አንዳርጋቸው ጽጌ የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ዋና ጸሐፊ ሲሆኑ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሰፊ ተሳትፎ አላቸው። በ1960ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ፣ ኢሕአዴግ መንበረ ሥልጣኑን በያዘበት በ1983 ማግስት ለአጭር ጊዜ፣ በ1997 ምርጫ ወቅት ከቅንጅት ለዴሞክራሲና ለአንድነት እንዲሁም የሠላማዊ ትግል አላዋጣ ሲላቸው ደግሞ ግንቦት 7 ኋላ ላይም አርበኞች ግንቦት 7 የተባለ ድርጅት መሥርተው ኤርትራ በረሃ በመውረድ በነፍጥ ትግል ተሳትፈዋል። ከሎንዶን ወደ ኤርትራ በማምራት ላይ እያሉ የመን፣ ሰንአ አየር ማረፊያ ላይ ለኢትዮጵያ የደኅንነት ሰዎች ተላልፈው በመሰጠት ለዓመታት በእስር አሳልፈዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ በተካሔደው የፖለቲካ ለውጥ ምክንያት ከእስር ተፈተው አሁንም ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውን ቀጥለውበታል። አንዳርጋቸው በአንደበተ ርዕቱነታቸው ብቻ ሳይሆን አንዳንዶች ‹‹የሰላ›› ብለው በሚጠሩት ብዕራቸውም ይታወቃሉ። በቅርቡም በእስር ቤት ውስጥ የጻፉትን “እኛም እንናገር፥ ትውልድ አይደናገር” በሚል ርዕስ ለአንባቢያን ያበረክታሉ። የአዲስ ማለዳው ታምራት አስታጥቄ ከአንዳርጋቸው ጽጌ ጋር ቆይታ አድርጓል።
አዲስ ማለዳ፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአርበኞች ግንቦት 7 በኩል የሚደረገው እንቅስቃሴ ቀዝቀዝ ያለ ይመስላል። በተወሰነ ደረጃ የሚደረገው እንቅስቃሴም ቢሆን በሊቀ መንበራችሁ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ብቻ የተገደበ ይመስላል። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእርሶም ተሳትፎ ቀንሷል። ለምን?
አንዳርጋቸው ጽጌ፡ ለመጀመሪያ ጥቂት ሳምንታት ግልጽ ነው። ሕጋዊ በሆነ መንገድ እድል አግኝተን በአደባባይ በተለያየ መንገድ ከኛ ጋር ይሰሠሩ የነበሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ቀጥተኛ የምንገኛኝበት ወቅት ስለነበረ በሥፋት ከሕዝብ ጋር የመገናኘት ሁኔታ ነበር። ያ ደግሞ ሁል ጊዜ ሊቀጥል አይችልም።
ዋናው መሠረታዊ የሆነው ሥራ ድርጅታዊ መርሕና አወቃቀር ተከትሎ ወደሚሠራው ሥራ ላይ በደንብ ትኩረት በማድረጋችንና ይሄ ደግሞ ትልልቅ ሕዝባዊ ስብሰባዎች የሚጠይቅ ባለመሆኑ ጭምር ነው።
እኛ ልንሄድበት ያሰብነው ድርጅታዊ አሠራር መጀመሪያ ከአገሪቷ የፖለቲካ ችግር ተነስቶ የተቀረጸ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ አንዱና ዋነኛው ሊኖር ያልቻለበት ምክንያት እስካሁን ድረስ የተፈጠሩት [ፓርቲዎች] ዴሞክራሲያዊ ስላልነበሩ ነው የሚል እምንት ነው ያለኝ።
ስለዚህ እንዴት አድርገን ዴሞክራሲያዊ ድርጅት እንፈጥራለን ብለን ጠየቅን፤ የድርጅቱን ሥልጣን በአባላት ቁጥጥር ሥር እንዲወድቅ ማድረግ አወቃቀሩን ከታች ወደ ላይ መሆን እንዳለበት ወሰንን። ስለዚህ እያንዳንዱን የምርጫ ወረዳ መሠረት ያደረገ፣ በወረዳ ነዋሪዎቹ አባላት ምልመላ ላይ የተመሠረተ፣ እነዚህ አባላት በየደረጃው የሚቆጣጠሩት የወረዳዎች የፓርቲ መዋቅር በመዘርጋት ከእያንዳንዱ ወረዳ ወደ ላይ በሚመረጡ የጉባኤው ተሳታፊዎች አማካኝነት የሚፈጠር የፖለቲካ ፓርቲ ለመፍጠር እየሠራን እንገኛለን።
በእኛ አሠራር ሁሉም የአርበኛች ግንቦት 7 አመራር በሙሉ ወደ ሚኖሩበት ወረዳቸው ወርደው፣ የወረዳው አባላትና ሕዝብ ሲመርጣቸው ብቻ ነው ከአሁን በኋላ አመራር የሚሆኑት፤ አስቀድሞ የተያዘ የአመራር ቦታ አይኖርም። ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በጋራ የምንሠራበትንም መርህ ይሄንኑ አድርገናል።
ከኔ መጥፋት ጋር በተያያዘ የምከታተለው ሕክምና ስለነበረ እንግሊዝ ነበርኩኝ። ከእስራቴ ጋር በተያያዘ [ተከሻዬ አካባቢ] የተላቀቀ ነገር ስላለ ረጅም ‹‹ፊዚዮቴራፒ›› መከታተል ያስፈልገኝ ስለነበረ ነው።
አርበኞች ግንቦት 7 ከንቅናቄነት ወደፖለቲካ ፓርቲነት በአጭር ጊዜው ውስጥ ለመለወጥ ያልቻለበት መሠረታዊ ምክንያት/ቶች ምንድን ናቸው?
