“ሃይማኖት በሰዎች ድካም፣ ስቃይና መከራ ውስጥ ትርጉም ይፈልጋል።”

0
1346

ከሃምሳ አምስት ቀናት የጾም ቆይታ በኋላ የሚመጣውና በክርስትና እምነት በድምቀት የሚከበረው የትንሣኤ በዓል ዘንድሮ እንደቀደሙት ዓመታት በጥብቅ ቤተሰባዊና ማኅበራዊ መስተጋብር አይከበርም። ይህ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓሉን በሚያከብሩ የዓለም አገራት ዘንድም የታየ ነው። ከበዓሉ ቀድሞ የሚገኘውን ስቅለት እንዲሁም ሰሞነ ሕማማትን የክርስትና እምነት ተከታዮች በየቤታቸው ሆነው በትዕይንተ መስኮቶቻቸው አሻግረው እየተመለከቱ ጸሎትና ምስጋናቸውን እንዲያደርሱ ግድ ብሏቸዋል። የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ።

የዛሬው የአዲስ ማለዳ እንግዳ በዓሉንና ወረርሽኙን በሚመለከት ሐሳባቸውን አካፍለዋል። ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ በሕክምና ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል። ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በሥነ መለኮት ተመርቀዋል። በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሕጻናት ሕክምና ስፔሻሊቲያቸውን የሠሩ ሲሆን፤ በአሁን ሰዓት በአርሲ ዩንቨርስቲ የሕክምና ሳይንስ በማስተማር እና በሕክምና ሙያ በማገልገል ላይ ይገኛሉ፤ ዲያቆን ዶክተር አቤል ኃይሉ።

‹የማዕዘን ራስ› የተሰኘ ሃይማኖታዊ መጽሐፍ ለንባብ ያበቁ ሲሆን፣ እንዲሁም ‹ጤና ይስጥልኝ› በተባለው መጽሔት ሕክምና አምድ ላይ በተከታታይ ጽሑፎችን ለንባብ በማድረስ ይታወቃሉ። ከዚህም ሁሉ ጎን ለጎን በዳራጎት ሚዲያ ውስጥ በማኔጂንግ ዳይሬክተርነት እያገለገሉ ይገኛሉ።

የትንሣኤ በዓልን በሚመለከት እንዲሁም ከሳይንስና እምነት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳዮች በማንሳት የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጋር ተከታዩን ቆታ አድርገዋል።

በቅድሚያ እንኳን አደረስዎ?
አሜን፤ ሁላችንንም እንኳን አደረሰን።

ፋሲካ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበር በዓል እንደሆነ ይታወቃል። ይህን በዓል ትልቅ ያደረገው ምንድን ነው?

ፋሲካ ክርስቶስ የመጣበት ዓላማ የተፈጸመበት ነው። ማንም ሰው ለመሞት አይደለም የሚወለደው። መሞት የሕይወት አንድ ክፍል ስለሆነ ነው የምንሞተው። በዋናነት በዚህች ዓለም ላይ ለመሞት ብሎ ብቻ የመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ለምንድን ነው የሚሞተው ሲባል ደግሞ፣ የሞት ሞትን ትሞታለህ ተብሎ የተፈረደበት አዳም ያንን ሊሻገር የሚችለው በጌታ ሞት ብቻ ስለነበር ነው።

ጌታ ከሞተ ለምን ሰዎች ይሞታሉ ብለው የሚጠይቁ ይኖራሉ። እኛ ሞት የምንለው ከእግዚአብሔር ለዘለዓለም መለየትን ነው እንጂ የሥጋ ሞትን አይደለም። ሥጋዊ ሞት ለማናችንም አይቀርም። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳም ላይ የተፈረደበትን ከእግዚአብሔር ተለይቶ መኖርን፣ያስቀረለት በሞቱ ነው።

ሞት መሸነፍ ነበረበት። ሞት ተሸነፈ የሚባለው ደግሞ የሞተ ሰው ሲነሳ ነው። እናም ጌታ ሞቶ በመነሳቱ ምክንያት ሞት ራሱ ሞተ ማለት ነው። ሞት ድል በመንሳት ተዋጠ የተባለው ለዛ ነው። ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ ድል መንሳትህ የት አለ? ብሎ አስቀድሞ ነብያት ትንቢት የተነገረውን የፈጸመው ጌታችን ነው።

ሞቶ በመነሳቱም ምክንያት ሞትን ነጭ አድርጎልናል። በድሮ ዘመን የነበሩ ሰዎች ሞትን ይፈሩ ነበር። ምክንያቱም ከሞቱ በኋላ ወደ ሲኦል ነው የሚሄዱት። ጸሎቱ ሁሉ አቤቱ ወደ ሞት አትውሰደኝ ነበር። ከክርስቶስ መምጣትና ትንሣኤ በኋላ ግን ሞትም ጥቅም ነው ተብሏል። ምክንያቱም ብንሞት ሊያስነሳን ከሚችለው ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንተባበራለን፣ ለዘለዓለም ከእርሱ ጋር እንኖርበታለን። እናም እንደ ክርስትያን ከመቃብር በስተጀርባ ዘለዓለማዊ ሕይወት እንደሚጠብቀን እናውቃለን።

