ጥበብ – በፈተና ጊዜ

0
729

ሙዚቀኞች የተለመደ የሙዚቃ ሥራቸውን እንዳያከናውኑ ሆነዋል። ለምርቃት የታሰቡ ፊልሞች መመረቂያቸው ሲራዘም ቴአትሮች መታየት አቁመዋል። ቀድመው የተቀረጹ ፊልሞች ለእይታ እንዳይበቁ ሲኒማ ቤቶች ተዘግተዋል። ጥበብ አሁን ስለጥበብ የምትኖርበት ጊዜ አይደለም። ይልቁንም ጥበብ ለማኅበራዊ አገልግሎት የምትተጋበት የተጋችበትም ጊዜ ነው።

አሁን ላይ የሚታዩ ፈጠራ የታከለባቸው ጥበባዊ ሥራዎች ሁሉ ትኩረታቸውን በኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ላይ ያደረጉ ናቸው። ከዚህም ውስጥ አንደኛውና በተደጋጋሚ የሚታየው ‹እናልፈዋለን ተጋግዘን› የተሰኘው የእሱባለው ይታየው የሺ አጭር ሙዚቃ ነው። ይህ ኹለት ደቂቃ የማይሞላ የሙዚቃ ሥራ፣ አንድም በጥንቃቄ አንድም በመደጋገፍ ይህን ክፉ ጊዜ እናልፈዋለን የሚል መልዕክት ያለው ነው።

ሌላው ሙዚቃ ደግሞ በሆፕ ኢንተርቴይመንት የተለቀቀው ‹እጅ እንንሳ› የሚል የኹለት ድምጻያን የጋራ ሥራ ነው። ይህ ሙዚቃ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ላለመያዝ መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች በሙዚቃ ተከሽኖ ቀርቦበታል። የተሳተፉ ድምጻውያን ትንሳኤ ጎበና እና ሚሚ ሙሉቀን ሲሆኑ በማቀናበሩ አበጋዝ ክብረወርቅ ተሳትፏል። ሙዚቃውን ፕሮድዩስ የማድረጉን ሥራም አበጋዝ ክብረወርቅና ዓለማየሁ ደመቀ በጥምረት ተሳትፈውበታል።

ሙዚቃው፤
‹‹እጅ ልንሳ…በአያቶቻችን ወግ
…እጅህን ሳልነካ ሰላምታዬን እንካ
እጅ ልንሳ…እጅ ንሺ…በአያቶቻችን ወግ
….እጅሽን ሳልነካ ሰላምታዬን እንኪ››
የሚሉ ስንኞች የጠቋጠሩበት ነው።

እነዚህ የሙዚቃ ሥራዎች ሆነው ሳለ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ የኪነጥበብ ባለሞያዎች መልእክቶችን በማኅበራዊ ሚድያ እንዲሁም በማስታወቂያ መልክ በቴሌቭዥን ስርጭቶች እያስተላለፉ ይገኛሉ። እነዚህ መልእክቶች ትልቅ ለውጥ ለማምጣት ቀላል የማይባል ተጽእኖ ያላቸው ናቸው። የዘርፉ ሰዎች እንደሚናገሩትም፣ በቃል ያለ ይረሳል በጽሑፍ ያለ ይታወሳል እንደሚባለው፣ በደረቁ ከተነገረ ይልቅ በጥበባዊ መንገድ የተነገረ ለመተግበር የተሻለ እድል ያለው እንደሆነ ይታመናል።

የተለያዩ የማስታወቂያና የፊልም ሥራዎችን ከሚሠሩት መካከል የ16 ፊልም ፕሮዳክሽን አንዱ ነው። ዘንድሮ አራተኛ ዓመት የሞላው ይህ የፊልም ፕሮዳክሽን፣ በአራተኛ ዓመቱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንደ ሌሎ ዘርፎች ሁሉ ፈተናው ሆኖ ተጋርጧል። እንደ ሥራ አስኪያጁ ታደሰ ማስረሻ ገለጻ ግን፣ ይህን ክፉ ጊዜ ለማለፍ ከእኛ የሚጠበቀውን እናደርጋለን፣ ጥበብም ሚናዋን ትወጣለች የሚል ጽኑ አቋም ተይዟል።