አሁን እየሠራነው ባለው የወረዳ አደረጃጀት መዋቅር ጋር በተያያዘ ነው። በአራት ወራት ውስጥ በጠቅላላ ከሌሎች ድርጅቶችም ጋር የምናካሒደውን ከወረዳ ጀምሮ መዋሃድ አልቆ ጉባኤ ተጠርቶ፣ የድርጅት ሕገ ደንቡን፣ ይፋዊ መርሃ ግብር በአዲሱ ጉባዔ በማፀደቅ እንዲሁም ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በምናደርገው ውህደት ጭምር ወደሥራ እንገባለን። ሌላው አርበኞች ግንቦት 7 የሚለውን ለማስመዝገብ ያልፈለግነው ስማችን አዲስ ሆኖ ሊወጣ ይችላል በሚል ነው።
በእናንተም ሆነ በሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተተኪን ከማፍራት አንጻር ያለባችሁ ድክመት በሠፊው ይጠቀሳል። የአንጋፋዎቹ የፖለቲካ ንቁ ተሳታፊነትና አመራር አብቅቶ አዲስ የወጣት ፊት የምናየው መቼ ነው?
ይሄ ለእኛ ለራሳችንም አሳሳቢ ጉዳይ ነው። በዋነኛነት በፖለቲካ ውስጥ እየተሳተፍኩ ያለሁት በአጭር ጊዜ ውስጥ ብቃትና አቅም ያላቸው ወጣቶች በአስቸኳይ ወጥተው ይሔንን ኃላፊነት የሚረከቡበትን ሁኔታ ለመፍጠር እንጂ ከዚህ በኋላ በቋሚነት ለረጅም ጊዜ ፖለቲካ ውስጥ እቀጥላለሁ የሚል እምነት የለኝም።
ወጣቶች እንዳይኖሩ ያደረገው ወያኔ ነው። በምርጫ 97 ላይ በተወሰነ ደረጃ ከደርግ ጊዜ ጀምሮ ፖለቲካ ውስጥ አልገባም ብሎ የነበረውን ብሩህ የሆነ ወጣት በሥፋት መንቀሳቀስ የጀመረበት ዕድል ተፈጥሮ ነበር። የወያኔ እመቃ እንደገና ተመልሶ በመቀጠሉ ‹ፖለቲካና ኮረንቲን በሩቁ› ወደሚለው አስገባው። እናም ፖለቲካ የደፋሮች፣ የባለጌዎች እና የተወሰነ ደረጃ ሌላ ሥራ ማግኘት የማይችሉ ሰዎች መናኸሪያ የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በዚህ የተነሳ አቅም፣ ጉልበትና ብሩህ አዕምሮ ያላቸው ወጣቶች ወደ ፖለቲካ መምጣት ያልቻሉበት ሁኔታ በመፍጠሩ የተነሳ ትልቅ ክፍተት በአገር ደረጃ ተፈጥሯል። በኢሕአዴግም ውስጥ የተፈጠረውም ይሄ በመሆኑ በአመራር ደረጃ ወጣቶች አልመጡም። በዚህ የተነሳ አገሪቷን ሲመራት የነበረው 3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ጭንቅላት ነው።
እውነት ነው ችግሩ በእኛም ውስጥ አለ። እኛ ዛሬ ዕድሚያችን ገፍቶ በማረፊያችን ሰዓት እስካሁን ፖለቲካ ውስጥ እንድንደፋደፍ እያደረገን ነው። ይህንን ለመቀየር ሠፊ የወጣቶች ተሳትፎ የሚኖርበት ሁኔታ ለመፍጠር በከፍተኛ ትኩረት እየሰራን እንገኛለን። ወጣቱ በራሱ ተደራጅቶ እንደ አንድ አገራዊ ቡድን የሚንቀሳቀስበትና ኃላፊነት መሸከም የሚችልበትን ሁኔታ መፈጠር አስፈላጊ ነው።
ሌላው ሊቀመንበራችሁ መጪውን አገራዊ ምርጫ በተመለከተ ‹‹ምርጫው ይራዘም አይራዘም ሳይሆን መሠረታዊው ጥያቄ የዴሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ መሆኑን›› በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይሰማል። ይሁንና መንግሥት እነዚህን ተቋማት ለማሻሻል እየሠራ ይገኛል። ከዚህ አንጻር የእናንተ የፖለቲካ እንቅስቃሴና የመርጫ ተሳተፎ ጉዳይ ከጊዜው አጭርነት አንጻር አያሳስባችሁም? ‹ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ› ስ አይሆንባችሁም?
