‹‹በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 35 ማስፈጸሚያ ደንብና መመሪያ ሊቀመጥ ይገባል››

0
861

የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን ከማስጨነቁ በላይ የተለያዩ አሳሳቢ ክስተቶችንም እያስከተለ ነው። ከዚህም መካከል አንደኛው ቫይረሱን ለመቆጣጠር እንዲያስችል ቤት ውስጥ መቀመጥ አማራጭ መሆኑ፣ የቤት ውስጥ ጥቃትን እንዲጠነክር ማድረጉ የሚታወስ ነው። ይህም አሁን ላይ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ ሆኗል።

በኢትዮጵያም አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመታወጁ ጋር ተያይዞ እንዲሁም በሴቶች ላይ የሚደርስ የቤት ውስጥ ጥቃት ቀድሞም ቤተኛ ከመሆኑ ጋር ነገሩ የባሰ እንዳይሆን የፈሩ ጥቂቶች አይደሉም።

ይህንን በሚመለከት በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የልዩ ልዩ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክተር ወሰንየለሽ አድማሱ ሐሳባቸውን አካፍለዋል። ወሰንየለሽ ከዚህ ቀደም ፍትህ ሚኒስቴር ይባል በነበረው በአሁኑ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ ዐቃቤ ሕግ በመሆን አገልግለዋል። የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮ ላይ ዐቃቤ ሕግ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን፣ ከሰባት ዓመት በላይ ደግሞ የሴቶችና ሕጻናት ጥቃት መመርመርና ውሳኔ ማሰጠት ጉዳይ ላይ ከጀማሪ ዐቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ቡድን አስተባባሪነት እስከ ማስተባበሪያ ኃላፊነት ድረስ ሠርተዋል። ከአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጋር ወቅታዊ ሁኔታዎችን እንዲሁም የተለያዩ ሐሳቦችን በማንሳት ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማይነካቸው መብቶች አሉ። አንቀጽ 35 የሴቶች መብት ጉዳይ በዚህ አልተካተተም። ተዘንግቶ ነው ወይስ ከማይነኩ መብቶች ውስጥ መካተት አያስፈልገውም?
የአንቀጽ 35 ንዑስ አንቀጾች ላይ የተቀመጡ መብቶች በአብዛኛው የእኩልነት መብትን የሚይዙ ናቸው። የእኩልነት መብት ማለት የትኛዋም ሴት ከማንኛውም ወንድ ጋር በሕግ ፊት እኩል ናት የሚል ነው። በትዳር ወይም ከትዳር ውጪ ባላቸው ግንኙነት ሴት መሆኗ የሚያሳንሳት አይደለም፤ ሕግ ያጎናጸፋትና ከመሆኑ ላይ እንደሰው የተሰጣት ሰብአዊ መብት ነው። ሴት መሆኗ ያንን መብት ያሳጣት ተደርጋ ልትወሰድ አይገባም የሚለውን የሚያስገነዝብ ነው።

የአንቀጽ 35 ንዑስ ቁጥር ሦስት ሐሳብ ሲወሰድ ደግሞ፣ የታሪክ ቅርስ ሴቶች ላይ ያመጣውን አሉታዊ ሁኔታ ማስቀረት የሚያስችሉ አሠራና ሕግ መፍጠር ግዴታ ነው ይላል። ለዚህም አዎንታዊ እርምጃ መውሰድ አንደኛው የአሠራር ማዕቀፍ ነው የሚል ሐሳብ ያስቀምጣል።

ከንዑስ ቁጥር አራት እስከ ዘጠኝ ያሉት የወሊድ መብት፣ ሥራ የመሥራት፣ እኩል ክፍያ የማግኘት መብት ወዘተ ጋር የተገናኙ ናቸው። እና አብዛኞቹ ለሴት ስለተደረጉ ብቻ የማይነኩ መብቶች ናቸው፣ ከአካል ደኅንነትና በሕይወት ከመኖር መብት ጋር የተገናኙ ጉዳዮችም ናቸው። እናም አንቀጽ 35 አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲወጣ በልዩነት ሊታይ ይገባል የምንለው አይደለም።

በዛ ውስጥ ማኅበረሰብ፣ የፖለቲካ መዋቅር፣ የእኛ የግንዛቤ ችግር እየፈጠራቸው ከመጡ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ፣ ሴትነትን የማነስ መነሻ፣ ጾታ የልዩነት ምክንያት የሚያደርግ ኅብረተሰብ ውስጥ ስለሆንንና እሱ ደግሞ ሴቶች ላይ ጫና የፈጠረ ነው። በዚህ ላይ ተጨማምሮ እድል ለመስጠት የመጣ ድንጋጌ ነው። እንጂ ሌሎች ሰብአዊ መብቶች የሌሉ ስለሆነ፣ ወይም በአንቀጽ 35 የተነሳ ለሴቶች ሰብአዊ መብት ይሰጣቸው ተብሎ የተቀመጠ አይደለም።

