• ሥራ ሲጀምር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ብረታ ብረት ፋብሪካ ይሆናል
ፖስኮ የተሰኘ እና መቀመጫውን በደቡብ ኮሪያ ያደረገ ብረታ ብረት ፋብሪካ በኢትዮጵያ ሥራ ለመጀመር የአዋጭነት ጥናት ሠርቶ ማጠናቀቁ ተገለጸ። ኩባንያው በኢትዮጵያ በሚጀምረው የብረታ ብረት ፋብሪካ ከዚህ ቀደም በብረታ ብረት ፋብሪካዎች ይሠራ የነበረውን የብረት ምርት ማምረቻ ግብዓት እዚሁ ማምረት ይጀምራል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ብረታ ብረት ልማት ኢንቲትዮት ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው፣ ኩባንያው እስከዛሬ ከነበረው የብረታ ብረት ዘርፍ የአፈር ማዕድን (አይረን ኦር) ከውጭ አገር በማስመጣት ነገር ግን የመጨረሻ ደረጃው ላይ በማድረስ ሂደቱ በአገር ውስጥ እንዲያልቅ የሚደርግ ነው ተብሏል። ከዚህ ቀደም በአገር ውስጥ የሚገኙ የብረታ ብረት አምራቾች ለተለያዩ ምርቶች የሚሆኑ የብረት ጥሬ ዕቃዎችን (ቢሌት) ወደ አገር ውስጥ በማስገባት የምርት ሂደቶችን ያካሂዱ እንደነበር የኢንስቲትዩቱ ፕላን ዳይሬክተር ጥላሁን አባይ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ጥላሁን አያይዘው ፖስኮ ኩባንያ አንድ ደረጃ መለስ ብሎ ሂደቱን ወደ ኋላ በማስኬድ የማምረት ደረጃውን ለማሳደግ የሚረዳ ግብዓት እንደሚሆንም አስረድተዋል። ከውጭ አገር ለብረታ ብረት የሚሆን የማዕድን አፈር በማስመጣት ወደ ብርት የመድረስ ደረጃው አስኪጠናቀቅ ያለው ሂደት በአገር ውስጥ ሲጀመር፣ በርካታ የውጭ ምንዛሪን ከማስቀረት አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አዲስ ማለዳ ከኢንስቲትዩቱ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።
አብዛኛውን የአገር ሀብት በውጭ ምንዛሬ ከሚባክንባቸው ዘርፎች ውስጥ ለአምራች ዘርፉ ግብዓትነት የሚውሉ የጥሬ እቃዎች ማስመጣት አንዱ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ ለብረታ ብረት ኢንዱስትሪው እንደሆነ ተገልጿል።
በዚህም በአገር ውስጥ የሚመረቱትን እቃዎች መጨመር እና ጥሬ እቃዎችን አገር ውስጥ በመመረታቸው ምክንያት ከአቅም በላይ ወጪዎችን እንዲቀንስ ያደርጋልም ተብሏል።
ከዛም በተጨማሪ መንግሥት በተዘዋዋሪ እያወጣው ያለው ወጪ አብዛኛውን ለብረታ ብረት ኢንዱስትሪው ነው ያሉት ጥላሁን፣ ነገር ግን ትኩረት ተሰጥቶት ቢሠራ በዘላቂነት የሚወጣውን ወጪ ቀንሶ ትርፋማነቱን ማብዛት ይቻላል ይላሉ።
‹‹ለምሳሌ መንግሥት ካወጣው ከዐስሩ ዓመት ሪፖርት ካስገባቸውና ትልቅ ወጪ ካወጣባቸው ምርቶች ውስጥ ሦስቱ የብረታ ብረት ኢንጅነሪንግ ዘርፍ ሲሆኑ፣ ከሦስቱ ደግሞ አንደኛ እና ኹለተኛ ደረጃን የያዘው ብረታ በረት ነው።›› ብለዋል።
ይህ የሚያሳየው አብዛኛውን የውጭ ምንዛሬ እያስወጣ ያለው ዘርፍ ይሄ መሆኑ ነው ሲሉ ጠቁመዋል። ነገር ግን ወደ ኢንቨስትመንት ቢቀየር እና ወደ አገር ውስጥ የሚገባው ላይ ቅናሽ ቢደረግ፣ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ይቀንሳል በማለት ጥላሁን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞ አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ የሰጡት የኢትዮጵያ መሠረታዊ ብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ ኢንስቲትዩት ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰለሞን ሙሉጌታ እንደተናገሩት፣ ቀድሞ ሊጀመር የሚገባ ነገር እንደነበርና ኢንዱስትሪው በኢትዮጵያ ደረጃ ከፍተኛውን የውጭ ምንዛሪ የሚፈልግ ዘርፍ ነው። ይህም የአገሪቷን 50 በመቶ የሚሆነውን የሚይዝ ሲሆን፣ ሰፊ የሆነ የኮንስትራክሽን ምርት ፍላጎት አለ ብለዋል።
ነገር ግን እንደዚህ አይነት ትልቅ ኢንቨስትመንት ሲጀመር ትልቅ ተፅዕኖ ይኖረዋል። እና አቅም ይጠይቃል ያሉት ሥራ አስኪያጁ ‹‹ከምርት ማምረት ሂደት ጀመሮ አልቆለት ማሰራጨት ደረጃ እስኪደርስ ድረስ የትራንስፖርት እና የሎጂስቲክስ አገልግሎት መሟላት፣ የሰው ኃይል ውስንነት ሊኖር አይገባም። የውሃ አቅርቦት ማለትም ከአፈሩ ማዕድን ግብአት አንስቶ እስከ ጥሬ እቃነት ደረጃ ለማድረስ ያለውን ሂደት፣ እናም የምርቱ መጠን አዋጪነቱ በብዛት ሲመረት እንደመሆኑ መጠን የአቅም ውስንነት ሊያስከትል ይችላል ሲሉም ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።
ቅጽ 2 ቁጥር 75 ሚያዝያ 3 2012



