“የብዙኃን መገናኛዎች ፍርድ” ከፍርድ ቤት ውሳኔ በፊት እንደነጻ የመቆጠር መብት

0
996

በቅርቡ በከባድ ሙስናና እና የሰብኣዊ መብቶች ጥሰቶች የተጠረጠሩ ግለሰቦችን መንግሥት በዘመቻ ማሰሩ ይታወቃል። ይህንኑ ተከትሎ ብዙኃን መገናኛዎች ጥናታዊ ዘገባዎችን እያቀረቡ ሲሆን፣ የዘገባዎቹ መቅረብ የፍርድ ሒደቱን ነጻነት ሊነፍገው ይችላል የሚል አስተያየት እየተሰነዘረ ነው። ይህንን ጉዳይ ከአገራዊ እና ዓለም ዐቀፋዊ ነባራዊ እውነታዎች እና ሕግጋት አንፃር በመገምገም ፈቃዱ አዱኛ የሚከተለውን ትንታኔ ያስነብቡናል።

በቅርቡ መንግሥት በከባድ ሙስና የተጠረጠሩ ከፍተኛ የጦር መኮንንችን ጨምሮ ባለሀብቶችና ሌሎች ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን በይፋ መግለጹና ተጠርጣሪዎቹም ፍ/ቤት ቀርበው የጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀባቸው መሆኑንም ሰምተናል፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በመንግሥትና በሌሎችም የመገናኛ ብዙኃን በተለይም ግለሰቦቹ ከተጠረጠሩበት ከብሔራዊ ብረታብረትና ኢንጂነሪነግ ኮርፖሬሽን (METEC) ጉዳይ ጋር በተገናኘ እና በቅርቡ ደግሞ በሰብኣዊ መብቶች ጥሰቶች ዙሪያ በተሠሩት ዶክመንተሪ ፊልሞች ላይ የተለያዩ ተቃራኒ አስተያቶች ሲደመጡ የነበረ በመሆኑና በአንድ ወገን የዜጎች መረጃ የማግኘት መብት(Freedom of information) በሌላ ወገን ተጠርጣሪዎቹ ጉዳያቸው በመታየት ላይ ያለ በመሆኑ ከፍርድ ቤት ውሳኔ በፊት እንደነጻ የመቆጠር መብታቸው(Presumption of innocence until proven guilty) እንዴት ይታያል የሚለውን ጉዳይ ከሕግ አንፃር ለመዳሰስ እሞክራለሁ።
የዜጎች መረጃ የማግኘት መብት
የመረጃ ነጻነት በተለያዩ የዓለም ዐቀፍ ሰብኣዊ መብቶች ድንጋጌዎች አንዱ የሰብኣዊ መብት ተብሎ ዕውቅና የተሰጠው እሳቤ ነው – መረጃን የማግኘት፣ የማስተላላፍ እና ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት። ዓለም ዐቀፍ የሰብኣዊ መብቶች ድንጋጌ (UDHR,Art.19)ዓለም ዐቀፍ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን (ICCPR,Art.19(2)) የአፍሪካ ሰብኣዊ መብቶችቻርተር (ACPHR,Art.9)እንዲሁም የኢፌዴሪ ሕገመንግሥት አንቀፅ 29(2) ይህንኑ ያረጋግጣሉ።የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 29 ንዑስ ቁጥር 3 ሚዲያዎች የሕዝብን ጥቅም የሚነካ መረጃ የማግኘት መብት ያላቸው መሆኑ በተለየ ሁኔታ ተደንግጎ እናገኘዋለን።