የኮቪድ-19 ‹በረከቶች›

0
961

የብሔር ብዝኀነትን እንዲሁም የሃይማኖት ልዩነትን ወደ ግጭት የሚወስዱ የሐሳብ ተሽከርካሪዎች ላይ ተሳፍራ የቆየችው ኢትዮጵያ አስፈሪ ወደሆነና ወደማይገመት ቁልቁለት እየወረደች እንደሆነ በማሰብ ብዙዎች ሰግተው ነበር። ይህ ከወራት በፊት የነበረ እውነት ነው። ከማኅበራዊ ሚድያ በሚነሱ የግለሰቦች አስተያየት ምክንያት የብዙዎች ሕይወት በአንድ ጀንበር ሲነጠቅና ብዙዎችም ሲፈናቀሉ መታዘብ ተችሏል። ታሪክም ምስክር ሊሆን መዝግቦታል። በዚህ መካከል ነበር፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በድንገት ተከስቶ የተያዘውን መንገድ ያስቀየረው።
አሁን አጀንዳው ሁሉ ኮቪድ 19 የተሰኘው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሆነበት ጊዜ፣ ጎልተው እየተሰሙ ያሉ ዜናዎች ደግሞ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ናቸው። የሌላውን ችግር እንደራስ አይቶ መርዳትና ማገዝ፣ ካለው ላይ ማካፈልና ቀንሶ መስጠትም ይታያል። ይህም ከመንግሥት ጀምሮ በባለሀብቶች እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ጭምር ሲደረግ መታዘብ ተችሏል።
ታድያ በበጎ አድራጎትና ልገሳ ዙሪያ ሰዎች የተለያየ አመለካከት አላቸው። አንዳንዶች ልገሳን በገንዘብ ሲተምኑት ሁሌም ከእነርሱ የተሻለ የገንዘብ አቅም ያለው የተሻለ ይሰጣል ብለው ያምናሉ። በአንጻሩ ሰው ከልቡ ካሰበ የሚሰጠው ነገር አያጣም የሚሉም አሉ። ለእነዚህ ደግሞ ‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው!› መርሐቸው ነው። ይህንንና አሁን ላይ ወረርሽኙን አስመልክቶ የሚደረጉ የድጋፍ ማሰባሰቢያ ተግባራት ያሉበትን ሂደትና ደረጃ፣ ምን አይነት በጎ አድራጎት ሥራዎች ተሠሩ በሚልና ተያያዥ ጉዳይ ላይ፣ ባለሐሳቦችን፣ ባለሞያዎችንና በጎ አድራጊ ግለሰቦችን በማናገር እንዲሁም መዛግብትን በማገላበጥ የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጋዋለች።

በየእለቱ (አንዳንዴም በየኹለት ቀን) ባለመኪናዋ ወይዘሮ 24 ተብሎ በሚታወቀው ሰፈር አካባቢ፣ ወደ መገናኛ በሚወስደው መስቀለኛ መንገድ ላይ ይታያሉ። መኪናቸውን መብራቱን ሳይሻገሩ ካለው እግረኛ መንገድ ላይ ተጠግተው ያቆማሉ። ከመኪናው ቀልጠፍ ብለው ይወርዱናም የመኪናውን የኋላ ወንበር ከፍተው አንዳንዴ ተለቅ ባለ ፌስታል ሌላ ጊዜ ደግሞ ትልቅ የፕላስቲክ ሳህን ያወጣሉ። ቀጥለው አሻግረው ከጎዳናው የእግረኛ መንገድ ተሰብስበው ወደተቀመጡ ልጆች ይመለከታሉ።

ልጆቹ ያውቋቸዋል። ‹ማዘር› ነው የሚሏቸው እንጂ ሥማቸውን ግን የሚያውቁ አይመስሉም። መምጣታቸውን ሲያዩ በፍጥነት ይሰበሰባሉ። የሚያስተባብርላቸው አንድ ወጣት ተጠግቶ ያመጡትንና በስስ ፌስታል የተቋጠረውን ምግብ ያከፋፍልላቸዋል። ተከፋፍሎ እስኪዳረስ ይጠብቃሉ። ምግቡም በልካቸው ነውና የሚዘጋጀው በአካባቢው ላሉ 21 ልጆች ይደርሳቸዋል። ‹ራቅ ራቅ ብላችሁ! ራሳችሁን ጠብቁ እሺ!› ሲሉም ልጆቹን ይመክራሉ። ብዙም አይቆዩም፣ ልጆቹን ተሰናብተው መኪናቸውን አስነስተው ይሄዳሉ። በማግስቱም እንደዛው፣ በሌላ ቀንም በተመሳሳይ።

በአቅራቢያው ባሉ የንግድ ሱቆች ውስጥ የሚገኙና ጉዳዩን የሚታዘቡ ሰዎች ለእኚህ ሴት ምስጋና ነፍገው አያውቁም። አዲስ ማለዳ ይህን ሐተታ ለመሥራት ልታናግራቸው ፈልጋ ተጠግታ ነበር። ምሳሌ እንዲሆን ያህል ብቻ ሲሉ ከሐሳባቸው ጥቂት ነው ያካፈሏት እንጂ ስለራሳቸው ብዙ ማውራትን አልፈለጉም።
እንዲህ ነው። የረር በር አካባቢ የሚኖሩት እኚህ እናት፣ በቅርብ የሚያውቋቸውን ጎረቤቶቻቸውን ‹ልጆቹን ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ ምግብ እናብላቸው› ሲሉ ያማክራሉ። እነዚህም ሰዎች ፈቃደኛ በመሆን የተጠየቁትን ያደርጋሉ። እኚህ እናት ደግሞ ፈቃደኛ የሆኑላቸው ሰዎች ግብዓት እንዲያሟሉ ብቻ ይጠይቃሉ።
ምግቡን ቤታቸው አብስለው፣ አሰናድተው በፌስታል ቋጥረው፣ በእለቱ ለማብላት ፈቃደኛ የሆነውን ወይም የሆነችውን ግለሰብ ይዘው ወደ ልጆቹ ይሄዳሉ። አብረው መሄዳቸው ጥቅም እንዳለው ጠቅሰዋል። ይልቁንም በወር አንድ ቀን ትንሽ ብር በመስጠት ልጆቹን በቀን አንዴ ለመመገብ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች፣ ቦታው ድረስ ሄደው ለልጆቹ ምግቡን ራሳቸው መስጠታቸው፣ ቢያንስ በወር ኹለት ጊዜና ከዚያ በላይም ያንን በጎ አድራጎት ለመፈጸም ይገፋፋቸዋል ብለው ስለሚያምኑ ነው።
አሁን በዚህ የበጎ አድራት ሥራ ኹለተኛ ሳምንታቸውን የያዙት እኚህ እናት፣ የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ልጆቹን የሚቀርባቸው ስለሌለና የከተማ መስተዳደሩም ቃል እንደገባው እስኪያነሳቸው ድረስ የአቅሜን ላድርግ ብዬ ነው የሚል ሐሳብም ሰጥተዋል።

