የኮሮና ወረርሽኝ እና የዓለማቀፉ ኢኮኖሚ መጻኢ እጣ፡ እንደምን እንዳን?

0
652

የኮቪድ 19 የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የዓለም የምጣኔ ሀብት ላይ መናጋት ፈጥሯል። የቫይረሱ ስርጭት ቀጥሎ ዓለም ከዚህ ሕማሟ በቶሎ የማትላቀቅ ከሆነም፣ የክስተቱ ጠባሳ ከሦስት ዓመታት በላይ ዘልቆ በኢኮኖሚው ላይ እንደሚታይ ባለሞያዎች እያሳሰቡ ነው። ይህን ለመቋቋም ኢትዮጵያ ግብርና ላይ ትኩረቷን ብታደርግ ይበጃል ያሉት ታደሰ ጥላዬ፣ የተለያዩ ማንጸሪያ ጉዳዮችን በማንሳትም፣ ወደ ግብርና የሚደረግ ትኩረት በችግር ሰዓት ሕዝብን በሚገባ መመገብ ከማስቻል አልፎ ለዘላቂ እድገት ማርሽ ቀያሪ ነው ብለው ይሞግታሉ።

የፈረንሳይ ግብርና ሚኒስትር ዲድየር ጉዊላዉሜ ተናገሩት ብሎ “ኢዩ ኦብዘርቨር” ይዞት የወጣው ጽሑፍ ላይ እንዲህ ይነበባል። ‹‹በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት በአኅጉሪቱ ውስጥ የሰዎች እንቅስቃሴ በመገደቡ በሚቀጠሉት ሦስት ወራት የግብርና ምርቶቻችንን ለመሰብሰብ የሚያስፈልጉንን 200 ሺሕ የውጪ አገር ሠራተኞች ልናገኝ አንችልም››

ይህ የሆነው የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት በጣሉት ድንበር ተሻጋሪ የእንቅስቃሴዎች ገደብ ምክንያት ነው። ሚኒስትሩ ይቀጥላሉ፤ ‹‹በራችሁን ዘግታችሁ ያለሥራ የተቀመጣችሁ የአገሬ ሰዎች፤ ለእናንተ አንድ ጥሪ አለኝ። እየገነባነው ያለነውን የፈረንሳይ የግብርና ሠራዊት ተቀላቀሉ። አሁን እንደ ወንድማማቾች በጋራ ቆመን የግብርና ምርታችን በአግባቡ እንዲሰበሰብ ማድረግ ይኖርብናል። አለበለዚያ ሁላችንም የምንበላው ላይኖረን ይችላልና›› ይላሉ።

የአውሮፓዋ ግዙፍ ኢኮኖሚ ጀርመንም ድንበሯን መዝጋቷን ተከትሎ ከ 300 ሺሕ በላይ የሠራተኛ እጥረት እንደሚገጥማት ከተረዳች በኋላ ጥበቃውን ላላ ልታደርግ እንዳሰበች እየተነገረ ይገኛል። ከዚሁ ከግብርና ምርት መስተጓጎል ጋር ተያይዞ፣ የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ የግብርና ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀመንበር ኖርበርት ሊንስ፣ የዚህ ከግብርና ምርት መስተጓጎል ጋር ሊከሰት የሚችለው ጣጣ የተገለጠላቸው ይመስላል።

‹‹ለኅብረቱ አባል አገራት ግብርና ሚኒስትሮች ጥሪ ማድረግ እፈልጋለሁ። በራችሁን ለውጪ አገራት ሠራተኞች ክፍት አድርጋችሁ የግብርናው እንቅስቃሴ እንዲቀጥል መፍቀድ አለባችሁ። ደኅንነትን ለማረጋገጥ የተለዩ አውቶቡሶች እና ባቡሮች አዘጋጁና የምታደርጉትን አድርጉ፤ ካስፈለገ ለምን አውሮፕላን ማዘጋጀት አይሆንም›› በማለት ‹‹በር ልዝጋ›› የሚለው አካሄድ ብዙም እንደማያዋጣ አሳስበዋል። በር መዝጋት፣ በተለይ በግብርና ላይ ሲሆን ውሎ አድሮ ጉሮሮንም ይዘጋል በሚል።
የኮሮና ወረርሽኝ የዓለምን መሠረቶች ማናወጥ ከጀመረ እነሆ ሦስት ወር ሆነው። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ‹እውነት› የማይመስሉ ነገሮች ሆነዋል። የጠበቅናቸው ደግሞ ሳይከሰቱ ቀርተዋል። ለዓለማችን እንደ መድኅን ሆነው ይቆጠሩ የነበሩት የምዕራብ አገራት ራሳቸውን እንኳን መታደግ አቅቷቸው ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከባለሥልጣን እስከ መደበኛው ዜጋ ቤታቸው ተከርችመዋል።