እውነት ነው ተወልዷል፣ ስለተወለደ ብቻ ግን ዓለም አልዳነም። ብዙ ተአምራት አድርጓል፣ በዛ ብቻ ግን የሰው ልጅ አልዳነም። ብዙ ፈውሶችን አምጥቷል፣ ብዙ ሰዎችን አስተምሯል። ግን የመጣበት ዋና ዓላማ ሞቶ ዓለምን ማዳን ስለሆነ፣ ትንሣኤን ከሁሉም በዓላት በላይ ትልቅ የሚያደርገው ይህ ነው። መስቀል ላይ ‹ተፈጸመ› ነው ያለው።  የሰው ልጅ መዳኑ የተበሰረበት ወይም እርግጠኛ የተሆነበት ጌታችን ስለተነሳ ነው። ለበዓላት ሁሉ እንደማሳረጊያም ጭምር ነው የምንቆጥረው።

ቅዱስ ጳውሎም ‹ጌታ ካልተነሳማ ስብከታችን ሁሉ ከንቱ ነው› ይላል። ይህ ማለት ያለ ትንሣኤ እምነታችን ከንቱ ነው። ክርስትያኖች ተስፋ ቆርጠው እንደገና ወደ ተስፋ የመለሳቸው የክርስቶስ መነሳት ነው። ትንሣኤ የሌለበት ክርስትና የለም። ጌታ ከተነሳ በኋላ ነው ክርስትናም የተስፋፋው። እናም ዋናው ምክንያት ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣበት ምክንያት የተፈጸመበት፣ እኛም ያንን የተረዳንና በግልጽ ያወቅንበት፣ የዳንንበት፣ ያም የተረጋገጠበት መሆኑ ነው ትልቅ በዓል ያደረገው።

የፋሲካ በዓል ታስቦ ብቻ ሳይሆን በተግባር በሚገለጥ መንገድ እንዲከበር የሚጠበቅ በዓል እንደሆነ ይነገራል። አሁን ያለው ሁኔታ ከከፋና ከበረታ፣ ከፍቅር አንጻር ከሕዝብ ምን ይጠበቃል?

ፋሲካ የፍቅር በዓል ነው። በፍቅር ደግሞ አንዱ የአንዱን ሸክም የሚሸከምበት ነው። ሁኔታው ሌላ ዓለም ላይ እንዳየነው እየበረታ የሚመጣ ከሆነ፣ የምንተሳሰብበት በዓል ሊሆን ይገባል። ፋሲካ በጋራ የሚከበር በዓል ነው፣ አሁን ደግሞ በበሽታ ምክንያት በአካል መቀራብ አይፈቀድምና፣ በመንፈስ በጋራ ሆነን አንዱ አንዱን መርዳት ክርስትያናዊ የውዴታ ግዴታው ነው።

ስለዚህ እርስ በእርሳችን መረዳዳት፣ አንዳችን የሌላችንን ሸክም የምንሸከምበት ሊሆን ይገባል እላለሁ። ፍቅር ደግሞ ዘር፣ ቀለም፣ ሃይማኖት ወይም የኑሮ ሁኔታን አይመርጥም። ስለዚህም በዚህ በዓል ሙስሊም ክርስትያን ወይም ሌላ እምነት ሳንል፣ ሁላችንም እርስ በእርሳችን የምንረዳዳበት መሆን አለበት። መረዳዳታችንና ፍቅራችን በአንድ ሃይማኖት ወይም ደግሞ በአንድ ዘርና ብሔር አጥር ውስጥ ማጠር የለብንም።

ፋሲካ በክርስትና የደስታ በዓል ነው፣ ዘንድሮ ግን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተከስቷልና፣ በዓሉን በምን መንፈስ ነው ማክበር የሚያስፈልገው?

የፋሲካ በዓል መንፈስ ደስታ ነው፤ ጌታ ተነስቷልና። በዓሉን በተስፋም ነው ማክበር ያለብን። ፋሲካ ያስተማርን ነገር ቢኖር እሱ ነው። ኢ-ፍትሐዊነት ክርስቶስን ወደ መቃብር አውርዳ ለማስቀረት አለመቻሏን ነው። ለክርስትያን ፋሲካ ብዙ መልእክት አለው። ተሰቅሎና ሞቶ ቢቀር ኖሮ፣ ክርስትና የአንድ ምስኪን ሰው ታሪክ ነበር የሚሆነው። ወይም ደግ ሰው አይበረክትም ብለን ወደ ኦሪት እንመለስ ነበር።

ፋሲካ ግን እንደዛ አይደለም። ‹ሞት ሆይ መውጊህ የት አለ? ሲኦል ሆይ ድል መንሳትህ የት አለ?› ብለን መዘመር የምንችልበትን አቅም አጎናጽፎናል። ስለዚህ የፋሲካ መሠረታዊ ትርጉሙ ራሱ ማለፍ ማለት ነው። በኢንግሊዘኛው ፋሲካን ሲተረጉመው ‹Passover› ነው የሚለው። ስለዚህ ይህንን ክፉ ጊዜ እንደምናልፈው የጸና እምነት አለን ማለት ነው።

