በአዲስ አበባ የጎዳና ተዳዳሪዎችን በቋሚነት ወደ መጠለያ ለማስገባት እየተሠራ ነው

0
602

በከተማዋ 52 ሺሕ የሚደርሱ የጎዳና ተዳዳሪዎች ይገኛሉ።

የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር በአዲስ አበባ 52 ሺሕ ለሚደርሱ የጎዳና ተዳዳሪዎች በቋሚነት መጠለያ በማዘጋጀት ላይ እንደሆነ አስታወቀ። ሚኒስቴሩ ጨምሮ እንደገለጸው፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተከትሎ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ተጋላጭነት ለመቀነስ እየተሠራ ቢሆንም፣ ከወረርሽኙ ባለፈ ግን በዘላቂነት በመጠለያ የሚኖሩበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየተሠራ እንደሆነ ተገልጿል።

የሚኒስቴሩ ሕዝብ ግንኙነት አድነው አበራ እንደገለጹት፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችን እጅ በማስታጠብ እና አልፎ አልፎ በመጎብኘት ዘላቂ ውጤት ማምጣት አይቻልም። ይልቁንም መፍትሄው ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ አማካኝ ምን ያህል የጎዳና ተዳዳሪዎች አሉ የሚለውን ከተለየ በኋላ ለእነርሱ የሚሆን መጠለያ ማዘጋጀት ቀዳሚ ነው ብለዋል።

ይህን ሥራ ለይተን ጨርሰናል የሚሉት ኃላፊው፣ ካሉት 52 ሺሕ የጎዳና ተዳዳሪዎች 12 ሺሕ የሚሆኑት አዋቂዎች ሲሆኑ የተቀሩት ታዳጊዎች መሆናቸው ታውቋል ብለዋል። በጎዳና ላይ የሚገኙትን ሰዎች ወደሚዘጋጅላቸው መጠለያ እንዲገቡ ማድረግ፤ የበሽታውን ስርጭት እንዲቀንስ የማድረጉን ሥራ እንደሚያጠናክርም ጠቁመዋል።

‹‹ከዚሁ በተጨማሪም በሕጻናት ማሳደጊያ ማእከላት የሚገኙ ሕፃናትን እና በማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ሴቶችን እየለየን እንዲጎበኙ ከማድረግ ባሻገር ከተለያዩ አካላት እርዳታ በማሰባሰብ ሊሟላላቸው የሚገቡ ቁሳቁሶች ማለትም ( ሳኒታይዠር፣ አልኮል ፣ ሳሙናዎች) እንዲሟሉላቸው ማድረግ ላይም እየተሠራ ነው።›› ሲሉ አስታውቀዋል።

ሚኒስቴር መሥርያ ቤቱ የኮሮና ቫይረስ አገር ውስጥ መግባቱን ተከትሎ፣ የወረርሽኙ ፍጥነት ከፍተኛ በመሆኑ እና ታዳጊዎቹ ጎዳና ላይ ከመሆናቸው አኳያ እነሱ ተጋላጭነታቸው ከሌላው የኅብረተሰብ ክፍል አንፃር እንደሚብስ በማሰብ፤ የግንዛቤ ማስጨበጫ እየተሠራ ነው በማለት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በተያያዘም አዲስ ማለዳ በአዲስ አበባ ከተማ የጎዳና ሕይወት የሚኖሩ ታዳጊዎችን አነጋግራለች። ከዛም መካከል ብሩክ አብዬ የተባለ ታዳጊ ሜክሲኮ አካባቢ ጎዳና ላይ መኖር ከጀመረ አራት ዓመት እንደሆነው በመግለጽ፣ በአሁኑ በወረርሽኝ መልክ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ሰዎች ሲያወሩ እንደሰማ ያነሳል። ነገር ግን ስለ በሽታው በቂ እውቀት እና በሽታው እንዳይዘው ምን ማድረግ እንዳለበት እንደማያውቅም ይናገራል።

እንደ ብሩክ ገለፃ ከሆነ፣ ከመንግሥት አካላት የተወጣጡ ግለሰቦች ወደ ብሩክ እና ሌሎች የጎዳና ተዳዳሪዎች በመቅረብ ከአካባቢው እንደሚያነሷቸው እንደሚነግሯቸው ያወሳል። ‹‹እኔና ጓደኞቼ ባለንበት አካባባቢ ተደጋጋሚ የመንግሥት ሠራተኞች ከዚህ ቦታ ልናነሳችሁ ነው ብለው ከመናገር ባሻገር እርዳታም ሆነ ዘላቂ የሆነ መፍትሄ የሰጠን አካል የለም›› በማለት ያስረዳል።

በተጨማሪም ‹‹የበሽታው ስርጭት እንዲቀንስም እኛም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለን እንደመሆናችን፣ ሊዛመት ስለሚችል፣ መንግሥት መኖሪያ አስተካክሎ እንዲወስደን እንፈልጋለን›› በማለት ብሩክ ተናግሯል። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ‹‹ኮሮና ምን ማለት እንደሆነ አላውቅም›› የሚለው እስጢፋኖስ አካባቢ እንደሚኖር የሚናገረው ትዝታው ድንበር ነው። እርሱም በመንግሥት በኩል ኹለት ጊዜ ወደ ማእከል ገብቶ እንደነበርና ኹለት ጊዜም እንደወጣ ያስታውሳል።

ትዝታው እንደሚለው ማእከል ውስጥ ከሚኖሩት ኑሮ የጎዳናው ይሻላል። ምክንያቱም እንዲህ ነው፤ ‹‹ጎዳና ላይ ሰው የለም ለማለት እንጂ ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ለማምጣት አይደለም እኛን የሚያስገቡን። እንክብካቤ የለም፣ ብንታመምም ሕክምና ለማግኘት አንችልም። በተጨማሪም አቅም ያለን ልጆች በራሳችን ሠርተን እንድንተዳደር ሊያደርግን የሚችል እድል ካልፈጠረልን፣ አንድ ቦታ መሰባሰባችን ለእኛ ጥቅም የለውም›› ሲል ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።

ቅጽ 2 ቁጥር 74 መጋቢት 26 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here