ወረርሽኞች እና የሴቷ ሸክም

0
596

በተለያየ ጊጊ ዓለማችን ያስተናገደቻቸው ወረርሽኞች በተለያዩ የዓለም ገጾች ላይ የተለያየ ተጽእኖ ማሳረፋቸው ግልጽ ነው። በዚህም ታድያ በሴቶች ላይ የሚኖራው ተጽእኖ ደግሞ በሕይወታቸው የሚበረታ እንደሆነ በተለያየ ጊዜ ይነገራል። ሕሊና ብርሃኑም ይህን ጉዳይ በማንሳት፣ ወረርሽኞች በማኅበራዊ ሕይወት ከሚያሳድሩት ጫና ላይ በሴቶች ትከሻና ጫንቃ ላይ የሚያኖሯቸውን ክብደቶች አስቃኝተዋል።

ኮቪድ-19 ወይም ኮሮና በመባል የሚታወቀው ወረረሽኝ ዓለማችንን ከሌላው ጊዜ በተለየ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ እየጣለ ያለ የማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እርከኖችን ሳይለይ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል እያጠቃ የሚገኝ ቫይረስ ነው። ይህን ስንል ታድያ በስርጭት ደረጃ እነዚህ እርከኖችን አይለይ እንጂ በእልቂትና በኑሮ ቀውስ ላይ የማኅበራዊ ማንነትና የኢኮኖሚ ጥንካሬ ፋይዳ የለውም ማለት አይደለም።

ፆታን ጨምሮ ዘር፣ ቀለም፣ የትምህርት ደረጃ፣ የገቢ ምንጭና የመኖሪያ አካባቢ ቫይረሱ ለሚኖረው ተፅእኖ አይነተኛ ሚና ይጫወታል። ስለዚህም እነዚህን የማኅበራዊ እርከኖች ጠንቅቆ መመርመር ቫይረሱ ሊያስከትል የሚችለው ክፉኛ እልቂትና ተጽዕኖ ለመገታት አንደኛው መንገድ ነው። በዛሬ ጽሑፌም በስርዓተ ፆታ መነፅር ቫይረሱ ሴቶች ላይ የሚያሳድረውን ልዩ ተጽዕኖ የምመለከት ይሆናል።

እዚህ ጋር መታወቅ ያለበት፤ ስርዓተ ፆታ ማለት ሴቶች ማለት አይደለም። ስርዓተ ፆታ ማለት ተፈጥሯዊ የፆታ ልዩነትን ተከትሎ የሚመጣ በሴቶችና በወንዶች መካከል ያለ የኃይልና መብቶች መበላለጥን እንዲሁም የድርሻ ወይም ሚና ድልድልን በአድሎ የሚወስን ስርዓተ ማኅበር ነው።

ይህ ስርዓተ ማኅበርም በኹለቱም ፆታዎች ላይ የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲኖረው፣ ሴቶች ላይ ለሚኖሩ ጅምላ ፍረጃና የኑሮ ገደቦች ግን በንፅፅር ከፍተኛ የሆነ ሚና አለው። በዚህም ምክንያት ስርዓተ ፆታ ትንተናና ጥናት ሴቶች የተጣለባቸውን ማኅበራዊ ሸክም ለማጋለጥ በተደጋጋሚ የምንጠቀምበት ሁነኛ መንጽርና የአሰራር መንገድ ሆኖ እናገኘዋለን።

ኮቪድ-19 እና ፆታ
በቅድሚያ በፆታ ደረጃ የቫይረሱን ጉዳይ እንመልከት። በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወንዶች በቫይረሱ ምክንያት እየሞቱ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በተለይም ላንሰንት (Lancet) የተባለው ተዓማኒ ሳይንሳዊ የጥናት መጽሔት (ጆርናል) ላይ የታተሙ የምርምር ውጤቶች እንደሚያሳዩት፣ ወንዶች በቫይረሱ ከፍተኛ እልቂት እየደረሰባቸው ያለው በአኗኗር ዘይቤና በሥነ ሕይወታዊ (Biological) ምክንያቶች እንደሆነ ይገልጻሉ።

ለምሳሌ፤ ሴቶች ባላቸው የኤስትሮጅን ሆርሞን መጠንና የኤክስ-ክሮሞዞሞች ምክንያት በሽታን የመከላከል አቅማቸው ከፍ ያለ መሆኑን እንደ አንድ ምክንያት ያስቀምጣሉ። በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ ከሴቶች ይልቅ ወንዶች የበለጠ ሲጋራ አጫሽ መሆናቸውና ይህም ለመተንፈሻ አካላት ችግሮች ተጋላጭ እንደሚያደርጋቸው ጠቁመዋል። እንዲሁም እንደ የደም ግፊት፣ የልብና ስር የሰደደ የሳንባ በሽታ የመሳሰሉት የጤና እክሎች በብዛት በወንዶች ላይ የሚስተዋሉ ሲሆን፣ ለፈጣን ስርጭትና ሞት ትልቁን ድርሻም እንደሚይዙ ይገልጻሉ።