እንዲህም አሉ፤ ‹‹ሲመስለኝ ይህ ለአገራችን፣ እኛው እርስ በእርሳችን ተጠፋፍተን እንዳናልቅ የመጣ ማስጠንቀቂያ ደወል ነው። ለዓለማችን ኢኮኖሚ እንዲሁም ማኅበራዊ ሕይወት ብዙ ቀውስ አምጥቶ ይሆናል። እኛ በራሳችን ላይ ካደረግነው የከፋ አይደለም። በጦርነት ስንተላለቅ ኖረናል። እናም ክስተቱን እንደ ማንቂያ ደወል ለኢትዮጵያም እንደ በረከት ምንጭ ሊቆጠር ይችላል ብዬ አምናለሁ።››

የእኚህ እናት ድርጊት ለእርሳቸው የመጀመሪያ አይመስልም። በዝርዝር ለመግለጽ አልወደዱም እንጂ ኑሯቸውን ጎዳና ላደረጉ ልጆች ምግብ የመስጠትና የማድረስ ልምድ እንዳላቸው ንግግራቸው ያሳብቃል።

ቀጣዩ ደግሞ ሌላ ታሪክ ነው። ‹‹ሊመጣ ይችላል እየተባለ የሚጠበቀው ነገር ያስፈራል። አሁን እየሆነ ያለው ግን ተስፋ ሰጪና ደስ የሚያሰኝ ነው።›› አለች። ወጣት ናት፤ በሰዎች ቤት እየተዘዋወረች ልብሶችን ታጥባለች። ዳዒቱ (ሥሟ የተቀየረ) ነዋሪነቷ ገርጂ መብራት ኃይል አካባቢ ነው። በኑሮ አጋጣሚ የሕይወት መንገዷ መቀየሩንና፣ ትምህርቷን አቋርጣ በገባችበት የትዳር ሕይወት ልጆች አፍርታ ነገር ግን የኑሮ ዳገት በቀላሉ አልገፋ ብሏት በየሰው ቤት የምትችለውን ሁሉ በመሥራት እየታገለች የምትገኝ ሴት ናት።

‹‹ሦስት ልጆች አሉኝ። ኹለቱ መዋዕለ ሕጻናት ነው ያሉት። የመጀመሪያዋ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብታለች። አሁን ግን ሦስቱም ቤት ናቸው። ወጥቼ እንደበፊቱ ሥራ ለመሥራት አልቻልኩም። ለጎረቤት ሰጥቶ እዛ እንዲውሉ ማድረግም የሚቻል አይደለም። ማዋያ ባገኝ እንኳ ምን እሠራለሁ? ማንም ቤት ለሥራ መሄድ ከባድ ነው።›› ስትል የሆነውን ታስረዳለች።

በምትኖርበት ወረዳ ታድያ ከፋሲካ በዓል በፊት በመሄድ የተወሰነ ድጋፍ ማግኘቷን አንስታለች። ‹ላለው ይጨመርለታል…› እንዲሉ፣ የተወሰኑ አሠሪዎቿ ነገሮች እስኪስተካከሉ ድረስ በአቅማቸው ያላቸውን እንደሚሰጧትና ደሞዝም እንደሚከፍሏት ነግረዋታል። ልጆቿን ለብቻዋ የምታሳድገው ዳዒቱ ስለተደረገላት ነገር ታመሰግናለች።

‹‹አሠሪዎቼ እንዲህ ያደርጉልኛል ብዬ አላሰብኩም ነበር። ባያደርጉልኝም ብዙ አልከፋም ነበር፤ ምክንያቱም ይሄ ከሁላችንም አቅም በላይ ነው። ግን እኔንም ልጆቼንም ምን ይውጠን እንደነበር ሳስብ እደነግጣለሁ። ብዙ የማውቃቸው ሴቶች ያለሥራ ሲቀሩ አይቻለሁ። እናም በሽታው ብዙ መከራን በዓለም ላይ ያመጣ ቢሆንም፣ በዛም ውስጥ የአንዳንድ ሰዎችን በጎነት አሳይቶናል። ይህ ቀን አልፎ ለመመሰጋገን እንዲያበቃን ምኞቴ ነው›› ስትል ሁኔታውን ገልጻለች።

የሃይማኖት ሰዎች በሽታ የበረከት ምንጭ ወይም ምክንያት ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል ሲናገሩ ይደመጣል። ምክንያቱም ሰው ወደ ፈጣሪ ለመመለስና ልብ ለመግዛት የሰውነቱን ደካማነት መረዳት አለበት ተብሎ ስለሚታመን። ከትዕቢትና መታበይ ለመቆጠብ ሕመም ትልቅ አጋጣሚ ይሆናል በሚልም ነው። በተጓዳኝ ደግሞ መልካም ሥራን ለመሥራት፣ እርስ በእርስ ለመደጋገፍና ለመተሳሰብም አጋጣሚ ይፈጥራል።

