በቤንሻንጉል ክልል በሦሰት ወራት ውስጥ ሦስት ሰዎች በአንበሳ ተበልተው ሕይወታቸው አለፈ

0
507

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባምባሲ ወረዳ ከየካቲት 12/2012 ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 7/2012 ድረስ ባሉት ሦስት ወራት ሦስት ሰዎች በአንበሳ ተበልተው ሕይወታቸው ማለፉን የወረዳው ፖሊስ ጽ/ቤት አስታወቀ። አንበሶች በአካባቢው ላይ በሚያደርሱት ጥቃትም ከሞት ባሻገር የመቁሰል አደጋ በሰዎች ላይ እና በእንስሳት ላይ ደግሞ መበላት አደጋ እንዳደረሱ የፖሊስ ጽሕፈት ቤቱ ጨምሮ ገልጿል።

የባምባሲ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ባልደረባ ምክትል ኢንስፔክተር ጌታቸው ተረፈ እንዳስታወቁት፣ በቅርቡ አንበሳ ባደረሰው ጉዳት የኹለት ሰው ሕይወት ማለፉን የጠቆሙ ሲሆን፣ በ5 ሠዎች ላይ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው በባምባሲ ከተማ ጤና ጣቢያ በሕክምና ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጸሕፈት ቤት ኃላፊ መለሰ በየነ ችግር የተፈጠረው በአካባቢው በሚገኝ ‹አንበሳ ጫካ› ተብሎ በሚጠራ ጫካ ውስጥ የሚኖሩ አንበሳዎችን ወጣቶች በአንበሳው ላይ ባደረሱበት ትንኮሳ ጉዳት እንዳደረሰባቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ፖሊስ በበኩሉም በሰዎች ላይ ጥቃት እያደረሰች የምትገኘው የአንበሳ ደቦል በሰዎች መሸጡን መረጃ እንዳለውም አመልክቷል።

ኃላፊው አክለውም በክልሉ የሚገኙ የእንስሳት መገኛ ጫካዎች ጥበቃ ስለማይደረግላቸው በተለያየ ጊዜ በአካባቢው ኗሪዎች ላይ እና በቤት እንሰሳቶች ላይ ጥቃት እንደሚደርስ አስታውሰዋል። ይህ እንዳይሆን በክልሉ የሚገኙ የእንሰሳት መኖሪያ ጫካዎች ጥበቃ ቢደረግላቸው የሚደርሰውን ችግር ከማስቀረት ባሻገር የገቢ ምንጭ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ሚያዚያ 6/2012 ሽንግላ ቀበሌ ምሽት ኹለት ሰዓት አካባቢ በእርሻ ሥራ ላይ የተሰማራ አንድ ሰው በአንበሳ ተበልቶ ሕይወቱ ማለፉን ፖሊስ አስታውቋል። አንበሳው ግምታቸው ወደ 10 ሺሕ ብር በሚጠጉ የቤት እንስሳቶት ላይ ጉዳት እንደደረሱም ነው የተገለጸው።

የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አዛዥ ኢንስፔክተር ያሲር አብዱልማጅድ በወረዳው የጎልማ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ ኹለት እና የሽንግላ ቀበሌ ነዋሪ የሆነ አንድ በድምሩ ሦስት ሰዎች በአንበሳው ጉዳት ደርሶባቸው ሕይወታቸው ማለፉን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም በወረዳው ስር በሚገኙት መንደር 47፣ ቦሽማ ቀርገጌ፣ ጎልማ በተባሉ ቀበሌዎች ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች በሕክምና ላይ መሆናቸው ገልጸዋል።
አንበሳው በተለያዩ ቀናት በሰው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰው በጫካ ውስጥ በሥራ ላይ በነበሩበት ወቅት እንደሆነም ኃላፊው ተናግረዋል።

በአካባቢው ላይ ከዚህ በፊትም አልፎ አልፎ እንዲህ አይነት ሁነቶች እንደሚከሰቱ የአካባቢው የአዲስ ማለዳ ምንጮች ተናግረዋል። እንደ አካባቢው ኗሪዎች ገለፃ አንበሳው በሰዎች ላይ ጉዳት የሚያደርሰው በሚኖርበት አካባቢ ሲንቀሳቀሱ ሲያገኛቸው መሆኑን ገልጸዋል።

አንበሳውን ለመከላከል ያለው አቅም ከባድ እንደሆነ እና በሰው ኃይል ለመከላከል ስለማይቻል ጉዳት ሊደርስ እንደቻለ ተናግረዋል። እንደ አዲስ ማለዳ ምንጮች ገለጻ አንበሳውን በመሣሪያ ማጥቃት በሕግ የተከለከለ በመሆኑ መግደል እንደማይቻል ጠቅሰው፣ በመኖሪያ አካባቢው የሚሰሩና የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ሕይወት እንዲሁም እንስሳቶች ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሰለሞን ወርቁ ችግር መከሰቱን ባለሥልጣኑ ቢሰማም ክልሉ ድጋፍ ስላልጠየቀ እስከ አሁን ባለሥልጣኑ የወሰደው እርምጃ አለመኖሩን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ነገር ግን ባለሥልጣኑ ችግሩ የከፋ ከሆነና አሁን ባለበት ሁኔታ የማይገታ ከሆነ እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ሕግ በዱር እንስሳት እና በሰው መካከል በደረሰ ጉዳት ላይ የሚወሰደው እርምጃ እንስሳቱ ሰውንና እንስሳትን የማጥቃት ልማድ ካለባቸው፣ ሰዎችም ሆነ እንስሳት ከዱር እንስሳቶቹ መኖሪያ አካባቢ አስፈላጊውን ርቀት ጠብቀው እንዲኖሩና እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ የመጀመሪያው እርምጃ ነው ብለዋል።

ቢሆንም እንስሳቱ የቤት እንስሳትንና ሰዎች ላይ የሚያደርሱት ጉዳት እና አድኖ የማጥቃት ልምድ ካሳዩ፣ የዱር እንስሳቱ የአኗኗር ዘይቤ ስለሚቀየር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ ከመጣ እንደየ አስፈላጊነቱ አካባቢው ላይ ያለውን ሙሉ ሁኔታ በባለሙያዎች ተጠንቶ የሚወሰደው እርምጃ እንስሳቱን ማስወገድ ነው። ነገር ግን ይህ የሚሆነው ችግሩ የከፋ ከሆነና መቋቋም የማይችልበት ደረጃ ሲደርስ መሆኑን ሰለሞን ጠቁመዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 76 ሚያዝያ 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here