አንደኛ ብዙ ሰዎች ቢሞቱም ነገ የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ እርግጠኞች ነን። ከዚህ የባሱ ጊዜያትም ታልፈዋል። ስለዚህ በዓሉ ከቀራንዮ ማግስት በኋላ እንደመምጣቱ፣ ይህ በዓል ሊያስተምረን የሚገባው ነገር ይህንን ጊዜ እንደምናልፍ መረዳትን ነው። እናም በተቻለ መጠን በምንናገረው ነገር ሁሉ ለሰዎች ተስፋ ልንሰጣቸው ይገባል። ይህም እንደሚያልፍ አስረግጠን ልንነግራቸው ይገባል።

ሁኔታው በበዓሉ ከመብላት ከመጠጣት ባይከለክለንም፣ ሰው ከምግብ በላይ ተስፋን ነው የሚፈልገው። በተለይ ተስፋ በመቁረጥና በጽኑ ሐዘን ውስጥ የሚገኙ አሉ። ምናልባት እኛ አገር አሁን ባለንበት ሁኔታ ይህ ነገር ያን ያህል ላይታይ ይችላል። እንደ ዓለማቀፍ ግን እጅግ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ያሉ ሰዎች አሉ፤ ከጭንቀት የተነሳ ራሳቸውን የሚያጠፉ አሉ። በዚህ ጊዜ ልላቸው የምፈልገውም፣ እንደምናልፍ ነው።

እንደውም ፖፕ ፍራሲስ ሲናገሩ፤ ማንም ሰው የማይቀማን ነገር አለ ሲሉ ነበር። ይህም ተስፋ ማድረግን ነው፣ ነው ያሉት (The Right to Hope) ስለዚህ ይህን በዓል የምናከብረው በተስፋ ነው። ይህም አልፎ ነገ የተሻለ ቀን ይመጣል ብለን በማሰብ በትልቅ ተስፋ ልናከብረው ይገባል።

እንደ በርካታ ሃይማኖታዊ በዓላት ሁሉ ፋሲካን የሚከተሉ በርካታ ማኅበራዊ ክዋኔዎች/በጎ ልማዶችም አሉን፣ አሁን ለጊዜው (በኮሮና ምክንያት) መታጎላቸው ከባድና ቀጣይ ተጽእኖ ያሳድር ይሆን?

ይህ ቫይረስ እንደ አገር አይደለም እንደ ዓለም ብዙ ማኅበራዊ ተጽእኖ ጎትቶ ማምጣቱ አይቀርም። በዓለም ዐቀፍ ደረጃ እንኳ ስናየው የዓለምን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መዘውሩን በብዙ መንገድ አቅጣጫውን ያስቀይራል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ አሁን የመጣ ነገር አይደለም።

ለምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ስናይ፣ በምድር ላይ ረሃብ ሆነ ይላል። በዚያ ጊዜ ብቸኛ ምግብ የነበረባት አገር ግብጽ ነበረች። በዮሴፍ በሳል አመራር ምክንያት ምግብ በግብጽ በደንብ ተገኝቶ ነበር። እናም እስራኤላውያን ከከነዓን ተነስተው ምግብ ፍለጋ ግብጽ ወርደዋል። ምግብ ፍለጋ ወርደውም በግብጽ 230 ዘመን ኖረዋል፤ ከባርነታቸው በሙሴ እስኪወጡ ድረስ።

እናም እንደ ዓለማቀፍ የሚከሰቱ ነገሮች፣ ባህልን ይቅርና የምንኖርበትን አገር እስከ መጨረሻ የሕዝብ አሰፋፈሩንና ቁጥሩን (ዲሞግራፊውን) ሊቀይሩ ይችላሉ።

አሁን ስለ ቫይረሱ አስቸጋሪ የሆነው ነገር መቼ ነው በሽታው የሚያበቃው፣ እስከ መቼ ነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚቆየው የሚለው ላይ ማናችንም እርግጠኛ አይደለንም። እናም አንደኛው ከፋሲካ በኋላ የሚኖረው ክዋኔ ሰርግ ነው። ይህን የሰርግ መርሃ ግብርን ማጠፍ ግድ ሊሆንብን ይችላል ማለት ነው። ይህ ግን ጊዜያዊ የሆነ ተጽእኖ ነው።

‹አክፋይ› የሚባል በዓል አለን፤ ከዘመድ የምንጠያየቅበት። እየቆየ ሲሄድ እነዚህን ነገሮች ላይ ማኅበራዊ ተጽእኖ ሊኖር ይችላል፤ በጣም ከቆየ ማለት ነው። ግን እኔ ይቆያል ብዬ አላስብም። እየተማርን ያለነው ነገር ቫይረሱን መቆጣጠር እንደሚቻል አይተናል፣ በቻይና። ክትባቱም በቅርብ በአራትና በአምስት ወር  ማግኘት የሚቻል ከሆነ፣ ምናልባት  በሽታው በቶሎ በቁጥጥር ስር ከዋለ ማኅበራዊ እንቅስቃሴያችን ላይ ያን ያህል ተጽእኖ ይኖረዋል ብዬ አላስብም።