በእርግጥም የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሰብአዊነትን የቀሰቀሰ ይመስላል። በመካከል አጋጣሚውን ለመጠቀም የሚሹና ማኅበረሰቡ እኩይ በሚላቸው ምግብር ውስጥ የሚገኙ ጥቂቶች ቢኖሩም፣ ከየአካባቢው የሚወጡ መልካም ዜናዎች ደግሞ በአንጻሩ የሚናገሩ ናቸው።

የጥሪ ድምጾች
‹ሴቭ ዘ ቺልድረን› የተባው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ይህ ወረርሽኝ ትውልድ ካያቸው አስከፊ ቀውሶች መካከል አንዱ ነው ሲል በድረ ገጹ አስነብቧል። ‹ሳይረፍድ ልጆችን እንርዳ!› የሚል ጥሪውንም ከወራት ቀድሞ ሲያስተላልፍም ሰንብቷል። ለዚህም መቶ ሚሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል ብሏል፣ ድርጅቱ። ይህም ለእርዳታ አስፈላጊ ነው የተባለ፣ በተቋም የ100 ዓመት ታሪክ ከፍተኛው የሆነ የገንዘብ መጠን ነው።

የጤና ስርዓቱ ትኩረት ከመሰረቁ በተጓዳኝ ኢኮኖሚ እየወረደ መምጣቱ አንድ ፈተና ሆኖ ሳለ፣ ጎነ ለጎን 1.5 ቢሊዮን የሚደርሱ ሕጻናት መደበኛ ትምህርታቸውን አቋርጠዋል። የቤተሰብ አባላት በአንድ ጎን ወጥተው መሥራትና ገቢ ማግኘት ባለመቻላቸው፣ ሲብስ ደግሞ በመታመማቸውና ሕይወታቸው በማለፉ፣ በደሃ አገራት ድህነት ጭራሽ ጸንቷል።

ይህ አንዱ ጥሪ ነው። ለልጆች እንድረስላቸው የሚል የድጋፍና እርዳታ ጥሪ። ታድያ በኢትዮጵያም ያሉ መንግሥታዊ ያልሆነ በጎ አድራጊ ድርጅቶች ተመሳሳይ ጥሪዎችን ተሰሚ ናቸው ባሏቸው ሰዎች በኩል ሲያስተላልፉ ተሰምቷል። ወረርሽኙም ያስከተለባቸው ጫናም ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ያስረዳሉ።

አዲስ ማለዳ ከስለእናት በጎ አድራጎት ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ልዑልሰናይ ደመና ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርጋለች። ‹‹እኛ እንደተቋም የወሰድናቸው እርምጃዎች አሉ።›› ያሉት ልዑልሰናይ፣ ሞግዚቶች መንቀሳቀስ ስለማይችሉ በጊቢው እንዲቆዩ መደረጉ፣ ምግብ በማብሰል የሚያገለግሉ እንዲሁም ጥበቃ ላይ የተሰማሩ ሠራተኞችም በዛው መልክ እንደቀድሞው መውጣት መግባት አለመቻላቸውን አንስተዋል። ይህም በአንድ በኩል የትርፍ ሰዓት ክፍያን በተጨማሪም ለተጨማሪ ሰዎች ምግብ ማዘጋጀትን ግድ ብሏል። በድምሩ ወጪ ነው።

‹‹በዛም ላይ መጥቶ የሚጠይቅና የሚጎበኝ አይኖርም። ያ ካልሆነና ሰዉ እየተሠራ ያለውን ካላየ ደግሞ ሊያግዝ አይችልም፣ ይቸገራል። ጉዳዮም የዓለም ስለሆነ አገር ውስጥ ሲጠፋ ወደ ውጪ ይኬዳል የሚባል ነገር የለም። እንደውም እነርሱ ከእኛ የባሰ ተቸግረዋል። አማራጭ የለም። በሁሉም አቅጣጫ ከባድ ጫና ነው እያሳደረ ያለው።›› በማለት አስረድተዋል።

እርግጥ ነው! ወረርሽኙ ያስከተለውን ጥፋት ልብ በሚነኩ አገላለጾች ብዙዎች ተናግረውታል። አሳዛኝም ነው። በዚህ መካከል አብርቶ የሚታይ በጎነት ደግሞ አለ። በተለይም የበጎ አድራጎት ሥራዎችና ልገሳዎች በስፋት እየታዩ ነው።

ስለ በጎ አድራጎት ምን ያስባሉ?
የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ስርጭት መጠን በጨመረ ቁጥር የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን እንዲሁም ሊደረግ የሚገባው ድጋፍ በዛው ልክ ይጨምራል። በኃያላኑ አገራት በእነ አሜሪካ ሳይቀር በጥቂት ወራት ከ2.2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሥራ አጥ ሆነዋል። ይህም የኢኮኖሚ ቀውስ ከመሆኑ በላይ ማኅበራዊ ሕይወትና በየአንዳንዱ ግለሰብ ሕይወት ላይ ከባድ አሉታዊ ተጽእኖ አለው። እናም አቅም ያላቸው ሰዎች ኪሳቸውን ፈተሽ ፈተሽ እያደረጉና የበጎ አድራጎት ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ።