ዞሮ ዞሮ እኔም የምደግመው ብርሃኑ የተናገረውን ነው። እኛ ምርጫ በዚህ አገር ላይ መደረግ አለበት ወይም የለበትም፤ ይቻላል አይቻልም ውሳኔያችን የሚመጣው ከድርጅቱ [አርበኞች ግንቦት 7] ቁመና ጋር ተያይዞ አይደለም።
አርበኞች ግንቦት 7 አገር ውስጥ መንቀሳቀስ የጀመረው በቅርብ ጊዜ፣ ሠፊ የኅብረተሰብ ክፍልን አልደረሰም፣ ያሰብናቸውን ሥራዎች አልሠራም የሚል እምንት የለንም።
ስለምርጫው የምንናገረው ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ነው። አገራችን ሠላማዊ፣ የተረጋጋች፣ የሕግ የበላይነት የሠፈነባት እስከሆነች ድረስ እና ምርጫን ነፃና ፍትሐዊ የሚያደርጉ ተቋማት መኖር በሕዝብና ፓርቲዎች እስከታመነ ድረስ ምርጫ ማድረግ ይቻላል። እነዚህ በሌሉበት ሁኔታ ግን የምርጫ ቀን ተቆርጧልና መደረግ አለበት በሚል መንገድ የሚሔዱ የአገር ኅልውናን፣ ሠላምና መረጋጋትን የሚያደፈርሱ ይሆናሉ። ‹ምርጫው ተጭበርብሯል፣ ባልተሟላ ነፃ ባልሆነ ተቋማት ሥር እንዲካሄድ ተደርጓል› የሚል ክርክርና ጭቅጭቅ የሚያስነሳ እስከሆነ ድረስ ምርጫው መካሔድ የለበትም። በሚቀጥለው አንድ ዓመት ተኩል እጥፍ ጊዜ ቢሠራ መንግሥት ማቃለል የማይችለው መሠረታዊ የሆኑ ችግሮች አሉ።
መሠረታዊ ያሏቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
መንግሥት በእጁ ያሉትን ተቋማት ደህንነቱን፣ መከላለያውን፣ ፖሊሱን፣ ምርጫ ቦርድንና ፍርድ ቤትን በቀላሉ ነፃ አድርጎ ሊያደራጅ ይችላል። እዚህ አገር ያለው ችግር በየክልሉ ገለልተኛና ነፃ ያልሆኑ በክልል ፓርቲዎች ቁጥጥር ሥር ያሉ፣ ራሳቸው ያደራጇቸው፣ የራሳቸው ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ፣ ድህንነትና የፖሊስ ኃይል አላቸው። ይሄ ኃይል ዴሞክራሲ ላይ ተጽዕኖ ማድረስ፣ አመፅንም መጠቀም የሚችል ኃይል ነው። በፌደራል ደረጃ ይህንን አስተካክሎ በክልል ደረጃ ማስተካከል ሳይቻል ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማድረግ ይቻላል የሚል እምንት የለኝም።
ለምሳሌ ትግራይን መውሰድ ትችላለህ። ለማዕከላዊ መንግሥት ወንጀለኛና ሌባ አሳልፎ ላለመስጠት እየተግደረደረ ያለው በሌላ ነገር ሳይሆን ባለው ኃይል፣ ሚሊሻ፣ የታጠቀ ፖሊስና ሌላ ኃይል ነው። አገሪቱ በዚህ ደረጃ ባለችበት ሁኔታ ምን ዓይነት ምርጫ ነው የምታካሒደው? ስለዚህ ተፎካካሪዎች እንዴት አድርገው ነው ነፃ ሁኔታ አለ ብለው ወደ ክልሉ ለውድድር የሚሄዱት? ነፃና ፍትሓዊ ምርጫ ተደርጎስ ብታሸንፍ እነዚህ በየአካባቢው ያሉት ኃይሎች ውጤቱን እሺ ብለው ይቀበላሉ?
ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሔድ እንደሚታሰበው ቀላልና በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚቃለል ችግር አይደለም። ይሄንን በሚገባ ሕዝብ፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ማወቅ ይገባቸዋል፤ ሥልጣንም ላይ ያለው መንግሥትም መረዳት ይገባዋል። ተቋማትን ነፃና ገለልተኛ በማድረግ ብቻ ሳይሆን በየክልሉ ያለው ነገር ነፃና ገለልተኛ መሆን ከዴሞክራሲያዊነት ጋር በቀጥታ ስለሚተሳሰር ሠፊ ውይይት ይጠይቃል።
የፌደራል መንግሥቱ ተቋማትን ነፃና ገለልተኛ ለማድረግ እየወሰደ ስላለው እርምጃዎች ምን ይላሉ?