በዚህም መሠረት የፊልም ፕሮዳክሽኑ የተለያዩ ቪድዮዎችን በራሱ ተነሳሽነት እየሠራ ሲሆን ለዚህም ጥቂት የማይባሉ የኪነጥበባ ባለሞያዎችና አርቲስቶችን ይዟል። ‹‹እስከ አሁን ለማኅበራዊ ሚድያ እና ለቴሌቭዥን የሚሆኑ ኹለት ሥራዎችን ሠርተናል።›› ሲሉ ያስታወሱት ታደሰ፣ አሁን ደግሞ አዲስ ቪድዮ ክሊፕ እየሠሩ መሆኑንና በቅርቡም ለእይታ እንደሚበቃ አስታውቀዋል።

ይህም ድምጻውያን ሔለን በርሄ፣ አቤል ሙሉጌታ እና ዘቢባ ግርማ የተሳተፉበት የሙዚቃ ሥራ ቀርጻ ላይ ነው ብለዋል። ‹‹እኛ ሥራችን ማምረት ነው። ለሕዝቡ ተደራሽ ለሚያደርጉት ሥራዎቹን እንሰጣለን። እነርሱም ለእይታ ያቀርቡታል።›› ሲሉ የሥራውን ትስስርም አስረድተዋል።

ታድያ በዚህ ላይ የኪነጥበብ ባለሞያዎች ትብብር አድንቀዋል። ‹‹ያለምንም ጥርጥር በአንድ ስልክ ጥሪ ነው እሺታቸውን የሚገልጹት።›› ሲሉ የገለጹት ሲሆን፣ ይህም የሚጠበቅና ባለሞያዎቹም በእኔነት ስሜት እየሠሩ መሆኑን ነው የጠቀሱት።

ታድያ ፊልም ፕሮዳክሽኑ እስከ አሁን የቢዝነስ ሥራዎችን እንዳቆመ አውስተዋል። ለቀረጻም ሆነ የተለየ ርዕሰ ጉዳይ ለማንሳት ጊዜው አመቺ ባለመሆኑ ሙሉ ትኩረታቸውን ጥበብ ለአገር ችግር ደራሽ እንድትሆንና እንድታግዝ ማድረግ ላይ ነው ብለዋልም። ‹‹ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች በእጃችን ስለሆኑ በአቅማችን፣ ደግሞም የሁሉም ጉዳይ ስለሆነም አብን እየሠራን ነው ያለነው።›› በማለት ባለው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ቀኑን ለማለፍ እየተደረገ ያለውን ርብርብ ይበርታ በማለት አስምረዋል።

‹‹ሁሉም በአቅሙና በሙያው የቻለውን ያድርግ እንላለን። ብዙ ተጽእኖ ፈጣሪዎች እና ማስተማር የሚችሉ አሉ። ሳይሰስቱ ይሥሩ፣ ይህቺ አገር በሰላም ይህን ጊዜ ብታልፍ ሁሉም ተጠቃሚ ነውና፣ ሁሉም የተቻለውን ቢያደርግ እላለሁ›› ሲሉም በ16 ፊልም ፕሮዳክሽን ሥም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

እንዲህ ያሉ የኪነጥበብ ሥራዎችን ለማኅበራዊ አገልግሎት ለማዋል በግል ከሚንቀሳቀሱት በተጓዳኝ በመንግሥት ተሳትፎም የሚደረጉ ጥረቶች ይታያሉ። ተመሳሳይነት ያላቸውን እንቅስቃሴዎች ከሚያስተባበሩና ለማስተባበርም እየተንቀሳቀሱ ካሉት መካከል የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ተጠቃሽ ነው። በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አድነው ለአዲስ ማለዳ እንደጠቀሱት፣ በቫይረሱ ዙሪያ ግንዛቤ መስጠት ላይ ጥበብን የመጠቀም ሥራ እየተሠራ ነው። ይህ ከጥበብ ባለሞያዎች በግል ተነሳሽነትና ፈቃደኝነት የተገኘን መልካም አጋጣሚ ለአሁን ብቻ ሳይሆን ለወደፊትም መሥሪያ ቤቱ ለመጠቀም መንገድ አሳይቶታል ብለዋል።
መሥሪያ ቤቱ የቫይረሱ ስርጭት በኢትዮጵያ ከጀመረ ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎችን ይሠራ እንደነበር ያነሱት አድነው፣ ይህም ከኪነጥበብ ውጪ አስፈላጊ ግብአቶችን ተደራሽ ማድረግና ማሰራጨትን የሚያካትት እንደሆነ ጠቅሰዋል። ዓላማውም ባለድርሻዎችን ማብዛት ሲሆን፣ በዚህም ከኪነጥበብ ባለሞያዎች በተጨማሪ ባለሀብቶችንና ሎሌችንም በማካተት መልእክቶችን ማድረስ፣ ግንዛቤ ማስፋትና መረዳዳቱን ለማጠናከር ግብ አድርጓል።