ማንም ማንንም አይረዳም። ትምህርት ቤቶች በዘመቻ ተዘግተዋል፤ የአምልኮ ቤቶችም ያለ ልዩነት መፍትሄ ከሚያፈልቁት ሳይሆን ከሚሸሹት ወገን ሆነዋል። በኮሮና ፊት ገንዘብም፣ እውቀትም ምንም እንዳልፈየዱ ታይቷል። ኮሮና ድሃውንም ሃብታሙንም እኩል አድርጎታል። በዚህ አስገራሚ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ታዲያ‹‹ምድርን በቁጥጥራችን ስር አውለናታል›› ብለው የሚያስቡት አገሮች ሳይቀር፣ ወደጥንቱ እየተመለሱ ያሉ ይመስላል። በዚህ ወቅት የዓለም ሁሉ ትኩረት ተዓምር መሥራት የሚችለው ፈጣሪና ከረሃብ የሚያተርፈው ግብርና ላይ እየሆነ ነውና።

ዓለማቀፉ ኢኮኖሚ ወዴት እየሄደ ነው?
ማክ ኪንሲ ኤንድ ካፓኒ የተሰኘው የሥራ አመራር አማካሪ ድርጅትን ጠቅሶ ወርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም እንዳደረገው ትንበያ ከሆነ፣ የዓለም ኢኮኖሚ ከዚህ ወረርሽኝ አመጣሽ ውድቀት ለማገገም እስከ ሦስት ዓመት ይፈጅበታል። ይህ ግን በተስፋ ላይ የተመሰረተ ትንበያ እንጂ የተረጋገጠ ሃቅ አይደለም። የዓለም ችግር ከዚህም ለተራዘመ ጊዜ ሊቀጥል የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነውና።

በሽታውን የመቆጣጠር ጥረት በአጭር ጊዜ ተሳክቶ መደበኛ እንቅስቃሴ ቢጀመርም በዜጎች ላይ የሚፈጥረው መገረን (HANGOVER) በቀላሉ የሚቀለበስ አይሆንም። ከፍርሃት የተነሳ የዜጎች ገንዘብን አውጥቶ የመሸመት ፍላጎት ሊቀዛቀዝ ይችላል። ይህም ኢኮኖሚው እንዳይነቃቃ ያደርገዋል። በተጨማሪም ትላልቅ የግል አልሚዎች ላልተወሰነ ጊዜ የባንክ ብድሮቻቸውን መክፈል ስለማይችሉ ባንኮች የግለሰብ ቁጠባዎችን መመለስ የማይችሉ፣ ለመንግሥትም ሆነ ለግል ባለሃብቶች ማበደር የማይችሉ ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል በጣም ከፍተኛ ነው።

እነዚህን ያፈጠጡ ሃቆች ላይ ተመስርተን ስናየው፣ የዓለም ኢኮኖሚ በሦስት ዓመትም ወደ መስመር ላይመለስ ይችላል። ምናልባትም በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ ዓለምን አጋጥሟት ከነበረው የኢኮኖሚ ድቀት ባልተናነሰ ሁኔታ ከሰባት እስከ ዐስር ዓመት ሊቆይ ይችላል። በዓለም ታሪክ ላይ ከባዱ ተብሎ የሚቀመጠው ‹ታላቁ የኢኮኖሚ ቀውስ› እ.ኤ.አ. በ1929 ሲከሰት፣ ቀጥሎ የታየው ክስተት የአክሲዮን ገበያው በ22 በመቶ ማሽቆልቆል ነበር።