ከዚሁ ጋር ተያይዞ የመንግሥት አሠራር ግልጽነት እንዲሁም ተጠያቂነት ያካተተ ሊሆን እንደሚገባው አጠያያቂ አይደለም። ዜጎች መረጃ የማግኘት መብታቸው እንደአንድ የሰብኣዊ መብትነቱ በምንም መልኩ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ የማይገባው ከመሆኑም በላይ፥ ጉዳዩን ከዚህ ይበልጥ ጠንከር የሚያደርገው ደግሞ የመረጡት እና በሥልጣን ላይ ያስቀመጡት መንግሥት ኃላፊነቱን በአግባቡ ስለመወጣቱ ለመጠየቅ፣ ለመተቸትና ተጠያቂነትን ለማስፈን የመንግሥት የአሠራር ሒደት በመሠረታዊነት ግልጽነት ሊኖረው ይገባል። በአጠቃላይ ዜጎች በየትኛውም ጉዳይ ላይ በተለይም መንግሥት በሚያከናውናቸው ተግባራት ሁሉ ትክክለኛ መረጃ የማግኘት በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና ያገኘ ሰብአዊ መብታቸው ነው።
የተጠርጣሪዎች እንደ ንፁህ የመቆጠር መብት
ማንኛውም ተጠርጣሪ ወይም ተከሳሽ ፍርድ ቤት የመጨረሻ የጥፋተኝነት ውሳኔ እሰከሚሰጥበት ድረስ ንፁህ እንደሆነ ተደርጎ ይገመታል፤ እዚህ ላይ ጉዳዩን ይበልጥ ለማብራራት በተጠርጣሪና በተከሳሽ መካከል ያለውን ልዩነትም ማስቀመጥ ተገቢ ነው።አንድ ግለሰብ ተጠርጣሪ የሚባለው ፖሊስ በወንጀል ጠርጥሮ ከያዘው በኋላ ክስ ሳይመሠረትበት ባለው ሒደት ማለት ነው።ማንኛውም ተጠርጣሪ በፖሊስ ሲያዝ ያሉት መብቶች፦ አንደኛ፣ የተጠረጠረበትን ወንጀል ምን እንደሆነ በሚረዳው ቋንቋ ሊነገረው ይገባል። ሁለተኛ፣ ወንጀል ቃሉን እንዲሰጥ ይጠየቃል፤ ቃል ያለመስጠት መብትም እንዳለው ሊነገረው ይገባል።ሦስተኛ፣ በተያዘ በአርባስምንት ሰዐት ውስጥ ፍርድ ቤት ሊቀርብ ይገባል(ይህ ሰዐት ተጠርጣሪው ከተያዘበት ቦታ ወደ ፍርድ ቤት ለማቅረብ የሚወስደውን ጊዜ አያካትትም)። አራተኛ፣ ኢሰብኣዊ ከሆነ አያዝ የመጠበቅ መብትና ጠበቃ የማማከር መብትም አለው።ፖሊስ ተጠርጣሪውን ፍርድ ቤት ሲያቀርብ በምን ወንጀል እንደጠረጠረው፣ ተጠርጣሪውን በሕግ ቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ ማድረግ ያስፈለገበትን ሁኔታ ማስረዳት ይጠበቅበታል።ተጠርጣሪውም እራሱ ወይንም በጠበቃው በኩልበፖሊስ የቀረበውን ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ላይ አስተያየት የመስጠት መብቱ ይጠበቃል። ፍርድ ቤቱ በፖሊስ የቀረበውን የተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ካላመነበት ተጠርጣሪውን ወዲያውኑ በዋስ እንዲለቀቅ ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል።አሊያም የተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ሊፈቅድ ይችላል።ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ከ14 ቀናት ሊበልጥ አይችልም።