ኹለተኛ ደግሞ ባህል ማለት ለብዙ ዘመን ከሰው ጋር አብሮ የኖረ ነው። እናም እንዲህ ለብዙ ዘመን የቆየ ባህል በሦስትና አራት ወራት ችግር ይፈታል ብዬ አላስብም። ከቆየ ግን አይደለም ባህላችንን የኑሮ አሰፋፈርን ይለውጠዋል። ምንም ጥያቄ የለውም።

ኮሮና የፈጣሪ ቁጣ ነው የሚሉ አሉ፣ በአንጻሩ አይደለም ሲሉ ሳይንሳዊ ትንታኔ ብቻ የሚሰጡም ይሰማሉ፤ ሆነ ተብሎ የተፈጠረ ነው የሚሉም ይገኛሉ። በዚህ ላይ እርሶ የሚሰጡት ሐሳብ ምንድን ነው?

ሆነ ተብሎ የተፈጠረ ነው የሚለውን እኔ አላውቅም። በሴራ ደረጃ ነው የምንሰማቸው፤ ተፈጥሮም ከሆነ የፈጠሩት ናቸው የሚያውቁት።

ሳይንስና እምነት የሚስማሙበትም የሚለያዩበትም መንገድ አለ። ይህም የሚመለከቱበት መነጽር ነው። ቀላል ማስረጃ ስናስቀምጥ፣ መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ ምዕራፍ አምስትና ስድስት ላይ፣ ፍልስጤማውያን ከእስራኤላውያን ታቦቷን ነጥቀው በወሰዱ ጊዜ እግዚአብሔር በእባጭ መታቸው ይላል። እባጭ የሚባለው በኢንግሊዘኛው ‹Plague› የሚባል በሽታ አለ። እና ይህ በሽታ የሚመጣው አይጦች ከቁንጫዎች የሚወስዱትን ባክቴሪያ፣ ወደ ሰው ሲያስተላልፉ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ላይ በሽታው ለምን መጣባቸው ሲል፣ ሳይገባቸው ታቦቷን ስለነጠቁ እግዚአብሔር በቁጣ ነው ያመጣባቸው ይላል። ሳይንስና እምነትን እዚህ ጋር ተመልከቺ። ሳይንስ በሽታው የተከሰተው ከአይጥ በመጣ ባክቴሪያ ነው እያለ መንገዱን ያብራራል።

ሳይንስ ሕይወት ላይ ትርጉም አይፈልግም፣ የሆነውን ነገር ማብራራት ነው። እውነት ነው እግዚአብሔር ሰዎቹ ላይ በሽታውን ያመጣው ከአይጦች በተነሳ ቁንጫ ነው። ግን በሽታው ራሱ ሲጀመር ለምን በዛ ጊዜና ሰዓት ላይ፣ ከቃልኪዳን ታቦት ጋር አገናኝቶ መጣ ሲባል፣ የቃልኪዳኗን ታቦት ስላላከበሩ ነው።

የኮሮና ቫይረስንም በኹለት መንገድ ልንመለከተው እንችላለን። የእግዚአብሔር ቁጣ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ማናችንም እርግጠኛ ሆነን መናገር አንችልም። ግን እንደ ቅዱስ መጽሐፍ ስንመለከት፣ በሽታ መጀመሪያ የተፈጠረበት ምክንያት አዳም ከሳተ በኋላ የመጣበት የባህሪ መጎስቆል ነው።

ባህሪው ጎሰቆለ ስንል ደካማ ሆነ ማለታችን ነው። ደካማ ስለሆነ የተለያዩ ኃይላት ሊሠለጥኑበት ይችላሉ። መሠረታዊ ነገሩ ይህ ነው። እግዚአብሔር ደግሞ በሽታን ለተለያየ ነገር ሊጠቀምበት ይችላል። ለምሳሌ እግዚአብሔር ሰዎችን ሊቀጣበት ወይም ደግሞ ሊያርምበት ይችላል።

አባት አንደኛው ልጁን ሲገረፍ ሌላው ልጁ በተገረፈው ልጅ ምክንያት ሊማር ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዕብራውያን ምዕራፍ 12 ላይ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው ይላል። አባቱ የማይቀጣው ወይም ሳይቀጣ ያደገ ልጅ የለም። አባት ልጁን የሚቀጣው ስለሚጠላው አይደለም፣ ይልቁንም እንዲስተካከልለት ስለሚፈልግ ነው።

ስለዚህ በዚህ በሽታ ምክንያት ሰዎች ሲደነግጡና የእግዚአብሔርን ሥም መጥራት ሲጀምሩ ሰምተናል። እና ለማነቃቃት፣ ስለሚወደን፣ በአባታዊ ቅጣቱ አባታዊ አርጩሜው ሰዎችን ሊያስተካክልበት ይችላል።

