የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ በግንባታ ግብዓት እጥረት ሥራውን በከፊል እንዳቆመና ሠራተኞችን ለመቀነስ እንደተገደደ አስታወቀ። ኢንተርፕራይዙ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው የኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ የግንባታ ግብዓቶችን በበቂ ሁኔታ ማቅረብ ባለመቻሉ የግንባታ እንቅስቃሴው ሊገታ ነው።
ኢንተርፕራይዙ በዋናነት ከሚያከናውናቸው የግንባታ ፕሮጀክቶች ውስጥ የመንገድ ግንባታ አንዱ መሆኑ ይታወቃል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ፕሮጀክቶች ላይ በነዳጅ አቅርቦት እጥረት የግንባታው እንቅስቃሴ እየተስተጓጎለ መሆኑን የኢንተርፕራይዙ የሰው ሀብት አስተዳደር ኃላፊ ፍቅሩ አበበ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ፍቅሩ አያይዘውም ኢንተርፕራይዙ ካጋጠመው የግንባታ ግብዓት ዕጥረት በከፍተኛ ሁኔታ የነዳጅ ዕጥረቱ ካልተስተካከለ ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴ ለማቆም እንደሚገደድ አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት 10 ሺሕ ቋሚ እና ጊዜያዊ ሠራተኞች ያሉት ኢንተርፕራይዙ፣ ፈቃድ ያላቸውን በፈቃድ፤ ፈቃድ የሌላቸውን ደግሞ በግዴታ ፈቃድ እንዲወጡ እያደረገ እንደሚገኝ ፍቅሩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ችግር በተመለከተ ቫይረሱ በግንባታ ዘርፍ ላይ እያሳደረ የሚገኘው ጫና ከፍተኛ እንደሆነ የኢፌዴሪ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
ቫይረሱ የግንባታ ኢንዲስትሪው ላይ እያሳደረ ያለው ጫና እየበረታ መምጣቱንም የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ላቀው አበጀ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በተከሰተው ወረርሽኝ ምክንያት ከውጭ የሚገቡ የግንባታ እቃዎች በሚፈለገው ልክ ማስገባት አለመቻሉ በሕንፃና በመንገድ የግንባታ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑንም ገልጸዋል። የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ መከሰት በግንባታ ኢንዱስትሪዎች ላይ የግብዓት እጥረት በማጋጠሙ በአገሪቱ ያሉ የግንባታ ድርጅቶች ሥራ ለማቆም እና የሠራተኛ ቅነሳ ለማድረግ መገደዳቸውንም ጠቅሰዋል።
የግንባታው ኢንዱስትሪ በባህሪው ከስፍራ ስፍራ ተንቀሳቃሽና የበርካታ ባለሙያዎች ተሳትፎ ያለበት፣ አያሌ ግብዓቶችን የሚጠቀም እንደመሆኑ የግብዓት እጥረት ሲጋጥም ተቋቁሞ ለመቀጠል የሚችልበት አጋጣሚ ከባድ እንደሚሆን ገልጸዋል። ፍቅሩ አያይዘውም ወረርሽኙ በተለይም በኢትዮጵያ ከተከሰተ በኋላ ግብዓቶች የገቢ ንግድ መቀዛቀዙን አስታውሰው፣ የግብዓት እጥረቱ ሊቀጥል ይችላል የሚል ግምት አለኝ ብለዋል።
ፍስኃ ኃይለሚካኤል ጠቅላላ አስመጪ እስከ አሁን ለግንባታ አገልግሎት የሚውሉ የተለያዩ ግበአቶችን ያቀርብ የነበረ ሲሆን በወረርሽኙ መከሰት ምክንያት ሙሉ በሙሉ ሥራ ማቆሙን የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ፍስኃ ኃይለሚካኤል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ፍስኃ ድርጅታቸዉ የግንባታ እቃዎች ከውጭ ማስገባት ያቆመበት ዋና ምክንያት የግንባታ እቃዎችን የሚያዙ የግንባታ ተቋራጮች ሥራ በማቆማቸዉ እና ሥራ በመቀዝቀዙ ለሠራተኞች ደምወዝ መክፈል ባለመቻላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
በመንግሥት እና በሌሎች የግል የግንባታ ተቋማት እየተገነቡ ያሉ ግንባታዎች ያሉበትን ሁኔታ ለመፈተሽ በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ካሊድ አብዱራህማን የተመራ ቡድን በአዲስ አበባ በሚገኙ አንዳንድ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ቅኝት ማድረጉን ላቀው ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። ቡድኑ ባደረገው ቅኝት ቫይረሱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪዎች ላይ እያሳደረ ያለው ጫና እየበረታ መምጣቱን መታዘቡንም ጠቁመዋል።
በአገሪቱ ዘርፉ ለበሽታው ያለውን ተጋላጭነት መሰረት በማድረግ አስፈላጊ የሆኑ ጥንቃቄዎችን ለማድረግ የሚረዱ የመተዳደሪያ ደንቦች በማውጣትና ተግባራዊ በማድረግ የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው፣ በተለይም ዘርፉ ንክኪ ስለሚበዛው ለበሽታው ያለው ተጋላጭነት የጎላ በመሆኑ በወጣው ደረጃ መሰረት አስፈላጊ ጥንቃቄዎችን በማድረግ በሽታውን መከላከል እንደሚገባ ጠቁመዋል።
‹‹የአካል ንክኪ የሚጨምሩ ሥራዎችን በመቀነስና በማሽን የሚሠሩ ሥራዎችን ላይ ትኩረት በመስጠት፣ ዘርፉ እንዳይዳከም ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል›› ሲሉም አሳስበዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 75 ሚያዝያ 3 2012



