የግል ትምህርት ቤቶችን ክፍያ በተመለከተ አዲስ ውሳኔ ሊተላለፍ ነው

0
694

የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ምክንያት በማድረግ የመማር ማስተማር ሒደቱ ቢቋረጥም፣ ልጆች ላልተማሩበት እንዲከፍሉ መደረጋቸውን ተከትሎ መንግሥት አዲስ ውሳኔ ሊያስተላልፍ እንደሆነ ተገለጸ።

ከመጋቢት 7/2012 ጀምሮ መንግሥት ትምህርት ቤቶችን ለ15 ቀናት እንዲዘጉ ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ፣ በኢትዮጵያ በኹሉም አካባቢዎች ይሰጥ የነበረው የመማር ማስተማር ሂደቱ ተቋርጧል። ይሁንና የግል ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን ላላስተማሩበት ወላጆች እንዲከፍሉ መደረጉ በወላጆች ዘንድ ቅሬታ ፈጥሮ ቆይቷል። መንግሥትም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር እየሠራበት እንደሚገኝ የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን አቤቱታ ምርመራ ዳይሬክተር ጌትነት አሸናፊ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ አያይዘው እንደጠቀሱት፣ በመንግሥት በኩል እስከ መቼ ድረስ ትምህርት እንደሚቋረጥ በውል ባለመታወቁ፣ ለውሳኔ መቸገራቸውን ጠቅሰዋል። ነገር ግን በቀጣይ በእርግጠኝነት የሚወሰነው ውሳኔ ታይቶ ወላጆች ለተጠቀሱት ጊዜያት የልጆቻቸውን ክፍያ መክፈል እንደማይኖርባቸው አስታውቀዋል። ውሳኔው በግልጽ ይፋ እስኪሆን ድረስም ውሳኔዎችን አስተላልፎ ተጠቃሚው የአገልግሎቱን ያህል ብቻ መክፈል እንዲኖርበት ለማድረግ እየሠራን ነው በማለት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ወላጆች ለልጆቻቸው የትምህርት ቤት ክፍያ መክፈል በሚያቆሙበት ጊዜ ትምህርት ቤቶች ለአስተማሪዎች የሚከፍሉት ደሞዝ ሊቋረጥ ስለሚችል፣ ለከፋ ማኅበራዊ ቀውስ ሊዳርግ እንደሚችል ታስቦበታል ብለዋል ዳይሬክተሩ። ይህንንም ታሳቢ በማድረግ መንግሥት ለአገልግሎቱ የተወሰነ ያህል ድጎማ ማድረግ እና የአስተማሪዎችን ክፍያ መሸፈን ሊታሰብበት ያስፈልጋልም ብለዋል።

ከወላጆች ዘንድ በርካታ ቅሬታዎች መቅረባቸውን የተናገሩት ጌትነት፣ የምንሠራውን ሥራ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን፣ የንግድ እና ኢንዱስትሪን እና የትምህርት ቢሮን ጨምሮ ፌዴራል መንግሥትም አንድ ላይ በመሆን ሁሉንም ያገናዘብ ውሳኔ ለመወሰን የተለያዩ ምልከታዎችን እያደረግን ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። የመማር ማስተማሩ ሂደት በተቋረጠበትም የትምህርት ስርዓቱ ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ለመፍታት፣ ትምህርት ቤቶች የተለያዩ የተዘጋጁ ማስተማርያ ወረቀቶችን በመበተን የትምህርት ሂደቱ እንዳይቋርጥ ለማድረግ እየተሠራ ነው። ይህንን ስርአትም ከመዋዕለ ሕፃናት ውጪ ያሉ ትምህርት ቤቶች እንዲከተሉ እያደረግን እና የመለየት ሥራም እየተሠራ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

ከዛም በተጨማሪም እንደ ጌትነት ገለጻ፣ እንደ ቀደመው ጊዜ የአገልግሎት ክፍያ መጠየቂያ ጊዜ ቁርጥ አድርገን መዝጋት እና መወሰን እንዳንችል ከሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር አንድ ላይ በመሆን በመሥራት ላይ የሚገኙ የመንግሥት ባለድርሻ አካለት አሉ። አንድ ላይ በመሆን ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ በማለትም አክለዋል።
ከባለ ድርሻ አካለት መካከል ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አንዱ ነው። አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በሚመለከት የሚኒስቴሩን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወንድሙ ፍላቴን ባነጋገረችበት ወቅት እንደተናገሩት፣ አሁን ላይ ዓለማቀፋዊ ችግር እንደመሆኑ መጠን ይህን ያስከተለው ውሳኔዎችን ለመወሰን መንግሥት የተለያዩ ድጎማዎችን ለማድረግ ገና በመሰብሰብ ላይ እንደመሆኑ መጠን በአንድ በኩል የሚወሰነው ውሳኔ ለሌላው ችግር መፍጠር ስለሌለበት በጥንቃቄ እየተሄደበት ስለሆነ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

በሌላ በኩል የትምህርት ቤት ባለንብረቶች ከአስተማሪ ክፍያ ባሻገር ለቤት ኪራይ የሚሆን ገንዘብ መሸፈን እንደሚኖርብን መንግሥት የተረዳው አይመስለንም ሲሉ ይስተዋላል። ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን የሰጡ የግል ትምህርት ቤት ባለንብረቶች እንደሚሉት፣ መንግሥት መራጩን ሕዝብ ለማስደሰት እየሠራ እንደሆነና የግሉን የትምህርት ዘርፍ ከመጀመሪያው ጀምሮ እያቀጨጨው እንደሚገኝ ጠቁመዋል። ቀለብ እየሰፈረ፣ የደንብ ልብስ እየገዛ እና የትምህርት ግብዓቶችን እያሟላ ኅብረተሰቡን ለማስደሰት እንጂ የግሉን የትምህርት ዘርፍ ለመደገፍ ሲንቀሳቀስ አይታይም ሲሉ ወቀሳቸውን አቅርበዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 75 ሚያዝያ 3 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here