አዲስ አበባ ከተማ በምግብ ራሷን እንድትችል የሚያደርግ እና የከተማ ግብርናን የሚያበረታታ አዲስ ስትራቴጂ እየተዘጋጀ መሆኑን የከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን አስታወቀ። ኮሚሽኑ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገረው፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አርሶ አድርና የከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን በአዲስ አበባ የከተማ ግብርና ልማትን ለማጠናከር እንዲሁም በከተማዋ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት እቅድ አየተዘጋጀ መሆኑን ይፋ አድርጓል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ፈትያ መሐመድ፣ ኮሚሽኑ በእቅዱ ካስቀመጣቸዉ ዋና ዋና ተግባራት መካከል የአዲስ አባባ ከተማ የከተማ ግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ መገንባት እና በከተማዋ የከተማ ግብርና እንዲመሰረት ማድረግ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርኩንም በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ ለመገንባት እቅድ እንደተያዘ ፈትያ አክለው ጠቁመዋል።
የከተማ ግብርና ሥራው በተቀናጀ መልኩ ወደ ሥራ ሲገባ፣ በአዲስ አባባ ከተማ በሕንጻዎች እና መኖሪያ ቤቶችም ጭምር ለከተማ ግብርና ምርት እንዲያገለግሉ እንደሚደረግ ኮሚሽነሯ ተናግረዋል። የከተማ ግብርና ሥራው የሚከናወነው እንደ ገጠራማው የግብርና ሥራ በሰፊ መሬት ላይ የሚደረግ ሳይሆን፣ በትንሽ ስፍራ ላይ ተመስርቶ በተደራራቢ ዘዴ በመጠቀም እንደሚሆንም ኮሚሽነሯ አመላክተዋል። አያይዘውም ተደራራቢ በሆነ መልኩ ወደ ላይ በማስፋት በቀጣይ ባሉት ሦስትና አራት ዓመታት ውስጥ ለመተግበር እየተሠራ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የከተማ ግብርና ሥራው ዕቅዱ ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባ 50 ሺሕ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር እና ይህንን ሐሳባቸውንም ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር እንደተረዱላቸው ፈትያ ጠቁመዋል። የፌዴራል መንግሥት እና ከተማ አስተዳደሩ በከተማ ግብርና ዘርፉ ለሚሰማሩ ወጣቶች ሁኔታዎችን ምቹ እንደሚያደርጉም ፈትያ ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ያከናወናቸው ተግባራት እንዳሉ የገለጹት ኮሚሽነሯ፣ ከተጀመሩት ሥራዎች ውስጥ ወደ ሥራ መግባት ለሚፈልጉ አካላት ሥልጠና የመስጠት እና የማማከር ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል። እንደ ኮሚሽነሯ ገለጻ፣ የተጀመረዉ የከተማ ግብርና ልማት ተጠናክሮ ሲቀጥል ከሥራ ዕድል ፈጠራ ባሻገር ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት በማስገባት የምትጠቀማቸውን ምርቶች በአገር ውስጥ ምርት ለመተካትና በአገር ውስጥ በሚመረቱ ምርቶች ለመጠቀም ያስችላል ብለዋል።
አዲስ አበባ 27 ወንዞች እንዳሏት ያስታወሱት ኮሚሽነሯ፣ ከተማዋ ያላትን ሀብት በአግባቡ ከተጠቀመች እራሷን በከተማ ግብርና መመገብ እንደምትችልም አብራርተዋል። ወንዞችን ጽዱ በማድረግ በኩል የሸገር ፕሮጀክት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።
ዘርፉን ለማሳደግ በከተማ ግብርና ልማት ልምድ ካላቸዉ አገራት ልምድ ለመጋራት እቅድ መያዙንም ኮሚሽነሯ ጠቅሰዋል።
ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገውን የሰዎች ፍልሰት ታሳቢ በማድረግ ከተማዋ የራሷ የሆነ ከተማ ግብርና እንዲኖራት በማስፈለጉ የተቋቋመው ኮሚሽኑ፣ ሰባት ወራት ዕድሜ አለው። ከወጣቶች እና ወደ ከተማ ግብርና ለመግባት ፍላጎት ካላቸው ግለሰቦች ጋርም በሙያዊ እና ቴክኒካዊ ድጋፍ ለማድረግ በጋራ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ኮሚሽኑ የግማሽ ዓመቱን የዕቅድ አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት እንዳስታወቀው፣ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ለተሰማሩ ማኅበራት ሕጋዊ ሰውነት መስጠቱንና ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውቋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 74 መጋቢት 26 2012