በአገር ውስጥ አድማጮች ዘንድ ‹ወሰንኩ› እና ‹ቡና› በሚሉ ሙዚቃዎቿ ትታወቃለች፡፡ በቀደመው ጊዜም በብሔራዊ ትያትር ተወዛዋዥነቷ ከእነ ኩሪባቸው ወልደማሪያም (ኩሪ) እና እንዬ ታከለ ጋር በነበራት ጥምረት ብዙዎች ያስታውሷታል፡፡ ተወዛዥ፣ ተዋናይት እና ድምጻዊት ምንይሹ ክፍሌ ግን ዓለም አቀፍ ዕውቅናዋ ከዚህ በእጅጉ ላቅ ይላል፡፡ በቅርቡ ለዓለም ዐቀፍ አድማጮቿ ያደረሰችው የተሰኘ አልበሟ ‹ትራንስ ግሎባል› በተሰኘ ዓለም ዐቀፍ የሙዚቃ ደረጃ ሰንጠረዥ የኅዳር ወር ደረጃ ከታዋቂዋ ደቡብ አፍሪካዊት አርቲስት አንጀሊክ ኪጆ በመብለጥ ስደስተኛ ደረጃን አግኝቷል፡፡
ምንይሹ የተወለደችው በድሬዳዋ ከተማ ቢሆንም እድገቷ ግን በመዲናይቱ አዲስ አበባ ነበር፡፡ በ17 ዓመቷ ብሔራዊ ትያትርን የተቀላቀለችው ምንይሹ 35 አገራትን ባዳራሰው እና አራት ወር በፈጀው ‹‹የሕዝብ ለሕዝብ ዓለም ዐቀፍ የሙዚቃ ጉዞ›› ውስጥ ከተካተቱ አርቲስቶች መካከል ነበረች፡፡ በዚህም ከእነ ሙላቱ አስታጥቄ፣ መሐሙድ አህመድ፣ ጥላሁን ገሠሠ እና ብዙነሽ በቀለ ጋር የመሥራት ዕድል ገጥሟታል፡፡ አገር ውስጥ እያለች ሰናይት በተሰኘ ፊልም ላይ መሪ ተዋናይ ሆና ተውና የምታውቀው ምንይሹ እ.አ.አ በ1996 ወደ አውሮፓ ተጉዛለች፡፡
በአውሮፓ ቆይታዋ ‹ሳን ግራትስማ› ከተባለ የሙዚቃ ማነጀር እና አዘጋጅ ጋር ሞዛይክ ቪቫንት በተባለ የሙዚቃ አቅራቢ ጋር መሥራት ችላለች፡፡ እ.አ.አ 1997-1999 ከሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ አርቲስቶች ጋር በመሆን አፍሪካ ዩናይት የተሰኘ ተካታታይ የሙዚቃ ድግሶችን ያቀረበች ሲሆን የመድረክ ሙዚቃዎቹ በሲዲ ተለቀው ነበር፡፡ ምንይሹ እ.አ.አ 2002 ‹‹መባ›› የተሰኘ አልበም የሠራች ሲሆን ይህም አልበም በኔዘርላንድ፣ ቤልጂየም እና ጀርመን ከፍተኛ ተቀባይነትን አስገኝቶላታል፡፡ ‹‹ድሬ ዳዋ›› የተሰኘውን ሁለተኛ አልበሟን ሚ ኤንድ ማይ ሪከርድስ ከተሰኘ የሙዚቃ አቅራቢ ጋር የሠራች ሲሆን ይህም በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች የሙዚቃ ዝግጅቶን እንድታቀርብ በሮችን ከፍቶላታል፡፡
በአፍሪካ ውስጥም በሁለተኛው ‹የፓን አፍሪካን ፌስቲቫል› እና ‹ዓለም ዐቀፉ የጥቁር ጥበብ ፌስቲቫል› ላይ ሳሊፍ ኬታን ጨምሮ አንጀሊክ ኪጆ፣ ዮሱ ዱር እና ባባ ማል ከተሰኙ ታዋቂ የአፍሪካ አርቲቶች ጋር ከውናለች፡፡ ከዚህም ባለፈ አንጋፋ ከሆኑ አውሮፓዊ ባንዶች እና አርቲስቶች ጋር ተጣምራ የሙዚቃ ዝግጅቶችን አቅርባለች፡፡ ጥቁር ቀለም የተሰኘው ሦስተኛ አልበሟን በ2013 መልቀቋ ይታወሳል፡፡
መድረክ ላይ በምታሳያቸው እንቅስቃሴዎች ማራኪነት የምትታወቀው ምንይሹ ለዚህ ችሎታዋ በብሄራዊ ትያትር በምትሰራበት ወቅት ከእነ ታደሰ ወርቁ፣ ጌታቸው አብዲ፣ ዓለምፀሐይ ወዳጆ እና ከሌሎችም ያገኘችው ልምድ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳደረገላት ትናገራለች፡፡ ነዋሪነቷን ባደረገችበት በኔዘርላንድስ ውስጥም የኢትዮጵያን ባሕላዊ ጭፈራዎች ለዜጎቹ የምታስተምር ሲሆን በኬሪዮግራፈርነትም ጥቂት የማይባሉ መድረኮችን አሰናድታለች፡፡
እ.አ.አ ጥቅምት 26 2018 የለቀቀችው ‹‹ዳዴ›› የተሰኘ አራተኛ አልበሟን ‹አርክ ሚውዚክ› ከተባለ ድርጅት ጋር የሠራች ሲሆን በውስጡም 13 ዘፈኖች ተካተውበታል፡፡ አልበሙ ‹ዳልቶን› በተባለ ስቱዲዮ ኤንዶቨን ኔዘርላንድስ ውስጥ የተቀረፀ ሲሆን በትዝታ ስልት የተዜመው የአልበሙ መጠሪያ የሆነው ዳዴ ጨምሮ ይቅርታ፣ የታል፣ አንተነህ፣ ሀይሎጋ፣ ወላይታ እና ገለቱማ የተሰኙ የኢትዮጵያን ቅኝቶ ከዘመናዊ ስልቶችና መሣሪያዎች ጋር በማዋሃድ የተሰሩ ሙዚቃዎችም ተካተዋል፡፡
አልበሙ በተለቀቀበት የመጀመሪያ ወር ‹በትራንስ ግሎባል የሙዚቃ ሰንጠረዥ› ሰባተኛ ደረጃን ያገኘ ሲሆን በኅዳር ወር ደግሞ ስድስተኛ ደረጃን ተቀዳጅቶ ቆይቷል፡፡ ትራንስ ግሎባ ባወጣው የ2018 ምርጥ መቶ አልበሞች ዝርዝር ውስጥም የምንይሹ ዳዴ አልበም 40ኛ ደረጃን አግኝቷል፡፡
ቅጽ 1 ቁጥር 5 ታኅሣሥ 6 ቀን 2011