በጎ አድራጎት ከኪስ ብቻ የሚወጣ ነውን? ለዚህ ጥያቄ ወደ መልስ የሚገፋ አንድ ጥናት ተደርጓል። ይህም ጥናት የበጎ አድራጎትና ልገሳ ገንዘብ ካላቸው ባለሀብቶች ብቻ የሚጠበቅ አይደለም ወይም ከእነርሱ ብቻ መጠበቅ የለበትም ሲል ያስታውቃል። “Passing the buck to the wealthier: Reference-dependent standards of generosity”, በተሰኘና በአሚት ባቻርዤ እንዲሁም ባልደረቦቻቸው የተዘጋጀ ጥናታዊ ወረቀት ላይ፣ ከገቢ መጠን ማነስ ወይም መብዛት ባሻገር፣ ሰዎች ከእነርሱ የተሻለ ገቢ ያላቸው ሰዎች እንዲለግሱ ይጠብቃሉ ይላል።

የሚገርመው ታድያ እንዲያ የሚባሉት ባለሀብቶችም በራሳቸው ከእነርሱ በላይ የገንዘብ አቅም ያላቸው ባለሀብቶች የበለጠውን ልገሳ እንድሰጡ መጠበቃቸው ነው። ‹‹በዚህም ምክንያት…›› ይላል ጥናቱ፣ ‹‹በዚህም ምክንያት በጣም ባለሀብት የሆኑ ሰዎች ሳይቀሩ የሰጡት የተወሰነ የገንዘብ መጠን በቂ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይህ ግላዊ ስሜት ድጋፍ የመስጠትን መጠን እንዲቀንስ ያደርገዋል››

ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ ለመረዳትና የቆሙበትን ለማወቅ ከሌሎች ጋር ራሳቸውን ያነጻጽራሉ። አጥኚዎቹ ይህንን መሠረት አድርገው የተለያየ የጥናት ዘዴዎችን በመጠቀም ሐሳባቸውን እንደሚከተለው አካፍለዋል።

እንደ ጥያቄ ያነሱት ሰዎች ድጋፍ መስጠትን በተመለከተ ለራሳቸው ኃላፊነት ሲሰጡና ለሌሎች ያንኑ ኃላፊነት ሲሰጡ ያለውን ልዩነት በማጤን ነው። እንዲህ አደረጉ፣ 505 የጥናቱ አካል የሆኑ ግለሰቦችን አንድ ጥያቄ ጠየቁ። ጥያቄውም ‹‹ዓመታዊ ገቢያቸው ከ50 ሺሕ ዶላር በላይ የሆነ ሰዎች፣ ከዚህ ውስጥ ለድጋፍ የሚውል ስንት ቢሰጡ መልካም ነው?›› ይላል።

ኹለተኛ ደግሞ 1 ሺሕ 2 የጥናቱ አካል የሆኑ ሰዎችን፣ በእነርሱ ደረጃ ያለ ሰው ለድጋፍ ምን ያህል መስጠት አለበት የሚል ጥያቄ አቀረቡ። በእነዚህ ኹለት ጥያቄዎች የተሰጠው መልስ ሲታይ ታድያ፣ ከተጠቀሰው 50 ሺሕ ዶላር ገንዘብ ያነሰ ገቢ የሚያገኙና ገቢያቸውም ከዛ እያነሰ በሄደ ቁጥር፣ ለእርዳታ ሊሰጥ የሚችለውን የገንዘብ መጠን ከፍ እያደረጉ ነበር የሚጠሩት።

በተጨማሪም ጥናቱ ተገላቢጦሽ የሆነ ሌላ መልክ አሳይቷል። ይህም ሰዎች ገቢያቸው ዝቅተኛ እየሆነ በሄደ ቁጥር ከእነርሱ እጅግ የበለጠ ገቢ የሚያገኝ ሰው ለድጋፍ ሊሰጥ የሚገባውን የገንዘብ መጠን ከፍ እያደረጉት ይሄዳሉ። በአንጻሩ ገቢያቸው ከተጠቀሰው የገንዘብ መጠን እየተጠጋ በሄደ ቁጥር፣ ለድጋፍ ሊሰጥ የሚችለውን የገንዘብ መጠን ይቀንሱታል።

በጥቅሉ በሁሉም የገቢ ደረጃ ላይ፣ ሰዎች፣ ራሳቸው እንዲሁም አነስተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ድጋፍ የመስጠት ግዴታ እንዳይኖርባቸው ምህረት ሊደረግላቸው ወይም ሊታለፉ ይገባል የሚል ዓይነት አስተያየት ነበር የሰጡት።

አጥኚዎቹ ባማረ አገላለጽ እንዳስቀመጡት፣ ሰዎች የተሻለ ገንዘብ ማግኘት ሲጀምሩ፣ ወጪያቸውንም ይጨምራሉ። እናም ድጋፍ ለማድረግና ለእርዳታ ለመስጠት ከዛ የበለጠ ገቢ ማግኘትን ይጠብቃሉ። ይህ በሌላ አገላለጽ፣ እርዳታ አልያም ድጋፍ የመስጠት ነገር ሲነሳ፣ አንደኛ ጉዳዩን ይበልጡናል ወደሚሏቸው ባለሀብቶች ያስተላልፉታል። ካልሆነም ለወደፊት ያስቀምጡታል፣ ነገ ከዛሬ የበለጠ ገንዘብ ስለማገኝ ያኔ እለግሳለሁ በሚል ስሜት።

ይህ በ2019 የተደረገው ጥናት 400 ባለሀብቶችን ያሳተፈ ነበር። ባለሀብቶቹ በበርክሌይ ባንክ መሠረት የተቀመጡ ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ባለሀብቶች ወስጥ 75 በመቶ የሚሆኑት ታድያ የልግስና ሥራን ከእነርሱ በላይ ሀብታም የሆኑ ሰዎች ኃላፊነት እንደሆነ አድርገው ነው ያሰቡት። ‹ውፍረት ለራስ አይታወቅም…› እንደሚባለው፣ ብዙ ባለሀብቶች ራሳቸውን እንደ ባለሀብትም ሆነ በገንዘብ ስጋት እንደሌለባቸው አድርገው አይቆጥሩም።