ግን ንዑስ ቁጥር አራት የሴቶችን የአካል ደኅንነት፣ የመኖር መብት የሚጋፉ የሆኑ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች፣ የሃይማኖት እምነት ወዘተ ጋር የተገናኙ ድርጊቶችን የማስቀረት ሕጋዊ ግዴታ መንግሥት ላይ አለ። ይህንን አስተዳደራዊ እርምጃ በመውሰድ ሊያስተካክለው ይገባል የሚል ነጥብ በተቀሩት ንዑስ ቁጥሮች ላይ የተቀመጠ ነው።

አስድዶ መድፈር ለምሳሌ ስንወስድ፣ የሚያመጣው ጉዳት ሥነልቦና ብቻ አይደለም። ወይም የአካል ጉዳት ብቻም ተብሎ የሚቀመጥ አይደል። ኢኮኖሚ ብቻ ነው ተብሎም አይጠቀስም። ሁሉም ዓይነት ጉዳቶች አሉት፣ በዋናነት ግን አካላዊ ጉዳቱ አብሮ ይመጣል። አንዳንዴ በርከት ያሉ ወንዶች አንዲትን ሴት ሲደፍሩ፣ የሕይወት ኅልፈትን ያስከትላል።

እና እነዚህን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት አንቀጽ 35 በልዩነት የተቀመጠ ቢሆን ኖሮ፣ ይህን መከላከል ያስችል ነበር ብለን የምናነሳ ከሆነ፣ ዋናው የሴቷ መብት የሚነሳው ከአንቀጽ 14 እስከ 18 በተቀመጡ ድንጋጌዎች ነው።

ግን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ሲኮን ከመደበኛ ስርዓት የወጡ ሰፋ ያለ የማስገደድና የመጫን፣ እንዲሁም ጫና የማሳደር ጉልበት መጠቀም ኃይሎችን ለመንግሥት የሚሰጥ ነው። ስለሆነም መንግሥት ወይም ኮማንድ ፖስት ብለን የምናስቀምጠው አካል፣ የሚወስዳቸወ እርምጃዎች ስርዓተ ጾታ ተኮር እንዲሆን አድርገን ካልሄድን አንቀጽ 35ን ለመጣስ ብዙ ክፍተቶች ይፈጥራል ብለን የምናነሳ ከሆነ ግን እስማማለሁ።

እንደ ማኅበረሰብ የሚወሰድ ከሆነ ግን፣ እንደውም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጅ ሁሉንም ሰው ይሰበስባል። ግን አንዳንድ ሴቶች ለጥቃት ተጋላጭ የሚሆኑባቸው ጉዳዮች አሉ። በዛ ላይ ጥቃት እንዳይፈጸም ለማድረግ እድል ይፈጥራል።

አሁን ማስፈጸሚያ ደንብ ይወጣልና በዛ አንቀጽ 35 በደንብ ሊተገበር በሚችልበት ሁኔታ ተተንትኖ የሆኑ ዓይነት ነጥቦች ሊቀመጡ ይገባል የሚለው ያስማማኛል። አሁን ባለንት ሁኔታ የቤት ውስጥ ጥቃትን ለመቀነስ ሕግ ምን ያህል ያግዛል?
እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲፈጠር የቤት ውስጥ ጥቃትን በተመለከተ ሁኔታው ከባድ ነው። በመደበኛ ሁኔታም ከባድ የሆነ፣ እንዲህ ያለ ጤነኛ ያልሆነ ሁኔታ ውስጥ የሚወሰዱ እርምጃዎች ያበዙታል [ጥቃቱን]። ምክንያቱም በፈለግሽው ሰዓት ጥቆማ (ሪፖርት) አይደረግም። ማስረጃ ሳይጠፋ የፍትህ አካላትና ጤና ተቋማት ምላሽ እንዲሰጥ ማድረግ ያስቸግራል። መጠለያዎች ለምሳሌ በቫይረሱ ምክንያት ከዚህ በላይ ሰው መቀበል አንችልም እያሉ ነው። አሁን ሌላ አማራጭ ተወሰደ እንጂ።
እናም ለቤት ውስጥ ጥቃት መባባስ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ መሆናችን የሚኖረው አስተዋጽኦ አለ። ለምሳሌ የሕዝብ አመጸ በሚነሳባቸው ጊዜ፣ በመደበኛው የሕግ አሠራር በሚታወጅ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ ያኔም ብዙ ሴት ነው አስገድዶ መደፈር ሲፈጸምባት፣ ሲትደፈር የነበረው (2006/7)። በተመሳሳይ ሁኔታ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀባቸው የተባሉ ክልሎች ላይ የባሰ የመጣ ስለሆነ፣ ካለፈ በኋላ ነገሮች ሲፈተሹ በዛን ወቅት የሞቱ ሴቶች እንዳሉ መረጃዎች አሳይተውናል።