አሁን ግን የቺካጎ ዩኒቨርሲቲ የፋይናንስ ፕሮፌሰሮቹ ኒልስ ጆዋቺም እና ራልፍ ኮይጀን እንደሚሉት፣ የአውሮፓና የአሜሪካ የአክስዮን ገበያ በታሪክ ታይቶ በማይታዎቅ ሁኔታ በ30 በመቶ ቀንሷል። ‹‹አስተዉሉ!›› ይላሉ ፕሮፌሰሮቹ በጥናታቸው፤ ‹‹የአክስዮን ዋጋ ማለት የኢንቨስተሮች የወደፊት ገቢ ማለት ነው። ምክንያቱም የአክሲዮን ዋጋ ሰዎች ለወደፊት ባላቸው ተስፋ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ነው።››

ይህም ምናልባትም የዓለም ኢኮኖሚ በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት በገሚስ የመሽመድመድ አደጋ ተደቅኖባታል ማለት ሊሆን ይችላል።
የኢኮኖሚ ድቀት ዋነኛ ገፅታው ዜጎች ስለወደፊት እርግጠኝነት እንዲያጡ የሚያደርግ አደገኛ ተፅዕኖው ነው። ዜጎች በኹለት ዋና ዋና ምክንያቶች እርግጠኝነታቸውን ሊያጡ ይችላሉ፤ ቀድሞ በተፈጠረ ምስቅልቅል ከሚያድርባቸው ፍርሃት የተነሳና ድርጅቶች ከሚያደርጉት የሠራተኛ ቅነሳ። በአሁኑ የዓለማችን ቀውስ የመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ እንደመገኘታችን፣ ከሠራተኛ ቅነሳ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር እምብዛም አልተረዳነውም።

ሆኖም በረጅም ጊዜ መንግሥታት ድርጅቶችን መደጎም የማይችሉበት ሁኔታ ላይ ሲደርሱ፣ ሠራተኞችን በገፍ ማባረር መጀመራቸው አይቀርም። ልክ በታላቁ የኢኮኖሚ ድቀት ጊዜ እንደሆነው ቀጣዩ ተስፋ አስቆራጭ ጉዳይ የሥራ አጥነት ችግር የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው። ‹በታላቁ የኢኮኖሚ ድቀት› ጊዜ የኹለተኛው የዓለም ጦርነት እና የፕሬዝደንት ሮስቬልት ‹NEW DEAL› የተሰኘ ፖሊሲ ባይተገበር ኖሮ፣ ዓለም እንደ ታይታኒክ መርከብ እየሰመጠች ነበር። የዜጎች የግዢ ፍላጎት በ27 በመቶ ያሽቆለቆለበት፣ ዓለም አቀፍ ንግድ ደግሞ በ66 በመቶ የቀነሰበት አስቸጋሪ ጊዜ ነበር፣ ያ ጊዜ። የአሁኑ የዓለም እጣ ፈንታም ከዚህ የተሻለ የመሆን ዕድሉ ሲበዛ አናሳ ነው።

ዜጎች ከሥራ መቀነሳቸው ገበያው ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ እንዳለ ሆኖ፣ የባንኮች የማበደር አቅም መዳከም እንዲሁም ሥራ ላይ ያሉ ዜጎችም ስለነገ የሚኖራቸው እርግጠኛ ያለመሆን ሰዋዊ ስሜት ታላላቅ ድርጅቶችን እና የፋይናንስ ተቋማትን ከጨዋታ እንዳያወጣቸው ያሰጋል። በተጨማሪም ልክ ታላቁ የኢኮኖሚ ድቀት የኃይል ሚዛኑን ከአውሮፓ ወደ አሜሪካ የማዞር ትልቅ ሚና እንደተጫወተ ሁሉ፣ አሁንም የሚዛን መገለባበጥ መፈጠሩ የሚቀር አይመስልም። ምናልባትም ዓለም አዳዲስ ኃያላንን የምታይበት የታሪክ ምዕራፍ ላይ ደርሳ ይሆናል።