እዚህ ላይ አንድ መነሳት ያለበት ጉዳይ የኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ስርዓት ሕግ ክፍተት ያለበት መሆኑን ነው። በፖሊስ ለሚቀርብ የተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ ቢበዛ ከ14 ቀን መብለጥ እንደሌለበት ቢደነግግም ለምን ያህል ጊዜ ጥያቄው ሊቀርብ ይችላል ለሚለው ግን ገደብ አላስቀመጠም።ስለሆነም ፖሊስ የምርመራ ሒደቱን ካላጠናቀቀ በየጊዜው ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ሊጠይቅ ይችላል ማለት ነው።ይሁን እንጂ ፍርድ ቤቶች በዚህ የሕግ ክፍተት ፖሊስ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት እንዳይፈፅም ትኩረት በመስጠት ግለሰቡ የተጠረጠረበት ወንጀል የዋስትና መብት የማይከለክል ሆኖ ካገኙት ተጠርጣሪውን በዋስ የመልቀቅ አሠራር ይከተላሉ።የፀረ ሽብር ሕጉ የ14 ቀኑን ቀጠሮ ወደ 28 ሲያሳድገው የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ ቢበዛ ከ4 ወራት መብለጥ እንደሌለበት ያስቀምጣል።ወደ ዋናው ጉዳያችን ስንመለስ ተጠርጣሪው ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን አጣርቶ ለዐቃቤ ሕግ ሲሰጥና ዐቃቤ ሕጉ ተጠርጣሪውን የሚያስከስስ ማስረጃ እና ሕግ መኖሩን አረጋግጦ ግለሰቡ ላይ ክስ ሲመሠርት ተጠርጣሪው ተከሳሽ ይባላል። እዚህ ላይ አንድ ልብ ልንለው የሚገባ ጉዳይ የፖሊስ የምርመራ መዝገብ ተጣርቶ ዐቃቤ ሕጉ ጋር ሲደርስ ዐቃቤ ሕጉ በተጠርጣሪው ላይ የወንጀል ክስ ለማቅረብ የሚያስችል የሕግ መሠረት የሌለ መሆኑን ካመነ የምርመራ መዝገቡን በወንጀለኛ ሥነ ስርዓት ሕጉ ቁጥር 42 መሠረት ሊዘጋው ይችላል።
ተጠርጣሪው የቀረበበት ክስና ማስረጃ በግልጽ ችሎት ደርሶትመቃወሚያ ከሌለው የእምነት ክህደት ቃሉን ወደ መስጠትና የዐቃቤ ሕግ ማስረጃና ምስክር ወደመሰማቱ ሒደት ይገባል።እንደንፁህ የመገመት መብት ሲባል ተከሳሽ የቀረበበትን ክስ የማስረዳት ሸክምና ግዴታው የዐቃቤ ሕግ ነው ማለት ነው። ይህም ማለትንፁህ መሆንህን አስረዳ በሚል የሚጀምር ክርክር አይኖርም ማለት ነው። ተከሳሹ ንፁህ ነው። ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ቅድሚያ ጥፋተኛ ነው ስትል ጥፋቱን አስረዳ የሚል እሳቤ ነው። ተከሳሹን ጥፋተኛ ለማስባል በሕግ ቅቡልነት ያላቸውን ማስረጃዎች ይዞ ክሱን የማስረዳት ሸክሙ የዐቃቤ ሕግ ስለሆነ ነው። አንዳንዶች ይሄንን መብት በሌላ አቅጣጫ የሚተረጉሙበትም አካሔድ አለ፤ከፍርድ በፊት እንደ ንፁህ የመቆጠር መብት ፍፁማዊ መብት (absolute presumption) አይደለም፤ ይልቅስፍፁማዊ ያልሆነ(artificial presumption) ነው የሚሉ አሉ። ለዚህም ለምሳሌ ተከሳሹ የተጠረጠረበት (የተከሰሰበት ወንጀል) ከባድ ከሆነ የዋስ መብቱ ተከልክሎ በእስር ውስጥ ሆኖ ክርክሩንእንዲከታተል ፍርድ ቤቱ ሊያዝ ይችላል።
