በዘመነ ኮሮና የጤና ባለሙያዎችን ከጎናችሁ ነን ልንላቸው ይገባል!

0
503

የኖቭል ኮረናን ኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል በሚደረገው ሁለገብ ትግልና እንቅስቃሴ፣ ፊት ለፊት ተጋላጭ በመሆን የውጊያው ፊታውራሪዎች ሐኪሞች፣ ነርሶች እና የጤና መኮንኖች በአጠቃላይ የጤና ባለሙያዎች መሆናቸው አይታበይም። የጤና ባለሙያዎች በሥልጠና ከሚያገኙት እውቀት፣ ክህሎትና ጥበብ ባሻገር ሙያው መሰጠትን የሚጠይቅ ክቡር የሰው ልጅ ሕይወትን ለመታደግ የሚሠራ የመንፈስ እርካታም የሚሰጥ ነው።

ከብዙ ሙያዎች ሕክምናን የሚለየው ከሰው ልጅ ሕልውና ጋር በቀጥታ የሚገናኝ መሆኑ ሲሆን በሙያው የተመረቁ ባለሙያዎችም የሥራውን ክብደት በሚያሳይ መልኩ ከሚጠበቅባቸው ሙያዊ ሥነ ምግባር ባሻገር በምርቃታቸው ወቅት ቃለ መሐላ ይፈጽማሉ። ይህም የሙያውን ታላቅነት የሚመሰክር ለመሆኑ በእማኝነት መጥቀስ ይቻላል።

እንዲህ እንደወቅቱ የዓለማችንና የአገራችን ሁኔታ ድንበር ተሻጋሪ ወረርሽኝ ሲከሰት፣ በሽታውን በመዋጋት ግንባር ቀደም ሚና የሚጫወቱት እነዚሁ የጤና ባለሙያዎች ናቸው። በመከላከል ሒደት ውስጥም ራሳቸውን ለበሽታ ተጋላጭ ያደርጋሉ፤ ምንም እንኳን በሙያ የታገዘ የቅድመ መከላከል መርህን ተግባራዊ ቢያደርጉም።

ከተጋላጭነት ጋር በተያያዘ በኮቪድ 19 ክፉኛ የተጠቃችው የጣሊያን የጤና ባለሙያዎች በከፍተኛ መጠን የሕይወት መስዋዕትነት መክፈላቸውን ዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኅን በሰፊው መዘገባቸውን የተከታተሉትን ከፍተኛ ሐዘን ውስጥ ከቶ አልፏል። አሁንም ቢሆን በዓለም ላይም ይህንን ክፉ ወረርሽኝ በመዋጋት ራሳቸውን ተጋላጭ በማድረግ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የጤና ባለሙያዎች ያለመታከት ሙያዊ ኀላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።

አዲስ ማለዳ በአጠቃላይ ለእነዚህ የጤና ባለሙያዎች ላቅ ያለ ምስጋናዋን ታቀርባለች፤ እውቅናም ትሰጣለች። ለባለሙያዎቹ መንግሥትም ሆነ ሕዝቡ የሞራል ድጋፍ በማድረግ በሥራቸው ላይ ትጋትን እንዲጨምሩ፣ ውጤታማም እንዲሆኑና ከምንም በላይ ደግሞ ሊያጋጥም በሚችል የብዙ ሰዎች በወረርሽኙ መጠቃትና ሞት ጭንቀትና ድብታ ውስጥ እንዳይገቡ የሞራል ድጋፍ ሊደረግላቸው፣ ምሥጋናም ሊቀርብላቸው እንዲሁም እውቅና ሊሰጣቸው ይገባቸዋል ስትል አዲስ ማለዳ በአጽንዖት ታሳስባለች።