ግብርና – የተቀበረው መክሊታችን
በአውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ1929 ዓለም በኢኮኖሚ ቀውስ ስትሽመደመድና ለ400 ዓመታት ዓለምን ያሾረው የአውሮፓ ኃያልነት እንደጉም በኖ ሲጠፋ፣ አሜሪካ እና ኢትዮጵያ ኹለቱም በተቀራራቢ ጊዜ የምንጊዜም ተፅእኖ ፈጣሪ መሪዎቻቸውን ያገኙበት ምዕራፍ ላይ ነበሩ። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በ1930 ‹ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ› ተብለው ዘውድ ሲጭኑ፣ የአሜሪካው ፕሬዚደንት ፍራንክሊን ሮስቬልት ከኹለት ዓመት በኋላ 1933 ላይ 32ኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው ተመረጡ።

በወቅቱ አሜሪካ የታላቁ የኢኮኖሚ ቀውስ እያመሳት የነበረችበት፣ ኢትዮጵያ ደግሞ ከዳግማዊ ምኒልክ ሞት በኋላ ዙፋን አልረጋ ብሏት የምትታመስበት ወቅት ነበር። ኹለቱ የታሪክ መንትያዎች አገሮቻቸውን ከገቡበት ማቅ መንጭቀው በማውጣት ታሪክ የማይረሳው ሥራን ሠርተዋል።

የአሜሪካው ሮስቬልት ወደ መንበሩ ሲመጡ አገራቸው አሜሪካ እና መላው ዓለም ምጥ ላይ ነበር። በመሆኑም ልክ ሥልጣን እንደያዙ ከወሰዷቸው እርምጃዎች ውስጥ አንዱ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ድጋፍ ለማድረግ የማጠናከሪያ የ20 ዓመት እቅድ ማስተዋወቅ ነበር። ምክንያቱም የዓለም የንግድ እንቅስቃሴ 60 በመቶ ባሽቆለቆለበት ሁኔታ፣ የወጪ ንግድን ብቻ ተስፋ ማድረግ እንደማይኖርባቸው ተረድተዋልና ነው።

ይልቅስ የሕዝባቸውን ኑሮ በማቅለል የዜጎችን የመግዛት አቅም የሚያሳድግ ዘዴ ቀየሱ፤ ግብርናን መደገፍና ምርታማነቱን መጨመር። በዚህም የዜጎቻቸው የመግዛት አቅም ጨመረ። ከሌሎች የማሻሻያ ሥራዎች ጋር ተዳምሮም አሜሪካንና ዓለምን ከምስቅልቅል አወጣ።

‹‹ታላቁን የዓለም ኢኮኖሚ ድቀት›› ታሪክ እንደ ማነፃፀሪያ ያነሳሁት ያለምክንያት አይደለም። አንዳንድ ገጽታዎቹ እኛንም ስለሚመለከት እንጂ። በወቅቱ ምንም እንኳን የአክሲዮን ዋጋ ቢያሽቆለቁል፤ ምንም እንኳን የዓለም አቀፍ ንግድ ቢቀንስም፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ግን ምንም አይነት ተፅእኖ አልደረሰበትም ነበር ማለት ይቻላል። ምክንያቱም መቶ በመቶ በግብርና ላይ የተመሰረተ ስለነበረና ወደውጪም የምንልከው ‹እዚህ ግባ› የሚባል ስላልነበረ ነው።

ይህን የማነሳው መቶ በመቶ በግብርና ላይ የተመሰረተና ወደውጪ የማይልክ ኢኮኖሚ የሚያኮራ ሆኖ አይደለም፤ እንደውም የሚያሳፍር ነው። ሆኖም ያሁኑም አንፃራዊ ሁኔታችን ‹ታሪክ ራሱን ይደግማል› እንደሚባለው ተመሳሳይ ነው ብዬ በማመኔ ነው። በዚያን ወቅት ሁኔታውን የተረዱት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የውጪ ንግድንና ዘመናዊ አሰራሮችን ለማስተዋወቅ ብዙ ደክመዋል። ግብርናው ላይ ግን አንዳች ተዓምር እንዳለ የተገለጠላቸው በመጨረሻዎቹ የሥልጣናቸው ማብቂያ ዓመታት ላይ ነበር።

