ማይክል ሳታን ከመሰለ መሪ ይሰውረን!

0
673

አገራት ከሌሎች አገራት ጋር ያላቸውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት በጥንቃቄና በማስተዋል፣ በብልሃትም እንዲያደርጉት ይመከራል። ይህን ነጥብ መሠረት በማድረግ ግዛቸው አበበ፣ የዛምቢያ ፕሬዘደንት ሆነው ያገለገሉትን ማይክል ሳታን አውስተዋል። እኚህ ሰው ጸረ ቻይና አቋም የነበራቸው ሲሆኑ፣ ይህም አቋማቸው ሕዝባዊ ለመሆን እንዳበቃቸው የተለያዩ መገናኛ ብዙኀን በጊዜው ዘግበው ነበር።
እናም ዘመናት ባልተሸገረ አጭር የሥልጣን ዘመናቸው ብዙ ስህተቶችን ሠርተዋል፣ ጥፋቶችንም፣ የቻይና እና የዛምቢያን ግንኙነትም አበላሽተዋል ይላል። ይህንንም በማስታወስ ኢትዮጵያም በመንግሥትና በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል የምታደርገውን የውጪ አገራት ግንኙነት በጥንቃቄ፣ በስሜት አይደለ በማስተዋልና በስሌት ሊደረግ ይገባል ሲሉም ያሳስባሉ።

ጥቅምት 30/2008 (በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የተጠቀሰው ዘመን ሁሉ በፈረንጆች የዘመን አቆጣጠር ላይ የተመሰረተ ነው) ታዋቂው ቴሌግራፍ የተባለ የእንግሊዝ መገናኛ ብዙኀን ‹‹ጸረ ቻይና አቋም ያላቸው የዛምቢያ ፖለቲከኛ የአገሪቱ ፕሬዘደንት ለመሆን ተስፋ አደረጉ›› የሚል ዜና ይዞ ብቅ አለ። ቴሌግራፍ ይህን ዜና የሠራው የወቅቱ የዛምቢያ ፕሬዘደንት የነበሩት ሌቪ ማናዋሳ ነሐሴ 2008 ላይ መሞታቸውን ተከትሎ በእግራቸው ለመተካት ያቆበቆቡትን ማይክል ሳታ ቀጣዩ የአገሪቱ ፕሬዘደንት ይሆናሉ ለማለት ነው።

ማናዋሳ ላጋጠማቸው የልብ ድካም ሕመም ፈረንሳይ ውስጥ ሕክምና በመከታተል ላይ እንዳሉ፣ ሥልጣን ክፉኛ የጠማቸው ማይክል ሳታ የአገሪቱ ምክር ቤት የዶክተሮች ቡድን ወደ ፈረንሳይ ልኮ የማናዋሳን የጤንነት ሁኔታ እንዲያረጋግጥ ጠይቀው ነበር። ማናዋሳ ሲያርፉ በተደረገላቸው የቀብር ስነ-ስርዓት ላይ የማናዋሳ ባለቤት ‹የባለቤቴን ሕመም ለፖለቲካ ጨዋታ ሊጠቀሙ ሞክረዋል› በማለት ማይክል ሳታ ከቦታው እንዲባረሩ አድርገው ነበር።

ማይክል ሳታ ራሳቸው የልብ ጤንነት ችግር ቢኖርባቸውም ይህን እየካዱ በማናዋሳ ጤንነት መዘባበታቸው ለትዝብት የዳረጋቸው ጉዳይ ነበር። ማይክል ሳታ፣ በመሪዎች ታሪክ ከአገርና ከሕዝብ ይልቅ ራሳቸውን ወይም የራሳቸውን ጥቅም በማስቀደም መጠቀስ የሚገባቸው ሰው ናቸው። ማይክል ሳታ ፓርቲ በመቀያየርና ደካማ ሥነ ልቦናዎችን መረማመጃ በማድረግ የዛምቢያ ፕሬዘደንት ለመሆን ብዙ ላይ-ታች ያሉ ሰው ናቸው።

