ኢትዮጵያ በረሃብ ከሚጠቁ አገራት አንዷ እንደምትሆን ተገለጸ

0
671

በርካታ አገራት ትኩረታቸውን ወደ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከማድረጋቸው ጋር ተያይዞ የረሃብ አደጋ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል የተተነበየ ሲሆን ከዚህም ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታወቀ። ለጋሽ አገራት እንዲሁም ዓለም በአጠቃላይ ትኩረቱን ወደ ወረርሽኙ በማድረጉ ተረጂ አገራት ከፍተኛ የሆነ የረሃብ ችግር ሊያጋጥማቸው እንደሚችል የዓለም ምግብ ፐሮግራም ባወጣው ሪፖርት ላይ አስፍሯል።
በዚህም ሳቢያ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዓለማችን የረሃብ አደጋ ያጋጥማታል ሲል ያስጠነቀቀው ሪፖርቱ ከፍተኛ ትኩረት ካልተሰጠው በዓለም አቀፍ ደረጃ በዚህ ዓመት የምግብ እጥረት የሚያጋጥማቸው ሰዎች በእጥፍ ሊጨምር እንደሚችል አስታውቋል።
በፈረንጆቹ 2019 ላይ በመላው ዓለም አስቸኳይ የምግብ እርዳት ያስፈልጋቸው የነበሩ ሰዎች ቁጥር 135 ሚሊዮን ነበር። በያዝነው የፈረንጆቹ 2020 ግን በቫይረሱ ስርጭት ምክንያት ሰዎች ከቤት እንዳይወጡ ከመደረጉ ጋር ተደራርቦ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር 265 ሚሊዮን ይሆናል ብሏል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም በፈረንጆቹ 2020 በከፍተኛ ደረጃ በረሃብ የሚጠቁት 5 የዓለማችን አገራትን ለይቷል። እነዚህም የመን፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ አፍጋኒስታን፣ ቬንዙዌላ እና ኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹ አምስት አገራት ናቸው።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ጠቅላላ የሕዝብ ቁጥር 112.1 ሚሊዮን ነው ይላል። እንደ ድርጅቱ አሃዝ ከሆነ ከጠቅላላው ሕዝብ 8 ሚሊዮን የሚሆኑት አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ፣ ግጭቶች እና የምግብ ዋጋ መናር የአስቸኳይ ምግብ ፈላጊዎች ቁጥርን ከፍ አንዲል ስለማድረጉ ድርጅቱ አስታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 77 ሚያዝያ 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here