ፈትፋች የበዛበት የወረርሽኙ ውሳኔ፡ በአገራት እና በኢትዮጵያ

0
673

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን መከሰት ተከትሎ የተለያዩ አገሮች ጊዜያቸውን ቆፍጠን ብለው ወረርሽኙን በሙሉ ኃይል ከመዋጋት ይልቅ የአስጊነት ደረጃው ላይ ጥርጣሬ በማሳደር የጤና ባለሙያዎች ምክሮችን ለመተግበር ዳተኛ ሲሆኑ ታይተዋል። ፖለቲከኞች በየትኛውም አገራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ እንቅስቃሴያቸው ውስጥ ፖለቲካቸውን ማራመድ ቅድሚያ ከሚሰጧቸው ተግባራት አንዱ በመሆኑ ወረርሽኙን የማዳን እንቅስቃሴያቸውም ፖለቲካቸውን እንዲረዳ መንቀሳቀሳቸው ዓለም አቀፋዊ እውነታ ነው።

ይህም በግልጽ ከታየባቸው አገሮች አንዷ አሜሪካ ናት። በአወዛጋቢ ንግግራቸው፣ ጽንፈኛ ውሳኔያቸው እና ያለቅጥ የገዘፈ የግል ምናባቸው የሚታወቁት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቫይረሱ ዜጎቻቸውን ማጥቃት ሲጀምር “በቁጥጥራችን ስር ነው ያለው”፣ “ጉንፋን ዓይነቱን የቻይና ቫይረስ ለመቆጣጠር ያደረግነው ሥራ እጅግ ግሩም ነው” ሲሉ ነበር በተደጋጋሚ የሚናገሩት።

በጊዜው ግን የአገሪቱ የጤና ባለሙያዎች በቂ ምርመራ እየተደረገ እንዳልሆነ፣ ጤና ባለሙያዎችም ራሳቸውን የሚጠብቁበት አልባሳት እና ሌሎች እቃዎች እንደሌሏቸው፣ ወረርሽኙ እየተባባሰ እንደሚሔድ እና በአንድ ጊዜ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ስለሚሆን እንደመተንፈሻ ማገዣ ያሉ መሣሪያዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚገባ ሲመክሩ ነበር። ከዚህም ቀጥሎ ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተጠጋግተው የሚኖሩባቸው ከተሞች ላይ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ እንዲቆም ሲወተውቱ ነበር።

ነገር ግን የወረርሽኙን መጠን ለማመን የመቸገር ስሜት፣ ከተሞች ከመዝጋት ጋር የሚመጣው የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ችግር እና ይህ ተቀባይነታቸው ላይ ሊጥል የሚችለው ጥቁር ነጥብ ትራምፕ የጤና ባለሙያዎቹን ምክር በቶሎ እንዳይቀበሉ እንዳደረጓቸው ቮክስ የተባለ ድረ-ገፅ ላይ የወጣ ፅሑፍ ያሳያል። በፋሲካ በዓል ሁሉም ነገር ወደ ወትሮው እንቅስቃሴ መመለስ አለበት ሲሉም ያስቀመጡት የጊዜ ሰሌዳ የጤና ባለሙያዎቹን የማህበራዊ ፈቀቅታ ተግባራት ጊዜ ሰሌዳ የጠበቀ አልነበረም። እንዲያውም በግልጽ የጤና ባለሙያዎቹ ያመጡት ኢኮኖሚውን በጊዜያዊነት የመዝጋት “ፈውስ” ከችግሩ በላይ የከፋ ነው በማለት በፍጥነት ከተሞች እና የንግድ ተቋማት ወደ ሥራ እንዲገቡ ወትውተው ነበር።

ነገር ግን እርሳቸው ከባለሙያዎች ጋር ሲነታረኩ ባጠፉት ጊዜ ውስጥ ወረርሽኙ እጅጉን እየተስፋፋ ሔዶ አሁን አሜሪካ በዓለም በግንባር ቀደምትነት የተጠቃች አገር ለመሆን በቅታለች። አዲስ ማለዳ ለሕትመት እስክትገባ ድረስ አሜሪካ 850 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙባት ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 48 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ሞተዋል። ትራምፕም ከዘገየ በኋላ የጤና ባለሙያዎቻቸውን ሰምተው የማህበራዊ ፈቀቅታ መመሪያዎቹን ለማራዘም ተገደዋል።