ከዚህ በተቃራኒ ግን በተለይ በመዲናችን አዲስ አበባ አንዳንድ የጤና ባለሙያዎች ላይ በአንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍሎች የማግለል አዝማሚያዎች እየታዩ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። አንድ የጤና ባለሙያ በሕዝብ ትራንስፖርት ላይ በመሔድ ላይ እያለች ከሥራ አጋሯ ጋር ስለኮቪድ 19 ወረርሽኝ በማውራቷና አብረዋት የተሳፈሩት የጤና ባለሙያ መሆኗን ያወቁት ተጓዦች፣ ሹፌሩና ረዳቱ ተባብረው እንድትወርድ እንዳስገደዷት ለመገናኛ ብዙኀን መናገሯ ሰሞኑን ከተሰሙት መካከል አንዱ አሳዘኝ ሁነት ነው። በተመሳሳይ አንድ የጤና ባለሙያ በሥራው ምክንያት የተከራየበት ቤት በፍጥነት እንዲለቅ መደረጉን በተመለከተ ቅሬታውን ማሰማቱም ታውቋል። ከቤት እንዲለቅ የተደረገው ደግሞ ወረርሽኙን ታመጣብናለህ በሚል ሰንካላ ምክንያት መሆኑ ልብን ይነካል፤ ያሳዝናል!

እነዚህ ኹለት ድርጊቶች ለአብነት የተጠቀሱ መሆናቸው ሲታወቅና ሌሎች መሰል መገለሎች በጤና ባለሙያዎች ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል። እነዚህ ድርጊቶች እንደ ቀላል ጉዳይ መታየት የለባቸውም፤ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ናቸው። አዲስ ማለዳ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እነዚህ ኹለት አብነቶች እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ ተግባራት ናቸው ብላ ታወግዛለች። ሳይቃጠል በቅጠል እንደሚባለው መሰል አጸያፊ ተግባራት እንዳይበራከቱ እንደማኅበረሰብ አባል እያንዳንዳችን በግለሰብ ደረጃ፣ ከፍ ሲልም በማኅበረሰብም ሆነ በመንግሥት ደረጃ መሰል ድርጊቶችን በግልጽ ማውገዝ ይገባል። በተለይ መገናኛ ብዙኀን እንደዚህ ዓይነት አጸያፊ ድርጊቶችን በማጋለጥ ይጠበቅባቸዋል፤ ጎን ለጎንም በኅብረተሰቡ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መሥራት አለባቸው። የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጉዳዩን በመከታተል በፈጻሚዎች ላይ የማያዳግም አስተማሪ እርምጃ መውሰድ ይገባቸዋል ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

በእርግጥ ሁሉም የጤና ባለሙያዎች መገለል ይደርስባቸዋል ማለት እንዳልሆነ ግን ልብ ሊባል ይገባል። ይህንንም አንድ መልካም ምሳሌ በማንሳት ማስረገጥ ይቻላል። አንድ ወጣት ሕመም አጋጥሞት ወደ ጤና ጣቢያ በሔደበት ወቅት የኮቪድ 19 ምልክቶች ተገኝቶብሃል ተብሎ ለበለጠ ምርመራ ወደ ሌላ የሕክምና ቦታ ይወሰዳል። በጉዞውም ላይም በአንቡላንስ ውስጥ የነበሩት ሐኪሞች በሙሉ ሲያበረታቱት እና ምንም የሚከሰት ነገር እንደሌለ እየገለፁለት እና እንዳጽናኑት ሲገልጽ፤ “በበሽታው ብያዝ እንኳን አገግሜ እንደምድን በራስ የመተማመን ስሜት ፈጥረውብኛል” በማለት የጤና ባለሙያዎች ላደረጉለት ሙያዊና ሥነ ልቦናዊ ድጋፍ አመስግኗል፤ በአደባባይም እውቅና ሰጥቷል። ይሔ ሊበረታታ የሚገባው ሲሆን ተመሳሳይ እውነተኛ ታሪኮች ቢቀርቡ የኅብረተሰቡ ግንዛቤ ከማሳደጉም በተጨማሪ ምስጋና ለማቅረብም ሆነ እውቅና ለመስጠት ማነቃቂያ ይሆናሉ።