እስካሁን ድረስ እነ ዐቢይ (ዶ/ር) ላይ ምንም እንከን አላገኘሁባችም፤ እያደረጉ ያሉት ጥረት ሀቀኛ ነው ብዬ ነው የማስበው። ችግሩ ከራሳቸው ሳይሆን ከመጡበትና አገሪቷን የተረከቡበት ሁኔታ እጅግ አስቸጋሪ መሆኑ ይገባኛል።
ስለዚህ ቅድም እንደገለጽኩልህ ዴሞክራሲ እዚህ አገር ውስጥ እንዳይኖር ከፍላጎት ማጣት ሳይሆን ጠቅላላ የተወሳሰበና አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በመግባታቸው ነው። ያንን ሳያቃልሉ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም። ስለዚህ አንድ ዓመት ተኩል የቀረው ምርጫ ለማካሔድ ሁኔታዎች መስተካከል አለባቸው። የፌደራል መንግሥቱ ብዙ አቅም ማካበት ይገባዋል፤ በሕዝብም ውስጥ መሥራት ያለባቸው ብዙ ሥራዎች አሉ።
ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን አጣብቂኝ ሁኔታ ለመፍታት፣ ችግር ለማቃለል አንዳንዶች የሽግግር መንግሥት ወይም የሽግግር ምክር ቤት መቋቋም አለበት በሚል ይሞግታሉ። በዚህስ ላይ የናንተ አቋም ምንድን ነው?
የሽግግር መንግሥትን በተመለከተ በተደጋጋሚ ተነስቷል። አገሪቷ ውስጥ ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ ያካተተ የሥልጣን ክፍፍል በማድረግ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ችግሮች መፍታት አይቻልም።
አሁን ዐቢይ እየሰራ ያለው ተቋማትን ነፃ ማድረግ፣ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት፣ ሽብርተኛ የተባሉ ድርጅቶችን በሙሉ በአገር ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ የሽግግር መንግሥት ከሚሰራው በላይ በጥሩ ሁኔታ እየተሠራ ነው ብዬ አስባለሁ። የሽግግር መንግሥት ቢመጣ በአገሪቷ ውስጥ የበለጠ ቀውስ ይፈጥራል።
ስለዚህ መጀመሪያም ቢሆን ከ80 በላይ ፓርቲዎች ባሉበት አገር የሽግግር መንግሥት ማድረግ የሚታሰብ አይደለም። ወሳኝ በመሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማት እና የሕግ ጉዳዮች ላይ መምከር ይገባል። እሱም ላይ ቢሆን ከፓርተዎች ብዘት አንጻር መንግሥት የሆነ ነገር መደረግ አለበት።
በመንግሥት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች እንዲሁ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሹመትን በተመለከተ ተፎካካሪዎችን ‹የዳር ተመልካች› አድርጓል ስለሚባለውስ ምን ይላሉ?
ሹመቱን በተመለከተ እስካሁን ችግር አላየሁም። የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋና የፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ሹመትን በተመለከተ ወገንተኝነት ያላቸው አይደሉም። በቀላሉም ተፅእኖ ይደረግባቸዋል የሚል እምንት የለኝም። በቁርጠኝነትም ደረጃ ችግር ይኖርባቸዋል አልልም።
ያለቀ ሒደት ባለመሆኑ ለምሳሌ ምርጫ ቦርድን በተመለከተ ከተቃዋሚዎች ጋር በመመካከር ሌሎች አባላትን ለማሟላት ለመሥራት ዕድል ይኖራል። ቀና እስካሰብን፣ ሕዝብና አገርን እስካስቀደምን ድረስ ሊያሠራ የሚችል ባህል ሊኖረን ይገባል። ስለዚህ በተወሰነ ደረጃ መቻቻል ያለበት አሠራር መልመድ ይኖርብናል። የሚያጨቃጭቁ ጉዳዮች ከመጡ ግን ልንጨቃጨቅባቸው እንችላለን።
ያን ያክል የፖለቲካ መሥመር ልዩነት በሌለበት የተፎካካሪ ፓርቲዎች ብዛት፣ አብሮ ያለመስራት፣ ያለመዋሃድ፣ ያለመቀናጀት ወዘተ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
መሠረታዊው ምክንያት ከባሕል ጋር የተያያዘ ችግር ነው። እኔ ያልኩት ብቻ ካልሆነ፣ እኔ ብቻ የምለው ካልሆነ፣ የመምራት እንጂ የመመራት ግድ የሌለው፣ ሌሎች ያሉትን ያለመፈፀም ባሕል ወደ ዘመናዊነት እንዳንሸጋገር አድርጎናል። እያንዳንዱ ሰው የራሱን ትንንሽ ዘውድ በኪሱ ይዞ የሚዞር፣ እያንዳንዱ ለመንገሥ ፍላጎት ያለው ልኂቅ ነው ያፈራነው።
