ከአትክልት ተራ ወደ ጃን ሜዳ የተዛውሩ ነጋዴዎች እንግልት እየደረሰባቸው ነው

0
814

የኮሮና ኮቪድ 19 ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እና የሰዎች ጥግግትን ለመቀነስ ከአትክልት ተራ ተነስተው ወደ ጃን ሜዳ የተዛወሩ የአትክልት እና የአሳ ነጋዴዎች የሚሠሩበት ቦታ ሳይመቻች ከቦታቸው በመነሳታቸው እየተንገላቱና ንብረታቸው ከጥቅም ውጪ እየሆነባቸው ለኪሳራ እየተዳረጉ መሆኑን አስታወቁ።

ማክሰኞ፤ መጋቢት 29/2012 ማለዳ ግብይታቸውን ለማከናወን ሱቃቸውን ከፍተው በሥራ ላይ እንዳሉ ድንገት በፖሊስ ተደብድበዉ ንብረታቸውን ጥለው ከቦታው ላይ እንዲነሱ መደረጋቸውን ብዛት ያላቸው ነጋዴዎች ቅሬታቸዉን ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰራጨ የሚገኘው ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በዋነኛነት ማኅበራዊ ጥግግትን መቀነስ መፍትሔ በመሆኑ፣ የገበያ ስፍራው ሰፋ ወዳለ እና አካላዊ ንክኪን ሊቀንስ ይችላል ወደተባለው ጃን ሜዳ ተዛውሯል።

ይሁን እንጂ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውሳኔን ተከትሎ በቦታው ላይ የነበረው የአትክልት ግብይት ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ ወደ ጃን ሜዳ ቢዘዋወርም፣ ነጋዴዎች ለመሥራት የሚመች ሁኔታ እንደሌለ እና የመሥሪያ ቦታ ተለክቶ እንዳልተከፋፈሉ አዲስ ማለዳ ታዝባለች። በጃን ሜዳ ለመሥራት ሳይዘጋጁ በመነሳታቸውም እየተንገላቱ እንደሆነ ነጋዴዎቹ ገልጸዋል።

የአትክልት ነጋዴው ተስፋዬ በርሔ ‹‹ከአትክልት ተራ የተነሳነው በጃን ሜዳ ለመሥራት የሚያስችል ዝግጅት ሳናደርግ ነው። በመሆኑም ይህ ቦታ ሳይሠራ መዘጋቱ በእጄ ላይ ያለው አራት መኪና አትክልት መሸጫ አጥቼ፣ አንዱን መኪና አውጥቼ እላዩ ላይ ለመሸጥ ተገድጃለሁ። በተለይ ቲማቲሙ ከአንድ ቀን ካለፈ መጣል ነው ያለኝ እድል›› ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

ከነጋዴዎቹ በተጨማሪ አትክልት ተራ በመዘጋቱ ወደ ጃን ሜዳ የአትክልት ግብይቶችን ለማከናወን የሄዱ አትክልት ገዥዎች የሚፈልጉትን የአትክልት አይነት እንዳላገኙ እና በቦታው ላይ ያሉት አትክልት ሻጮች ከሦስት እንደማይበልጡ ተናግረዋል። አትክልት ገብይቱ እንደልብ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞም ዋጋ ጭምሪ በሽንኩርት ላይ መታየቱንም ጠቅሰዋል።

አዲስ ማለዳ በቦታው ላይ ያገኘቻቸው ሸማች ወንድወሰን ተገኝ ጃን ሜዳ እንደ አትክልት ተራ በአትክልት ምርቶች ሞልቶ እንደሚገኘው ለማግኘት አስበው ቢሄዱም፣ እንደጠበቁት መሆኑ ቀርቶ ጃን ሜዳ ከሰው ውጭ የአትክልት ክምችትና ግብይት እንደሌለ ተናግረዋል። ወንድወሰን አክለውም በተንጣለለው ጃን ሜዳ ሦስት ሽንኩርት የሚሸጡ ነጋዴዎችን አግኝተው አማራጭ በሌለበት ባለፈው ሳምንት አንድ ኪሎ ሽንኩርት በ13 ብር እንደገዙ ያስታውሳሉ። ጃን ሜዳ ሽንኩርት ኪሎ 18 ብር ገዝተው መመለሳቸውን እና ከአንድ ኪሎ የአምስት ብር ጭማሪ መታየቱንም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ሌላኛው የአትክልት ነጋዴ ሰይፉ ገብርሚካኤል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ችግሩ የአትክልት ገብያውን ወደ ጃን ሜዳ ማዛወሩ ሳይሆን ነጋዴዉ ለመገበያየት የሚያስችል በቂ ዝግጅት በቦታው ላይ ሳያደርግ መዘጋቱ፣ ከገበሬ ተቀብለው ያስገቡት አትክልት መሸጫ ቦታ ባለማዘጋጀታቸው መኪና ላይ እንዳለ እየተበላሸብን ነው ሲሉ ቅሬታቸውን አስምተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ ነጋዴዎቹ ያቀረቡት ቅሬታ ጊዜውን መሰረት ያደረገ እንዳልሆነና ተገቢ ያልሆነ ቅሬታ እንደሆነ ገልጾ፣ ለነጋዴዎቹ እንዲዘጋጁ እና ኅብረተሰቡ እንዲሰማ አንድ ሳምንት ጊዜ ሰጥተናል። ከዚህ በላይ ከተማ አስተዳደሩ ሊሰጠው የሚችለው ጊዜ የለም ብለዋል። የአትክልት መገበያያ ቦታውን ከተማ አስተዳደሩ ወደ ጃን ሜዳ ያዘዋወረው ለነጋዴዎች ደኅንነት ሲባል ስለሆነ፣ ቅሬታ ሊያነሱ አይገባቸውም ብሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 75 ሚያዝያ 3 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here