ለመባስ ምክንያት ነው። ግን ይህን እንዴት ነው ማስቀረት የሚቻለው ነው። ምክንያቱም የቤት ውስጥ ጥቃት አብዛኛው ፈጻሚዎች የቅርብ ሰዎች ናቸው። በእርሱ ሥልጣን ስር ያለች የሚያሳድጋት ሴት ወይ የቤት ሠራተኛው ትሆናለች።

ብዙ ጊዜ ስለ ቤት ሠራተኛ አይወራም እንጂ፣ በጣም የሚበዘበዙ ሴቶች አሉ። ሴቶቹ ራሳቸው በሴቶች ላይ የሚፈጽሙትም በደል አለ። የታዛቢ ያለህ የሚባልበት ሁኔታም የለም። ይህ የከፋ ያደርገዋል።

መከላከያ ሊሆን የሚችለው አስቀድሞ እንዳነሳነው፣ ለሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 35 በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ይተገበራል የሚለውን በተመለከተ፣ ማስፈጸሚያ ደንብና መመሪያዎች ጋር ሊቀመጥ ይገባል የሚል እምነት አለኝ። ቀጣይ ላይ የሕገ መንግሥት መሻሻያ የማድረግ እድል የሚኖር ከሆነ፣ አንቀጽ 35 ከዚህ አንጻር መታየት አለበት ብዬ አስባለሁ።

በዚህ ወቅት ፍርድ ቤቶች ተዘግተዋል። ለተወሰኑ ክብደት ሲሰጥ ለተቀሩት ይቆየን ተብሏል። ይህስ እንዴት ይታለፋል?
ይህ ልዩ ክፍል ሥራውን ማቆም አለበት የሚል እምነት የለኝም። ለምሳሌ አዳጋች ነገሮች ሲፈጠሩ በዝግ ችሎት ጉዳይ ይታያል። ይህን ጉዳይ በድፍረት የማነሳው እንደሌሎች ገዳዮች ማስረጃ አቆይቶ፣ የዛሬ ወርና ኹለት ወር ምስክር አሰማለሁ የሚባልበት አይደለም። በመደበኛው የክርክር ሂደት እንኳ በጣም ማስረጃ ከሚባክንባቸውና እጅግ ከሚቆጩኝ የወንጀል ዓይነቶች አንደኛው ነው።

ስለዚህ ችሎቱ በምንም አጋጣሚ ቢሆን፣ የተፈራው ኮሮና ከሆነ፣ የጤና መጠበቂያና መከላከያ መንገዶቹ ለዳኛና ለጠበቃ፣ ለተከሳሽ ወይም ለግል ተበዳይ ወይም ለሥነ ልና ባለሞያዎች፣ ብቻ ችሎቱን የተመለከቱ ማንኛውም በተለየ ሁኔታ ተመቻችቶለት ችሎት መቀጠል ነበረበት የሚል እምነት አለኝ። አሁን ችሎቱን የተመለከተ መረጃ የለኝም። ያኔ ችሎት ይቁም ሲባል ግን ጉዳዩን አንስቼ ነበር። የእስረኛ መዝገቦች ብቻ ይታያሉ ሲባል፣ በከባድ ወንጀል አንደኛው የጾታ ጥቃት ነው።

ለተከሳሽ ባየንበት ልክ ግን ከተጎጂ አንጻር አይተነዋል ወይ በሚል ነው ያሳሁት። አሁን ባለኝ መረጃ አይሠራም። ግን ማቆም አለበት ብዬ አላምንም። ከምርመራ አኳያ ፖሊስ አሁንም ሥራውን 24 ሰዓት እየሠራ ነው። እሱ ችግር ነው ብዬ አልወስድም። እኛም ጋር አሁን በደረቅ ወንጀሎች ሥራ አላቆምንም፣ እየሠራን ነው።