ይሁንና ምንም የባሕል አብዮት ሆነ ተሐድሶ ሳናካሒድ ይቺን አገር ገፍተን፣ ገፍተን አሁን የምትገኝበት ሁኔታ ላይ አድርሰናታል። ይህ ሁኔታ ልኂቁን ከእንቅልፉ እያነቃው ያለ ይመስለኛል። እነዐቢም ቢሆኑ መጽሐፍ በማንበብ ብቻ የመጡ አይመስለኝም፤ የዴሞክራሲ ጽናታቸው የመጣው የሕዝብ ስቃይ፣ የአገር መፍረስ የማይቀር መሆኑን እየተረዱ ስለመጡና አገር ማዳን የሚቻለው በግልፅነት፣ በተጠያቂነት፣ በዴሞክራሲያዊነት እና ሕዝብ ራሱ የሚቆጣጠረው አገር እንዲኖረው በማድረግ እንጂ ጥቂት ልኂቃን የሚቆጣጠሩት አገር ሲሆን እንዳልሆነ በመረዳታቸው ነው። ሌላውም እንዲሁ እየነቃ የመጣ ይመስለኛል።
አሁን ተቀራርቦ ለመሥራት፣ ለመዋሃድ፣ እየገፋን ያለነው መኖር የማንችልበት ለሁላችንም ሁኔታ ለሁላችንም በመፈጠሩ ነው። ተመሳሳይ እምነት ያላቸው ኃይሎች ተሳስበው፣ ተቻችለው እንዲሰሩ እያደረገ ነው። ሕዝብ ደግሞ የሚፈልገው የሚሰራለትን፣ ከችግርና መከራ የሚያድነውን፣ ከአፈና የሚያወጣውን፣ ቀናና ትሁት የሆነ አቅም ያለውን ሰው የመምረጥ ዕድል ስላለው ለመጀመሪያ ጊዜ በአገራችን በርካታ ድርጅቶች አንድ ሆነው ሕዝብ የሚቆጣጠረው የፖለቲካ ድርጅት አዲስ ባሕል በአገራችን እንደሚመጣ እምነትና ተስፋ አለኝ፡
ስለዕርቅና ይቅር ስለማለት እየተነገረ ባለበት ሁኔታ መንግሥት ከሰብኣዊ መብት ጥሰትና የተደራጀ ሌብነት ጋር በተያያዘ በቀድሞ ባለሥልጣናት ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ እንዴት አስታርቆ ማስኬድ ይቻላል? ለውጡንስ አይቀለብሰውም?
ሁለት ነገር ለይቶ ማየት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። የሕዝብ ሀብት የዘረፉት እስካላስረከቡ ድረስ በይቅርታ የሚታለፍ ነው ብዬ አላስብም።
በደንብ ከመረመርነው ዘረፋ ከሰብኣዊ መብት ጥሰት ሰውን በማሰቃየት ደረጃ የምትመዝነው ከሆነ በዘረፋ መንገድ የተፈጸመው ነገር በቀጥታ ከተፈጸመው ማሰቃየትም የከፋ ነው። የተዘረፈውና ያለአግባብ የባከነው ገንዘብ በቢሊዮን ስለሆነ ይህንን መመንዘር ብትጀምር ስንት እናቶች ናቸው በቂ ሕክምና ባለማግኘት የሞቱት፣ ስንት ሕጻናት ናቸው ሲወለዱ የሞቱት፣ ስንት ሕጻናት ናቸው በምግብ እጥረት የሞቱት፣ ስንት ሕዝብ አገልግሎት ባለማግኘቱ ሞተ፣ ተሰቃየ? ይሄ ብር በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዲያጡ፣ ያለአግባብ በጣርና በመከራ እንዲኖሩ፣ እንዲሰቃዩ አድርጓል። ስለዚህ ዘረፋው ራሱ በሰብኣዊ መብት ጥሰት መልኩ መለየት አለበት። እንደዚህ ዓይነት ሰዎች በሥርዓት፣ በሕግ፣ መጠየቅ ይኖርባቸዋል።
ከሰብኣዊ መብት ጥሰት ጋር የተያያዘውን መንግሥት ከፍተኛ ወንጀል የፈጸሙትን እና አላርፍ ያሉትን በፍርድ ቤት አስፈርዶ፤ የይቅርታው ነገር ቀጥሎ ሊመጣ ይችላል። በእስር ቤት ሊቀጡ የሚችሉበትን ሁኔታ ማምጣት ይቅርታውን የሚያዛባው አይሆንም።
የሰብኣዊ መብት ጥሰቱ በይቅርታ ሊዘጋ ይችላል። በቢሊየን የዘረፈን ሰው ግን በሠላምና ዕርቅ ሥም እንደው ዝም ብሎ ተጨባብጦ ሁለተኛ ሌብነት እንዳይደገም በሚል ብቻ መልቀቅ ላይ አላምንም።
የተበላሸውን ምዕራፍ ለመዝጋትና ኢትዮጵያ እያካሔደች ያለውን የፖለቲካ ለውጥ ለማስቀጠል የዕርቀ ሠላም አካሔዱ እንዴት መሆን አለበት?
የእኛን ችግር ውስብስብ ያደረገው የሰብኣዊ መብት ጥሰቱና ዘረፋው አንድ ላይ መምጣታቸው ይመስለኛል። በመጀመሪያ ከዘረፋ ጋር የተያያዘውን ግልፅ የሆነ አቅጣጫ ማስያዝ ያስፈልጋል። እያንዳንዱ በዘረፋና ሌብነት የወሰደውን ከመለሰ ይቅርታ ሊደረግ ይችላል። በቁርሾ መቀጠሉ ሊኖር አይገባም ባይ ነኝ።
ነገር ግን በአገሪቷ ውስጥ ዘረፋ እንዳይኖር የሚያስችል ሥርዓትና ደንብ መዋቅር መዘርጋት ይኖርበታል።
ከሰብኣዊ መብት ጋር በተያያዘ ደቡብ አፍሪካ ላይ በተካሔደው መንገድ ወንጀላቸውን ለሕዝብ ይፋ አድርጎ፣ ፀፀት ውስጥ የገቡት፣ ይቅርታ የጠየቁት የሚታሰሩበት ምክንያት አይታየኝም።
ስለትግራይ ሕዝብ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይሰማል? ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የፖለቲካ ሒደት የትግራይ ክልልና ሕዝብን ተሳትፎ እንዴት ይመለከቱታል?