ከላይ የተጠቀሰው ምንጭ ቻይናም ብትሆን ቫይረሱን አስመልክቶ በቂ መረጃ ለሕዝቧም ሆነ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዳይደርስ ደብቃ እንደቆየች አንድ ጥናትን በመጥቀስ ያሳያል። የቻይና መንግሥት የባለፈው የፈረንጆች ዓመት የመጨረሻ ቀን ላይ ያወጣው የቫይረሱን መከሰት የሚያውጅ ሪፖርት ላይ የተካተቱት የመጀመሪያው በበሽታው የተያዘ ሰው የተለየበት ጊዜ እና በዚያን ጊዜ የነበሩት ተያዦች ሁሉ ከዉሀን የምግብ ገበያ ጋር የተያያዙ መሆናቸው ሀሰት እንደሆነም ፅሁፉ ያትታል። እንደዘገባው ከሆነ የመጀመሪያው ሰው ሪፖርቱ ላይ ከተጠቀሰው ቀን 11 ቀናት ቀድሞ ነው የተገኘው፤ በጊዜው ከነበሩ ተያዦች ወስጥም ሲሶዎቹ ከዉሀን የምግብ ገበያ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ነበሩ።

ይህም የሚያሳየን የቻይና ፖለቲከኞችም ቫይረሱ ሊያስከትል ስለሚችለው መጠነ ሰፊ አደጋ ቀድመው ያልተረዱ የነበሩ መሆናቸውን ነው። ይህንን ነገር ከሕዝባቸው እና ከዓለም ማህበረሰብ በመደበቃቸው ወደ ዉሀን የሚደረጉ ጉዞዎች ቀጥለው ነበር። በመሆኑም ቫይረሱ ለመሰራጨት ምቹ ሁኔታን አግኝቷል። ዘገባው እንደሚገልፀው ቻይና ዉሀንን ከሦስት ሳምንታት በፊት ዘግታ የነበረ ቢሆን ኖሮ የተያዘውን ሰው ቁጥር በ95 በመቶ ትቀንሰው ነበር። ይህም በሽታው አሁን ባለው ሁኔታ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዳይስፋፋ ከማገዙም በተጨማሪ የተጠቁትን ቻይናውያን ቁጥር በእጅጉ ይቀንሰው ነበር።

ከአሜሪካ እና ከቻይና በተጨማሪ የተለያዩ አገር ፖለቲከኞችም (የብራዚል፣ ሜክሲኮ፣ ጣልያን፣ ስፔን እና ሌሎችም) የወረርሽኙን አስከፊነት ባለማመናቸው፣ የጤና ባለሙያዎችን ምክር ባለመስማታቸው እና የኢኮኖሚ ጥቅምን ቅድሚያ በመስጠታቸው የተነሳ ጥብቅ ውሳኔዎችን ዘግየት ብለው ወስነዋል። ይህም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ውድ የሰው ሕይወት በከንቱ እንዲጠፋ አድርጓል።

በተለይ እንዲህ የሰለጠነውንም ዓለም ረቶ ካሳየ በኋላ የወረርሽኙን አስከፊነት ለማመን ፖለቲከኞች ብዙም የሚቸገሩ አይመስልም። በመሆኑም የወረርሽኙ አስከፊነት በአሁን ጊዜ የሚያጠራጥር ባለመሆኑ ጥብቅ ውሳኔዎችን አሁንም በፍጥነት እንዳያስተላልፉ የሚያደርጓቸው ጉዳዮች ሌሎች ናቸው። እነዚህም፡- የፖለቲከኞች ወይም የፓርቲያቸው የወደፊት እጣ ፋንታ፣ የአገር ገፅታ ላይ የሚኖረው እንድምታ እና እርምጃዎቹ ኢኮኖሚውን ሊጎዱ ይችላሉ የሚለው እሳቤ እንደሆኑ ከላይ የተጠቀሰው ምንጭ ይገልጻል።