ኹለተኛው ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስንመለከት በሽታ የሚመጣበት ምክንያት ከፍ ላለ ክብር፣ ለፍጹምነት ሊያበቃን፣ ጥንካሬ፣ ፍቅርና ርህራሄ ሊያስተምረን ሲሻ ነው። የኢዮብን ቁስል ስንመለከት የኃጢአት ውጤት አይደለም። ኢዮብ ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ፣ የተሻለ እንዲበረታ ያሳየበት መንገድ ነው። እናም እግዚአብሔር በሽታን በዚህ መንገድ ሊያመጣ ይችላል።

ሦስተኛ በሽታ የሚመጣብን መሞት ስላለብን ነው። ዘላለማዊ አይደለንም፣ ሟች ነን። ሰው ዝንተ ዓለም ስለማይኖር፣ አንዱ ከዚህች ምድር ወደ ፈጣሪ የሚጠራበት መንገድ በሽታ ነው።

በአጠቃላይ ግን እንደ ክርስትያን መነሳት ያለበት አንድ ነገር አለ። በመጽሐፍ ቅዱስ ሉቃስ ምዕራፍ 13 ላይ፣ በዛን ጊዜም ሰዎች መጥተው ጲላጦስ ደማቸውን ከመስዋዕታቸው ጋር ስለደባለቀው ስለገሊላ ሰዎች አወሩለት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፣ እነዚህ የገሊላ ሰዎች ይህ ስለደረሰባቸው ከገሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ኃጢአተኛ የሆኑ ይመስላችኋልን? እላችኋለሁ አይደለም። ነገር ግን ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁም ትጠፋላችሁ ይላል።

ይህ ማለት፣ በስፔን ወይም በጣልያን፣ በአሜሪካ እየሆነባቸው ያለው በኃጢአታቸው ነው የሚል አለ። እናም ይህ ከቀደመው ጋር ተመሳሳይነት አለው። እነርሰ እየሞቱ ያሉት ከእኛ እዚህ አገር ካለነው የበለጠ ኃጢአተኛ ሆነው ነውን? አይደለም። ነገር ግን ሁላችንም ንስሐ ባንገባ መጨረሻችን ጥፋት ነው የሚሆነው። በዛ ቤት እሳቱ ሲነሳ እኛም ጋር ያ እንደሚመጣ አውቀን፣ በዚህች ጊዜ ውስጥ ልናስተውል ይገባል።

እንደውም በዛው የመጽሐፉ ክፍል ወረድ ብሎ እንዲህ ይላል። ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው። ፍሬ ሊፈልግባት መጥቶ ምንም አላገኘም። የወይን አትክልት ሠራተኛውም እነሆ ከዚህች በለስ ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም አላገኘሁም፣ ቁረጣት። ስለምን መሬቱን ታጎሳቁላለች አለው።

እሱም መልሶ ‹ጌታ ሆይ! ዙሪያውን እስክኮተኩትላትና ፋንድያ እስካፈስላት ድረስ በዚህች ዓመት ደግሞ ተዋት፣ ወደፊት እንድታፈራ ደኅና ነው፣ ያለበለዚያ ግን ትቆርጣታለህ አለው›› ይላል። እኔ የማስበው ሁልጊዜም ቢሆን ጌታ ከእኛ ፍሬ ሊፈልግ ይመጣል። ግን ደግሞ ባዶ ስንሆን ቁረጣት የሚል መልእክት ይወጣል።

ግን በቅዱሳኑ ምልጃ ይህችን ዓመት ተዋት የተባልን ብዙ ሰዎች ያለን ይመስለኛል። ምናልባት  ይህ በሽታ ያላገኘን ሰዎች፣ ፍሬ እንድናፈራ የተተውንበት ዓመት እንደሆነ ልናውቅ ይገባል። እና ሁላችን በአንክሮና በማስተዋል፣ አሁን የተፈጠረውን ነገር መመልከት ነው።

እናም ሳይንሱ የተለወጠ ቫይረስ ነው የበሽታው መምጫ ነው የሚለው። ሳይንሱ ውሸት አይደለም፣ በቫይረስ እንደሚተላለፍ ደርሰውበታል። እንዳልኩት ሰዎች በተለያየ ምክንያት ወደሞት ሊጠሩ ይችላሉ። እናም ሳይንሱም አልተሳሳተም። ሳይንስ በሰዎች መከራና ድካም ላይ ምንም ዓይነት ትርጉም አይፈልግም፤ የጥናቱ አካልም ሆነ አቅጣጫ አይደለም። ሃይማኖት ከሳይንስ የሚለየው እሱ ነው። ሃይማኖት በሰዎች ድካም፣ ስቃይና መከራ ውስጥ ትርጉም ነው የሚፈልገው።

