ዓለም አቀፍ ተቋማት ከ23 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምግብ ነክ ምርቶችን ከቀረጥ ነጻ እንዲያቀርቡ ጥሪ ቀረበ

0
300

የኢትዮጵያ መንግሥት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሊፈጠር የሚችለዉን ማኅበራዊ ችግር ለመቋቋም እና መሠረታዊ የሆኑ የምግብ ፍጆታዎች ላይ እጥረት እንዳያጋጥም፣ ዓለማቀፍ ኩባንያዎች 22 ሚሊዮን ኩንታል የምግብ ምርቶችን ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ ጥሪ አቀረበ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ቫይረሱ በአገር ውስጥ መከሰቱንና ስርጭቱ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ፣ ዓለማቀፍ ኩባንያዎች መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦችን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በዓመት 18.1 ሚሊዮን ኩንታል የዳቦ ስንዴ፣ 3.2 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር፣ 1.73 ሚሊዮን ኩንታል ሩዝ በጥቅሉ ከ23 ነጥብ 08 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የምግብ እና 1.45 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ከቀረጥ ነፃ ወደ አገር ውስጥ እንዲያስገቡ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጥሪ ማድረጉን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወንድሙ ፍላቴ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

መንግሥት ያቀረበው ዓለም ዐቀፍ የንግድ ኩባንያዎች ጥሪ የተደረገበት ምክንያት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መስፋፋት ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ለመቋቋም እና በአገሪቱ የማይመረቱና ተመርተውም በቂ ያልሆኑ የምግብ ፊጆታዎች ጥሪ በተደረገላቸውና ወደፊት ይሳተፋሉ ተብሎ በሚጠበቁ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት እንዲቀርቡ ለማድረግ መሆኑን ወንድሙ አስታውቀዋል።

እንደ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ገለጻ፣ መንግሥት ለዓለም ዐቀፍ የንግድ ተቋማት ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ ጥሪ ያቀረበው፣ አገሪቱ ያላት የውጭ ምንዛሬ ውስንነት ስላለባት፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በቂ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት አግኝተው አስፈላጊ ሸቀጦችን ማቅረብ ስለማይችሉ እንደሆነና ያለው አማራጪ ዓለም ዐቀፍ የንግድ ኩባንያዎችን መጋበዝ መሆኑን ጠቁመዋል።

መንግሥት ላቀረበው ጥሪ የመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች ወደ አገሪቱ የሚያስገቡትን መሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎችና ሸቀጦች በራሳቸዉ የውጭ ምንዛሬ እንደሚጠቀሙ ወንድሙ ጠቁመዋል። ወንድሙ አክለውም የቀረበውን ጥሪ ተቀብለው የሚመጡ የራሳቸው አቅምና ዶላር ሊኖራቸዉ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ኩባንያዎቹ በሚሠሩበት አገር ላይ የንግድ ፈቃድ ያላቸውና የራሳቸው የዶላር አቅርቦት እንዳላቸው የሚሳይ የውጭ ምንዛሬ ዝውውር የባንክ አካውንት መረጃ ያላቸው እንደሚሆኑ ተገልጿል።

በተፈቀዱት የምግብ ፍጆታዎች ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች ከመጋቢት 30/2012 እስከ ሚያዚያ 15/2012 ድረስ በኢትዮጵያ ተወካይ ያላቸው በወኪላቸዉ አማካኝነት በአካል ቀርበው እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ ተወካይ የሌላቸዉ ኩባንያዎች በኢሜል አድራሻ የፍላጎት ማሳያ ሰነዳቸውን ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንዲያስገቡ አሳስበዋል።

ፍላጎት የሚያሳዩ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የስምምነት ውል እንደሚገቡ እና አገር ውስጥ ካሉ አከፋፋዮች ጋር ውል ገብተው ኩባንያዎች ለአከፋፋዮች እንዲያስረክቡና ለሸማቾች እንዲሸጡ እንደሚደርግ ወንድሙ ጠቁመዋል። ኩባንያዎቹ ከቀረጥ ነፃ የሚያስገቧቸው የምግብ ሸቀጦች ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ መንግሥት በተመነው ዋጋ እንደሚሸጡ ወንድሙ አክለው ገልጸዋል።

መንግሥት ከኩባንያዎች ጋር የሚገባው ስምምነት እንደየ ሁኔታው በመንግሥት ፍላጎት እየታየ በየዓመቱ ሊታደስ የሚችል እና ወረርሽኙ በአገሪቱ ሊያደርሰው የሚችለው ጉዳት በቀላሉ መግታት ከተቻለ፣ እንዲሁም አገሪቱ ወደ ቀድሞዉ የምርት አቅርቦትና ግብይት ከተመለሰችና የኅብረተሰቡን ፍላጎት በአገር ውስጥ ምርት ማርካት ከተቻለ፣ የስምምነት ውሉ ሊቋረጥ እንደሚችል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አመላክተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 75 ሚያዝያ 3 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here