ይህ ወረርሽኝ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንድምታ ቢኖረውም በመሠረታዊነት ግን የጤና ቀውስ ነው። ፖለቲከኞች ግን ከሁሉ በፊት የጤና ቀውስነቱን ለማየት በመቸገር ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንድምታውን የሚያስቀድሙበት አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው። ለዚህም ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው በቻይና የቫይረሱን መከሰት እና ሕክምና የሚማሩ ሌሎች ጓደኞቹ እንዲጠነቀቁ ከመንግሥት መግለጫ በፊት በትዊተር ያስጠነቀቀው ዶ/ር ሊ ዌንሊያንግ በኮሮና ተይዞ ከመሞቱ በፊት በእኩለ ሌሊት በፖሊስ ተይዞ ግሳጼ ተሰጥቶት የነበረ መሆኑ ነው። በአሜሪካ ሰሞኑን እየታዩ ያሉት የንግድ እንቅስቃሴዎች ይከፈቱ የሚሉ የፕሬዝዳንቱ ደጋፊዎች ሰልፎችም የጤና ባለሙያዎች ለተጨማሪ ሳምንታት ተዘግተው መቆየት አለባቸው ከማለቻቸው ጋር የሚጻረር ነው። ነገር ግን ፖለቲከኞች የሚወስዷቸው እርምጃዎች የጤና ባለሙያዎችን ምክሮች የተመረኮዙ መሆን ይገባቸዋል።

የብሩክ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ብሩክ አለማየሁ የሕክምና ባለሙያዎች መንግሥታት ሊወስዷቸው ይገባሉ የሚሏቸው እርምጃዎች በተለይም ከኢንፍሉዌንዛ በሽታ ጥናቶች የተወሰዱ ናቸው ይላሉ። ኢንፍሉዌንዛ እና ሌሎች በየጊዜው የሚነሱ መሰል በሽታዎች በተለያዩ ቫይረሶች የሚከሰቱ ቢሆኑም ቫይረሱን በያዘ የአየር ባንቧ ፈሳሽ (ምራቅ) የሚተላለፉ መሆናቸው የጋራ ባህሪያቸው እንደሆነ ያስረዳሉ። እንደእርሳቸው አባባል የሕክምና ባለሙያዎች ምክር በአጠቃላይ መርህነት ማህበራዊ ፈቀቅታን የሚያካትት ነው። ከዚህም በተጨማሪ የአየር ባንቧ ፈሳሾቹን መበተን ተከትሎ ቫይረሶቹ የተለያዩ በአካባቢያችን ያሉ አካላት ላይ አርፈው ለቀናት ሊቆዩ ስለሚችሉ በተደጋጋሚ እነዚህን አካላት እና እጃችንን ማፅዳት ይመከራል ሲሉም አክለዋል።

ዋነኛው ችግርም እነዚህ ምክሮች በጅምላው የሚሰጡ እንጂ በግልጽ ፈቀቅታው መቼ ምን ዓይነት እርምጃ ያስፈልገዋል የሚለውን የማይወስኑ መሆኑ ላይ ነው። ለምሳሌ አሁን በአገራችን ባለው የስርጭት መጠን ርቀትን ጠብቆ የተለመደውን አሠራር መቀጠል ይበቃል ወይስ ሙሉ ከተማው ላይ እንቅስቃሴ ታግዶ ሕዝቡ ቤቱ መቀመጥ አለበት የሚለውን ቁርጥ አድርጎ የሕክምናው ሳይንስ አይወስንም።

ይህም ክፍተት ፖለቲከኞች በውሳኔ አሰጣጣቸው ላይ ሌሎችን ጉዳዮች ግምት ውስጥ እንዲከቱ እድሉን በመስጠት ውሳኔውን ሕክምናዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ እንዲሆን በር ይከፍታል። በመሆኑም ፖለቲከኞች የኢኮኖሚው ሁኔታ የማይጎዳበት፣ ዜጎች በሥራ አጥነትና ማህበራዊ ቀውስ የማይቸገሩበት ዘለል ሲልም የራሳቸው የፖለቲካ ግብ የማይደናቀፍበትን መንገድ መርጠው ወረርሽኙን የሚከላከሉበት መንገድ ላይ ይወስናሉ።

ዶ/ር ብሩክ ጉዳዩን ከሕክምና አንጻር ብቻ ሳየው የእንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ መቆም (lockdown) ምርጡ ውሳኔ ነው ይላሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህር እና ኤፒዲሞሎጂስት የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር ፍቅሬ እንቁስላሴ ሰዎች ተረጋግተው በአንድ ቦታ እንዲያሳልፉ ማድረግ ቢቻል የተሻለው አማራጭ እንደሚሆን ይጠቅሳሉ። ነገር ግን ኹለቱም ይህንን ዓይነቱን የሕክምና ውሳኔ መተግበር በአገራችን ሁኔታ እጅጉን የሚከብድ ነው ብለው ያምናሉ።
በዚህም መሠረት በመንግሥታት የሚሰጡ ውሳኔዎች የእንቅስቃሴዎች ሙሉ ለሙሉ መቆም እና እንቅስቃሴዎች እንዳሉ መቀጠል መካከል የሚሰጡ ናቸው ማለት ነው። በመሆኑም ለመንግሥታት ትልቁ ፈተና የሕክምናው ምክሮችን ካለው የበሽታ ስርጭት መጠን እና የአገራዊ ነባራዊ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ ጋር አስተያይቶ ተመጣጣኝ የሆነውን እርምጃ መውሰድ ነው።

