
በዚህ ወር በወጣው የእንግሊዘኛው ‹ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው› መፅሔት ላይ የሥራ ባልደረባዬ ተኬ አለሙ (ዶ/ር) በ“ጥቁር ገበያ” የሚካሄደውን ገበያ ሕጋዊ ቢደረግ ጥሩ ነው የሚል በጣም ጥሩ ፅሁፍ አውጥተው ነበር። እውነትም ነው ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ሊሰማው የሚገባ ጉዳይ ነው። ሆኖም ይህ ሃሳባቸውን በውል ያልተረዱ ሰዎች በአጠቃላይ የዶላር ገበያው ነፃ ይሁን ተባለ የሚል አንድምታ እንዳያሠጡት ይኼን ማስታወሻ ለመፃፍ ፈቀድኩ።
በዚህ ወር በወጣው የእንግሊዘኛው ‹ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው› መጽሔት ላይ የሥራ ባልደረባዬ ተኬ ዓለሙ (ዶ/ር) በ“ጥቁር ገበያ” የሚካሔደውን ገበያ ሕጋዊ ቢደረግ ጥሩ ነው የሚል በጣም ጥሩ ጽሑፍ አውጥተው ነበር። እውነትም ነው፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ሊሰማው የሚገባ ጉዳይ ነው። ሆኖም ይህ ሐሳባቸውን በውል ያልተረዱ ሰዎች በአጠቃላይ የዶላር ገበያው ነጻ ይሁን ተባለ የሚል አንድምታ እንዳያሰጡት ይኼን ማስታወሻ ለመጻፍ ፈቀድኩ።
በመጀመሪያ “ጥቁር ገበያ” የሚለው አባባል አልተስማማኝም። ፈረንጆቹ ጥልቅ መጥፎና ሕገወጥ ነገርን ነጭ ገበያ ከማለት ይልቅ ጥቁር ገበያ ማለት ይቀናቸዋል። እኛ ደግሞ ሐሳቡን ሳንመረምር እንደግመውና ዘረኛ አስተሳሰብን እናስፋፋለን። እኔ በእንግሊዝ አፍ ስጽፍ ‹Parallel Market› (ትይዩ ገበያ) የሚለውን ነው የምጠቀመው። ይህንን ገበያ ሕጋዊ በማድረግ ጉዳይ ሁለት ነጥቦችን አስፍሬ ጽሑፌን አበቃለሁ።
የመጀመሪያውና አንደኛው ነጥቤ ተኬ ሕጋዊ ቢሆን ጥሩ ነው ያሉት ትክክል መሆኑን መጠቆም ነው። ለዚህም ምክንያቱን ተኬ ዘርዘር አርገው በዛ መጽሔት ላይ ስላብራሩት መድገም አያስፈልግም። የዛ ሕገ ወጥ የዶላር ገበያ ፍላጎትና አቅርቦትም ከየት ከየት እንደሚመጣ ጥሩ አድርገው ስላብራሩት የሳቸውን ጽሑፍ ማየት ጥሩ ነው። አዲስ ማለዳም ተርጉማ ታቀርበዋለች ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ተኬንም እናመሰግናለን።
ሆኖም ሁለት ነገር እሳቸው ማብራሪያ ላይ ልጨምር እወዳለሁ። አንደኛው በሕገ ወጥ የዶላር ገበያ ላይ ለዶላር ያለው ፍላጎት የሚመጣው ሰዎች በወንጀልና በሙስና (በሌብነት) ያገኙትን ብር በዶላር ለማሸሽ በሚያደርጉት ክንዋኔና የውጭ ድርጅቶችም አገር ውስጥ በብር ያካበቱቱን ሀብት ወደ አገራቸው ለማሳደድ በመሆኑም ጭምር መሆኑን ነው። ሁለተኛውና ጠቀሜታውን በሚመለከት እሳቸው ያላነሱት ጉዳይ መንግሥት በሕገ ወጡ የዶላር ገበያ ላይ በስውር በመግባት፣ ዶላርን በመሸጥና በመግዛት ገበያውን ለማረጋጋት መቻሉን ነው። ይሔ ዓይነቱ የምንዛሪ ፖሊሲ ወደ ትክክለኛው ገበያ መር ምንዛሪ ፖሊሲ መለማመጃ በመሆን ልምድ ለመቅሰም በጣም ጥሩ ነው።
ይህን ካልኩ በኋላ ወደ ዋናው ነጥቤ ስመጣ፣ እኔ እንደገባኝ የተኬ ነጥብ የምንዛሬ ገበያውን በሁለት በመክፈል (ሕገ ወጡን ሕጋዊ ማድረግ አንጂ ሁለቱን ገበያዎች መቀላቀል አይደለም። ሐሳባቸው እንዲዛ ከሆነ ልክ ናቸው። አይ ሁለቱ ገበያዎች ተቀላቅለው አንድ መሆን አለባቸው ካሉ ግን በኔ ግምት ስህተት ነው። አንዳንድ ታዋቂ ነጋዴዎችም አንድ ነጻ የሆነና በአቅርቦትና በፍላጎት ላይ የተመሠረተ የዶላር ገበያ የኢትዮጵያን የወጪ ምንዛሪ ችግር ይፈታል ብለው በመገናኛ ብዙኃን ሲናገሩ ስለሰማሁ ይህንን አደገኛና በዕውቀትና ምርምር ያልተደገፈ ምክረ ሐሳብ ማቅረብ አደገኛ መሆኑን ለመንገር ብዬ ነው ይህን ማስታወሻ መጻፌ። ለዚህ ደግሞ ብዙም ሳልለፋ ጥሩ ማስረጃዬ ባለፈው ሁለት ሳምንት በሰሜን ሱዳን የሆነው ጉዳይ ይሄው መሆኑ ነው።