የትግራይን ሕዝብ ከትግሉ ወቅት ጀምሮ አውቀዋለሁ። ስለዛ ሕዝብ ደግነት፣ በጎነት እና ለሌሎች ለተበደሉ ወገኖቸቹ ያለውን ስሜት ስለማውቅ ሁል ጊዜ እዚህ ነገር ላይ ግልጽ የሆነ አቋም አለኝ።
ነገር ግን ከሕዝቡ አብራክ የወጡ፣ እሱን እንመራለን ያሉ ሰዎች፣ እሱኑ ጭምር ነው ትተው የግል ሀብትና ንብረት ሲያካብቱ የነበሩት። በ1985 ኢሕአዴግን ጥዬ በሔድኩበት ወቅት የተናገርኩት የቤት፣ የመኪና፣ የከተማ ውስጥ ቅንጦት በረሀ እነሱን እያበላ ሲያታግል የነበረውን ሕዝብ ያስረሳቸው መሆኑን ጠቅሼ ነው የለቀቅኩት።
በዛን ጊዜ በተቀዳ ቪዲዮ ላይ ይህንን ስናገር ‹ከመቼ ጀምሮ ነው ለትግራይ ሕዝብ ተቆርቋሪ የሆንከው?› በሚል አንድ ትግሪኛ ተናጋሪ ሰው መልስ ሰጥቶኛል። አሁንም ቪዲዮው አለ መመልከት ይቻላል።
ውሎ አድሮ የትግራይ ሕዝብን ወያኔ ችግር ውስጥ ሊከተው እንደሚችል 1985 ላይ ነው የተናገርኩት። ያኔ ያን ያክል ብዙ ነገር አይቼ ሳይሆን ትንንሽ ነገሮችን ተመልክቼ ነው። አሁን ግን ከዚያ ሕዝብ በወጡ ጥቂት ግለሰቦች የተካሔደውን ከፍተኛ ዘረፋ ከእነሱ ጋር በመሞዳሞድ ሌሎች ብሔሮችን ጨምሮ የተካሔደ ነው። ከፖለቲካው ጋር በቀጥታ ሳይያያዝ በንግድ ዓለም ያሉ ዘረፋዎችንም እናውቃልን።
ነገር ግን በአንዳንድ ተቋማት ውስጥ ያመጣው ችግር ተቋሙ ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ደረጃ በትግራይ ልጆች እንዲያዝ ማድረጋቸው ነው። ለምሳሌ እስር ቤት በነበርኩበት ጊዜ ያገኘኋቸው 25 ሰዎች በሙሉ ትግሪኛ ተናጋሪዎች ናቸው፡- ጠባቂዎች፣ ዘበኛው፣ መከና የሚነዳው፣ ምግብ የምታቀርበው፣ ለሕክምና የመጣችው። ይህንን ተመልክቼ እኔ በትግራይ ሕዝብ ላይ ጥላቻ አላሳደርኩም። ለሚሰሩት ግፍና በደል ሌላው ብሔር ከተቀላቀለ ምስጢር ይወጣል በሚል እሳቤ ነው።
ነርሷ እህተማሪያም ደግ ሰው ነች። እቃ ግዢ ተብላ ስትላክ ለእኔ በገዛ ገንዘቧ ካኒተራና ፓንት ገዝታልኛልች። እነዚህን ሰዎች እዚህ ውስጥ የከተቱት እነጌታቸው አሰፋ ናቸው። ከሌሎች መርጠው ያመጧቸው የሚያሰሯቸው በቋንቋና በብሔር ስለምንገናኝ ምስጢር አያወጡም በሚል ነው። ሕዝብ እየተነሳ መክሰስ ሲጀምር፣ ችግር ሲፈጥሩ የነበሩት የትግሪኛ ተናጋሪዎች ናቸው ማለት ጀመረ። ይሄ እውነት ነው! የትግራይ ሕዝብ ማወቅ አለበት። ይህንን ሆን ብለው ያደረጉት እነጌታቸው ናቸው። ከዘረፋውም ሆነ ከሰብኣዊ መብት ጥሰት ጋር አድዋ፣ ሽሬ፣ አዲግራት ወዘተ ያለ ገበሬ ምንም የሚያገናኘው ነገር የለውም።
እስር ቤት ቁጭ ብዬ በጻፍኩት ጽሑፍ ደኅንነቱ በዚህ መንገድ መደራጀትና ከትግሪኛ ተናጋሪ ውጪ ማስገባት አለመቻሉ ‹የነብር ጭራ አይዙም …› በማለት ደኅንነቱ የገባበትን አጣብቂኝ ገልጫለሁ። ሌለው ቀርቶ ‹ለአገር ተቆርቋሪነት ከኛ በላይ የለም› በሚል ቅዠት ውስጥ ገብታችኋል በሚል ጽፌላቸው ነበር።
ይህንን እውነት የትግራይ ሕዝብ ማወቅ አለበት፤ ሌላውም እንደዚሁ ማወቅ አለበት። ይህንን በደል የፈጸሙት ጥቂቶች ናቸው፤ ብትደምራቸው ከመቶ አይበልጡም። የትግራይ ሕዝብን ሌላው በሙሉ በርሱ ላይ ሊዘመትበት እንደሆነ በማስመሰል በወንጀላቸውና ጥፋታቸው እንዳይቀጡ መሸሸጊያና መደበቂያ አድርገውታል።
የትግራይ ሕዝብ ምን ያድርግ?