ሕክምናው ሌሎችን ጉዳዮች ግምት ውስጥ ሳያስገባ ምርጡ መፍትሔ ብሎ የሚያስቀምጠው ሁሉንም እንቅስቃሴዎችን ማገድን እውን ላለማድረግ በዋነኛነት የሚጠቀሰው ምክንያት የኢኮኖሚው ሁኔታ ነው። እንቅስቃሴዎች መቀዛቀዛቸው እንኳን የግለሰቦችን እና የድርጅቶችን ሁኔታ ምን ያህል እየተፈታተነው እንዳለ መገንዘብ ይቻላል። በመሆኑም ሙሉ በሙሉ መዝጋት ችግሮችን አባብሶ ወደ ማህበራዊ ቀውስ ሊወስድ ይችላል የሚለው የመሪዎች እሳቤ የሚያስኬድ ነው።
ነገር ግን የኢኮኖሚው እና የጤናው ጉዳይ ሚዛን ላይ ተቀምጠው አሁን የጤናው ጉዳይ ስለባሰ ሙሉ በሙሉ መዝጋት አለብን ሊያስብል የሚችለው ሁኔታ ስንት ሰው በቫይረሱ ሲያዝ እና ስንት ሲሞት እንደሆነ ለመወሰን አዳጋች ነው። የኢኮኖሚውን ሁኔታ ለመደገፍ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው። በመሆኑም በአጭር ጊዜ እቅድም ሆነ በረጅም ጊዜ እቅድ የግለሰቦችን እና የድርጅቶችን ህልውና ሊያረጋግጡ የሚችሉ ተግባራትን ለይቶ የአጭር ጊዜዎቹን በማስፋፋት የሕክምናው ምክር እንዲያይል መሥራት የአገሪቱን በወረርሽኝ የመጠቃት መጠን የሚወስን ይሆናል።

ከመንግሥት የሚሰሙት አንዳንድ ነገሮች ግን ይህንን የጤና እና የኢኮኖሚ ሚዛን በኢኮኖሚው በኩል ከሚያስፈልገው በላይ እንዳይጫኑት የሚያስፈሩ ናቸው። ለምሳሌ የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ የሆኑት እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በቅርቡ ብዙ የምናጣው ነገር ስላለ ኢኮኖሚው ላይ ረጅም ጊዜ የሚቆይ መናወጥ መተው አንችልም ማለታቸው ይህንኑ ከጤናው ይልቅ ኢኮኖሚውን የመምረጥ አዝማሚያ የሚያሳይ ነው።

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የሆኑት ታከለ ኡማም ሙሉ በሙሉ የምንዘጋው በወረርሽኙ የተሸነፍን ከሆነ ብቻ ነው ማለታቸው ይህንን ለኢኮኖሚው የበለጠ ቦታ የመስጠት ዝንባሌ ያሳያል። በተለይ ደግሞ ወረርሽኙ የተሻለ የጤና ስርዓት እና የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ የመስጠት ብቃት አላቸው የሚባሉትን የበለፀጉትን አገራት ግራ በሚያጋባ ሁኔታ ከአቅማቸው በላይ ሆኖ አሳይቶን የሚያሸንፈን ከሆነ ብሎ መጠራጠር የተጋረጠውን አደጋ በቅጡ ያለመገንዘብ ነው።

በመሆኑም የከፋ ሁኔታ ቢከሰት ራሱን ከቤቱ ሆኖ መመገብ የማይችለውን የህብረተሰብ ክፍል ለመድረስ የሚሰሩትን ሥራዎች በጊዜ ማጠናቀቅ፣ ለድርጅቶች ደግሞ ችግሩ ካለፈ በኋላ የማበረታቻ ድጎማ የሚደረግበትን መንገድ በማመቻቸት ለከፋው ከወዲሁ ተዘጋጅቶ መጠበቅ ያስፈልጋል።

