የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ዘመን ሊተላለፍ ይችላል

0
684

የኮቪድ 19 የወረርሽኝ ስርጭትን በአጭር ጊዜ ውስጥ መቆጣጠር ካልተቻለ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ፕሮግራማቸውን ወደሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ሊራዘም እንደሚችል የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ደቻሳ ጉርሙ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ እስከ አሁን ባለው ሁኔታ የዩኒቨርስቲዎች የትምህርት ሂደት እንዴት መሆን እንዳለበት እና ወደ መደበኛው የትምህርት አካሄድ ሂደት መመለስ ይቻል አይቻል የሚለው አልተወሰነም። ምክንያቱም የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ በጤና ሚኒስቴር ይፋ የሆነው መጋቢት2/2012 ሲሆን ከዛ በኋላ ለአስራ አምስት ቀናት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በጊቢያቸው ውስጥ ነበሩ።

ነገር ግን ተማሪዎቹ ወደመጡበት እንዲመለሱ ከተደረጉ አስራ አምስት ቀን እንደመሆኑ ውሳኔ ላይ አልደረስንም ብለዋል። እንደታሰበው የወረርሽኙ ስርጭት በአጭር ጊዜ መቆጣጠር ካልተቻለ እና ስርጭት መጠኑ በከፍተኛ ሁኔት ከጨመረ በሽታውን ስርጭትን የተማሪዎች ወደ ዩኚቨርስቲው መመለሳቸው ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ማስከተሉ ስለማይቀር የትምህርት ጊዜው ወደሚቀጥለው ዓመት ሊዘዋወር እንደሚችል (2013) ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ግን የወረርሽኙ ስርጭት በአጭር ጊዜ የሚገታ ሆኖ ከተገኘ የእረፍት ጊዜን በመጠቀም ማለትም ወደ ክርምት በመግፋት እና ትምህርት አሰጣጡን በማሸጋሸግ ወደሚቀጥለው ዓመት ማለትም 2013 ሳይገባ በወጣለት መርሃ ግብር ለማገባደድ እንደታሰበ ሚኒስቴሩ ለአዲስ ማለዳ አሳውቋል።

ሚኒስቴሩ እንደገለፀው፣ ትምህርት አሁን ባለው ወረርሽኝ ምክንያት እንዲቋረጥ እንደተደረገ እና ይህም ደግሞ በትምህርት ሴክተሩ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ እንደ አገር ወረርሺኙን ለመግታት የተወሰደ እርምጃ ነው ብለዋል። በተያያዘም የኮሮና ቫይረስ ስርጭቱን በአጭር ጊዜ ለመግታት የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ከሚደረግባቸው እና በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎችን ለመለየት (የለይቶ ማቆያ) በመሆን እያገለገሉ ካሉት ተቋማት መካከል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዋነኛ መሆናቸው መገለፁንም አውስቷል።

በኢትዮጵያ ያሉ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በዋነት ትኩረታቸውን ወረርሽኙን በመግታት ላይ እንዳደረጉ የጠቀሰው ሚኒስቴሩ፣ በተለይም ደግሞ የእጅ ማጽጃ ሳኒታይዘሮችን እና ከፍተኛ የጤና ድጋፍ የሚያደርጉ የምርምር ሥራዎችንም በማድረግ ላይ እንደሆኑ አስታውቋል። በተለይም ደግሞ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ በቫይረሱ ለተጠቁ እና በጽኑ ሕሙማን ሕክምና መስጫ ክፍል ለሚገኙ ሰዎች የሚውል የመተንፈሻ ቬንቲሌተር እንደተሠራ አስታውቋል።
ከዚህም ባሻገር የከፍተኛ ትምህርት መምህራንም ወረርሽኙን ለመግታት በበጎ ፈቃድ ተግባር ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ እና ከትምህርት መርሃ ግብሩ ባሻገር ወረርሽኙን መግታት ላይ ትኩረት እንደተሰጠ ጠቁሟል።

የፌደራል ቴክኒክ እና ሙያ የሥነ ልቦና መምህር እና አማካሪ አታለል ካሳ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ሐሳብ፣ ተማሪዎች ቤት የሚውሉበትን አጋጣሚ በመጠቀም ራሳቸውን በራሳቸው ማስተማር የሚችሉበትን መንገድ መፍጠርና መፈለግ አለባቸው። በቀጥታ ስርጭት የሚተላለፉ ትምህርቶችንም በአግቡ ሊከታተሉ ይገባል ብለዋል።

የትምህርት ስርዓቱን እና ሌሎች እንቅስቃሴዎችን ማስቀጠል በማይቻልበት ጊዜ ሌሎች አማራጮችን መከተል ያስፈልጋል ያሉት አታለል፣ አያይዘውም አሁን ያለው ሁኔታ በተማሪዎች ላይ ከሚፈጥረው ሥነ ልቦናዊ ቀውስ አንፃር ወረርሽኙ እስከመቼ እንደሚቆይ ስለማይታወቅ በትምህርት መስመር ውስጥ የነበሩትን ልጆች ከመስመሩ ይወጣሉ። ይህም መልሶ ወደዛ ሂደት ማስገባት እና ውጤታማ ለማድረግ ከባድ ያደርገዋል ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ ሥነ-ልቦና ባለሙያው ገለፃ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ቤት በመሆናቸው የሚቀርባቸው አንድ ነገር ለሚሰጣቸው የቤት ሥራ የመመዘኛ ውጤት ነው። ይህንን ደግሞ በቀጥታ ስርጭት በሚሰጣቸው ትምህርት ውስጥ እንዲያገኙት በማድረግ ስርአቱ እንዳይዘነፍ ማድረግ ይቻላል ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 76 ሚያዝያ 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here