ከዚያ በኋላ ነበር የአስራ አምስት ዓመት የግብርና ልማት ስትራቴጂ ነድፈው ወደሥራ ያስገቡት። ሆኖም ግማሽ መንገድ እንኳን ሳይጓዝና ጥንካሬውና ድክመቱ በአግባቡ ሳይገመገም የንጉሡ ፍፃሜ ሆነ። ዕቅዱም ‹‹የአገሪቱን የምግብ ዋስትና ያረጋግጣል፣ ለውጪ ገበያም ይተርፋል›› ተብሎ ተጠብቆ አንዱንም ሳያሳካ በአጭር ተቀጨ።

በታላቁ የዓለም ኢኮኖሚ ቀውስ አጣብቂኝ ውስጥ ገብታ የነበረችው አሜሪካ በብልሁ መሪዋ ሮዝቬልት ተመርታ የዓለም አይነኬ ኃያል ሃገር ሰትሆን፣ ምንም ችግር ያልገጠማት ኢትዮጵያ ግን ዛሬም የዛሬ 90 ዓመት የነበረችበት ላይ ትገኛለች። ጥያቄው ትላንት አሜሪካ እንዳደረገችው ይህን ቀውስ ተጠቅመን ተአምር እንሠራለን? ወይስ ዛሬም እንደትላንቱ ዓለም እላያችን ላይ ሚዛን ሲቀይር ቆመን እናያለን? ነው።

በኔ እምነት ይህ ታሪካዊ ክስተት በአግባቡ ከተጠቀምንበት ለእንደኛ አይነት ድሃ አገር ከቀውሱ በኋላ አቀማመጥን ለማስተካከል መልካም አጋጣሚ ነው። ምክንያቱም ልክ እንደትላንቱ ሁሉ ዛሬም የኛ ኢኮኖሚ የውጪ ንግድ ላይ ብዙም ያልተንጠለጠለ እና መሰረታዊ ጥሬ ዕቃዎችን ብቻ የሚያመርት ኢኮኖሚ በመሆኑ በዓለም አቀፉ ነውጥ እምብዛም ሊደቅ አይችልም። በተጨማሪም የኛን የተወዳዳሪነት አማራጭ (COMPARATIVE ADVANTAGE) ይዘን ለመቅረብ ዕድልን ይፈጥርልናል።

ለዓለማቀፍ ቀውሶች ያለን ተጋላጭነት
የአሜሪካው ሲአይኤን (CIA WORLD FACTS BOOK) የ2017 መረጃ እዚህ ጋር እጠቀማለሁ። የአገራችን ኢኮኖሚ በዓለማቀፍ ቀውሶች የመጠቃት እድሉ ምን ያህል ነው?

በዚህ ተቋም መረጃ መሰረት በ2017 የኢትዮጵያ አጠቃላዊ አገራዊ ምርት 80.87 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነበር። ከዚህ ውስጥም 34.8 በመቶ የሚሆነው ከግብርና የሚገኝ ነው። ኢንዱስትሪና አገልግሎት ሰጪ ዘርፉ እያንዳንዳቸው በቅደም ተከተል 21.6 በመቶ እና 43.6 በመቶ ዓመታዊ የምርት ምጣኔ ያዋጣሉ።

የወጪ ንግድ
በዚህ ዓለማቀፍ ቀውስ በዋናነት ተጠቂ ነው ተብሎ የሚታመነው ዋነኛ ዘርፍ የወጪ ንግዱ እንደሆነ ይታወቃል። በዚህ መረጃ መሰረት ከውጪ ንግድ የምናገኘውን ዓመታዊ የምርት ገቢ ብናየው 2.5 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው። ይህም ከአብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት የውጪ ንግድ ገቢ አንጻር በእጅጉ ያነሰ ነው።
ለምሳሌ ግብጽን በንፅፅር ለማየት ብንሞክር፣ ከነበራት 235 ቢሊዮን ጠቅላላ ዓመታዊ ምርት ውስጥ የግብርና አስተዋፅዖ 11.7 በመቶ ብቻ ነበር። ኢንዱስትሪው 34.3 በመቶ ሲያዋጣ፣ አገልግሎት ዘርፉ ደግሞ 54 በመቶ አስተዋፅዖ ነበራቸው። የግብጽ የአገልግሎት ዘርፏ ገቢም በአብዛኛው ከቱሪዝም ጋር የተያያዘ በመሆኑ በዚህ ቀውስ በእጅጉ ተጎጂ ነው።