የጤና ባለሙያዎች ከሚደርስባቸው መገለል ባሻገር ከሙያው ባሕሪይ አስገዳጅነት አንጻር ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው ስለሚሠሩ፣ መንግሥትም የተለየ ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል። በዚህ ረገድ አንዳንድ አገሮች በተግባር ላይ ያዋሉትን ተመክሮ መቅሰም ያስፈልጋል ስትል አዲስ ማለዳ ለመንግሥት ወይም ለሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ጥቆማዋን ታቀርባለች። ለምሳሌ በአንዳንድ አገሮች የጤና ባለሙያዎቻቸው በሙሉ የሕይወት ኢንሹራንስ እንዲገባላቸው በማድረግ በጎ እና አበረታች እርምጃ ወስደዋል። በተመሳሳይ ለእኛዎቹም የጤና ባለሙያዎች እንደዚህ ዓይነት እገዛ የሚደረግበት መንገድ ቢፈለግ መልካም ነው።

በአጠቃለይ አዲስ ማለዳ ከሰሞኑ በአንዳንድ ሕክምና ባለሙያዎች ላይ እየደረሰ ያለውን እንግልትና መገለል እንዲሁም መድሎ በጽኑ ትቃወማለች። ከዚህም ባለፈ የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት የጸጥታ አስከባሪዎችንም ጨምሮ በሕክምና ባለሙያዎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በመከላከል ደኅንነታቸውን ማረጋጋጥ እንደሚኖርባቸውም አበክራ ታስገነዝባለች።

ወረርሽኙ ከዚህ ቀደም በከፋ መልኩ ጉዳት ያደረሰባቸው አገራት ላይ ከሌላው ኅብረተሰብ ክፍል ይልቅ ቀድመው በመድረስ ራሳቸውን መስዋዕት አድርገው ለወገንና ለሕዝብ በማገልገል በወረርሽኙ ተጠቅተው ለኅልፈት የተዳረጉ ባለሙያዎች ቀላል ቁጥር አይደሉም። ይህ ኹሉ እየታየና እየተሰማ ባለበት የጤና ባለሙያዎቻችን ለአፍታም ሳይደነግጡ ወረርሽኙን በቆራጥነት ከሕዝባቸው ቀድመው ለመጋፈጥ በተሰለፉ በዚህ ወቅት መደገፍ እና ማበረታታ እንጂ ማኅበራዊ ተሳትፏቸውን መገደብ ወይም ማግለል በጥብቅ መወገዝ ያለበት ጉዳይ ነው።

ከዚህም ባለፈ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በኅብረተሰቡ ዘንድ በማሰራጨት በሕክምና ባለሙያዎች ላይ የሚደርሰውን እንግልት እንዲቀንስ ማድረግ ይገባል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በቅርቡ በአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ እንዲሁም ሚኒስትሮች በመዲናችን ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ በመዘዋወር ግንዛቤ ሲያስጨብጡ የተስተዋሉ ሲሆን እንዲህ ያለ እንቅስቃሴ በተመሳሳይ ወደ ክልሎችና ገጠር ከተሞች መስፋፋት ይኖርበታል።

ወረርሽኝ በየትኛውም መጠን በኢትዮጵያ ውስጥ በተከሰተ ጊዜ ከማንም በፊት ለአገራዊ ግዴታ የሚሰለፉት የጤና ባለሙያዎች መሆናቸው ታውቆ ማሸማቀቁና ማግለሉ ይቁም። በልበ ሙሉነት የወረርሽኙን የመከላከልና የመቆጣጠር ሙያዊ አበርክቷቸውን እንዲያደርጉ የጤና ባለሙያዎችን ሁላችንም ከጎናቸው መሆናችንን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እንግለጽላቸው፣ እናበረታታቸው ስትል አዲስ ማለዳ አደራ ትላለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 75 ሚያዝያ 3 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here