የኮቪድ 19 ቀጣይ መዳረሻ የት ይሆን?

0
741

በአጭር ጊዜ ዓለምን በቁመቷ እና በስፋቷ አዳርሷታል። ከምሥራቅ የተነሳው ወረርሽኝ ምዕራብን ጎብኝቷል፣ ሰሜን እና ደቡብንም አልማረም። የዓለም ጤና ድርጅት ይህ ጽሑፍ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በ209 አገራት እና ግዛቶች ወረርሽኙ መዛመቱን አስታውቋል።

ወረርሽኙ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ያደረሰው ጉዳት እና ያሳየውን ፈጣን ስርጭትም ተከትሎ አዲስ ማለዳ ማተሚያ ቤት እስከ ገባችበት ሰዓት ድረስ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የዓለም ሕዝብ በወረርሽኙ ተጠቅቷል። ከ82 ሺሕ በላይ ሰዎችም ውድ ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከ300 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ደግሞ የሞት ሽረት ትግል አድርገው ትንቅንቁን በድል ተወጥተዋል።

ይሁን እንጂ አሁንም የወረርሽኙ ግስጋሴ በአንዳንድ አገራት ላይ እያሳደረ ያለው ጫና በተለይም ደግሞ በሰዎች ሕይወት ላይ ከፍተኛ ሞትን እያስከተለ ይገኛል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ወረርሽኙን በመቋቋም እና አስፈላጊውን ግብረ መልስ በመስጠት፣ ተቋርጠው የነበሩትን ኹሉንም እንቅስቃሴዎቿን በማስጀመር የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቿን ቻይና ጀምራለች።

በዋናነት በመጀመሪያ ደረጃ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ የተነሳባት የሁቤይ ግዛት መዲና ዉሃንም ከ11 ሳምንታት የመዘጋት ቆይታ በኋላ መጋቢት 29/2012 ወደ ሙሉ እንቅስቃሴዋ ተመልሳለች።

ኘዋሪዎቿም ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን የሚያሳውቅ ካርድ ይዘው ከቦታ ቦታ እንደልባቸው በናፈቃቸው ጎዳና ላይ ሽር እያሉ ነው። ይሁንና አሁንም ቢሆን ወረርሽኙ ዳግም እንዳያገረሽ ስጋቶች አሉ። ቫይረሱ የሚታይና የሚዳሰስ፣ የሚጨበጥም አይደለምና፣ አሁንም በአንድ ሰው ምክንያት ስርጭቱ ዳግም ሊቀሰቀስ ስለሚችል የቻይና መንግሥት ጥንቃቄ እንዳይቀር ማሳሰባቸው አልቀረም።

ቻይና የወረርሽኙ መጠንሰሻ አገር ብትሆንም ኮቪድ 19 ያስከተለባት ጉዳት ከአውሮፓ አገራት እና ከአሜሪካ አንጻር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በተለይም ደግሞ የሟቾች ቁጥር እንደ ዓለም ጤና ድርጅት መሰረት 81 ሺሕ የሚሻገሩ ዜጎቿ ተይዘው 77 ሺሕ የሚልቁት አገግመው ወደ ቤታቸው የሄዱ ሲሆን፣ ሦስት ሺሕ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ይህ ግን በየቀኑ በአውሮፓ እና በአሜሪካ ከሚረግፈው የሰው ልጅ ቁጥር ጋር ሲነጻጸር እጅጉን ያነሰ እንደሆነ ቁጥሮች ያሳያሉ።

ኮቪድ 19 በአውሮፓዊቷ ኢጣሊያ ከባድ ጫና ፈጥሮ የቆየ ሲሆን፣ አሁንም ድረስ በየእለቱ የሚመዘገበው የሟቾች ቁጥር በአንጻራዊነት እየቀነሰ ነው። ሆኖም በወረርሽኙ የሚጠቃው የሰው ቁጥር አሁንም ማሻቀቡን ቀጥሏል። በዚህም መሰረት በኢጣሊያ ወረርሽኙ ከገባ ጀምሮ ይህ ጽሑፍ ማተሚያ ቤት እስከገባበት ሰዓት ድረስ 135 ሺሕ በላይ ሰዎች በቫይረሱ እንደተጠቁ የተገለጸ ሲሆን፣ ከ17 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ውድ ሕይወታቸውን አጥተዋል። ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛው ሞት የተመዘገበባት አገር አድርጓታል።