ኹለቱን በዚህ አቅጣጫ ነው ማጤና ያለብን። ዋናው መልእክት ግን፣ እኛ ጻድቅ ሆነን ወይም እነርሱ ከእኛ የባሰ ኃጢአተኛ ሆነው አይደለም ይህ የሆነው። ይልቁንም ሁላችንም ፍሬ እንድናፈራበት መልካም ነገረ ማድረግና ለሌሎች ማዘን አንዱ ሸክም መሸከም ነው እንጂ ያለበት፣ አላስፈላጊ የሆነ እግዚአብሔር ብቻ መፍረድ የሚገባው ላይ እኛ ፍርድ ልንሰጥ እንደማይገባ ማወቅ አለብን።

ሰዎች ተጠንቀቁ ሲባል ወይም አካላዊ መቀራረቡን ለመቀነስ ወደ አብያተ ክርስትያናት አትሂዱ ሲባሉ፣ መፍራትና እምነት ማጣት አድርገው ይቆጥሩታል። ጥንቃቄ ከእምነት ማነስ ጋር ይገናኛል?

አንድ በእምነት ውስጥ ያለ ሰው ሊኖረው የሚገባ አንዱ ነገር ጥንቃቄ ነው። እምነት በሰው ልጆች ላይ ያለን ንዝህላልነት ሊያጠፋ ይገባል። እምነት የተሰጠን ፈታ ብለን ሌሎች ሲጠነቀቁ እኛ በዋልጌነት እንድንኖር አይደለም። ይልቁንም አብዝተን ልንጠነቀቅ የሚገባን እምነት ውስጥ ያለን ሰዎች ነን ብዬ አስባለሁ።

ይህን ስንል እንፍራ ማለት አይደለም። መጠንቀቅ አንድ ነገር ነው፤ አለመፍራት ሌላ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ ኦሪት ዘጸዓት ምዕራፍ 21 ቁጥር 33 ላይ ስናነብ፣ ሰው ጉድጓድ ቢከፍት ወይ ጉድጓድ ቢቆፍር፣ ባይከድነው፣ በመንገደ ያለፈ በሬ ወይም አህያ ቢወድቅበት፣ የጉድጓዱ ባለቤት ዋጋቸውን ለበሬው ወይም ለአህያው ባለቤት ይክፈል ይላል።

ያ ሰው ጉድጓድ የቆፈረው ወይ ለመጸዳጃ ቤት፣ ወይ ከሰል ሊያከስልበት አስቦና ፈልጎ፣ አልያም ለውሃ ማቆሪያ ካልሆነ ለሌላ ለተለየ ሥራ ይሆናል። ግን መክደን ግዴታው ነው። እኔ የቆፈርኩት ለመልካም ነገር ነው ተብሎ አይተውም። የሌላ ሰው አህያ ቢወድቅና ቢሞት፣ መክፈል እንዳለበት ያስቀምጣል።

ሰዎች ለመልካም ብለው በሚያደርጉት ነገር ውስጥ ራሱ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ነው መልእክቱ። ቤተክርስትያንና የአምልኮ ስፍራ መሄድ መልካም ቢሆንም፣ ጥንቃቄ አድርጉ ከተባለ ሰው ጥንቃቄ ማድረግ አለበት። ሰዎች በእለት ተእለት ኑሯቸው ይህን ገንዘብ ሊያደርጉ ይገባል። ‹ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ› የሚለው ተረታችን የሚያስረዳው፣ ጤናችን የሚጠበቀው ስንጠነቀቅ እንደሆነ ነው።

ይህ ሐሳብ እንዳለ ይዘን አሁን ወደተፈጠረው ነገር ስንመጣ፣ ቤተክርስትያን አትምጡ የተባልነው በሽታው የሚተላለፈው በሰዎች መቀራረብ ምክንያት ስለሆነ ነው። እንጂ መንግሥት እምነቱን ስለጠላ ወይም በክርስትያኖች ላይ ብቻ ተለይቶ የተፈጸመ ነገር አይደለም። አትሂድ የተባለውም በሽታው በቁጥጥር ስር እስኪውል ድረስ ነው።

እናም አንድ ማወቅ ያለብን፣ እግዚአብሔር ሰዎችን በተለያየ መንገድ ያድናል። በራሱ በተዓምር ሊያድነን ይችላል፣ በወታደር ሊያድነን ይችላል፣ በካህን ሊያድነን ይችላል፣ ወይም እንቅልፍ ውስጥ ሆነን ሊያድነን ይችላል። የኮሮና ቫይረስ የሚተላለፍበትን መንገድ ማወቃችን በራሱ፣ እግዚአብሔር እኛን የሚጠብቅበት መንገድ ነው። የሚተላለፍበትን መንገድ ባናውቅኮ ሁላችን ልንሞት እንችል ይችላል።

በኦሪቱ ጊዜ ፋሲካን እስራኤላውያን ሲያከብሩ ከቤት እንዳትወጡ ተብለው ነበር። መቃኑንና ጎበኑን ደም ቀቡ፣ ከዛም ቀሳፊው መልአክ አይነካችሁም ተባሉ። ማንም ከቤት አይውጣም ተብሏል። ችግር የለም እግዚአብሔር ይጠብቀኛል ብሎ ከቤት ቢወጣ፣ ሞት ይጠብቀዋል። እናም ሰዎች መጠንቀቅ አለባቸው።ሰው ሕይወቱን መጠበቅ አለበት።