የውጪ ንግዳቸውን በምናይበት ጊዜ 29.4 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ይህም የኢትዮጵያን ጠቅላላ አገራዊ ምርት አንድ ሦስተኛ እንደማለት ነው። ስለሆነም ይህ የኢኮኖሚ ቀውስ ኹለቱ አገራት ላይ በንጽጽር የሚያደርሰውን ጫና ብንመለከት፣ ለግብጽ የወጪ ንግድ 5.91 በመቶ የዓመታዊ ምርቷ አስተዋጽዖ ሲኖረው፣ በታቃራኒው ለኢትዮጵያ ግን 0.52 በመቶ ብቻ ይኖረዋል ማለት ነው።

ከውጪ በቀጥታ የሚላክ ገንዘብ (REMITTANCE)
እንደ ዓለም ባንክ ሪፖርት፣ 2018 የአፍሪካ ሃገራት ከፍተኛ የሆነ ሬሚታንስ የሰበሰቡበት ዓመት ነበር። በዚሁ ዓመት ታዲያ አገራችን 436 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ስታገኝ በተቃራኒው ግብጽ 29 ቢሊዮን ዶላር በመሰብሰብ የአፍሪካን ሪከርድ ሰብራለች። የዓለም ኢኮኖሚ ቀውስ አይቀሬ ከሆነ በቀጥታ ከሚስተጓጎሉት ነገሮች ውስጥ አንዱ ይኸው ሬሚታንስ ቢሆንም፣ ከዚህም አንፃር ለኢትዮጵያ ‹ያው በገሌ› ዓይነት ነው፤ ብዙም የሚያሳስባት ነገር አይሆንም። በተቃራኒው እንደ ግብጽ ላሉ አገራት ግን ኪሳራው የትየለሌ እንደሚሆን ግልጽ ነው።

ከሥራ አጥነት ችግር (UNEMPLOYMENT) አንፃር
ከዓለም ኢኮኖሚ ድቀት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ሌላ ጣጣ ‹የሥራ አጥነት› ችግር መሆኑ ግልፅ ነው። ከዚህም አንፃር ብናየው በቀውስ ጊዜ ግብርና ተኮር መሆን ያዋጣል። በዚሁ የመረጃ ምንጭ መሰረት ከአገራችን የሰው ኃይል ውስጥ መደ 72.7 በመቶ (3/4ኛ) የሚሆነው በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ተሰማርቶ ይገኛል።
ከዚህ አንፃር የኢኮኖሚ ቀውሱ ለሚፈጥረው የሥራ አጥነት ጫና የመጋለጥ ዕድሉ አነስተኛ ነው ማለት ነው። በተቃራኒው የግብጽን ሁኔታ ስንመለከት ግን 25.8 በመቶ (1/4ኛ) ሕዝቧ ብቻ ነው በግብርና ተሰማርቶ የሚገኘው። ስለዚህ 3/4ኛ እጅ ሕዝቧ ከሥራ አጥነት ጋር ለተያያዘ ቀውስ የመጋለጥ ዕድሉ ከፍተኛ ነው።

ክተት ወደግብርና
ኢትዮጵያ 72.7 በመቶ ሕዝቧን የያዘውን ግብርና በሙሉ ትኩረት ብታለማው ብዙ ነገር መለወጥ ትችላለች። አብዛኛውን የሕዝባችንን ክፍል የያዘው ግብርና ከምርታማነት አንጻር ያለው ሪከርድ ሲበዛ ደካማ ነው። ሦስት አራተኛ እጅ የሚሆነውን የሠራተኛ ኃይል አቅፎ ለአገራዊ ምርት ያለው አስተዋጽዖ ግን አንድ ሦስተኛ እጅ ብቻ ነው። ይህንን ሁኔታ ከስሩ መቀየር መቻል ማለት በፈጣሪም ሆነ በሰው ፊት የሚያስመሰግን ነው።