ስለዚህ ሪፖርት ማድረግ ቢፈለግ መጥቶ መጠቆም ይቻላል። ትልቁ ችግር የሚነሳው በሕግ ምላሽ የሚሰጥበት ሁኔታ ይገደባል። ተጋላጭነቱ አለ ብዬ ስለማምን ነው። ችሎቱ አሁንም የሚራዘም ከሆነ ይህ ችሎት እንዲሠራ መደረግ አለበት። እንዳልኩት የዲ.ኤን.ኤ ውጤት ጠፊ ነው፣ የተለያዩ ተፈላጊ ናሙናዎች ይጠፋሉ። ጥቃት የሚፈጸምባቸው ሴቶች ደግሞ ከታችኛው ያሉ ስለሆኑ ማቆያ ቦታ ከሌለ አድራሻ ይጠፋል። እናም በፍትህ ምላሽ ለማግኘት ከባድ ያደርገዋል።

አንዳንዱ ነገር እንዲህ ሲከሰት ከጾታ ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን፣ ቀድመን እያነሳን ማሰብ ያስፈልጋል። ለዛ የሚሆን አሠራር ከስር ከስር እያመቻቸን የምንሄድ ካልሆነ፣ እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ሴቶች ግንባር ቀደም ተጎጂ መሆናቸው አይቀርም። የጎዳና ላይ ንግድ የሚሠሩ ቤታቸው ደግሞ ጥቃት የሚደርስባቸው ሴቶች ቀላል ስላልሆኑ ማለት ነው።

(ይህ ቃለመጠይቅ ተጠናቆ በተዘጋጀበት ሰዓት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዜዳንት መዓዛ አሸናፊ በትዊተር ገጻቸው ላይ ተከታዩን ሐሳብ አስፍረው ነበር። ‹‹የኮሮና ስርጭትን ለመከላከል ኅብረተሰቡ በቤት እንዲቆይ በሚደረግበት ወቅት በቤት ውስጥ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ሊጨምሩ እንደሚችሉ ታስቦ፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከሚያዩቸው ጥቂት አስቸኳይ ጉዳዮች መካከል የቤት ውስጥ ጥቃት ክስ እንዲሆን መመሪያ ተሰጥቷል።››)

ሴቶች ወደ ሥልጣን ማምጣት ሲመከር ነበር። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ሆነው መዓዛ አሸናፊ ወደ ፍርድ ቤት ሲመጡ፣ ቀድሞ በሕግ ባለሞያ ሴቶ ማኅበር የነበራቸውን እንቅስቃሴ በማየት በሴቶች ጉዳይ ላይ ትልቅ ተዐምር ተጠብቆ ነበር። የተጠበቀውን ያህል እንዳልተሠራ የሚናገሩ አሉ፣ ፕሬዝደንቷን የፍርድ ቤቶች የኖረ አሠራር ፈትኗቸዋል ወይም ጊዜ የሚወስድ ጉዳይ ነው?
ይጠበቃል። ተስፋ ይኖራል። በተለይ ጎልቶ የሚታወቅ አካባቢ ላይ የነበረ ሰው የሆነ ቦታ ሲሄድ በተመሳሳይ ይጠበቃል። እኔ የሚመስለኝ ኹለት ነገር ነው። በአንድ በኩል የተለየ እየተሠራ ያለ ነገር ስለሌለ ነው። ፍርድ ቤት አስቸጋሪ ስለሆነ አይደለም። እንደውም ፍርድ ቤት በዚህ ደረጃ ጥሩ ነው። ኹለቱንም ተቋማት በቅርበት ስለማውቃቸው ነው ይህን የምለው።

ከሴቶች ጥቃት ጋር ተያይዞ ጠቅላይ ዐቃቤ ብዙ ተሞክሮ ወስዶ ከሆነ ከፍርድ ቤት ነው የወሰደው። በዚህ ቀድሞ የነበሩ የፍርድ ቤት አመራሮች ሊመሰገኑ ነው የሚገባው። ለምሳሌ የተለየ ችሎት ቢወሰድ፣ ማንም ሳይለው ከሌለች አገራት ተሞክሮ ወስዶ፣ አንድ ልዩ ችሎት ልደታ ላይ የከፈተው ፍርድ ቤት በራሱ ተነሳሽነት ነው።

ኹለተኛ ይህ ችሎት ብቻውን መሆኑ ጫና እያመጣ ነው፣ በክፍለ ከተማ ያሉትን ሁሉንም ጉዳዮች አንድ ችሎት አሳይቶ ቶሎ ውሳኔ ማሰጠት የሚባሉ ብዙ ችግሮችን ማስቀረት አልቻለም ብለን ነበር። እንደ አቃቤ ሕግ ይህንን ጥያቄ ስናነሳ፣ የካን ጨምሮ 5 የሚሆኑ ቦታዎች ላይ ችሎቶቹን አስፍቷል።