ይህም በመሆኑ ምንም እንኳ እንደ ደቡብ ኮሪያ ባሉ አገራት በቫይረሱ የተያዙ ሴቶች ቁጥር ከፍ ያለ ቢሆንም፣ ወንዶች የበለጠ እየሞቱ እንደሆነ ይታያል።
ታዲያ እነዚህ የሳይንስ ውጤቶች ወደ ስርዓተ ፆታ እይታቸው ሲመጡ፣ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ወንዶች በአሁኑ ሰዓት በበሽታው ከተያዙት ቁጥራቸው የሚበልጥ ቢሆንም ሴቶች በቀጣይነት ለቫይረሱ ተጋላጭነታቸውና ከዚህ ጋር ተያይዘው በሚመጡ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ከፍተኛ ተጎጂ መሆናቸው አይቀሬ ነው ሲሉ ይጠቁማሉ።

ለምን? ወደሚለው ስንመጣ ከዚህ ቀደም የነበሩ ወረርሽኞችን እንደ መነሻ በመውሰድ፤ ሴቶች ያለባቸው ማኅበራዊ ኃላፊነቶች ከቅድመ መከላከል ማለትም የቤተሰብ ጤናን መጠበቅ፣ የቤት መቀመጥ ጥሪ ተከትሎ የሚመጡ ዝግጅቶች እስከ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን መንከባከብ ያሉ ማኅበራዊና ሙያዊ ግዴታዎችን ይፈትሻሉ።
በምዕራብ አፍሪካ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015-2016 የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያት በፓስፊክ ውቅያኖስ፣ እስያ፣ አሜሪካ እና አፍሪካ ውስጥ የተመዘገበው ዚካ ቫይረስ፣ በተጨማሪም ኮሮና ቫይረስ በቅድሚያ ያጠቃቸው አገራትን ሁኔታ በመመልከት ከስር የምዘረዝራቸው ምክንያቶች ቫይረሱ ሴቶች ላይ የሚኖረውን ልዩ ተጽዕኖ ያሳያሉ።

ሴቶችና የጤናው ዘርፍ
የዓለማቀፉ የጤና ድርጅት ባወጣው መረጃ በመቶ አራት አገራት ውስጥ ሰባ በመቶ የሚሆኑት የጤና እና ማኅበራዊ እንክብካቤ ሠራተኞች ሴቶች ሲሆኑ ኮቪድ-19 ለማጥፋት በሚደረገው ውጊያ እንዲሁም በሽተኞች ቅድሚያ እርዳታን በሚሹበት የጤና ማእከላት ግንባር ላይ ግንባር ቀደም መልስ ሰጪና ተንከባካቢ ናቸው። ይህም ከሙያው ባህሪ አንፃር ለበሽታው ተጋላጭነታቸውን ከመጨመሩ በላይ በሥራው አጨናናቂ ባህርይ ምክንያት ሥነልቦናዊ ተጽዕኖውም ከፍ ያለ ነው።
ታዲያ የእነዚህን ሕይወታችንን ለመታደግ ደፋ ቀና የሚሉ ባለሙያዎችን ጥያቄና ፍላጎት ለመረዳት ወንዳዊ ፍላጎትን በመደበኛ ወይም በተለምዶአዊ ዐይን ከሚያየው አሰራር ወጣ ብሎ የሴቶችን ሁናቴ ያገናዘበ የስርዓተ ፆታዊ እይታን ግድ ይላል።

እንደ ምሳሌ ያህል ወረርሽኙ ቻይና ውስጥ በተስፋፋበት ወቅት በአገሪቱ በብዛት ተሰማርተው የነበሩ የጤና ባለሙያዎች የተሰራላቸው ልብስ ሽንት ቤት ለመመላለስ ስለማያመች የአዋቂ ዳይፐር (የሽንት ጨርቅ) እንዲያደርጉ ተገደው ነበር። ይህም ለሽንት መፍትሔ ቢሆንም ለወር አበባ ግን ሊያገለግላቸው አይችልም።

እናም ለብቻ የንጽህና መጠበቂያ እንዲቀርብላቸው ቢጠይቁም እንደ ቅንጦት ተቆጥሮባቸው፣ የአገሪቱ ሕዝብ በማኅበራዊ ሚድያ ጥሪ ከማሰማቱ በፊት በተደጋጋሚ ጥያቄያቸው ውድቅ ሆኖ ነበር። የሴቶችን ፍላጎት ገሸሽ ያደረገ አሰራር ማለት ይህ አይደለምን?