እናም ይህ ቅብብል መቆምና ሁሉም ባለበት ቀና ብሎ እገሌ ምን አደረገ የሚለውን ሳይሆን ምን ማድረግ እችላለሁ የሚለውን በማየት መለገስ አለበት የሚል ጠቅለል ያለ መልእክት አስተላልፈዋል፤ አጥኚዎቹ።

የብዙዎች ጥያቄ ከዚህ አይርቅም። ‹ምን ልሰጥ እችላለሁ?› ይላሉ። በጎ አድራጊነትም በገንዘብና በቁሳቁስ ብቻ የሚተመን ሲመስላቸው፣ ሊሰጡ የሚችሉት እያለ ነገር ግን እንደሌላቸው በመሆን ከመለገስ እንዲታቀቡ ያደርጋል።

ዲያቆን ሔኖክ ኃይሌ ሰውን ለመርዳት አንዳች መንገድ እንደማይጠፋ ያነሳሉ። በክርስትናው እንደውም ለመርዳት መፈለግ በራሱ ትልቅ ዋጋ እንዳለው ጠቅሰዋል። በተጨማሪም ድጋፍ የሚያደርጉና እርዳታ የሚሰጡ ሰዎችንም ማመስገን በራሱ አንድ ትብብር ነው ሲሉ፣ አያይዘውም ‹‹እኔ የምሰጠው ባይኖረኝ ግን የሚለግሰውን ደግሞ የማጣጥል ከሆነ ልክ አይሆንም›› ብለዋል።

ታድያ በቅዱሱ መጽሐፍም ላይ ገንዘብ ያለው ብቻ ሳይሆን የሌለውም ሊያደርግ የሚችለው በጎ አድራጎት ስለመኖሩ ጠቅሰው ያስረዳሉ። በዚህም ‹ብራብ አላበላችሁኝም፣ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝም፣ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝም፣ ታርዤ አላለበሳችሁኝም፣ ታምሜ፣ ታስሬም አልጠየቃችሁኝም›› የሚለውን ቃል ያነሳሉ። ‹‹ምግብ ለማብላት ብር ያስፈልግ ይሆናል፤ ውሃ ለማጠጣት ግን አያስፈልግም። የታመመን ለመጠየቅ ወይም እስር ቤት ለመሄድ ገንዘብ ግድ ሊኖረን አይገባም። እንዲሁ [ያለገንዘብ] ሊደረጉ የሚችሉ በጎ ሥራዎች አሉ›› በማለት ከገንዘብ ባሻገር ሊሰጥ የሚችል በጎ አድራጎት ስለመኖሩ ያነሳሉ።

ለዚህ አንድ ማሳያ ሰላም ኢትዮጵያ ነው። ሰላም ኢትዮጵያ በባህል ዙሪያ የሚሠራ በጎ አድራጎት ድርጅት ነው። የድርጅቱ ካንትሪ ዳይሬክተር ሳሙኤል ሙሉጌታም በዚህ ላይ ሐሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ ሲያካፍሉ እንዳሉት፣ ሰው በጎ አደረገ የሚባለው ባለው ችሎታና አቅም ያለውን ለኅብረተሰቡ መስጠት ሲችል ነው። ‹‹ሙዚቃ የሚማሩ፣ ሰርከስ የሚችሉ ወይም ፊልም የሚሠሩ አሉ። ሙያቸውና የሚችሉት እሱን ነው። እንዴት ላስተምር የሚለውን በሚችሉት መንገድ መግለጽ ይችላሉ። ሁሉም ተመሳሳይ ነገር መሥራት አለበት ብዬ አላምንም። ባላቸው ማገልገላቸው ትልቅ ድርሻ ነው። ብዙ ነገር ማድረግ ይቻላል፤ ባለን እውቀትና አቅም።›› ብለዋል።
ለዚህም ድርጅታቸው ሰላም ኢትዮጵያ በተለያዩ ቋንቋዎች ስለቫይረሱና ሊደረጉ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች የሚያስተላልፉትን መልእክቶች አንስተዋል። ‹አስቸጋሪውን ጊዜ አሸንፈን እንሻገር› የሚል መሪ ሐሳብ ያነገበው አጠር ያለ ግንዛቤ ማስጨበጫ አጭር ቪዲዮም በመደበኛ መገናኛ ብዙኀን እንዲሁም በማኅበራዊ ሚድያዎች ላይ ብዙዎች የተጋሩት ነው። ይህም በአንድ ጎን ባለሞያዎች ዝናቸውን፣ ችሎታና አቅማቸውን በመጠቀም መልእክትን ለማስተላለፍ መፍቀዳቸው በጎ ፈቃድ በዚህም ሊገለጥ እንደሚችል ማሳያ ነው ብለዋል።

በበጎ አድራጎት ሥራ እንቅስቃሴዎች ግንባር ቀደም ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ ይገኛል፤ ያሬድ ሹመቴ። ያሬድ በበኩሉ ጉልበትንም እንደ በጎ አድራጎት መለገስና መስጠት ይቻላል ባይ ነው። ሰው ሊሰጠው የሚችለው ነገር ሊያጣ አይችልም ሲል ቀጥሎ፣ የመቄዶንያ መሥራች ቢንያም በለጠ መሪ ሐሳብ የሆነውን ‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው› የሚለውን ነጥብ አንስቷል።

‹በጎ ማድረግ ከራስ አልፎ ለሌላ ሰው ማሰብና መጨነቅ መሆኑን ከተማመንን፣ በምን ማገዝ እንዳለብን እናውቃለን። አንድ ሰው በሚጠጣው ቡና ወይም ሻይ ሦስት ማንኪያ ስኳር የሚያደርግ ከነበረ፣ አንዷን መተው ይችላል። ለራሱም ጤና ነው፣ ለሌለውም ያንን ያቀምሳል። ይህን ለማድረግ አቅም አነሰኝ ማንም ሊል አይችልም።›› ብሏል።

