በአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር የጉለሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ይኖሩ የነበሩ እና ከአማራ ክልል የመጡ የቀን ሠራተኞችን እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችን ከክፍለ ከተማው እና ከሚቀበላቸው አካል ጋር ሳይነጋገሩ ወደ አማራ ክልል በመመለሳቸው በክፍለ ከተማው የወረዳ ስምንት የጸጥታ እና ሰላም ክፍል የሥራ ኃላፊዎች ከሥራ መታገዳቸው ተገለፀ።
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በላይ ደጀን ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ተገቢውን ቅደም ተከትል ሳይከተሉ እና በደብዳቤው ውስጥ ”የጎዳና ተዳዳሪዎች“ ተብሎ የጠጠቀሰው ስህተት መሆኑን ገልጸዋል ።ዋና ሥራ አስፈጻሚው አያይዘውም የወረዳው አመራሮች ጉዳዮ እስኪጣራ ድረስ ከሥራ ገበታቸው መታገዳቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
በክፍለ ከተማው ውስጥ ባሉ በሌሎች ወረዳዎች ከዚህ በፊት ከክፍለ ከተማው እና ከከተማ አስተዳደሩ ውጪ ሰዎችን ወደ መጡበት የመመለስ ተግባር ከመፈጸሙ ጋር ተያይዞ በውል የሚታወቁ እንዳሉ ተጠቁሟል። በዚህም ምክንያት በውል የታወቁ የተመለሱ ሰዎች ብዛትና የሄዱበት ቦታ እየተለየ፣ ከኹለት ሳምንት በፊት ወደ ደቡብ ክልል ከ190 በላይ ሰዎች እንዲሁም ቅዳሜ ሚያዚያ 3/2012 ወደ አማራ ክልል የተላኩ 252 ሰዎች መሆናቸውን ሥራ አስፈጻሚው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በጥቅሉ 442 ተመላሾች መሆናቸው ታውቋል።
ሚያዚያ 3/2012 ወደ አማራ ክልል ከተመለሱት ሰዎች ጋር በተያያዘ የአማራ ክልል የሠራተኛ እና ማኅበራዊ ቢሮ ቅሬታውን ከማሰማቱ ጋር ተያይዞ የጉለሌ ክፍለ ከተማ በበኩሉ ቅሬታው ትክክል መሆኑን በማመን ‹‹ስህተቱ የተፈጠረው በክፍለ ከተማው በወረዳ ስምንት የሚኖሩ ከሌላ ክልል የመጡ ሰዎች ወደ ቤተሰባችን መልሱን ተቸግረናል በማለታቸው፣ እነሱን ለማገዝ በማሰብ ነው›› ብሏል። ነገር ግን ክፍለ ከተማውና ከተማ አስተዳደሩ ጉዳዩን ከመከሰቱ በፊት ቀድሞ እንደማያውቀው እና የተፈጠረው ስህተት በወረዳዎች እንጂ በክፍለ ከተማው ወይም በከተማ አስተዳደሩ እንዳልሆነ በላይ ጠቁመዋል።
በክፍለ ከተማው እንዲሁም በሌሎች ከተማ አስተዳደሮች አሁንም ወደ መጣንበት ቦታ እንመለስ፣ አግዙን፣ ሥራ አጥተን ተቸግረናል የሚሉ ሰዎች ብዙዎች እንዳሉ ገልጸዋል። ነገር ግን ከዚህ በኋላ ማንም ሰው በግለሰብ ደረጃ ወደ መጣበት ቦታ በፍላጎቱ ሊመለስ ይችላል እንጂ፣ እንደባለፈው በቡድን የመላኩ ሁኔታ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ማለትም ከፌዴራል መንግሥት እንዲሁም ከከተማ አስተዳደሩ አቅጣጫ ሳይሰጥ እንደማይደገም በላይ አብራርተዋል።
የአማራ ክልል ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደረጀ አበጀ በበኩላቸው፣ በጉዳዩ ላይ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ምላሽ ክልሉ ቅድመ መረጃ ስላልነበረው ተመላሾች በድንገት መግባታቸውን እንደሰሙና ቅዳሜ ሚያዚያ 3/2012 ምሽት ኹለት ሰዓት ላይ ባረፉበት ባህር ዳር ከተማ በዕለቱ የከተማ እንቅስቃሴ ታግዶ ስለነበር ማረፊያ ያላቸው ወደ ማረፊያ ቤተሰቦቻቸው ተበትነው 240 ተመላሾችን የሚያርፉበት ቦታ በማጣታቸው በአንድ ቦታ ላይ ተሰባስበው እንዳገኟቸው ተናግረዋል።
እንደ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ገለፃ፣ ተመላሾች ስለአመጣጣቸው ከጉለሌ ክፍለ ከተማ ከተሰጣቸው የይለፍ ደብዳቤ ውጭ የሚገልጽ መረጃ እንደሌላቸውና የመጡበት ምክንያት በፈቃዳቸው ይሁን በግዳጅ የታወቀ ነገር አለመኖሩን ተናግረዋል። ኃላፊው አክለውም፣ ባህር ዳር ከተማ ተከማችተው የተገኙት 240 ሰዎች የሰጧቸው ምላሽ ሌሎች አብረዋቸው የተጓዙ ቁጥራቸው ያልታወቀ አንድ መኪና ሰዎች ከደጀን ጀምሮ እስከ ባህር ዳር ድረስ እየወረዱ ወደየ ቤተሰባቸው እንዳቀኑ ተናግረዋል ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት በአሁኑ ጊዜ በባህር ዳር ከተማ ተሰባስበው ያገኛቸውን 240 ሰዎች በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ማደሪያ ለ14 ቀን በለይቶ ማቆያ ክፍል እንዲቆዩ ተደርጎ የጤና ሁኔታቸው በጤና ባለሙያዎች ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑ ደረጀ ገለጸዋል። ባህር ዳር ሳይደርሱ የተበተኑ ተመላሾች የገቡበት ቦታ በግልጽ ስላልታወቀ ለዞኖችና ለወረዳዎች ወደ አካባቢያቸው የሚመጡ ሰዎችን ክትትል አድርገው በለይቶ ማቆያ እንዲያቆዩ ጥሪ ማስተላለፋቸውንም ደረጀ ጠቅመዋል።
‹‹ከአዲስ አበባ ወደ አማራ ክልል የተላኩት ሰዎች በትልቅ ስህተት የተደረገ ነው። መታረም አለበት›› ነው ያሉት የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶ/ር) ከአዲስ አበባ በኹለተኛ ቀን በድጋሚ ሊላኩ የነበሩ ሰዎችን ማስቀረታቸውን እና ከአዲስ አበባ ወደ ክልሉ የሚላክበት ሁኔታ ሕጋዊ አግባብነት እንደሌለውም ለክልሉ መገናኛ ብዙኀን ተናግረዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 76 ሚያዝያ 10 2012