ከወጣት ጥፋተኞች ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤት ችሎቶች አሉት። ስለዚህ ፍርድ ቤቱ አስቸጋሪ ቦታ ነው ብሎ ለማንሳት ይከብደኛል። በሴቶችና ሕጻናት ጥቃት ጋር በተያያዘ ማለት ነው።

እንደ ሰው ግን የሚሰማኝ አንድ ንጥል ሥራ ላይ መሥራትና በሰፊው ሥራ ውስጥ ስትገቢ፣ ለእያንዳንዱ የሚሰጠው ትኩረት ይለያያል። በዛ ውስጥ ሁኔታዎችም አስገዳጅነት አላቸው። አሁን ከከፍተኛ ጀምሮ ያሉ ሁሉም ፍርድ ቤቶች በእርሳቸው ላይ ነው ያለው። እነዚህ ሁሉ በየደረጃው የተለያዩ ችሎቶች አሉ። እነዚህን ሁሉ በጠቅላላ ይዘሽ ነው፣ በዛ ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ለይተሸ የምትሠሪው።

ምንአልባት የለይዋቸውን [የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት መዓዛ አሸናፊ] ነጥቦች አላውቅም። ግን ከነዛ ውስጥ ይህን እንደ አንድ ያልወሰዱት ከሆነ ችግር ነው የሚሆነው።

አሁን ላይ የጸጥታ አስከባሪዎች ሳይቀሩ በሴቶች ላይ ጥቃት የማድረሳቸው ዜና ይሰማል። አሁንም ወረርሽኙን ተከትሎ ተመሳሳይ ክስተቶች በተለያዩ አገራት ተሰምተዋል። ለዚህስ ሕጉ ምን ይለናል?
አንደኛ የወንጀል ሕጉ በተለየ ሁኔታ ከሙያ ወይም ከማኅበራዊ ኃላፊነት አንጻር ጥበቃ የማድረግ ኃላፊነት ያለው ሰው በሴቲቱ ወይም በሕጻን ላይ ጥቃት ፈጽሞ ከሆነ፣ እንደ መደበኛ ወይም ማንኛውንም ጥቃት እንደሚፈጽመው አይደለም የሚስተናገደው። ቅጣቱም በዛ ደረጃ አይደለም።

እንደ ምሳሌ አንቀጽ 624 ስንወስድ፣ ሆስፒታል ያለች በሐኪም፣ በመጠለያ ተቋም ውስጥ ያለች መጠለያውን በሚጠብቅ የበላይ ኃላፊ፣ ማረፊያ ቤት ያለች ደግሞ ፖሊስ ጥቃት ተፈጽሞባት ከሆነ፣ ከፍ ያለ ኃላፊነት ያለው ስለሆነ ቅጣቱም በዛ ደረጃ ከፍ ያለ እንደሚሆን ያስቀምጣል።

በወንጀል ሕጉ የቅጣት ማክበጃ ምክንያት ተደርገው ከሚወሰዱ ነገሮች መካከል አንደኛው እንደዚህ ዓይነት ኃላፊነት ላይ ያለ ሰው ጥቃቱን ፈጽሞ ከሆነ ነው። ስለዚህ በሱ የሚታይ ነው።

እኛ አገር ይህ ተግባራዊ እየሆነ ነው ወይ? ከሆነስ እንዲህ ባለ አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ብቻ ነው ወይ ተግባራዊ የሚሆነው ከተባለ፤ አይደለም። በፖሊስ ጥቃት የተፈጸመባቸውና ውሳኔ ያሰጠንባቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ግን ይብሳል። ያንን ለመጠበቅ አንደኛው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ፣ የሚወጣው አዋጅ አንድ ማእቀፍ ይዞ መውጣት የሚያስፈልገውም ለዚህ ነው።