ከፍርድ በፊት እስር ማለት ነው፤ይህም ማለት አንድ ተጠርጣሪ በፖሊስ ም ርመራ አልፎና ዐቃቤሕግም አምኖበት ወደ ክስ መመሥረት ሲያመራ ሁለት የማጣራት ሒደቶችን አልፏል። የመጨረሻውናሦስተኛ ደረጃ ተከሳሹን “ነጻ” ወይንም “ጥፋተኛ” ለሚለው ፍርድ ቤት የሚተው ይሆናል። እዚህ ጋርፍርድ ቤቱ የተከሳሽን የዋስትና መብት ሲከለክል የሚያሳየን ነገር መጀመሪያውኑም ተከሳሹ እንደንፁህ የመቆጠር መብት ሳይሆን ግምት ነው ያለው የሚለውን ነው። ይህ ግምት ደግሞ ተቃራኒ ማስረጃ ከቀረበበት ውድቅ ሊሆን የሚችል(rebuttable presumption) ነው፤ በመሆኑም የዐቃቤ ሕግ ክሱን የማስረዳት ሸክሙ እንደተጠበቀ ሆኖፍርድ ቤቱ ተከሳሽ ከተከሰሰበት የሕግ አንቀፅ አንፃር የዋስትና መብቱን ሲከለክል መብቱን አጥፎታል ብለው ይከራከራሉ።የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በዚህ ሐሳብ አይስማሙም።
በአንዳንድ አገሮች በከባድ የሰው ግድያም ጭምር የተጠረጠሩ ተከሳሾች የዋስትና መብት አይነፈጉም። ጠቅለል ስናደርገው የወንጀል ክስ ቅጣቱ በተለይ የግለሰብን ሕይወት፣ ነጻነትና ንብረትንም ሊያሳጣ የሚችል በመሆኑ ከፖሊስ የምርመራ ሒደት ጀምሮ የዐቃቤሕግ ብሎም የመጨረሻው ፍርድ ሰጪ ተቋም ፍርድ ቤት አሠራር በከፍተኛ ጥንቃቄና ሕግን በተከተለ መልኩ ሊከናወን ይገባል። እንደ ነጻየመቆጠር መብት ልክ እንደሌሎች ሰብኣዊ መብቶችሁሉ በዓለም ዐቀፍ የሰብኣዊ መብቶች ድንጋጌ ሰፍሮ እናገኘዋለን። UDHR,Art.11፤ ICCPR,Art.14(2) እንዲሁም በኢፌድሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 20(2) ውስጥም ተካትቶ የሚገኝ ሕገ መንግሥታዊም መብት ነው።
ጥቂት ስለ ‘ሚቴክ’
በእንግሊዘኛው ምሕፃረቃል‘MetEC’ (‘ሚቴክ’) በመባል የሚታወቀውና የኢትየጵያ ብረታብረትና ኢንጂነሪነግ ኮርፖሬሽን በሚንስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 183/2002፣ በሰኔ ወር 2002 የተመሠረተ፣ መንግሥታዊ የሆነ ተቋም ነው። ይህ ተቋም አሁን በመልሶ ማዋቀር ሥያሜው ተቀይሮና የመዋቅር ማሻሻያ አድርጎ ወታደራዊ ቁሳቁስና ግብአት የሚያመርተው ክፍል ወደ መከላከያ ሚንስቴር ሥር ሆኖ፣ የሲቪል ሥራዎቹን አሁን በአዲስ ሥያሜ ለተቋቋመው ተቋም ተሰጥቶዋል።የሚቴክ ተቋማዊ አሠራር ልክ እንደሌሎቹ የልማት ድርጅቶች ሁሉ የመንግሥትን የፋይናንስ ሕግ መሠረት ባደረገ መልኩ በአዋጅ ቁጥር 25፣ 1992 እንዲመራ በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ በግልጽ የሰፈረ ከመሆኑ ውጪ፣ አሠራሩን በተመለከተ ከሌሎች የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በተለየሁኔታ የተሰጠው ልዩ መብት የለም።
የዘጋቢ ፊልሙ ነገር
