የአዲስ አበባ ፖሊስ 8 የተሰረቁ ተሸከርካሪዎች ከ16 ተጠርጣሪዎች ጋር መያዙን አስታወቀ

0
663

አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በተለያዩ ጊዜ የተሰረቁ 8 ተሽከርካሪዎችን ከ 16 ተጠርጣሪዎች ጋር ይዞ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የልዩ ልዩ እና የተደራጁ ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮማንደር አለማየሁ አያልቄ እንደተናገሩት ከኮሚሽኑ የክትትልና ኦፕሬሽን ዳይሬክቶሬት ጋር በመቀናጀት በተሰሩ ጥብቅ ስራዎች በአዲስ አበባ በተደጋጋሚ የሚፈፀሙ የመኪና ስርቆት ወንጀሎችን መቀነስ ተችሏል፡፡
የተሰረቁ ተሸከርካሪዎችን የማስመለስና ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ ሲሰራ መቆየቱን የጠቆሙት ኮማንደር አለማየሁ በቅርቡም በተለያዩ ጊዜያት ከከተማችን ተሰርቀው ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተወሰዱ 8 ተሸከርካሪዎችን በከፍተኛ ክትትልና ጥረት ማስመለስ እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡
የኮድ 2 ሰሌዳ ያላቸውን ተሸከርካሪዎች በድብቅ እያከራዩ ተሸከርካሪያቸው ሳይመለስላቸው ሲቀር ተሰረቀብን ብለው የሚያመለክቱ ግለሰቦች መኖራቸውን እና ወንጀሉ ሲጣራ ስርቆት ሳይሆን ማታለል አልያም እምነት ማጉደል ሆኖ እንደሚገኝ ያስታወሱት ኮማንደር አለማየሁ አያልቄ ከዚህ በተጨማሪ አሽከርካሪዎችና የተሸከርካሪ ባለንብረቶች መኪናቸውን ሲያቆሙ በሚያሳዩት ቸልተኝነት የወንጀሉን ቁጥር ሊጨምረው መቻሉን አስረድተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተሸከርካሪ ስርቆት ወንጀልን ለመቀነስ በሰራው ጠንካራ ስራ ውጤት ቢያገኝም አሁንም ወንጀሉን ለመቀነስ ብሎም ከምንጩ ለማድረቅ እንሰራለን ብለዋል ኮማንደር አለማየሁ አያልቄ፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 77 ሚያዝያ 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here