‹‹መረጃዎች ከዓለም ጤና ድርጅት ጀምሮ፣ ከኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከሕክምና ባለሞያዎችና ከሚመለከታቸው ይተላለፋሉ። ነገር ግን በበቂ ሁኔታ ተግባራዊ ሲሆኑ አይታይም። በዚህም ኪነጥበብን የማካተት ሥራም መረጃዎችን ሳቢና ጥበብ በተሞላበት መልኩ ለማድረስ ነው የታሰበው።›› በማለትም ጥበብ ለራሷ ውበት ብቻ ሳይሆን ለማኅበረሰብ አገልግሎት የምትሰጥ መሆኗን ያሰምሩበታል።

በተለይም ማኅበራዊ ርቀትን ከመጠበቅ አንጻር የሚያስፈራ ሁኔታ ነው ያለው ያሉት አድነው፣ እናም መረጃዎችን በአንድ ጣዕም ብቻ ከመስጠት ጥበብን ማካተት ከብልህነት ይቆጠራል ብለዋል። ይህም በአንድ ድንጋይ ኹለት ወፍ የሚሉትን ዓይነት ሐሳብ የሚያቀብል ሲሆን፣ በአንድ በኩል የኪነጥበብ ባለሞያዎች እንቅስቃሴ የጉዳዩ አሳሳቢነት ያጎላል፣ የተሰጠውንም ክብደት ያሳያል ይላሉ። እንዲሁም መረጃና የጥንቃቄ ማሳሰቢያዎች አቀራረብ የተለየ ውጤት ሊያመጣ ስለሚችል፣ በዛ ላይ አጠናክሮ መሥራት አማራጭ የማይገኝለት ሆኖ ስለተገኘ ነው።

‹‹ተባብሮ የጋራ ሥራ መሥራት ነው ዋና ትኩረታችን።›› ሲሉ አስረውታል። ታድያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የኪነጥበብ ባሞያዎችን ብቻ ሳይሆን፣ የሚመለከተው የወጣትና የሴቶች እንዲሁም የሕጻናት ጉዳይ ነውና፣ ሁሉንም አሳታፊ ሊሆን ይገባው እንደነበር ሳያወሱ አላለፉም። የኪነጥበብ ባለሞያዎች ተሳትፎ ግዴታ መሆኑን ግን አስቀምጠዋል። ‹‹አሁን የምናገኘውን ጥሩ ልምድ እየተጠቀምን ወደፊት ደግሞ እንቀጥላለን፣ ጥበብን ብንጠቀም፣ ባለሞያዎቹ ለአገራቸው እንዲሠሩ እድል የመስጠት ጥቅምም አለው›› ሲሉም ቋጭተዋል።

ጊዜን የተሻገሩት
የሙዚቃ አቀናባሪ፣ የግጥም ደራሲና የዜማ ቀማሪ ኤሊያስ መልካ ሲታወስበት ከሚኖርባቸው በርካታ ሥራዎች መካከል እንዲህ ባለ አስጨናቂ ጊዜ የሚነሱም አሉ። ይልቁንም ኤች አይ ቪ ኤድስ ወረርሽኝ በነበረበትና የብዙ ወጣቶችን ሕይወት በቀጠፈበት ጊዜ፣ ‹‹እንዴት በፍቅራችን አፈር እንልበስ!›› የሚል ስንኝ የቋጠረ ኅብረ ዝማሬን አሰምቶ ነበር።

ምኒልክ ወስናቸው፣ ኢዮብ መኮንን፣ ዓለማየሁ እሸቴ፣ ዘሪቱ ከበደ፣ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ታምራት ሞላ፣ ፀደንያ ገብረማርቆስ፣ ጸጋዬ እሸቱ፣ አብዱ ኪያርና ሌሎችም የተሳተፉበት ይህ ሙዚቃ፣ ዛሬም ቢሰማ መልዕክቱ የሚደርስ ነው።
‹‹ሁሉ ነገር በእኛ…አንሁን ቸልተኛ
ሕይወት ይሁን ትጋት…እያሰቡ መሥራት
መላ መላ መላ…ወገን አትበል ችላ

እስኪ መላ በሉ…የአገር ልጆች ሁሉ›› ሲሉ በጊዜው ያሰሙት ድምጽ፣ ዛሬም ለሚታየው ቸልታ ትልቅ መልእክት የሚያስተላፍ ሙዚቃ ሆኖ ዘልቋል። ይህም ጎዜን የሚሻገር እንደሚሆን ግልጽ ነው።