“ምናባዊ” በሚል ርዕስ በተለያዩ የመገናኛ ተቋማት የቀረበው ዘጋቢ ፊልም(ዶክመንተሪ) የክርክር መነሻ የሆነ ይመስላል። በአንድ በኩል ተቃውሞ በሌላ በኩል ድጋፍና ቁጭት። ዘጋቢ ፊልሙ ‘ሚቴክ’ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በተቋሙ ውስጥ የነበረውን የፋይናንስና የሀብት አጠቃቀምን መረጃው ከነበራቸውና የማጣራት ሒደቱን ካከናወኑ ግለሰቦች ጋር የተካሔደን ቃለምልልስ ያካተተ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በተቋሙ ሕግን እና መመሪያን ባልተከተለ አሠራር በርካታ ቢሊዮን ብር እንደባከነ፣ በርካታ የመንግሥትና የሕዝብ ንብረት ለብልሽት ተዳርገው እና ሳር በቅሎባቸው ያሉ መሆኑን፣ በርካታ የአገልግሎት ዘመናቸው ያበቃ ኬሚካሎችና የግንባታ ቁሳቁሶች በተቋሙ ውስጥ እንደሚገኙ፣ ከዚህም በላይ ከንግድ መርከብ በእርጅና ሊወገዱ የነበሩ የብረት አካላቸውን አቅልጦ ለመጠቀም በሚል የተገዙ መርከቦች በተከለከሉ እና ማዕቀብ ባለባቸው የባሕር አካላትና ወደቦች ሲሠሩ የነበሩ መሆናቸውንየሚያትት ዘጋቢ ፊልም ነው። ይህንን መረጃ የለቀቀው የራሱ የተቋሙ ባለቤት የሆነው መንግሥት በመሆኑ ተቋሙ ላይ የሥም ማጥፋት ተግባር ተፈፅሟል ለማለት አይቻልም። ይህ ዘጋቢ ፊልም በሌላ ሦስተኛ ወገን የተለቀቀ ቢሆን ኖሮ ‘ሚቴክ’ እራሱ ሥሙንና መልካም ዝናውን የሚያጎድፍ ዘገባ ተሰርቶብኛል ካለ ዘጋቢ ፊልሙን ባቀረበው ተቋም ላይ ክስ ለማቅረብ መብት ይኖረው ነበር። መንግሥት በተቋሙ ላይ በራሱ የአሰራር ሒደት ማጣራት አድርጎ የደረሰበትን ውጤት ‘ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ነው ወይስ መደበቅ ነው ያለበት?’ የሚለውን ምላሽ ለመስጠት ቀጣዩን ንዑስ ርዕስ እንመልከት።
ዘጋቢ ፊልሙ እና የዳኝነት ሒደቱ
እዚህ ላይ ከላይ ያነሳናቸው መብቶች የሚላተሙ ይመስላሉ። ዜጎች መረጃ የማግኘት መብታቸው እንዴት ሊከበር ይገባል?የመንግሥት የግልጽነትና የተጠያቂነት መርሕን መከተል እንዴት ተግባራዊ ሊሆን ይችላል? የሚለው በአንድ ወገን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የተጠርጣሪዎች እንደ ንፁሕ የመቆጠር መብታቸውስ እንዴት ይታያል? የሚሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች ናቸው። በቅድሚያ የተሠራው ዘጋቢ ፊልም ማንን ማዕከል አድርጎ የተሠራ ነው?ግለሰቦችን ወይስ ተቋሙን የሚለውን ለይቶ ማየትም ተገቢ ነው፤ዘጋቢፊልሙ በዋነኛነት ሜቴክ የተባለና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ የተቋቋመውን ኮርፖሬሽን መነሻ በማድረግ የተሠራና ከምሥረታው ጀምሮ ያለውን ሒደት ለመዳሰስና ተፈጠሩ የተባሉ ችግሮችን ለማሳያት ይሞክራል። ይህ ተቋም የመንግሥት ነው። መንግሥት በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ ተቋሙን አስመልክቶ ስለአሠራሩና ስለ ጠንካራም ይሁን ደካማ ጎኑ መረጃዎችን ለሕዝብ ግልጽ ማድረጉ ግዴታው ነው።
የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 12 “የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን አለበት” ከሚለው ድንጋጌ አንፃር የሚቴክን ብቻ ሳይሆን የሁሉንም የመንግሥት ተቋማት አሠራር ይፋ ማድረግ ተገቢነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም። ነገርግን ዘገባው የግለሰብን ሥም እየጠቀሰ“እገሌ የሚባለው ኃላፊ ወይም ሠራተኛ ይሄንን ያህል ብርና ንብረት ለግል ጥቅሙ አውሏል” እና መሰል አገላለጽ ከተጠቀመ የግለሰቦችን (የተጠርጣሪዎችን) መብት የሚነካ ሊሆን ይችላል።
የሚዲያ ነጻነት በዳበረባቸው አገራት የመሪዎች የግል ጉዳይ ሳይቀር በብዙኃን መገናኛዎች እየተለቀቀ ለክርክር መነሻ ሲሆን ይስተዋላል። ለምሳሌ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን‘የኋይት ሀውስ’ሠራተኛ ከነበረችው ሞኒካ ልዊኒስኪ ጋር የነበራቸው ግንኙነት በብዙኃን መገናኛዎች ከወጣ በኋላ በተነሳው ውዝግብ፣ ፕሬዚዳንቱ ይከሰሱ አይከሰሱ የሚለውን ጉዳይ አስከ አገሪቱ ኮንግረስ ድረስ ቀርቦ የነበረ መሆኑ ይታወሳል። የተሻለ የብዙኃን መገናኛ ነጻነት ባለቸው አገራት ብዙ ወንጀሎች ከፖሊስ ይልቅ ቀድመው የሚደርሱት ለብዙኃን መገናኛው ነው። ለዚህ ነው ሚዲያ አራተኛው የዴሞክራሲ ምሰሦየሚባለው።
የዳኝነት ሒደትን መዘገብ
ብዙኃን መገናኛዎች በፍርድ ሒደት ላይ ያለን ጉዳይም ቢሆን ከመዘገብ የሚግዳቸው ሕግ የለም። በመሠረታዊነት አንድ ተጠርጣሪ በፍርድ ቤት ቀርቦ ክስ ሲመሠረትበት ዐቃቤ ሕግ ያቀረበው የሰው፣ የሰነድም ይሁን ሌሎች ማስረጃዎች ሁሉ ለተከሳሽ ይደርሱታል። በተለየ ሁኔታ ከአገር ደኅንነት ጋር በተያያዘ ወይም በሌላ ልዩ ምክንያት ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን በዝግ ችሎት እንዲታይ እስካልወሰነ ድረስ ማንኛውም የፍርድ ሒደት በግልጽ ችሎት የሚታይ ነው። ይህም አንድ ትክክለኛ ፍትሕን ከመስጠት አኳያ ተከሳሽ በግልጽ ችሎት የመዳኘት መብቱን ለመጠበቅ ሲባል የሚደረግ ነው። የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 451(1) ቢሆን የዳኝነትሒደትላይ ያለን ጉዳይ ትክክለኛ ያልሆነ ወይም የተዛባ መረጃን መግለጽን እንጂ በክስ ሒደት ላይ ያለ ጉዳይ ፈጽሞ ዘገባ እንዳይሠራበት የሚከለክል ድንጋጌ የለውም። በአንዳንድ አገሮች በጣም ከፍተኛ የሕዝብ ትኩረትን በሚስቡ ክሶች ላይ የችሎቱ ሒደት ራሱ በቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት (እንደ እግር ኳስ ማለት ነው) የሚተላላፍበት ሁኔታ አለ። እንደ ምሳሌ ደቡብ አፍሪካንመጥቀስ ይቻላል፤በአንዳንድ አገሮች ደግሞ እንኳንስ የቀጥታ ስርጭት ቀርቶ የዳኞቹን ደኅንነት ከመጠበቅ አኳያ በሚል በተለይ ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ ያሉ ጉዳዮችን የሚያዩት ዳኞች ማንነታቸው እንዳይታወቅ ፊታቸው ተሸፍኖ የዳኝነት ሥራቸውን የሚያከናውኑበት ሁኔታም አለ። ላቲን አሜሪካዋ አገር ፔሩ በዚህ መልክ በተሰጠ ውሳኔ ጉዳዩ በተባባሩት መንግሥታት ሰብኣዊ መብቶችኮሚሽን ቅሬታ ቀርቦበት አካሔዱ ትክክል አለመሆኑና የICCPR አንቀፅ 14ን የሚጻረር ነው በሚልተተችቷል።
