የበረሃ አንበጣ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ተገለጸ

0
917

በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከተከሰተው የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ በበለጠ አዲስ የአንበጣ መንጋ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው፣ የአንበጣ መንጋ ከዚህ ቀደም ባልተከሰተባቸው አካባቢዎች የመከሰት አዝማሚያ በማሳየቱ እና መጤ ባለመሆኑ የሚያደርሰውን ጉዳት ያከፋዋል።

የግብርና ሚኒስቴር ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሞገስ ኃይሉ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ቀድሞ ገብቶ የነበረው የአንበጣ መንጋ የጣለውና አሁን እየተፈለፈለ የሚገኘው እንቁላል፣ ከዚህ ቀደም ተከስቶ ባልነበረባቸው አካባቢዎች ነው። ይህም ደግሞ የበረሃ አንበጣው እስከ አሁን ካደረሰው ጉዳት የባሰ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል ተብሎ እንዲጠበቅ አድርጎታል።

እንደ ሞገስ ገለፃ፣ በአዳዲስ ቦታዎች ላይ እንቁላሎች እንዲፈለፈሉ እና የሚያካልሉት ቦታ እንዲበዛ የሆነበት ምክንያት፣ ለአራት ሳምንታት የቆየው የአየር ንብረት መለዋወጥ እና የበረሃ አንበጣው እንቁላል የጣለበት ቦታ በፍጥነት አለመታወቁ ነው።

በተጨማሪም አንበጣዎቹ እንቁላላቸውን ጥለው በመፈልፈል ያሉባቸው ቦታዎች ስድስት እንደሆኑም ማወቅ ተችሏል። ከዚህም ጋር በተያያዘ አሳሳቢ ጉዳይ የተባለው የበረሃ አንበጣ መንጋ ወረርሽኝን በተመለከተ፣ የእጽዋት ጤና እና ቁጥጥር ዳይሬክተር ጄነራል ወልደሐዋርያት ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ከዚህ ቀደም እንደ ኬንያ ካሉ ጎረቤት አገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚገባውን የበረሃ አንበጣ ለመከላከል ቅድመ መከላከል ይደረግ ነበር። አሁን ግን በአገር ውስጥ መፈልፈል መጀመሩ እና ቦታዎችን በአፋጣኝ ለይቶ ማወቅ ባለመቻሉ፣ ጉዳቱን የከፋ ያደርገዋል ሱሉ ገልጸዋል።

ከ2012 አጋማሽ የካቲት ወር ላይ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራዎች እንደተጀመሩ የሚገልጹት ዳይሬክተሩ፣ ‹‹ከዓመቱ አጋማሽ ጀምሮ ማለትም ከየካቲት ጀምሮ በዚሁ ሥራ ላይ ነበር የተጠመድነው። በተለይም ከጎረቤት አገራት የገቡትን የበረሃ አንበጣዎች ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቶ ተሠርቶበት ነበር።›› በማለት ያስታውሳሉ። ነገር ግን አሁን ላይ በአገር ውስጥ አዳዲስ ቦታዎች ላይ መፈልፈል መጀመሩ ‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ› እንዲሆን አድርጎታል በማለት ተናግረዋል።
ዳይሬክተር ጄነራሉ እንደጠቀሱት፣ አንበጣው በሚገኝባቸው አካባቢዎች ጉዳት አድርሷል። ይሁንና የጉዳቱ መጠን ግን ምን ያህል ነው ለሚለው መልስ ለመስጠት አንበጣው የሸፈነውን ቦታ ለማወቅ የወደመውን መለየት እንዳልተቻለ ተናግረዋል።

‹‹ጸረ ተባይ የመርጨት ሥራ እየሠራን ነው ያለነው።›› ይላሉ ዳይሬክተር ጄነራሉ። በዚህም አምስት እርጭት የሚከናወንባቸው አውሮፕላኖች ተከራይተዋል። መሬት ለመሬት ፀረ ተባይ መርጫ መኪናም እንደተዘጋጀና ከዛም በተጨማሪ በእጅ የሚታዘዙ የፀረ ተባይ መርጫዎች ወደ ሥራ ገብተው መከላከል ሥራው እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ የበረሃ አንበጣውን በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር ይከብዳል ብላው እንደሚያስቡም ወልደ ሃዋርያት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የዳይሬክተሩን ሐሳብ የሚጋሩት የግብርና ሚኒስቴር ሕዝብ ግንኙነት፣ በግብርና ሚኒስቴር በኩል አንበጣውን በፍጥነት ለመቆጣጠር ተሰራጭቶ ያለበት ቦታ ላይ የፀረ ተባይ ርጭት የማከናወን ሥራ እየተከወነ ይገኛል። ነገር ግን የአንበጣው የመፈልፈል ፍጥነት እና እርጥበት አዘል አየር ከከፍተኛ ሙቀት ጋር እየተለዋወጠ በመሆኑ፣ ሥራው ውጤታማ እንዳይሆን ማድረጉን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በደቡብ ክልል በኬኒያ በኩል ወደ ኢትዮጵያ የገባ ቦረና ጉጂ ዞን ተፈልፍሎ ከፍተኛ የእድገት ደረጃ ላይ መድረሱን እና የመከላከል ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። ከዛም በተጨማሪ የበረሃ አንበጦቹ የተፈለፈሉበት ቦታ ላይ ከፍተኛ የሚባል ጉዳት በሰብል ላይ እያደረሱ እንዳሉ ተናግረው፣ ነገር ግን የጉዳቱ መጠን በውል እንደማይታወቅም ገልጸዋል።

ከዛም በተጨማሪ በሶማሌ እና በድሬዳዋ፣ በምሥራቅ ሃረርጌ፣ በአርሲ ባሌ አካባቢ ከዛም በተጨማሪ ቦረና ምዕራብ ጉጂ እና ምሥራቅ ጉጂ አካባቢ እንዲሁም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በኮንሶ እና አካባቢው በሚገኙ ወረዳዎች ላይ መጤ የሆኑት የበረሃ አንበጦች ላይ የፀረ ተባይ እርጭት በማከናወን ላይ ነን በማለት ተገልፀዋል።

ነገር ግን በአገር ውስጥ መፈልፈል የጀመረው የበረሃ አንበጣ፣ በደቡብ ኦሮሚያ ቦረናና ጉጂ እንዲሁም በደቡብ ደግሞ ኮንሶ ላይ በመስተዋሉ የቁጥጥር ሥራ መስራት ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 74 መጋቢት 26 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here