ኢትዮጵያ ለነዳጅ ምርት የምታወጣው ወጪ በአንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሚቀንስ ተገለጸ

የነዳጅ ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ መቀዛቀዝ በማሳየቱ እና ቀድሞ ከነበረበት የበርሜል ዋጋ በመውረዱ ኢትዮጵያ በዓመት ከምታወጣው ወጪ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚሆነውን ልታስቀር እንደምትችል ሴፈስ ካፒታል የተሰኘ ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት አስታወቀ።

ድርጅቱ እንደገለጸው፤ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የዓለም ዐቀፉ ንግድ እንቅስቃሴ ከመገታቱ ጋር ተያይዞ የነዳጅ ዋጋም ከፍተኛ መቀዛቀዝ አሳይቷል። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ለዘርፉ በየዓመቱ የምታወጣውን ወጪ ተመሳሳይ መጠን ያለው የነዳጅ ምርት ብታስገባ አንኳን በአንድ ቢሊዮን ዶላር ወጪዋ ሊቀንስ እንደሚችል አስረድቷል።

እስከ ቀጣዩ ዓመት ይህ ዓለም ዐቀፉ ነዳጅ ዋጋ መቀዛቀዝ ከቀጠለ ለኢትዮጵያ መልካም ጊዜ እንደሚሆንና በየዓመቱ በአማካኝ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ለምታወጣበት የነዳጅ ምርት ውስጥ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚሆነውን ልታስቀር የምትችልበት እድል እንዳለ በጥናቱ አስታውቋል።

በዓለም ዐቀፍ ገበያ የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በፈረንጆች 2019 ከነበረበት የ57 ዶላር ዋጋ ከግማሽ በላይ ቅናሽ በማሳየት አንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ወደ 25 ዶላር ዝቅ ማለቱ ታውቋል። ይህን በመመርኮዝም ሲፈስ ካፒታል ኢትዮጵያ በየዓመቱ ወደ አገር ውስጥ የምታስገባውን 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ፣ በዚህ ዓመትም ብታስገባ ልታወጣ የምትችለው ገንዘብ ከዚህ ቀደም ከተለመደው የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቅናሽ ይኖረዋል ሲል ያስረዳል።

ጉዳዩን በሚመለከት አስተያየታቸውን የሰጡት የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አበበ አበባየሁ፣ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ያለው የነዳጅ ዋጋ መቀነስ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ ጥቅም እንዳለው እና በወረርሽኙ ምክንያት እንደ አገር ከሚደርስብን ጉዳት ባሻገር በመልካም ጎኑ ልናየው የምንችለው ጉዳይ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። አበበ አያይዘውም የነዳጅ ዋጋ ቢቀንስም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ግን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስ እና በዓለም ዐቀፍ ደረጃም እስከ 40 በመቶ ሊቀዛቀዝ እንደሚችል ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በኢፌዴሪ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ እንደገለጸው፣ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የታየው የነዳጅ ዋጋ መቀነስ እንደ አገር ከከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪ እንደሚያድናትና በከፍተኛ ወጪ ወደ አገር ውስጥ ከሚገቡ ምርቶች ውስጥ መሆኑ ደግሞ ጉዳዩን ከፍ ያደርገዋል ሲሉ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወንድሙ ፍላቴ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በኹለት መንገድ የነዳጅ ምርቶችን ከዓለም አቀፍ ገበያ እንደምታስገባ ይታወቃል። የመጀመሪያው በኢትዮጵያ እና በኹለተኛ አገራት መካከል በሚደረግ የመንግሥታት ስምምነት የሚደረግ ሲሆን ይህም ከጠቅላላው ግዢ የ50 በመቶውን ድርሻ እንደሚይዝ ለማወቅ ተችሏል። ቀሪውን 50 በመቶ ደግሞ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጨረታ በማውጣት የሚፈጸም ግዢ ነው።

ኢትዮጵያ ወደ አገር ውስጥ ከምታስገባቸው ምርቶችም በዋነኛነት ቤንዚን፣ ናፍጣ እና አውሮፕላን ነዳጅ ትልቁን ድርሻ ሲይዙ፤ ኬሮሲንም ወደ አገር ውስጥ ከሚገቡ የነዳጅ ምርቶች ውስጥ ይካተታል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ ክፍሎች 13 የነዳጅ ዲፖ ያለ ሲሆን፣ በድምር እስከ 370 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የመያዝ አቅም ያላቸው መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 75 ሚያዝያ 3 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here