እሱም ብቻ ሳይሆን እነዚህ ሰዎች፣ በተለይ ፖሊስ ቢሆን፣ ከዚህ ወቅት ጋር ተያይዞ አብዛኛው ሥልጣን የእነርሱ ስለሚሆን፣ እንደዛ ዓይነት ነገሮች ቢፈጠሩ ሊታይ የሚገባው በመደበኛ ፍርድ ቤት ነው ወይስ እነርሱ በሚዳኙበት በወታደራዊ ፍርድ ቤቶቻቸው ውስጥ ነው የሚለው፣ የሕግ ማዕቀፉ ምላሽ መስጠት አለበት። ይህም አዋጁን ለማስፈጸም የሚወጣው ደንብና መመሪያ የሚባለው ነው።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ በሥልጣን ላይ ሴቶች በብዛት ታይተዋል። ከታችስ የሕግ ጉዳዮች ላይ የታዩ ምን መሠረታዊ ለውጦችና የተሠራ ምን አዲስ ነገር አለ?
አዲስ የወጣ ሕግ አላውቅም። እያንዳንዱ ሕጎች በተገቢው መንገድ ተፈጻሚ መሆንና ምላሽ መስጠት እያስቻሉ ነው ወይ የሚለው ላይ ግን ጥናት እየተደረገበት እንደሆነ አውቃለሁ። አዲስ ሕግ ምንአልባት ከሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር የተገናኘ የተሻሻለበት አንዱ ነው። ከሕጻናት ጋር ተያይዞም ጉልበት ብዝበዛን በተመለከተ፣ ጉልበት ብዝበዛ በነበረው ሕግ ተሸፍኖ የነበረበት ሁኔታ አሻሚ ነበር። እሱን አሻሽሎ በአዲስ መልክ ያስተናገደው መሆኑ አውቃለሁ።
ከዛ ውጪ በአገሪቱ ያለው ሁኔታ በሂደት ላይ ያለ ስለሆነ፣ በሂደት ምንድን ነው የሚሆነው የሚለውን በሂደት የምናይ ነው የሚሆነው።

በቤት ውስጥ ጥቃት ከደረሰ በኋላ የሚሆነውን አንስተናል። ግን ቀድሞም ወደዛ ደረጃ እንዳይደርስ ምን ዓይነት ጥንቃቄ መውሰድ ይመከራል?
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከቤት ላይወጣ ይችላል። በተቻለ መጠን ቤት ውስጥ ለብቻ አለመሆን የተሻለ ነው። ኮሮና ለብቻችሁ ሁኑ ነው የሚለው (ሳቅ) ግን ይህኛው ብቻ አለመሆንን ይጠይቃል። እሱ አንደኛው ነው።

ሌላ ግን [ሴቶች] ወይ ዝም ነን አልያም ቁጣ የሞላን ነን። በኹለቱ ጽንፍ ላይ ነው ሴቶች ያለነው። በተቻለ መጠን የመነጋገሪያ ሰዓት መምረጥ፣ ባልና ሚስት ወይም ተመሳሳይ በሆነ ግንኙነት ውስጥ ያሉና በአንድ ቤት የሚኖሩ ከሆኑ፣ የማይግባቡበት ሰዓት ላይ ንግግር አለማብዛትና የተሻለ ሰዓት ላይ በምክንያታዊነት መነጋገርና ለመረዳዳት መሞከር፣ ይህንንም ባህል አድርጎ ማቆየት ይሻላል።

ምክንያቱም አሁን ብዙ ሰዓት ቤት ውስጥ ነን። ባልና ሚስት አሁን ቤት ውስጥ ሰፊ ሰዓት የሚቀመጡ ስለሆነ፣ በጣም መነጋገር አለ። ይህን ግንኙነት ራስን በመግዛት ማድረግና ቁጣና ንዴትን መቀነስ አስፈላጊ ነው።

እናም ዋናው የንግግር ሰዓት መመረጥ ቢችል። ሰው ስሜታዊ በሆነበት ሰዓት አለመነጋገር ነው። የአካላዊ አቅማችን የተለያየ ስለሆነ፣ በዛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል የሚል ምክር አለኝ። ይህንንም ለወንዶችም ጭምር የማስተላልፈው መልእክት ነው።

ከዛ ውጪ ሆትላይን (ጥቃት ማሳወቂያ/ሪፖርት ማድረጊያ) አገልግሎቶች አሉ። ከዚህ በላይ የከፋ እርምጃ ከመጣ ጎረቤት የሚባለው ዝም ማለት የለበትም። ‹‹ምን አገባኝ ባልና ሚስት ናቸው፣ ተቀጣሪና ሠራተኛ ናቸው፣ የቀጣሪና ሠራተኛ ግንኙነታቸው ምንአልባትም ሌላ ነገር የሚያስጠረጥር ነው፣ እና ፈልጋ ቢሆንስ›› ወዘተ የሚሉ ነገሮችን ብለን የምንተወውና ልንተወዉ የሚገባ ነገር አይደለም። አማራጭ በማጣት ውስጥ ዝም ማለት፣ መፈለግ ማለት አይደለም።