የትግራይ ሕዝብ ማወቅ ያለበት በሕዝብ ላይ የሚመጣ ጥቃት፣ በደል ካለ ጥቃቱን ዝም ብለን የምናየው አይሆንም። ጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ሕዝብ ሲበደል ዝም ብሎ እንደማያይ የትግራይ ሕዝብ እንዲረዳ እንፈልጋለን።
እኛ ትግሪኛ ተናጋሪ ባለመሆናችን ቀጥታ በትግሪኛ ልናናግረው አልቻልንም። ያለበት ሁኔታ የሚያሳስበን መሆኑ ግን እንናገራለን። ሐቁ፣ እውነቱ ይሄ ነው። በቋሚነት ስለትግራይ ሕዝብ ስንናገር እንደነበረው እንደኔ ዓይነት ሰው በተወሰነ ደረጃ ጆሮ ይኖረዋል ብዬ አስባለው። የተቻለንን ያክል እንናገራለን።
በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ ክልላዊ መንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት እንዴት ይገልጹታል?
በመጀመሪያ ፌደራላዊ ስርዓቱ ሲዋቀር እያንዳንዱ ክልል ራሱን የቻለ ማዕከላዊ መንግሥት መገዳደር የሚችል ጉልበት በሚኖረው ደረጃ ሠራዊትና ሌላ ነገር እንዲያቋቁሙ የተደረገበት መንገድ ውሎ አድሮ አሁን ያለው ሊፈጠር እንደሚችል ተነጋግረን ነበር።
በ1985 ባቀረብኩት ክርክር የብሔር መብት ማስከበር ቋንቋን፣ ባሕልን ማሳደግ፣ መጠቀምና ማስጠበቅ ጥሩ ሆኖ ሳለ ዞሮ ዞሮ ዘር ወደሚወልደው የብሔር አደረጃጀት መግባት አደገኛ መሆኑን አመላክቻለሁ። እያንዳንዱን አካባቢ ሥም እየጠራሁ ድርጅት መኖር የለበትም እስከማለት ድረስ ሔጂያለው፤ ክልል ነው መሆን አለበት በሚል። አማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሞ ወዘተ ብሎ ደርጅት የሚባል ከመጣ በክልሎቹ ውስጥ የሚኖሩ የሌላ ብሔር ተወላጆች ወዲያውኑ ይገለላሉ። አሁን የምናየው ፌደራሊዝሙ የተደራጀበት ውጤት ነው።
ለምን እንዲህ ማደራጀት አስፈለገ?
ጊዜያዊ ጥቅም የፈጠረው በደንብ ሳይታሰብበት የተገባበት ድንቁር ውጤት ነው። በዚህ መንገድ በማደራጀት ሠላምና መረጋጋት ካገኘን ሌላው በራሱ ጉዳይ ሲያተኩር እኛ ለማስተዳደር የምንችልበት ሁኔታ ይፈጠራል በሚል ስሌት ነው። በዚያን ጊዜ እንደአሁኑ በቢሊዮን ለመዝረፍ አስበውበት ነው የሚል አመለካከት የለኝም። በአጭሩ የበላይነትን ለማረጋገጥ የተሄደበት አካሄድ ዛሬ አገር የማፍረስ ደረጃ ላይ ደርሷል።
ምን ይደረግ?
ሕዝብን በማሳተፍ ለሕዝብ ጉዳቱ ምን እንደሆነ በሚገባ መግለጽ ያስፈልጋል። ሱማሌ ክልል በጣም አነስተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ያለው ሲሆን ነገር ግን በቁጥር የሚልቅው የኦሮሞ ሕዝብ ሊጋፋው ባልቻለው መንገድ አንድ ሚሊየን ሰዎች ማፈናቀል የሚችልበት ሁኔታ ከተፈጠረ አሸናፊና ተሸናፊ ሊባል የማይቻልበት ሁኔታ አገሪቱ እንዳለች ታያለህ። በብዛትህ ልትመካ አትችልም፤ ትንሹን አጠፋለሁ ለማለት የምትችልበት ሁኔታ አይደለም። ስለዚህ የርስ በርስ መጠፋፋት የሚያመጣ እስኪሆን እያንዳንዱ ገፈት ቀማሽ ሆኗል።
በአንድ በኩል ራስን በራስ ማስተዳደርን፣ ቋንቋ መጠቀምን፣ ባሕል ማሳደግ የመሳሰሉትን ነገሮች በሌላ በኩል ደግሞ ከዘር ጋር ተያይዞ የመጣውን ፍጥጫ የሚያጠፋ የፓርቲ አደረጃጀት አስተዳደራዊ መዋቅር በደንብ ሊታሰብበት ይገባል።
ጥናት ይጠይቃል፣ ንግግር ይጠይቃል። ይህንን ማቃለል እስካልቻልን ድረስ እድገትም፣ ብልፅግናም ዴሞክራሲም የለም። በረሀብ እየተጠበሱ እንኳን መኖር የማይቻልበት ሁኔታ መምጣቱ አይቀርም።
ከኤርትራ የመጣውንና እዚሁ አገር ውስጥ ሆኖ ሲታገል የነበረው የድርጅታችሁን ታጋዮች ትጥቅ የማስፈታትና መልሶ የማቋቋም ሥራ መጀመሩን ከዚህ ቀደም መግለፃችሁ ይታወሳል። ምን ላይ ደረሰ? መርሃ ግብሩን ለማካሔድ የገንዘብ ምንጫችሁስ ምንድን ነው?
