መንግሥት ከውጪ በሚያስገባው የምግብ ዘይት ላይ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉን አስታወቀ

0
885

መንግሥት ከውጪ በሚያስገባው የምግብ ዘይት ላይ በአንድ ሊትር የ4 ብር ከ30 ሳንቲም የዋጋ ማስተካከያ እንዲደረግ መወሰኑን አስታወቀ።
የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከውጪ አገራት በድጎማ ከሚያስገባቸው ምርቶች ውስጥ አንዱ የምግብ ዘይት መሆኑን የተናገሩት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ እሸቴ አስፋው፣ የዚህም ምርት የመሸጫ ዋጋ የሚወሰነው በዓለም ገበያ መሰረት መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት መንግሥት በድጎማ ከወጪ የሚያስገባው የምግብ ዘይት ከአሁን ቀደም ሲሸጥ ከነበረበት ዋጋ፣ ከሚያዚያ 6 ቀን 2012 ጀምሮ በሊትር የ4 ብር ከ30 ሳንቲም ጭማሪ መደረጉን ሚኒስትር ድኤታው አስታውቀዋል።
ዘይት ለማቅረብ ከክልሎች ተወክሎ የመጣ ማንኛውም አስመጪ ድርጅት በዚህ ዋጋ ለአከፋፋዮችና ለቸርቻሪዎች ማስረከብ እንደሚጠበቅበትም ሚኒስትር ድኤታው አሳስበዋል።
ቸርቻሪዎች ከአስመጪዎች የተረከቡትን ምርት በተመሳሳይ ዋጋ (አራት ብር ከሠላሳ ሳንቲም) በመጨመር ለኅብረተሰቡ ሽያጭ መፈጸም እንደሚገባቸው የተናገሩት አቶ እሸቴ አስፋው፣ ከዚህ ዋጋ ውጪ ግብይት ሲፈጽም በተገኘ ማንኛውም የንግድ ማኅበረሰብ ላይ መንግሥት እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።
መንግሥት ካስቀመጠው ዋጋ ውጪ ምርቱ ሲሸጥ ከተገኘ ኅብረተሰቡ ለሚመለከታቸው የከተማ አስተዳደር፣ ለክልል የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮዎች እና ለፀጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ ቀርቧል።

ቅጽ 2 ቁጥር 76 ሚያዝያ 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here