ማቴዎስ ምዕራፍ 10 ላይ በአንዲት ከተማ መከራ ቢያሳይዋችሁ ወደሌላይቱ ሽሹ ይላል። መከራ ቢያሳይዋችሁ ዝም ብላችሁ ተጋፈጡ አይደለም፣ ሽሹ ነው የተባለው። በዘመነ ሰማዕታት ጊዜ እንደውም ክርስትያኖች እየተገደሉ ሲቸገሩ፣ ዋሻ ውስጥ ነበር የሚኖሩት። ጸሎታችንም ሁሉ ደግሞ ወደ ፈተና አታግባን ነው፤ እንጂ በሽታና ፈተና አምጣ አይደለም።

ሌላው ነጥብ በቤት ውስጥ ሆኖ አምልኮ መቀጠል እንደሚችል ማወቅ አለበት። ዳዊት ምድር ሁሉ የእግዚአብሔር ናት ይላል። እናም ጸሎትና ስግደታችንን፣ ምህላችንን ቤት ውስጥ መቀጠል አለብን።

ሌላው ሰው ማወቅ ያለበት ቤተክርስትያን በሰው ልጅ መጥፋት አትተባበርም። ይልቁንም እኛና መንፈስ ቅዱስ አዘናል ብሎ የመናገር ሥልጣን ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ በሚለን መሠረት መታዘዝ እንደሚገባ ማወቅ አለብን። እምነት ውስጥ መሆን ንዝህላል መሆን አይደለም። ይህ ብቻ ሳይሆን አለመታዘዝ ያስነቅፋል። ሰዎች ከዚህ ጋር ባያገናኙት፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ራሱ መመሪያ እየሰጠ ነው፣ እኛ ከእነርሱ በላይ አናውቅምና፣ ላወጡት ሕግ የመታዘዝ ግዴታ አለብን።

 ኢትዮጵያ በብዙ መለያየት መካከል ነበረች፤ በብሔር፣ በሃይማኖትና በፖለቲካ ብዙ ግጭቶች ነበሩ። አድዋን እያነሱ የጋራ ጠላት ነው አንድ የሚያደርገን የሚሉ እይታዎች ይሰማሉ። ኮሮና የጋራ ጠላት ሆኖ በጎ ነገር ያወጣልን ይሆን?

ዘር፣ ቀለም፣ ሃይማኖት የማይለዩ ጠላቶች ሲመጡ ሰዎችን አንድ ማድረጋቸው አይቀርም። በቤተሰብ እንኳ ስታይው፣ የተጣሉ ዘመዳሞች ቤተሰብ ውስጥ ለቅሶ ሲፈጠር ተነጋግረው የማያውቁት ይታረቃሉ። ለቅሶ አንድ አደረጋቸው ማለት ነው።

መከራ ሕዝብን ይሰበስባል። የትኛው እንደሚጠቅመንና የትኛው እንደሚጎዳንም እናውቅበታለን። ዙሪያችንን እንድናጤነው፣ ከመለያየትና ከመበላላት ይልቅ አንድነት፣ መተባበርና መረዳዳት ነገን በተሻለ መንገድ እንደሚያሻግረን ያስተምረናል።

እኔ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለምም በጎ ነገር ያመጣል ብዬ አስባለሁ። ‹አቅምህን የምታውቀው ባላጋራህን ባሳደድክበት ጊዜ ሳይሆን ከሱ በሸሸህበት እለት ነው› ይባላል። ኮሮና ያመጣብን መሸበርና ፍርሃት ነገሮችን በጥልቀት እንድንፈትሽ፣ የትኛው ጋር እንደጎደለን ለማየት መንቃት ይፈጥራል። ብዙ ግኝቶችና ድሎች ዋዜማቸው መራራ የሆነ ለቅሶና ሽንፈት ነው።

ምናልባት ልትጠፋ የደረሰች ከተማ ነጋሪት ቢጎሰምላት አትሰመም እንደሚባለው ሆኖ ነገሩን ችላ ካላልነው በቀር፣ ይህ ቫይረስ ምናልባት ልጅ የሚያስታቅፍ ምጥ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ። ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ዓለምን አንድ እያደረገ ነው። ትልቁ የሚበልጠው ነገር ደግሞ ሰው እንደሆነም ተምረንበታል። ሰዎች ዘርና ቀለም፣ ብሔርና ሃይማኖትን፣ ሌላ ምንም ላይ ሳያተኩሩ እርስ በእርስ ሲረዳዱ ከማየት በላይ የሚያስደስት ነገር የለም። እና ይህ ቫይረስ ሰው መሆንን እንዳስተማረን አስባለሁ።

ስለ ዳረጎት መጽሔት እናንሳና እንተዋወቃት? መች ተመሠረተች፣ ምን ዓይነትስ ይዘት አላት?