የሴቶች ጤና
ስለ ሴቶች ጤና ሲነሳ አሁንም ከቀድሞ የወረርሽኝ መረጃዎች ማጣቀስ ግድ ይላል። ኢቦላ እና ዚካ ወረርሽኝ ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ የጤና ስርዓቶች እንዲህ ያሉ አስጨናቂ ጉዳዮች ሲያጋጥማቸው ከዚህ ቀደም አንገብጋቢ የነበሩ ጥያቄዎችን ገሸሽ ማድረጋቸው አይቀሬ ነው። ይህም ሁሉ ማኅበረሰብ ላይ የራሱ የሆነ ተጽዕኖ ቢኖረውም የማያቋርጥ ተፈጥሮአዊ የጤና ፍላጎት ያላቸው ሴቶች ላይ ግን መባሱ ግድ ነው።

ለምሳሌ ያህል፦ የእርግዝናና የወሊድ መቆጣጠሪያ ክትትሎችን ጨምሮ ያሉ ወሲባዊና የሥነተዋልዶ ጤና ፍላጎቶች እንዲሁም እንደ አፍሪካ ባሉ አኅጉራት በብዛት ሴቶችን የሚያጠቃው የኤች አይ ቪ ኤድስ ሕክምና ክትትል የሚጠቀሱ ይሆናል።

በሴቶች እና ሴት ሕጻናት ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃት
ፆታዊ ጥቃት በዓለም በከፍተኛ ደረጃና በተደጋጋሚ የሚነሳ የሴቶች ጤናና የሰብአዊ መብት ጉዳይ ነው። ይህን ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት በተለይም በቤት ውስጥ በተደጋጋሚ ሴቶች ላይ የሚከሰት ሲሆን፣ እንደ አሁኑ ያለ ወረርሽኝን ጨምሮ የተለያዩ ማኅበራዊ ቀውሶች ብቅ ሲሉ ከቀድሞ በበዛ መልኩ ይስተዋላል። ይህ ጥቃት እነዚህ ክስተቶችን ተከትሎ የሚወለድ ሳይሆን ቀድሞውን የነበረ የጭቆና እሳቤን አስታኮ በእጥፍ ድርብ በእነዚህ ጊዜያት የሚገለጥ ነው።

ቫይረሱ በቅድሚያ የታየባቸውንና ተከትሎም ከቤት አትውጡ የሚል ማስጠንቀቂያ ያወጁ አገራትን ቻይና እና ፈረንሳይን እንደምሳሌ ብንወስድ፤ በቻይና የቤት ውስጥ ጥቃት ጥቆማ በሦስት እጥፍ ማደጉንና ፈረንሳይም ቢሆን ሠላሳ በመቶ መጨመሩ ታይቷል/ተሰምቷል።

ይህ ሲሆን ሁሉም ሴቶች በግልፅ የመጠቆም እድሉን ያገኛሉ ማለት ስላልሆነ፣ እንደፈረንሳይ ያሉ አገራት ጥቆማ በምልክትና በኮድ የሚሰጥበትን ስርዓት እንዲዘረጉም ግድ ብሏል። ይህ ጥቃት በቤት ውስጥ የሚውሉ ሴት ሕጻናት ላይም በሚያውቁትና አብረው ከሚኖሩት ሰው በተደጋጋሚ ሲመጣ ተስተውሏል። አብዛኛው ጊዜ ሕጻናት የሚደርስባቸውን ችግር ለአስተማሪዎቻቸው አልያም ለሚቀርቡት ጎረቤት፣ ዘመድ ቢናገሩም ቤት ውስጥ መቀመጣቸው የሚሹትን እርዳታ እንዳያገኙ አድርጓቸዋል።

ኢኮኖሚያዊ ተመን ያልወጣለት ጾተኛ የቤት ውስጥ ሥራ ክፍፍልና ጫና
በጋብቻ ውስጥም ይሁን በሌሎች የግንኙነት መስመሮች፣ የሥነ ተዋልዶ ሚና ላይ ተንተርሶ የሚመጣ ፆተኛ የሆነ የቤት ውስጥ የሥራ ክፍፍል በስርዓተ ፆታና ወረርሽኞች ጥናት ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። ይህም የወላጅነት ኃላፊነትን ጨምሮ፣ ቤተሰብ ውስጥ ያሉና በእድሜያቸው የገፉ አልያም በተለያዩ የጤና እክሎች ምክንያት እንክብካቤን የሚሹ ግለሰቦችን መከታተል ቤት ውስጥ በሚቀመጡ ሴቶች ላይ ስለሚወድቅ ነው።