እናም በጎ አድራጎት ሲባል መንገድ ላይ ሆነው አብረቅራቂ ጃኬት ቢጤ ጣል አድርገው እጅ የሚያስታጥቡ፣ በታክሲ ተራዎች አካባቢ ሰዎች እንዲራራቁ የሚያሳስቡ፣ ለአላፊ አግዳሚ ውሃና የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር ያኖሩት፣ በትራንስፖርት ሰልፍ ሰዎች እንዳይጠጋጉ አራርቀው በቀለም ያሰመሩ፣ ከእነዚህ ተግባራት ጀምሮ ሆቴላቸውን፣ ሕንጻቸውን፣ ገንዘብና እውቀታቸውን እስከሰጡት ድረስ የሚያካትት ነው፤ እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ገለጻ።

በባህር ማዶ እንደ በጎ አድራጎትና ልገሳ የተቆጠሩ ድርጊቶች ለሰሚው ትንሽ ሊመስሉ የሚችሉት ጭምር ናቸው። ለምሳሌ ሲኤንኤን በዘገባው ያነሳውን አንድ ታሪክ እናንሳ። እንዲህ ነው፤ የአሜሪካዋ ኦሃዮ ግዛት የሚኖሩና በቫይረሱ ምክንያት ተገልለው ለብቻቸው የተቀመጡ የ70 ዓመት አዛውንት፣ የቫይረሱ ዜና ከተሰማ በኋላ በፊታቸው ላይ ፈገግታን የፈጠረ ክስተት ሆነ። ይህም የስድስት እና የዘጠኝ ዓመት ልጆች ከእኚህ እናት ደጅ ላይ ሆነው ቫዮሊን በተባለው የሙዚቃ መሣሪያ ያሰሙት ዜማ ነው። እኚህ ልጆች በአንድ ተመልካቻቸው ፊት፣ እልፍ ሰዎች ባሉበት መድረክ ላይ እንደቆሙ ሥራቸውን አድምቀው አቅርበዋል። ያንን ያደረጉት እኛን በእድሜ የገፉ ሴት ‹ከጎንሽ ነን፣ አልዘነጋንሽም› ሲሉ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ቴዎድሮስ አድኀኖም እንዲህ አሉ፤ ‹‹ሰዎች በጋራ እያደረጉት ያለውን ጭብጨባና ኅብረ ዝማሬ አይተን ተነክተናል። ይህንን አስደናቂ የስብእና ተግባር ከቫይረሱ በላይ አጥብቀን መያዝ አለብን። ለተወሰነ ጊዜ በአካል ብንራራቅም፣ ከዚህ ቀደም አድርገነው በማናውቅ መልኩ በሐሳብና በመንፈስ ልንቀራረብ እንችላለን። ሁላችንም በዚህ አብረን ነን። ልናሳካ የምንችለውም አብረን ስንሆን ብቻ ነው።››

የኮቪድ19 ‹በረከቶች›
ሰዎች አሁን እርስ በእርስ ይደጋገፋሉ፣ ይተሳሰባሉ። ሰውነት በራሱ አላግባባ ይላቸው የነበረ፣ አሁን ሰውነትን በሚጎዳ ወረርሽኝ ምክንያት ተግባብተው እየተደማመጡ፣ ለጋራ ችግራቸው የጋራ መፍትሄ እየፈለጉ ይመስላል። ‹በአካል እንዳትገናኙ!› ቢባልም፣ ከመቼውም በላይ ሰዎች በመንፈስና በሐሳብ እርስ በእርሳቸው ተሳስረዋል። ባለሀብቶችና ግለሰቦች ቤታቸውን ለማቆያነት ሰጥተዋል፣ ገንዘብ ለግሰዋል፣ ቋሚ ድጋፍ ለመስጠት ቃል ገብተዋል፣ ከጥቅማቸው አጉድለዋል ወዘተ።

ኢትዮጵያውያን ለበጎ አድራጎት ሥራዎች እንግዳ እንዳይደሉ ከባህልና ታሪክ ተጠቅሶ ይነገራል። አሁን የኮሮና ቫይረስ ስጋት በጣለበት ጊዜ ደግሞ እነዚህ የኖሩ የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴዎች ሲበረቱ፣ አዳዲስ ደግሞ በርካቶች ተፈጥረዋል። ይልቁንም በአገር አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ የእርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ ተመሥርቶም ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ማስተዋል ይቻላል።

ያሬድ ሹመቴ ከባልደረቦቹ ጋር በጋራ የሚያስተባብሩበት ‹ቅድሚያ ለሰብአዊነት – የሰብአዊነት ድጋፍ ጥምረት› የተሰኘው የድጋፍ አሰባሳቢ ኅብረት ይጠቀሳል። አዲስ ማለዳ ከያሬድ ጋር ባደረገቸው አጭር ቆይታ ያነሳችው አንዱ ጥያቄ፣ አሁን ወረርሽኙን ተከትሎ የሚታየው ድጋፍ የመስጠት እንቅስቃሴ ቀድሞ ይታይ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ምን መልክ አለው የሚል ነበር።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ እየተሰበሰበ ያለው ድጋፍ እንደወትሮው ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሚሄድ ሳይሆን ተደራሽነቱ ለአዲስ አበባ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብሏል። ከዛም ውጪ እነ ያሬድ ከሚሳተፉበት ‹ቅድሚያ ለሰብአዊነት› እንቅስቃሴ በተጨማሪ በመንግሥት ደረጃ እንዲሁም በተለያዩ ተቋማት ድጋፍ ሲደረግ መታየቱም የተለየ ያደርገዋል ሲል ጠቅሷል።