ዳረጎት መደበኛ በሆነ መልኩ ከተመሠረተ ስምንት ዓመት ሆኖናል። አሁን በተደራጀ መልኩ በቴሌግራምና በማኅበራዊ ሚድያ ማገልገል ከጀመርን ግን ሦስት ዓመት ነው። ስድስተኛ እትማችንም ከሳምንት በፊት ወጥቷል።

ዳረጎት ማለት ከራት በኋላ እንደማጠንከሪያ የሚቀርብ ቀለል ያለ ምግብ ነው። አሁን ላይ ‹ዲዘርት› ሊባል ይችላል። ለሚድያችን ይህን ሥያሜ የሰጠንበት ምክንያት፣ ቀለል ያለ ከራት በኋላ እንጂ ራትን የማይተካ ነውና፣ ቤተክርስትያን ባህረ ጥበባት እንደመሆኗ መጠን፣ እዛ ላይ የምንጽፈው ነገር ትምህርቷን ሙሉ ለሙሉ ይገልጻል ብለን ስለማናምን ነው። ዋናውን ራት ከሊቃውንት ቤተክርስትያን፣ ከመጻሕፍት ምስክርነትና ከደጋግ አበው ሕይወት፣ ከቤተክርስትያን ድልና ተጋድሎ እየተማሩ የእኛን ዳረጎት እንዲቀምሱልን ለማለት ነው።

ዓላማው ሰዎች እውቅትን መሰረት ባደረገ እምነት እንዲኖሩ፣ ስለቤተክርስትያናቸው እንዲያውቁ ቁጭትና እልህ፣ መነሳሳት የፈጠረ ማኀበር ነው። ተደራሽነቱ በቴሌግራም ዳረጎት ሚድያ (Daregot Media) ብለው ቢፈልጉ ያገኙታል፣ ዌብሳይትም አለው፣ ፌስቡክና ኢንስታግራም ላይም ይገኛል። ዘጠኝ ጸሐፊዎች አሏት፣ ከተለያየ ቦታ ሆነው የሚጽፉ። ቀለል ባለ መልኩ ነገረ ሃይማኖት፣ ማኅበራዊ ሕይወት፣ ተስፋን የሚያጭሩ ጽሑፎች ነው የምንለቀው።

ወደፊት በዩትዮብ እንዲሁም በቴሌቭዥንም ለመሥራte ሰፊ እቅድ ነው ያለው። እሱን ቀስ በቀስ በሂደት የምናየው ነው።

አዲስ ማለዳ የሴቶችን ጉዳይ በትኩረት ትከታተላለችና የመጨረሻ አንድ ጥያቄ ላንሳ፣ ዳረጎት ላይ የሴቶች ተሳትፎ ምን ይመስላል?

ሴቶችን በተመለከተ በእቅዳችን ይዘናል። አንድ ጉባኤ ውስጥ የምናገለግል፣ የአንድ መምህር ልጆች ነን የመሠረትነው። አጋጣሚ ነው ሴቶች ያልተገኙበት። እንጂ አንደኛው እትማችንም በሴቶች ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነበር፣ ስለሴቶችም ጉዳይ እናነሳለን። በፌሚኒዝም ዙሪያም እየተጻፉ ያሉ መጻሕፍት አሉን። ተጋባዥ ጸሐፍያንንም እንቀበላለን፣ መጻፍ ለሚፈልጉም እድሉ ክፍት ነው።

በዚሁ ከተነሳ አይቀር በትንሣኤ ሴቶች ትልቅ የሆነ ቦታ የያዙበት በዓል ነው። ጌታችን መድኃታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጀመሪያ ትንሣኤውን የገለጠው ለመግደላዊት ማርያም ነው። በዛን ጊዜ እስራኤል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ነበረች፣ ማንም ወደ መቃብር መጠጋት አይችልም ነበር። እንደ ሴት ሲታሰብ፣ ሌሊት ላይ መቃብር ጠባቂዎች ባሉበት ስፍራ መገኘት፣ ብዙ አደጋ አለው።

ግን ሴቶች በእጅጉ የደፈሩበት፣ ከወንዶች በፊት መቃብሩ ጋር ተገኝተው ማወቅ የቻሉት፣ ትንሣኤው የተገለጠላቸው ሴቶች ናቸው። እናም ትንሣኤ ውስጥ ትልቅ የሆነ ዋጋ አላቸው። ትንሣኤውን አስቀድመው የተናገሩትም ሴቶች ናቸው።

እና ዛሬም በዛ ብቻ ሳይሆን በአገር ትንሣኤ ውስጥ፣ በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊና ፖለቲካዊ ትንሣኤ ውስጥም ሴቶች ዋጋ ሊኖራቸው እንደሚገባ አሳይቷል ማለት ነው። ከዚህም የበለጠ አገር ላይ ትንሣኤ ማምጣት እንደሚችሉ እናምናለን። እህቶቻችንን ለዚህ በርቱ እንላለን።

ቅጽ 2 ቁጥር 76 ሚያዝያ 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here