በሌላ ጊዜ በትምህርት ቤትና በተመላላሽ ባለሙያዎች የሚሸፈኑ ሥራዎች ቤት ውስጥ የመቀመጥ ጥሪን ተከትሎ በአብዛኛው ቤተሰብ ውስጥ እናት፣ ሚስት እንዲሁም ሴት ልጆች ላይ ይጣላል። ይህም ሲሆን ከቤት ሆኖ የውጭ ሥራን መሥራት ለሴቶች የበለጠ ከባድ ከመሆኑም በላይ፣ ቤት ውስጥ የሚሠሩትንም ጫናውን ከፍ ያደርግባቸዋል።

ሴቶችና ኢኮኖሚ
ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው የሥራ ዘርፎች ማለትም የእለት ተከፋዮች፣ አነስተኛ የንግድ ሥራዎች እንዲሁም በመስተንግዶ፣ ፅዳትና እንክብካቤ ላይ ሴቶች ከፍተኛ ተሳትፎ አላቸው። ለምሳሌ ያህል፡ በቤት ውስጥ ሠራተኝነት የተሰማሩ ሴቶችን የገቢ ምንጭ ከማሳጣት ጀምሮ በቤት ውስጥ አብረው የሚኖሩትን ደግሞ በአሰሪዎቻቸው የሚደርስባቸውን ጭቆና ተቀብለው እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል።

ሰሞኑን ከተለያዩ አረብ አገራት የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በአብዛኛው በቤት ውስጥ ሠራተኝነት የተሰማሩ በተለይ የተሟላ ሰነዶች የሌላቸው ስደተኛ ሴቶች ሕይወት እጅጉን ጫና ውሰጥ ይገባል።

ሴቶች መደበኛ ባልሆኑ የሥራ ዘርፎች ላይ በብዛት ተሰማርተው ይገኛሉ። ይህም ማለት ሥራቸው ከቤት ውስጥ የሚሠራ ባለመሆኑና ከብዙዎችም ጋር ንክኪ ስለሚኖራቸው፣ በመንግሥት ደረጃ የሚነገሩ የጥንቃቄ መረጃዎችን ሙሉ በሙሉ የመቀበል አቅሙና የኑሮ ሁኔታ የላቸውም። አንገብጋቢ የኑሮ ጥያቄዎችም ስለሚኖራቸው በልተው ለማደር በሚል የሚተላለፉትን የጥንቃቄ መልእክቶች ችላ የማለት ግዴታ ውስጥ ይገባሉ።

በመንግሥት ግዴታዎች የሚጣልበት ሁኔታ ሲፈጠር በቤት ወስጥ የሆኑና የሚበላ የታጣ ጊዜም ሴቶች በጥቂቱ እንደሚበሉና አልያም በቤተሰባዊ መስዕዋትነት ስሜት ሙሉ ለሙሉ አለመብላትን እንደ አማራጭ እንዲወስዱ እንደሚገደዱ ብዙ ጥናቶች ያሳያሉ። ይህም በሽታን የመቋቋም ተፈጥሮአዊ ሁናቴአቸውን በከፍተኛ ደረጃ በመሸርሸር ለበሽታዎች ቀድሞ ተጋላጭ ያደርጋቸዋል።

በአጠቃላይ ካለፉት ወረርሽኞች የተገኙ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት፣ የስርዓተ ፆታ እይታዎች ከቅደመ ዝግጅት ጀምሮ ቢካተቱ የጤና ምላሾች ሙሉዕነትንና እኩልነት ለማረጋገጥ ቁልፍ ቦታ አላቸው። ከዚህ በተጨማሪ ስለ ቫይረሱ የሚደረጉ ውይይቶችና ጥሪዎች የሴቶችን ተሳትፎና ድምፅ፣ የሐሳብም ተሰሚነት ያማከሉ ካልሆነ ከዚህ ቀደም እንዳየነው የሴቶችን ጤንነት በበለጠ የሚጎዱና ፍላጎታቸውን የሚሸራርፉ ውሳኔዎች መወሰዳቸው አይቀሬ ነው።

እናም የስርዓተ ፆታ እይታ አገሪቱ ለሚኖሯት ውሳኔዎች ውጤታማነት አይነተኛ ሚና ይጫወታል። ይህ እይታና የእኩልነት በጤናና ሰላም ጊዜ ብቻ የምናነሳው የምቾት ሸቀጥ ሳይሆን፣ ለተጨባጭ ችግሮችና ለእለት ተእለት ማኅበራዊ ደኅንነት ቁልፍ የሆነ የአሰራር መንገድ ነው። ይታሰብበት!!
ሕሊና ብርሃኑ የሥርዓተ-ፆታና የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ፣ በአድራሻቸው bhilina.degefa@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 75 ሚያዝያ 3 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here