ብሩክ መንግሥት በተለይ ቫይረሱ ወደ አገራችን እንደገባ በታወቀበት የመጀመሪያ ጊዜያት ችግሩን ማራቅ እና እኛ ላይ አይደርስም የሚል ስሜት ባለሥልጣናት ይታይ ነበር ብለዋል። በዚያን ጊዜ ከፍተኛ ቸልተኝነት ይታይ ነበር። ለምሳሌ ጠ/ሚኒስትሩ የተገኙበት የብልጽግና ፓርቲ ገንዘብ ማሰባሰቢያ የቫይረሱ የመጀመሪያ ተያዥ በአገራችን ከተገኘ በኹለተኛው ቀን ነበር የተደረገው ሲሉም ቸልተኝነት እንደነበረ እማኝ ያቀርባሉ። የመንግሥት ባለሥልጣናት ያላቸውን ቁርጠኝነት ጥርጥር ላይ የሚጥለው ሌላው አጋጣሚ ደግሞ አስገዳጅ የሆኑትን የማህበራዊ ፈቀቅታ ተግባራት ቢያደርጉም አስገዳጅ ያልሆኑትን ሲያደርጉ ወይም ሲፈቅዱ መታየታቸው ነው ይላሉ። ይህም የሚመነጨው እኔ እና ሕዝባችን ላይ አደጋው ይደርሳል ብሎ ከልብ ካለማሰብ ነው ሲሉም ይተቻሉ።

ሌላው ብሩክ መንግሥት የጤና ባለሙያዎችን አስተያየት በሚገባው መጠን እየተቀበለ እንዳልሆነ ያሳዩበት ነጥብ በሙያው ላይ ከፍተኛ ልምድ እና ዓለማቀፋዊ እውቅና ያላቸውን ሰዎች እንኳን በጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም የማይገኙ መሆናቸው ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት ፖለቲካው ሙያተኛውን አቅርቦ የማያሠራ ሆኖ ስለቆየ ነው ብለውም ያምናሉ።

ተላላፊ በሽታ ላይ ያሉ ባለሙያዎች፣ ኤፒዲሞሎጂስቶች እና የማህበረሰብ ጤና ላይ የሚሠሩ በዓለም እውቅና ያላቸው የሚገርሙ ባለሙያዎች ያሉ ቢሆንም መንግሥት ሲጠቀምባቸው ግን አይታይም። የእነዚህ ከፍተኛ ባለሙያዎችን ሀሳብ መቀበል የሚያስችል አሠራር የሌለ መሆኑ እና አብዛኛው ሰው ወደ ሥልጣን የሚመጣው በፖለቲካ ፓርቲ አባልነት በመሆኑ ምርጥ የሚባለውን መንገድ መወሰን ላይም ችግር ሊኖር ይችላል ሲሉም ያስረዳሉ።

ጥቁር አንበሳም ሆነ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ሳይንስ ጥናት ክፍል ያሉት የጤና ባለሙያዎች በአብዛኛው ወረርሽኙን መከላከል ላይ እየተሳተፉ አይደለም። እንደውም አንድ የትምህርት ክፍል ኃላፊ እና ምንም ነገር አልተነገረንም ብሎ ነግሮኛል ብለው ያለውን የባለሙያዎች ተሳትፎ መጓደል ይገልጻሉ። ሲያጠቃልሉም እንደዚህ ዓይነት ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችን አቅርቦ የእነሱን አስተያየት እና እውቀት መውሰድ ያለመቻል የግንዛቤ እጥረት ፈጥሯል ብዮ እሰጋለሁ ብለዋል።
እንዲህ ዓይነቱ በሙያው ከፍተኛ ልምድ ያላቸውን ሰዎች ያገለለ አካሔድ ደግሞ በፖለቲካው ውስጥ ተሰሚ ሆነው ሙያው የሚያዘውን ብቻ ሳይሆን ሥልጣን ላይ ያሉትንም የሚያስደስተውን መንገድ ሊመርጡ ለሚችሉ ሰዎች በር የሚከፍት ነው። በመሆኑም መንግሥት ይህንን ሊያስተካክል ይገባል።

በመሆኑም መንግሥት በጤናው እና በኢኮኖሚው መካከል ያለውን ሚዛን እየተከታተለ ቀድሞ ብለን ያየናቸው አገሮች ፖለቲከኞች የጤና ባለሙያዎችን ምክር ሳይሰሙ ሕዝባቸው ላይ እንዳመጡት ከፍተኛ ችግር ዓይነት በእኛም አገር እንዳይከሰት የጤናው ጉዳይ ቅድሚያ ሊያገኝ የሚችልበትን ሁኔታ በፍጥነት ማመቻቸት አለበት፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 77 ሚያዝያ 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here