ያም ሆኖ አሁን ያለው የመስጠት አንቅስቃሴ ከዚህ ቀደም ከነበረው በታች ነው ብሎ ያስባል። ይህንንም ያለው ከተገኘው ገቢ አንጻር አይደለም። ይልቁንም አስቅድሞ ድጋፍና እርዳታ ላይ ይሳተፉ ከነበሩ ሰዎች ብዛት አንጻር ነው። በትምህርት ቤት ጓደኛማቾች፣ አንድ የሥራ ቦታ ያሉ የሥራ ባልደረባዎች፣ አንድ ኮንዶሚኒየም ውስጥ የሚኖሩ ግለሰቦች ወዘተ ሰዎች ሰብሰብ ብለው ድጋፎችን ይሰጡ ነበር። በአንጻሩ አሁን ግን ድርጅቶች ናቸው ልገሳ እያደረጉ ያሉት። ይህም የገንዘብ መጠኑን ከፍ አድርጎታል።

ይህ ምንአልባት አብዛኛው ሰው ለራሱም ጭምር የሰጋ ከመሆኑ ጋር ሊገናኝ ይችላል፣ በያሬድ እይታ። ያም ሆኖ ሰው ካለው ላይም ከማካፈል መቦዘን እንደማይኖርበት አንስቷል።

ታድያ ግን ቀድሞ በኅብረታቸው የድጋፍ ማሰባሰቢያ ሲደረግ ምክንያቱ በዐይን የሚታይና ሊጎበኝ የሚችል እንደነበርም ያወሳል። በተፈጥሮአዊ አደጋ ኑሯቸውና መኖሪያቸው የተጎዳ አልያም በሰዎች ጥፋት ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ነበሩ። ይህም በዐይን የሚታይ በመሆኑ ብዙዎች ለድጋፍ እንዲነሳሱ አድርጓል። ይህኛው ወረርሽኝ ግን በዐይን የሚታይ ጥፋት ሳይሆን በጊዜ እየበረታ የሚሄድ ማኅበራዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የሚያስከትል ነው። እናም በዐይን የሚታይ ባለመሆኑ የድጋፍና እርዳታ አስፈላጊነት ቢነገር እንኳ ሰርጾ እንዲገባና ብዙዎች በፍጥነት እንዲነሳሱ ማድረጉን አስቸጋሪ ያደርገዋል የሚል እምነት አለው።

የተደረጉ ድጋፎችና ዓላማቸው
ሰዎች በግለሰብ ደረጃ እንዲሁም እንደ ተቋም አሁን ላይ ቀላል የማይባሉ ድጋፎችን እያደረጉ ይታያል። ምን ያህሎቹ ከልብ ቅንነት በመነሳት፣ የእውነት ችግሩን ለመጋፈጥ በማሰብ፣ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች በትክክል በማሰብ፣ ማስታወቂያ ለመሥራት አጋጣሚን ለመጠቀም፣ በመንግሥት ግዴታ ተጥሎባቸውና በስጋት ወዘተ ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነ ለይቶ ማወቅ ያስቸግራል።

በጎ አድራጎት ሥራን አደባባይ አውጥቶ መናገርን በሚመለከት፣ የሚደግፉ እንዳሉ ሁሉ፣ ‹የግድ መታወቅ አያስፈልገውም፤ አደበባይ ወጥቶ መነገር የለበትም› የሚሉ አሉ። በዚህ ላይ ለአዲስ ማለዳ ሐሳባቸውን ያቀበሉት ዲያቆን ሔኖክ፣ ባይነገር መልካም ነው ይላሉ። በአንጻሩ ግን በጎ ሥራ በሰው ፊት ሊያበራ ይገባል ከሚለው ጋር የሚጋጭ ይመስላል ሲሉ ሊነሱ የሚችሉ የሐሳብ ሙግቶችን አንስተዋል። ታድያ ይህ መልካምነት ይታይልኝ ባይሉትም፣ እንደ ፀሐይ የሚያበራ እንጂ ሊሸሸግ የሚችል አይሆንምና፣ ሥራ ራሱ እንዲናገር ማድረግ ይቻላል።

‹‹ድሃን እያጎረሱ ፎቶ መነሳት የሰዎችን ስሜትም ይነካል። ካልተነገረልኝ አይሆንም የሚል ካለም፣ ይሁን። ለቸገረው ምግቡ አስፈላጊ ስለሆነ።›› ብለዋልም። በተጓዳኝ ብዙዎች በሐሳብም በድርጊትም የሚከተሏቸው ዝነኛዎች ድርጊታቸው በአረአያነት የሚቀመጥ በመሆኑ፣ ለምሳሌነትና በመገናኛ ብዙኀን ሊገለጽ እንደሚችል ጠቅሰዋል።

‹‹ለመወደድ ተብሎ የሚደረግ ድጋፍ ግን ያስታውቃል። ሰዉም ይገባዋል።›› ያሉት ሔኖክ፣ በመገናኛ ብዙኀን ሲነገር ለብዙዎች ምሳሌና አረአያ ሊሆን ስለሚችል፣ በእይታ ውስጥ ሆነውም ቢሆን መመጽወቱና ልገሳው መቀጠሉ አስፈላጊ ነው ሲሉ ሐሳባቸውን ቋጭተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ በየጊዜው ከቫይረሱ ስርጭት ጋር በተያያዘ በሚሰጡት መግለጫ ሲናገሩ፣ ፈተናዎችን ማለፍ የምንችለው በመረዳዳት ነው ብለዋል። ‹‹ማሸነፋችን አይቀርም። ግን በዚህ አንድም ሰው ወደኋላ መቅረት የለበትም። ከትንንሽ ሱቅ እስከ ከፍተኛው፣ ከሀብታም እስከ ደሃ ሁሉንም በማስተባበር፣ የሃይማኖት ልዩነት ሳይኖር፣ የማሸነፍ ትግሉን ተቀላቅለናል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበውን ጥሪ ሁሉም ዜጋና ነዋሪ ያለውን እንዲያካፍል፣ እጁ ላይ ባለው ነገር ይህን እንዲቀላቀል ሁሉም ዜጋና ነዋሪ ጎረቤቱን እንዲረዳና ትግሉን እንዲቀላቀል ሰምተናል። በዚህም በተሻለ ትግሉን መርተን እናሸንፋለን።›› የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።

