት የሚያሳዩ ሲኒማ ቤቶች፣ ‹ጭር አለብን› ሲሉ እንዳልኖሩ፣ አሁን ጭራሽ በራቸውን ዘግተዋል። ቴአትር ቤቶች ወርሷቸው ከኖረ ጭርታ ሊወጡ ቀና ባሉበት ሰዓት ወረርሽኙ ሌላ ጥላ ሆኖ ጭርታ እድሜያቸውን አራዝሞታል።

በደብረ ብርሃን ከተማ በሚዘጋጅ የግጥምና ዲስኩር ምሽት ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል። ጦቢያ ግጥም በጃዝን ጨምሮ፣ ብራና፣ ሰምና ወርቅ፣ ጦቢያ፣ የምስክር ጌታነው ፕሮዳክሽን እና በርካታ ክዋኔዎች ድምጻቸው ጠፍቷል። ይህን ያነሳው የቴአትር ባለሞያ፣ ገጣሚና ደራሲ አንዷለም አባተ ለአዲስ ማለዳ በሰጠው አስተያየት፣ ጉዳዩ በርካታ ጥበባዊ ክዋኔዎች ላይ ተጽእኖ እንደፈጠረ አንስቷል።

እነዚህ ክዋኔዎች አለመካሄዳቸው በባለቤትነት ከሚሠራው በላይ የሚሰናዱና የሚያዘጋጁት እንደተጎዱም ጠቅሷል። ሥራዎቻቸውን አቅርበው የሚከፈላቸው፣ አዳራሽ የሚያከራዩና መሰል በትስስሩ ላይ ጉዳት እንዳለው፣ ቢሮ ተከራይተው ለሚሠሩም የበለጠ ከባድ ይሆናል ብሏል።

‹‹ቀድሞም አትራፊ ሆኖ የሚኖርበት ዘርፍ አይደለም።›› ያለው አንዷለም፣ ያም ሆኖ አሁን በወረርሽኙ ወቅትም ግንዛቤ ለመስጠትና ቅስቀሳ ለማድረግ የኪነጥበብ ባለሞያው እንዳላረፈ ሳያነሳ አልቀረም። ኪነጥበብ እንዲህ ባለ አጋጣሚ ብቻ ሳይሆን በባህሪውም የሁሉም ልሳን በመሆኑ፣ ገቢ የሚያስገኘው ሥራ ጭር ቢልም አገልግሎቱ አልታጎለም።

ታድያ የሚበተኑ ሠራተኞች ሥራ የሚያጡ ይኖሩ እንደሆነ ድጋፍ ማድረግ በሚችል አቅም በተለያየ መንገድ ድጋፍ መስጠት ይገባል።እንደ አንዷለም ገለጻ ከሆነ፣ በዘርፉ በጠቅላላ ሊኖር ከሚችለው ኪሳራ በላይ የሕዝብ ጤና ይልቃልና፣ ግንዛቤ መስጠት ላይ የቀሩ የቤት ሥራዎችን ለመሥራት መረባረብ የግድ ነው ይላል።
ታድያ ከዛሬ ባሻገር፣ ነገ ላይ በሚወጡ ሥራዎች ጭብጥ ላይም ይህ ወረርሽኝ ምልክት ማስቀረቱ አይቀርም። በተለይም ጉዳቱ በዚህ ከቀጠለና ከበረታ፣ የዘመን መንፈስ ተቃኝቶበት፣ የዘመን አካፋይ ሆኖ ሊጠራ ይችላልም ይላል። ‹‹ከጣልያን አምስት ዓመት ጦርነት በኋላ አብዛኛው ጽሑፍ በአገርና በአርበኝነት ላይ ያተኮረ ነበር። እንዲህ ያለ ክስተትም በፍጹም መንፈሱን ይቀይረዋል።›› ብሏል።

ግጥሞች፣ ወጎችና ልብወለዶች፣ ዲስኩሮችና አነቃቂ ንግግሮች ኮሮና ከተሸኘ በኋላም ኮሮናን ጉዳይ አድርገው ማቆየታቸው አይቀርም። ይህም በችግር ሰዓት ወርቃማ መፍትሔዎች ይወለዳሉና፣ በዘመን መካከል ስለተፈጠረው አስከፊ ክስተት ብቻ ሳይሆን፣ ስለነበሩ መልካም ነገሮችም የሚነሳበት አጋጣሚ ብዙ ስለሚሆን ነው፣ እንደ አንዷለም አስተያየት።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ከመጋቢት 8 ቀን 2012 ጀምሮ አዳራሾቹን ዘግቶ፣ ሠራተኞቹ በየቤታቸው እንዲቀመጡ ብሏል። በሳምንት ስምንት ቴአትሮች ለእይታ ይቀርቡ እንደነበር ያነሱት የቴአትር ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በፍቃዱ ከፈለኝ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ተመልካቾች ቀርተዋል፣ አዳራሽ ተከራይተው የነበሩ ክዋኔያቸአውን ሰርዘዋል፣ በግላቸው የኪነጥበብ ዘርፍ ላይ የሚንቀሳቀሱ ያሰቧቸው ሥራዎች ቀርተዋል ብለዋል።

ይህም ታድያ ቴአትር ቤቱ ሊያገኝ የሚችለውን ከፍተኛ ገቢ አሳጥቶታል። ሠራተኞች ስለጤናቸውና ስለሌሎችም ጤና ሲባል ቤታቸው እንዲቀመጡ የተደረገ ሲሆን፣ በቋሚነት 14 ሰዎች ብቻ ቢሮ እንደሚገኙም በፍቃዱ አንስተዋል። ሁኔታዎች እስከሚረጋጉም ቴአትር ቤቱ ዝግ ሆኖ እንደሚቆይና፣ ሥራ ሲጀመር ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

እንደ ማሳያ ብሔራዊ ቴአትርን ጠቀስን እንጂ በተለይ በግል የሚንቀሳቀሱ የሲኒማ ማሳያ ቤቶች የሚደርስባቸው ኪሳራ ቀለል የሚባል እንደማይሆን ግልጽ ነው። ዋናው ግን ጤና ነውና፣ መረዳዳትን ባለመዘንጋትና በመተጋገዝ ውስጥ መቆየት እንደሚገባ የሁሉም ሐሳብ ነው። የከፋው ይመጣል ተብሎ ቢጠበቅም፣ የተሻለ ቀንም መምጣቱ አይቀርምና፣ ተስፋን ሳይቀንሱ ጥንቃቄን አጠንክሮ መቆየት ያሻል፤ የባለሞያዎቹ መልዕክት ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 74 መጋቢት 26 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here