እና ነግ በእኔ የሚባል ነገርን እያሰቡ፣ የራስ ኃላፊነት አድርጎ ሁሏም ሴት ልጅ፣ እህት አድርጋ፣ የእኔ ወገን በሚል ስሜት ችግሩም ሁሉም ቤት የሚያንኳኳ መሆኑን በመውሰድ፣ በንቃት ነገሮችን መጠበቅና ለመተባበር ዝግጁ መሆን፣ ለማዳን ለማገዝ ከፍቶ ከሄደ ደግሞ ምስክር ለመሆን ዝግጁ መሆን አለበት፣ የቅርብ ጎረቤት።
ተጎጂዎችን በሚመለከት መረጃዎችን መያዝና የከፋ ሁኔታ ከሆነ ወዲያው ስልክ ተጠቅሞ መረጃዎችን በድምጽ ወይም በቴክስት መላክ አንዱ ራሳቸውን መከላከል የሚችሉበት መንገድ ነው ብዬ ነው የማስበው።

ከዚህ ቀደም 1918 ስፓኒሽ ፍሉ ሲከሰት ከዓለም ጦርነት ማብቃት ጋር ተያይዞ ለፌሚኒዝም እንቅስቃሴ በር ከፍቷል ይባላል። አሁን ባለው ዘመን ላይ የሚከሰተው ወረርሽኝስ ምን ዓይነት ተጽእኖ ይፈጥር ይሆን?
ኮሮና አሁን ላይ የትኛው ኅብረተሰብ ክፍል ላይ ጉዳት ያስከትላል የሚለውን ማወቅ አንችልም። ዝም ብዬ ተጋላጭነትን ሳስብ ግን ሴቶች ችግር ውስጥ የምንገባ ይመስለኛል። እርግዝና አንዱ የመጋለጥ እድልን ያሰፋል፣ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ሥራዎች ላይ መሥራታችን ለተጋላጭነት እድል የሚያሰፋ ነው። መደበኛ የሆነ ሥራ የማንሠራ መሆናችን ማለት ነው።

የጎዳና ላይ ንግድ ብዙ ሴቶች ነው ያምናየው። ከጉሊት ችርቻሮ ጀምሮ መንገድ ላይ ሽያጭ አለ። ጎዳና ንግድ ሲባል ሴተኛ አዳሪዎችን ብቻ ነው የምናስበው። ግን በርካታ ሥራዎችን የሚሠሩም አሉ። እናም እድሉ የሰፋ ነው። የ1918 ዓይነት እንቅስቃሴ ለማምጣት እድል ይሰጠናል ወይ፣ እርግጠኛ ሆኜ መናገር አልችልም።
ግን በየቀዳዳው የሚመጡ እድሎች አሉ። ኮሮና አሁን ለብዙ ነገሮች መጥፎ እንደሆነ ብቻ አድርጌ አላየውም። ለምሳሌ በአገራችን ንጽህና የመጨረሻ የወረደ አመለካከት ነበር የነበረን። አሁን ላይ ግን በየመንገዱ እጅ መታጠብ፣ ቆሻሻ የሚጣልበት ቦታ የተሰናዳ መሆኑ ሲታይ፣ ይህ በሽታ ባይመጣ ኖሮ አገሪቱ በቆሻሻ ላይ ያላት አቋም በዛው ሊቀጥል ይችል ነበር።

ይህ በጣም ትንሹ ጉዳይ ነው። ግን ደግሞ ተጽእኖውና ውጤቱ ትንሽ አይደለም። አሁን አመራር ላይ ያሉ ሴቶች ላይ ብዙ ይጠበቃል። ግን ያመጣልን ምን እድል አለ ስንል፣ በምጣኔ ሀብት አኳያ የለም እያልኩ በስርዓተ ጾታ እድል አለ ልል አልችልም።

ግን አንድ የሚታየኝ ጥሩ ነገር፣ የሴትነትና የስርዓተ ጾታ ጉዳይ የፖለቲካ እይታ ብቻ ይዞ የተንጠለጠለ ነው። እሱ እንዳይሆን ማድረግ ላይ፣ ሁሉም ማሞቂያው እንዳያደርገው፣ አቅም ላይ ሳይሠራ ሴት ብቻ የሚያስቆጥር ነው። እኛም ጋር በዛው የሚቀጥል ከሆነ የፖለቲካ አጀንዳ ብቻ ሆኖ ይቀጥላል። እድል ከሰጠን በዛ አንጻር እንዳይታይና በሁሉም ሚና ያለው መሆኑን ለማሳየት ይረዳል ብዬ አስባለሁ።