ይህን ተከትሎ በርካታ ባለሀብቶች የቤት ኪራይ ለተከራዮቻቸው ከማቀረት ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን አድርገዋል። ይሁንና ‹በመንግሥት ግድ ተብለው ነው፤ ጫና ተደርጎባቸው ነው› የሚል አስተያየት በተደጋጋሚ ሲነሳ ይሰማል። በዚህ ላይ አንድ ሐሳብ ያነሳው ያሬድ፣ ‹መንግሥት ጠይቆ አሻፈረኝ ማለት የተለመደ አይደለም። ነገ እንጎዳለን ብለው በመፍራት የሰጡ ይኖራሉ። እንዲህ ባለ መልኩ ድጋፍ እንዲደረግ መሆኑ የጎንዮሽ ጉዳት ቢኖረውም፣ በዛ ልክ ድጋፍ ማሰባሰብ መቻሉ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው›› ብሏል።

የስለ እናት በጎ አድራጎት ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ልዑልሰናይም፣ እንቅስቃሴ በደንብ መኖሩን ከትዝብታቸው አጣቅሰው ገልጸዋል። አክለውም አሉ፤ ‹‹ዓላማው የተለያየ ነው። አንዳንዱ ለማስታወቂያ ይሆንና እሰጣለሁ ያለው የገንዘብ መጠን ተጠቅሶም ረድቷል ተብሎ፣ በአካል ሄደን ስንጠይቅ የለም። ሰዉ ግን በደንብ ይንቀሳቀሳል። ከአንድ ፍሬ ፓስታ ጀምሮ የተለያዩ በጎ ፈቃደኞችን የሚያስተባብሩ አርቲስቶችም ጥሩ እየሠሩ ነው።››

ሥማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ ከዚህ ባሻገር ያሉ ጉዳዮችን ታዝቤአለሁ ይላሉ። ይልቁንም አንዳንድ ቦታ ባልተቀናጀ መልኩ እየተሰበሰቡ ያሉ ድጋፎች ለግለሰብ ጥቅም እየዋሉ ነው ብለዋል። ለዚህ ማሳያ ማስረጃ ባያቀርቡም፣ ‹‹እንኳን እንዲህ ያለ አጋጣሚ አግኝተው፣ የኩላሊትና መሰል ሕመም እየጠሩ በልግስና ከሚሰጥ ሕዝብ የሚሰርቁ ብዙዎች አይደሉም ወይ?› ብለው መልሰው ይጠይቃሉ።

እናም ይህ አጋጣሚ ድጋፍ በማሰባሰብ ሥራ ላይ ያሉ የመንግሥት ሰዎችን ወደ ሙስና፣ ግለሰቦችን ደግሞ ወደለየለት ሌብነት ሊገፋ ይችላል ብለዋል። እናም የልገሳ አሰባሰብ ሥራው አሁንም ከቀደመው ይልቅ የተቀናጀ አሠራር ሊኖረው ይገባል የሚል መልእክት አስተላልፈዋል። በተለይም በወረዳና በክፍለ ከተማ ክትትል መደረግ አለበት ያሉት እኚህ አስተያየት ሰጪ፣ ‹ሰው ለሕሊናው ካልተገዛና በክፉ ዘመን የባሰ ክፉ ከሆነ፤ ምድራዊ ሕግ ስርዓት ሊያሲዘው ይገባል።›› በማለት አሳስበዋል።
በተለያዩ በተገለጹ ባልተጠቀሱ ምክንያቶች በአገር አቀፍ ደረጃ የተሰበሰቡ የእርዳታ ገንዘቦች መጠን በይፋ አልተገለጸም። ነገር ግን በተበጣጠሰ መንገድ የተገለጹ የድጋፍ መጠኖች አሉ። ከዚህም መካከል ባሳለፍነው ሳምንት (ሚያዝያ 10/2012) ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በወጣ ዘገባ፣ 340 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መሰብሰቡ ተገልጿል። ይህም ለእርዳታ ማሰባሰቢያ በተከፈተ ማእከል ብቻ የተሰበሰበ ነው ሲሉም የፕሬስ ሴክሬታሪ ንጉሡ ጥላሁን አስታውቀው ነበር።

ይበል!
የሰሙት ያደመጡት፣ ያዩት የተመለከቱት መልካም መሆኑን ለማጠየቅ ‹ይበል!› ይላሉ፣ ይሁን፣ ጥሩ ነው ይቀጥል ሲሉ ነው። በበጎ አድራጎት ሥራዎችም ላይ እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች በዛው ልክ ይበል የሚያሰኙ ናቸው። ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን የሰጡ በአንድ በኩል ይህ በጎ ተግባር መቀጠል እንዳለበት ያነሳሉ። ይህም ከልብ እንጂ ለታይታ እንዳይሆን፣ በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም እንዲገለጥ አደራ ብለዋል።

በተጨማሪም አጋጣሚውን በመጠቀም በእርዳታ ሥም ለራሳቸው ጥቅም የሚሰበስቡ ሊታረሙና ሊከለከሉ ይገባል የሚል ሐሳብንም አቀብለዋል። በጎ አድራጊዎች ለትክክለኛው ሰውም እንዳይሰጡ ጥርጣሬን የሚፈጥር በመሆኑ ነው። የበጎ አድራጊዎች ድካም ለከንቱ እንዳይሆንና በአጥፊዎችም ቅር እንዳይሰኙ፣ የተሰጡ ድጋፎችን በተገቢው መንገድ ለሚገባው ማድረስን የሚመለከተው የመንግሥት አካል፣ ድርጅት ወይም ተቋም ቸል ሳይል እንዲከውን ግን የሁሉም አደራ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 77 ሚያዝያ 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here