ከኤርትራ የመጡት ወደ 300 ገደማ ሲሆኑ አገር ውስጥ ሆነው አርበኞች ግንቦት 7 በተለያየ መንገድ ያስታጠቃቸውና ማዕከላዊነትን ባልጠበቀ መልኩ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አምስት ሺሕ ናቸው። ከኤርትራ ከመጡት አሁን ከመቶ በላይ ‹ካምፕ› ውስጥ አሉ፤ ከ‹ካምፕ› ወጥተው ወደየቤታቸው የተመለሱት የፌደራል መንግሥቱ ዘጠኝ ሺሕ ብር እየሰጠ መልሶ ማቋቋም መርሃ ግብሩ ሲጀመር በያሉበት ሆነው የሚሳተፉበት ምርጫ ይሰጣቸዋል። የጀርመን መንግሥት ለ35 ሺሕ በትጥቅ ትግል ለተሳተፉ ሰዎች የገንዘብ ድጋፍ (‹ፈንድ›) እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል። እሱን እየተጠባበቅን ነው ያለነው።
እርሶን ጨምሮ የውጪ አገር ፓስፖርት የያዙት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተሳተፎ ምን መሆን አለበት ይላሉ?
ዐቢይ (ዶ/ር) እንደተናገረው ከሆነ ኢትዮጵያዊ የትም ሆነ የት በስደት ቢኖርም ኢትዮጵያዊነቱን የሚያጣበት አይደለም። በዚህ ደረጃ ከኢትዮጵያ ጋር የተጣበቀውን ዳያስፖራ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ በፖለቲካው በሌላውም ዘርፍ ከፍተኛ ብቃትና ሙያ፣ ሀብት፣ ገንዘብ ያለውን ያገለለ ዓይነት አገር ግንባታ የማይታሰብ ከመሆኑ የተነሳ እንደ ፖሊሲ የሁለት አገር ዜግነት ፈቅዶ በሥፋት እንዲሳተፉ ማድረግ መቻል አለበት። ኢትዮጵያን የሚወድ ከሆነ መንግሥትም ይህንን ቢያደርግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ‹ትራንስፎርም› ማድረግ አለበት።
የፖለቲካ ተሳትፎንም በተመለከተ ጥምር ዜግነት እንደሚሰጡት አገሮች ዳያስፖራው በውጪ አገሮች በየኤምባሲዎች ድምጽ እንዲሰጥ ማድረግ አለበት። በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ገደብ ሊጣል ይችላል።
ይህንን የምለው ለኔ ስል አይደለም። እኔ ወጣቶችን አደራጅቼ ከፖለቲካ በፍጥነት የምወጣበት፣ ወደፊት የሚደረግ ምርጫ ውስጥም የውጪ አገር ዜግነት ሳላለኝ አልሳተፍም። እየሰራሁ ያለሁት መርዳት ላይ ነው።
የኢትዮጵያን መጻኢ ዕድል በተመለከተ ምን ይታዮታል?
እኔ የውሽት ተስፋ መስጠት አልወድም። ሁለት ነገር አለ። ብርሃን አለ፤ ጨለማ አለ። ተስፋ አለ፤ ተስፋ የሚያጨልም ነገር አለ። የኢትዮጵያ ልኂቃን በዋነኛነት አገሪቷና ሕዝቧ ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ተረድቶ አስፈላጊ የሆነ መቻቻል፣ ለአገር ይበጃል የሚል ነገር ቅድሚያ ሰጥቶ ካላስተካከለ÷ እሱም የኢትዮጵያ ሕዝብም መኖር የማይችሉበትን አገር ይፈጥራል።
አፍሪካ አይታ የማታውቀውን የርስ በርስ መተላለቅ፣ በምድር ላይ ሲኦል አለ ከተባለ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የሚባልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ይሔ ቀልድ አይደለም።
ከተሳካልን በአፍሪካ ውስጥ ከየትኛውም አገር በላይ ዴሞክራሲ የሰፈነባት፣ ምሳሌ የምትሆን አገር መፍጠር እንችላለን።
ቅጽ 1 ቁጥር 5 ታኅሣሥ 6 ቀን 2011