ጠቅለል አድርጌ የኔን ምክረ ሐሳብ አሁን ባለንበት ሁኔታ ሁለት ገበያዎች ይኑሩን። አንደኛው ሕጋዊው፣ ሁለተኛው እስካሁን ባለው ሁኔታ ሕገ ወጡ። ሕጋዊውንና ዋናውን ገበያ አሁን በለመድነውና ፈረንጆቹ (Managed fluating) በአማርኛ በዕውቀት የሚመራ የዶላር ገበያ በሚለው የመንግሥት ፖሊሲ እንግፋበት።
ሕገ ወጡን ደግሞ ተኬ ባሉት መንገድ ሕጋዊ አድርገን ነገር ግን ምን ያህል ወደ ላይ እንደሚወጣና ምን ያህል ወደ ታች እንደሚወርድ የመዋዠቅያ ጣሪያና ወለል ብሔራዊ ባንኩ በሕግ ወስኖ፣ በዛ ወሰን ውሰጥ ምንዛሪው እንዲጫወት በመተው፣ መንግሥት በዘወርዋራ የገንዘብ ፖሊሲ፣ ማለትም መንግሥት በገበያ ውስጥ እንደማንኛውም ተዋናይ ገብቶ ዶላር በመሸጥና በመግዛት (indirect Monetery Policy) እንምራው። በሒደትና የወጪ ንግዳችን በእጅጉ ሲዘምንና የውጪ ምንዛሪ አቅርቦታችን ሲጨምር ሁለቱን ገበያዎች በረዥም ጊዜ ዕቅድ እናዋህዳቸዋለን። ይህንን የፖሊሲ አቅጣጫ አለ ብለን ሁለቱን ገበያዎች አንድ አድርገን የውጪ ምንዛሬ ገበያውን ነጻ እናድርግ ካልን ግን በአንድ ሰከንድ ውስጥ የአንድ ዶላር ዋጋ 40 እና 50 ብር በላይ ሆኖ ግሽበቱ ጣራ ነክቶ ሰዎች ብራቸውን ለማውጣት ባንኮችን አጨናንቀው የባንክና የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ ነው የምንገባው (የሚከተለው)፤ ለዚህ ደግሞ ያለፈው ሳምንት የሱዳን ኦኮኖሚ ማየት በቂ ነው።
የሱዳን መንግሥት የውጪ ምንዛሪ ገበያውን ባለፈው ሳምንት ከፍቶ ባንድ ጊዜ የአንድ ዶላር ዋጋ ከነበረው 27 የሱዳን ብር 48 ገብቷል። ሕገ ወጥ በሆነው የዶላር ገበያ ደግሞ ከ58 የሱዳን ብር በላይ ሆናል። ይህንን ተከትሎ ሰው የብሩን መውደቅ በማየት በገንዘብ መክፈያ ማሽኖችና ባንኮች በራፍ ላይ ረዣዥም ሰልፎችን ሲሠራ ከርሟል። የተፈጠረውን የብር እጥረት ለመግታት የሱዳን መንግሥት ብር ማተሙን ቀጥሏል። እንግዲህ ይህ የታተመው የሱዳን ብር ወደ ገበያ ሲገባ የሚያወጣውን የዋጋ ንረት (የገንዘብ ግሽበት) መገመት ነብይነትን አይጠይቅም። ይህ ደግሞ አስከትሎ የሚያመጣው የማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ አስፈሪ ነው ። በአሁን ጊዜ አገራችን ኢትዮጵያ የዚህ ዓይነት ቀውስን የመቋቋም ምንም አቅም ስለሌላት ከተቻለ ባለው ፖሊሲ መቀጠል አንደኛ ምርጫ መሆን አለበት፤ ካልሆነ ደግሞ እኔ በዚህ ጽሑፍ ባልኩት መልክ መሔድ እንዳለብን ፖሊሲ አውጪዎቻችንና መንግሥት ይረዱታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
ዓለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) በአ.አ.ዩ. የምጣኔ ሀብት ፕሮፌሰር ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው ag112526@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።
ቅጽ 1 ቁጥር 5 ታኅሣሥ 6 ቀን 2011