በኢጣሊያ የታየው የሟቾች ቁጥር እና በየቀኑ የሚመዘገበው የሞት መጠን በተመሳሳይ ሁኔታ 141 ሺሕ በላይ ታማሚዎችን ወደ አስመዘገበችው ስፔን እያመራ ይመስላል። አዲስ ማለዳ ለህትመት እስከበቃችበት ድረስ ስፔን ከ14 ሺሕ በላይ ዜጎቿ ላይመለሱ አሸልበዋል። በኢጣሊያ እና በስፔን የታየው በወረርሽኙ የመጠቃት እና አዳዲስ የበሽታው ተጠቂዎች ቁጥር ቀንሷል።

ይሁን እንጂ አዳዲስ ግኝቶች ከመጨመራቸው ጋር ተያይዞ በርካታ ሕመምተኞችን በማስመዝገብ ግንባር ቀደም የሆነችው አገር አሜሪካ ሆናለች። 400 ሺሕ በላይ የበሽተኞች ቁጥር ያሉባት አሜሪካ፣ ከ12 ሺሕ 800 በላይ ዜጎቿን አጥታለች። በየቀኑ የሚመዘገበው የሟቾች ቁጥርም እጅግ እየከፋ እንደሆነ በርካታ የዓለም መገናኛ ብዙኀን እየተቀባበሉት የሚገኘው ጉዳይ ሆኗል።

በአገረ አሜሪካ በቀን ከ800 በላይ ሰዎች አሁንም ሕይወታቸውን እያጡ እንደሚገኙ ተገልጿል። ይህ ደግሞ በቀጣይ ወደ ከፍተኛ የሰዎች ሞት ቁጥር ይገሰግሳል የሚል አዝማሚያ እንዳለ ተጠቁሟል። አሜሪካ በመጋቢት 29/2012 ባስታወቀችው መሰረት 1 ሺሕ 700 ዜጎቿን በ24 ሰዓታት ውስጥ ማጣቷን አስታውቃለች። በታላላቅ የአገሪቱ የሥራ ኃላፊዎች ሳይቀር የሟቾችን ቁጥር ከመቶ እስከ ኹለት መቶ አርባ ሺሕ እንደሚደርስ የተሰላ ሲሆን፣ በዚህ ቁጥርም ከተገታ ግን እንደ ትልቅ ስኬት እንደሚቆጠር ተጠቁሟል።

አፍሪካ ከ12 ሺሕ በላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን በ52 አገራት ውስጥ ይዛ ያለች ሲሆን፣ 570 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ 1 ሺሕ 486 የሚሆኑት ደግሞ አገግመው ወጥተዋል። የወረርሽኙ በትር እንደ አጀማመሩ ሳይሆን እያደር እየከበዳት ይሄዳል የሚል ግምት አሁንም እየተሰጠ ይገኛል።

ይህ ቅብብል ይቀጥል ይሆን ወይስ እዚህ ላይ ይቆማል የሚለውም ሊገመት የማይችል ጉዳይ ሆኗል። ከቻይና ጣልያን፣ ከጣልያን ስፔን፣ ከስፔን አሜሪካ ሲቀባበሉት የታየ ከመሆኑ ላይ ጀርመን እና ፈረንሳይ ቅብብሉን ይከተላሉ የሚል ስጋትም ደጋግሞ ይነሳል። የሚሆነውን መገመት የሚቻል ባይሆንም፣ ከመጀመሪያው ወራትና ሳምንታት በኋላ አገራት የተሻለ ግንዛቤ በማግኘት ጥንቃቄ ማድረጋቸውና የታዘዙትን መተግበራቸው፣ ‹ዋ ብለው በአሳር› እንዳይማሩ እንደረዳቸውም ባለሞያዎች ያስረዳሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 75 ሚያዝያ 3 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here