ጊዜንና ወቅታዊ ሁኔታን ጠብቀው የሚሠሩ ጥበባዊ ሥራዎች የሚሻገሩ ባይመስሉም፣ አሁን ላይም እንደ አዲስ ለጆሮ ሳይሰለች የሚሰማውን ይህን ‹‹መላ መላ!› የተሰኘ ኅብረ ዝማሬ መጥቀስ ይቻላል። ሙዚቃው ምንም እንኳ ስለ ኤች አይ ቪ ተብሎ የተሠራ ቢሆንም፣ ጊዜን አቋርጦ ዛሬም ላይ ለኮቪድ 19 የኮሮና ቫይረስ ትግልና ጥሪ ደጋፊና ተጨማሪ ድምጽ ሆኖ ሊያገለግል በሚችልት አቅም ላይ ይገኛል።

አሁንም ወደፊት የሚወጡትን የምንጠብቅ ሲሆን፣ የእሱባለው ይታየው ዓይነት ‹እናልፈዋለን ተጋግዘን› የሙዚቃ ሥራዎችና አንዳንድ ግዙፍ መልእክት የተሸከሙ፣ ከዚህ ወረርሽኝ ትግል የሚልቁ ሐሳቦች ዘመን እንደሚሻገሩ ይገመታል። እነዚህም ይህ ቀን ሲነጋ፣ ወረርሽኙም አልፎ ወደፊት ሊከሰቱ በሚችሉ ፈታኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሳይቀር ተደማጭ ሊሆኑ የሚችሉ ዓይነት ናቸው።

ታድያ የጥበብ ባለሞያዎች እንደ ሙያቸው ይህን አስተዋጽኦ ሲያደርጉ፣ እንደ ግለሰብ ደግሞ በየፊናቸው የሚያደረጓቸው በጎ አድራጎቶችም አረአያ የሚሆኑ ናቸው። ለምሳሌ በቅርበት ያሉ ማሳያዎችን ብንጠቅስ፣ አንጋፋዋን ድምጻዊት ሐመልማል አባተን እናገኛለን። ሐመልማል መኖሪያ ቤቷን ለለይቶ ማቆያነት እንዲውል አበርክታለች።

መንግሥት ማንኛውም ወደ አገር ውስጥ የሚገባ ሰው በራሱ ወጪ ራሱን ለ14 ቀናት ያህል በሆቴል ውስጥ ለይቶ እንዲያቆይ የሚል ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ ነበር ሐመልማል ቤቷን ለለይቶ ማቆያነት የሰጠችው። ይህንንም እንድታደርግ ምክንያት የሆናት፣ ውሳኔው ገንዘብ ላላቸው የውጭ ዜጎች ይሁን፤ ገንዘብ የሌላቸውስ ምን ያደርጋሉ የሚል ሐሳብ ገብቷት እንደሆነ መናገሯን ቢቢሲ አማርኛ መዘገቡ ይታወሳል።

እንቋጭ፣ የፊልማ ባለሞያው ሰውመሆን ይስማው እንዲህ ሲል በፌስቡክ ገጹ ተከታዩን መልእክት አስነበበ፣
‹‹ሁሉም ኢትዮጵያዊ በዘመኑ የራሱን ትግል ታግሎ አልፏል ደግሞም አሸንፏል። ይህ የእኔና የእናንተ ትግል ነው። ልናሸንፈው ልናንበረክከው እንገጥመዋለን። ይህ የእኛ ዘመን ወራሪ ነው። የእኔና የአንተ፣ የአንቺ ዘመን ጠላት ነው። መንገድ አንሰጠውም። እንዲያልፍ አንፈቅድለትም። መካሪዎቻችንን፣ አባሽ ቀዳሽ መራቂዎቻችንን አያሳጣንም። እንፋለመዋለን። ነገን መልካም እናደርጋለን። መተሳሰብና መረዳዳት ብቻ በልባችን ይሁን።››
ትክክል ነው። ‹‹በጠመንጃ ብቻ አይደለም ጀግንነት፤

ይታጠቁለታል ለጤናም ጦርነት›› እንዳሉ፣ እንግዲህ ይህ ሰዓትም በእርግጥ የትግል ነው፤ ስለደኅንነትና ጤና የሚደረግ። ጥበብም ስለራሷ ይቆየኝ ብላ ለማኅበራዊ አገልግሎት የዋለችበት።

ቅጽ 2 ቁጥር 75 ሚያዝያ 3 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here