በአሜሪካ ውስጥም ይህጉዳይ በአንድ ወቅት እጅግ አከራካሪ የነበረ ሲሆን በተለይ አንዳንድ ከፍተኛ የሆነ ከአገርም አልፎ የዓለምን ትኩረት ሊስቡ በሚችሉ የወንጀል ጉዳዮች ላይ የኤሌክትሮኒክስ ሆኑ የኅትመት ብዙኃን መገናኛዎች ሰፋፊ ዘገባዎችን መሥራት የተለመደ ነው። ለምሳሌ እ.ኤ.አ አቆጣጠር በ1963 ዳላስ ውስጥ 35ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ግድያ ጋር ተያይዞ በመላው አሜሪካ በተፈጠረው ከፍተኛ የሕዝብሐዘንና ቁጭት፣ የተከሳሹ ጠበቃ በብዙኃን መገናኛዎች ሲቀርብ ከነበረው ዘጋባ አንፃር ቅሬታ አቅርቦ እንደነበረ ተመዝግቧል።
ይሁንና መሰል አጋጣሚዎች የፈጠሩትን ክስተት ተከትሎ በታሪካቸው ውስጥ የሚፈጠሩ መጥፎ አጋጣሚዎችን ወደ በጎ የመቀየር ልምድ ያላቸው አሜሪካኖች በነጻ ሚዲያ ላይ የማይናወፅና የፀና አቋም ያላቸው ቢሆንም በክስ ሒደት ላይ ያለን የፍርድ ሒደትንየበዛ የብዙኃን መገናኛዎች ጩኸት የሚመኩበትንና ለሌላውም ዓለም ተምሳሌት የሆነውን የፍትሕ ስርዓታቸውን እንዳያውከው ደግሞየሕገ መንግሥት ማሻሻያ ድረስ ሔደዋል። እጅግ ጠንካራ የሲቪል ማኅበራት ያሉባት አሜሪካ፣የብዙኃን መገናኛ ባለሙያዎችና የጠበቆች ማኅበር ሳይቀሩ በጋራ በመሆን በፍርድ ሒደት ላይ ያለን ጉዳይ እንዴት መዘገብ እንደሚቻል የሚደነግግ የሥነ ምግባር ደንብ ቀርፀዋል። በቨርጂኒያ ግዛት ነጻ ብዙኃን መገናኛዎች እና ፍትሐዊ ዳኝነት (free press fair trial) በሚል ሥራ ላይ የዋለ የሥነ ምግባር መመሪያ ለብዙኃን መገናኛዎችየተዘጋጀ ሲሆን፣ የዚሁ ተመሳሳይ የሆነ የሥነ ምግባር መመሪያ በአሜሪካ የጠበቆች ማኅበር በኩል ተግባራዊ ሆኖዋል። ብዙኃን መገናኛዎች በችሎት ተገኝተው በችሎቱ የነበረን እያንዳንዱን ሒደት መዘገብ የሚችሉ ቢሆንም ፎቶና ምስል መቅረፅ የተከለከለ ነው። ከችሎቱ ውጪ ያለውን ሒደት ግን በምስል መቅረፅም፣ በቀጥታ መዘገብም ይቻላል። መመሪያው በርካታ ዝርዝር ጉዳዮችን ያካተተ ሲሆን ሌላው ቀርቶ ዐቃቤ ሕግ ተከሳሽ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሲውል ወይም ወዲያውኑ እንደተያዘ ያለውን ሒደት በምስል ማሳየት የሚችል ቢሆንም፣ የክስ ሒደቱ ከተጀመረ በኋላ ግን የተከሳሽን ወይም የተጠርጣሪን ምስል ማሳየትን ግን ይከለክላል።