የቤት ውስጥ ጥቃት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ደሃ አገራት ብቻ ሳይሆን በሠለጠኑ እና አድገዋል በተባሉ አገራትም አሁን ላይ እየተስተዋለ ነው። የስርዓተ ፆታ እኩልነት የመማር ያለመማር ወይም የሥልጣኔ ጉዳይ አይደለም ማለት ነው?
ስለእኩልነት የምናነሳው ደሃና ሀብታም በመሆን አይደለም። ስለዚህ በዛ ላይ ልዩነት የለውም። ስለእኩልነት የምናወራው የተማረ ወይም ያልተማረ ኅብረተሰብ ውስጥ ስለሆንን አይደለም። ስለዚህ የትምህርትም ሆነ የሥልጣኑ ሁኔታ እኩልነት ላይ ለምናነሳው ነገር ልዩነት ያመጣል ብዬ በግሌ አላስብም። ግን መማርና ያደገ የሠለጠነ አገር ውስጥ መሆን፣ ለእኩልነት ጥያቄ ልትፈጥሪ የምትፈልጊው ጫና እና ክርክር ጉልበት እንዲኖረው ማድረግ ላይ አቅም ይሰጣል።

ባልተማርሽ ቁጥር ስለሴቶች ውክልና ስትጮኺ ብትውይ በብቃት መወዳደር ካልቻልሽ ዋጋ የለውም። የሆነ ጊዜ ላይ እንዳየነው ሳይሳካ ይቀራል። ይሄኔ ክርክር አታነሺም። ተጎዳሁ ብሎ ለመጮኽ ካልሆነ አቅም ኖሮሽ አትከራከሪም። የስርዓተ ፆታ አስፈላጊነትን ስናነሳ፣ በተግባር አንዲት ሴት ሴት በመሆኗ ብቻ ሊሟሉላት የሚገባ ጉዳዮችን በእቅድና በተጠና መንገድ እንዲሁም በሕግ እነዚህን ነገሮች አንስተሸ ምላሽ እንዲያገኙ መሥራት አለብኝ ስትይ፣ አገሪቱ የደሃ ደሃ ከሆነች ነገሩ ጩኸት ብቻ ይሆናል። እሱን ማሟላት አትችይም።

ክርክርሽ ‹ይገባኛል!› ከሆነ ባልሽበት ጊዜ የጠየቅሽውን እንድታገኚ ብቃት የለሽም። ወዲያው መሟላት አለበት ብለሽ ስታነሺ ለጠቅላላ ኅብረተሰቡ የሌለ ከሆነ ለአንቺም አይኖርም። ስለዚህ በማስፈጸምና በክርክር እውን ማድረግ ላይ እኩልነትን በተመለከተ ልዩነት አለ፤ የተማረና ያልተማረ በመሆን መካከል። ስለእኩልት ማውራት ግን የሠለጠነ አገርን አይጠብቅም።

ያ ማለት ግን የሠለጠነ አገር ሁሉ መቶ በመቶ የስርዓተ ፆታ እኩልነትን እውን አድርጓል ማለት አይደለም። ምክንያቱም ከብዙ አንጻር ስለሚታይ። የዴሞክራሲ አሠራር፣ የፖለቲካ አካሄድ ይወስነዋል። የማኅበረሰብ ግንዛቤም በጉዳዩ ላይ ይወስነዋል። እናም ማደግ ብቻውን እኩልነት አረጋግጠሻል አያስብልም።

ግን ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካን ብንወስድ፣ ደቡብ አፍሪካ የተማረ ሴትና ኢትዮጵያ የተማሩ ሴቶች ቁጥር እኩል አይሆንም። ኹለቱም ደሃ ሆነው በአንጻራዊነት ደቡብ አፍሪካ ከእኛ ትሻላለች። ስለዚህ በዚህ ላይ ለውጥና ልዩነት ሊኖር ይችላል።

ወረርሽኙ ሊያደርስ ከሚችለው ጉዳት አንጻር ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የሚባል ሌላ ሊጠቅሱት የሚችሉት ጉዳይ ካለ?
እነዚህ ድጋፍ የሚሰጡ ሰዎች፣ መንግሥትና ባለሀብቶች እንዲሁም በጎ አድራጊዎች ድጋፍ ሰጠን ሲሉ ይሰማል። ግን በወንጀል ተጎጂ የሆኑት ተረስተዋል። አሁን ሁሉም ሰው ወንጀል ስለፈጸሙ ሴቶችና ወንዶች ነው የሚያወራው። ግን የወንጀል ተጎጂ የሆኑ በየመጠለያው ያለማንም ድጋፍ ይገኛሉ። መንግሥታዊ ያልሆኑ መጠለያ ውስጥ ያሉም አሉ። በየግላቸው ተደብቀው የሚገኙና ቤተሰብ የሚያውቃቸውም እንደዛው።

እናም ለእነርሱ ምን ድጋፍ ይደረግ ለሚለው በመንግሥት መዋቅሩም በመንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማትም በጠቅላላ ማኅበረሰቡ የሚታይ ቢሆን ጥሩ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 75 ሚያዝያ 3 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here