ሁሉም ዜጎች፣ ማንም ይሁኑ ምን፣ ከሕግ በታች የመሆናቸው ጉዳይ – የሕግ የበላይነት ጉዳይ – ከዴሞክራሲ መርሖዎች አንዱ እና ዋነኛው ነው። ሕገ መንግሥቱ ደግሞ የሕጎች ሁሉ የበላይ መሆኑ እና ከሕገ መንግሥቱ የሚፃረሩ ሕግጋት ማውጣትና የሚጋጭ አካሔድ መከተል እንደማይቻል ሕገ መንግሥቱ በራሱ ያሳስባል። ሕገ መንግሥቱ ካስቀመጣቸው ድንጋጌዎች መካከል ደግሞ የመሬት ባለቤትነት መብት ይጠቀሳል። በአንቀጽ 40 ላይ የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ መሆኑን ይገልጻል። በተያያዘም የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች መሬት በነጻ የማግኘት፣ የመጠቀምና ከመሬታቸው ያለመፈናቀል መብት እንዳላቸውም ያትታል። ይሁንና መሬቱ ለላቀ ልማት ከተፈለገ መንግሥት ካሣ ከፍሎና ምትክ ቦታ ሰጥቶ ሊያስነሳ እንደሚችልም ተደንግጓል።
በዚህ ሒደት መታሰብ ያለባቸው ነገሮች ግን ሊዘነጉ አይገባም። ዴሞክራሲ አንድም ለሕግ ተገዥ መሆንን ሁለትም በውይይት እና ድርድር ማመንን ይጠይቃል። በሕግ ተገዥ መሆን ሲታሰብ በመንግሥትም በኩል ሆነ በባለይዞታው ግለሰብ መካከል ገዥ ሐሳብ ሆኖ መቀመጥ ያለበት ሕግ መሆኑን ሲያመለክት፣ በውይይት ማመን ደግሞ መሬቱ ለሌላ ልማት ሲፈለግ ጀምሮ አርሶ አደሩን ወይም ባለይዞታውን ከመሠረቱ የማወያየት እና ጥያቄዎችን በውይይት ፈትቶ መግባባት ላይ መድረስን ታሳቢ ያደርጋል። መንግሥት አቅም ስላለው ብቻ የሕዝብና የመንግሥት የጋራ ሀብት ነው ሲል ያስቀመጠውን መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ሲፈልገው “ሕዝቡ ምን አገባው” በሚል ኢ-ዴሞክራሲያዊ መንገድ በመከተል ከውይይት ይልቅ ወደ ማዘዝ ሊሻገር አይገባውም፤ በተግባር የሚስተዋለው አካሔድ ግን ይህንን ይመስላል።
በዚህ መነሻነትም በአዲስ አበባ ዙሪያ ለልማት የተነሱ አርሶ አደሮችም ይሁኑ ከመሐል ከተማዋ በመልሶ ማልማት ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖች መጀመሪያውኑ ተገቢው ውይይት ተካሒዶ፣ ተሳትፏቸውን በአረጋገጠ እና ገበያውን መሠረት ባደረገ ካሣ ተስማምተው እንዲነሱ ሲደረግ ሒደቱ ዴሞክራሲያዊ ነው ልንል እንችላለን። ከላይ ወደታች በሚወርድ ትዕዛዝ እና ተመን ብቻ አርሶ አደሮቹን ከእርሻ እና መኖሪያ ቦታቸው የመንቀል ስርዓቱ ግን ከዴሞክራሲ የሚፃረር አካሔድ ነው።
ከዴሞክራሲያዊ ስርዓቶች ዓላማ ውስጥ ዋነኛው በመንግሥት የሚከናወኑ ማኅበራዊም ይሁኑ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ለውጦች ሕዝቡን ማዕከል ያደረጉ እና ሕዝባዊ ቅቡልነት ያላቸው መሆን አለባቸው። የኢትየጵያ የልማት እርምጃዎች እና ለዚሁ ሲባል ነዋሪዎችን ማስነሳት በተደጋጋሚ የግጭት እና ሕዝባዊ ቅሬታ መንስዔ የሚኖረው ሕዝባዊ ተሳትፎዎች ስለማይደረጉበት እና ነዋሪዎቹን ተጠቃሚ የሚያደርግበት መንገድ ስለሌለ፣ ወይም ስለማይታወቅ፣ ወይም ደግሞ ስለማይታመንበት ነው።
ቅጽ 1 ቁጥር 5 ታኅሣሥ 6 ቀን 2011