ወደ አገራችን ስንመጣ ሚዲያዎች በፍርድ ቤት ላይ ያለን ጉዳይ አስመልክቶ እንዴት መዘገብ እንዳለባቸው ግልጽና ዝርዝር የሆነ መመሪያ ባይኖርም በፍርድ ሒደቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊኖረው የሚችል፣ በተለይም ከተከሳሽ መብት አኳያ አሉታዊ ውጤት የሚያመጣ፣ የፍርድ ቤቱን የዳኝነት ነጻነት የሚጥሱ ጉዳዮች ከተከሰቱ ግን ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሒደቱን በተገቢው መልኩ ለመምራት ከማስቻል አኳያ ተገቢውን ትዕዛዝ ከመስጠት የሚያግዳቸው አይኖርም። ስለሆነም ጉዳዩከፍተኛ ጥንቃቄ ያሻዋል፤ለአብነትም የችሎትን ውሎ የሚዘግብ ዘጋቢ እያንዳንዱን የችሎት ሒደት እንደወረደ ማስቀመጥ እንጂ ሀተታና ትንታኔ መስጠት የፍርድ ሒደቱ ላይ ተፀዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ለምሳሌ አንድ ችሎት እየተመለከተው ባለው ጉዳይ ላይ ከተከሳሽም ሆነ ከዐቃቤ ሕግ በኩል የቀረበን ማስረጃ ውድቅ ቢያደርግና ይሄንኑ ሒደት የሚዘግብ ጋዜጠኛ “መረጃውን ፍርድ ቤቱ ሊቀበለው ይገባ ነበር” ብሎ ቢዘግብ በቀጥታ የፍርድ ሒደቱን የመተቸትና የፍርድ ቤቱን ነጻነትም የመጋፋት ትርጉም ሊያሰጠው የሚችል አዘጋጋብ ነው። በነገራችን ላይ በአንድ ጉዳይ ላይ የመጨረሻ የፍርድ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ ግን ውሳኔውን ተችቶመጻፍ ራሱ ይቻላል። በተለያዩ የፍርድ ውሳኔዎች ላይ በአሉታዊም ሆነ በአወንታዊ መልኩ የሚጻፉ ትችቶችና አስተያየቶች በተለይም በሕግ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የምርምር መነሻ ሐሳብ ሆነው ያገለግላሉ።
መደምደሚያ
የዜጎች መረጃን የማግኘትና የመጠየቅ፣ የመገናኛ ብዙኃንም መረጃን የማስተላላፍ ነጻነት አንዱ የሰብኣዊ መብት በመሆኑ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው እሳቤ ሲሆን በሌላበኩል ጉዳያቸው በፍርድ ሒደት ላይ የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን እንደ ንፁህ የመቆጠር መብትና ፍትሓዊ ዳኝነት እንዲያገኙ ከማስቻል አኳያ ብዙኃን መገናኛዎች ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉና ሁለቱንም መብቶች ከማክበርና ከማስከበር አኳያ ሚዛናዊ ዘገባ ማቅረብ ይጠበቅባችዋል እንጂ በደፈናው አፋችሁን ዝጉ ዓይነት ተገቢ አይደለም፤በሌላ ረገድ መንግሥትም የሌሎችን አገራት ተሞክሮ በመውሰድ የሥነ ምግባር መመሪያ ቢያወጣና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ቢያዘጋጅ ተገቢ ነው።

ፈቃዱ አዱኛ የሕግ አማካሪ እና ጠበቃ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው fekaduadu@yahoo.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 5 ታኅሣሥ 6 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here