ምክንያቱም ከ 80 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ሕዝባችን ኑሮውን የመሰረተበት ዘርፍ በመሆኑ ግብርናውን ምርታማ እንዲሆን ማስቻል ማለት የገበሬውን የዘመናት ቀንበር መስበር ማለት ነውና። ከዚህ በተጨማሪም ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰትን በመቀነስ የከተማውን ጫና ለማቃለል ይረዳል። ለከተሜው መሰረታዊ የምግብ ፍጆታን በርካሽ ማቅረብ ስለሚቻልም በከተሜው ላይ ያፈጠጠውን የኑሮ ጫና ለማቃለል ያስችላል።

ከላይ የተጠቀሱት ሃቆች እንዳሉ ሆነው በተለይ በዚህ ዓለማችን ወደ ቀውስ እየተንደረደረች ባለችበት ጊዜ ግብርናችን ላይ የምናደርገው ትኩረት ማርሽ ቀያሪ (GAME CHANGER) አቅጣጫ ነው። ምክንያቱም አንደኛ ከውጪ የምናስገባቸውን መሰረታዊ የምግብ ምርቶች ማስገባት ባለመቻላችን ሊፈጠር የሚችለውን የምግብ ቀውስ በመቅረፍ የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንዲኖረን ያደርጋል። በግብርናው ኢንቨስትመንት ምክንያት በሚፈጠረው የሥራ ዕድል ቀጣይ ሊገጥመን ከሚችለው የሥራ አጥነት ማዕበል ይታደገናልም።

ከዚህ በተጨማሪም በቀጣይ የዓለም ዜጎችና አገራት ትኩረት መሰረታዊ ነገሮችን መሸመት ላይ ስለሚሆን የተረፈንን ኤክስፖርት በማድረግ ተመልሰን ወደ መስመር እንድንገባ ይረዳናል። ሌላው ቸል የተባለውን የአግሮ-ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ትኩረት እንዲያገኝና አስፈላጊ ግብዓቶችም በበቂ ሁኔታ እንዲመረቱ ስለሚረዳ፣ ከቀውሱ በኋላ ቀጠናው ላይ ትልቅ አግሮ-ፕሮሰሲንግ አገር ሆነን እንድንወጣ ሊያደርገን ይችላል።

ስለዚህ መንግሥትና ነባሩ ገበሬ የተጣመሩባቸው የግብርና (እርሻ) ፕሮግራሞችን በመተግበር ሊጀመር የሚችል ኋላም አነስተኛና መካከለኛ ባለሃብቶችን ከመንግሥት ጋር ያጣመሩ የአግሮ-ፕሮሰሲንግ እቅዶችን ወደመተግበር የሚሸጋገር የተቀናጀ የግብርና እቅድ መተግበር ይኖርበታል። ይህም የግሉ ዘርፍ ከመንግሥት ጋር በመደጋገፍ የዘመናዊ ግብርና እና ቴክኖሎጂን የመጠቀም አቅሙ እንዲያድግ ስለሚረዳ፣ የወደፊት የአመራረት ባህላችንን ከመቀየር አንፃር ትልቅ ሚና ይኖረዋል።

በአጠቃላይ የግብርና ዘርፉ የሚፈጥረው የፊትና የኋላ ትስስር የምግብ እጥረት ቀውስ እንዳይፈጠር ከማስቻል አንጻር፣ ከሥራ እድል ፈጠራ አንጻር፣ ከውጪ ምንዛሬ ግኝት አንጻር፣ ከምንም በላይ ግን የብዙኀኑን ሕዝባችንን ኑሮ ከመለወጥ አንጻር የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። በመሆኑም አሁን ጊዜው ግብርናን ማዘመን ላይ ሙሉ ኃይላችንን የምናፈስበት ወቅት ነው። የፈረንሳዩ ግብርና ሚኒስትር እንዳሉት፣ ‹የግብርና ሠራዊት የምናስነሳበት ጊዜው አሁን ነው።›
ታደሰ ጥላዬ የቢዝነስ ትንታኔ የሚሰጡ፣ የኢኮኖሚ ምሩቅና በሔሚስፌር ብሪጅ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው። በኢ-ሜይል አድራሻቸው tadinvela@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 76 ሚያዝያ 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here