ማይክል ሳታ እስከ 1991 (እስከ ቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ማክተሚያ) ከእነ ኬኒቲ ካውንዳ ጋር United National Independence Party አባል የነበሩ ሲሆን፣ ይህ ፓርቲ በአገሪቱ በተደረገው የመጀመሪያ ምርጫ በMMD (Movement for Multiparty Democracy) መሸነፉን ተከትሎ እሳቸውም የተሸነፈውን ፓርቲአቸውን ትተው ገዥ ፓርቲ የሆነውን MMDን ተቀላቀሉ። 2001 ላይ የMMD መሪና የዛምቢያም ፕሬዘደንት የነበሩት ችሉባ የነበሩት በቀጣዩ ምርጫ መወዳር ስለማይችሉ የገዥው ፓርቲ ፕሬዘደንትነታቸውን ለሌቪ ማናዋሳ ሲስረክቡ ማይክል ሳታ ፕሬዘደንት የመሆን ምኞታቸው በድጋሜ ከሸፈ። ገዥውን ፓርቲ ወክለው ለፕሬዘደንትንት ለመወዳደር ተስፋ አድርገው የነበሩት ሳታ አኩርፈው MMDን ጥለው በመውጣት ‘አርበኞች ግንባር’ ያሉትን የራሳቸውን ፓርቲ መሰረቱ። ‹አርነቦች ግንባር› የማይክል ሳታ የፖለቲካ ሕይወት ሦስተኛ ፓርቲ ሆነ።

የራሳቸውን ፓርቲ መሥርተው ለፕሬዘደንትነት መፎካከሩን እንደ አዋጭ ስትራቴጂ አድርገው የቆጠሩት ማይክል ሳታ፣ የድሆች አባት ነኝ እያሉ ማቀንቀን ጀመሩ። ማይክል ሳታ መስከረም 2006 በተካሄደው ምርጫ ድሆችን የሚያማልሉ ፕሮፓጋንዳዎችን በመሥራትና የተቀናቃኞቻቸውን ስብዕና የሚነካ ቅስቀሳ በማድረግ ተፎካክረው ነበረ። የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ በብዙዎች ዘንድ በቻይናና በቻይናዎች ላይ ከፍተኛ ጥላቻ እንዲጠነሰስ ማድረጉን ያውቃሉ።

ይህ ጥላቻም በዛምቢያ በተለይም በከተሜው ዛምቢያዊ፣ ይብሱን ደግሞ በወጣቱ ዛምቢያዊ ልብ የሰፈነውን ጥላቻ አሳምረው ስለሚያውቁ፣ ይህን ጥላቻ ወደ ሥልጣን መወጣጫ ሆኖ ያገለግላቸው ዘንድ ስትራቴጂ ነደፉ። እናም ቅስቀሳቸውን በዛምቢያ በሚገኙ የቻይና ኩባንያዎችና ቻይናውያን ላይ ነጣጠረ አደረጉት። በዚሁ አጋጣሚ ለምዕራባውያን እጅ በመንሳት ድጋፍ ለማግኘት ሲሉም ታይዋንን እና ሆንግ ኮንግን እንደ ሉዓላዊ አገር አድርገው መግለጽ አበዙ።

የዛምቢያን መሪዎች አገራቸውን ለቻይና የሸጡ እያሉ በማውገዝና በመሳሰሉት የውስጥና የውጭ ድጋፍ ለማግኘት ታትረዋል። ይህን ያህል ዘመቻ ቢያካሂዱም የ2006ቱ ምርጫ ግን አልተሳካላቸውም። ፕሬዘደንት መሆን አልቻሉም።

በ2008 ደግሞ የወቅቱ የዛምቢያ ፕሬዘደንት የነበሩት ማናዋሳ መሞታቸውን ተከትሎ ማይክል ሳታ እንደገና ለውድድር ቀረቡ። በዚህ ጊዜ ነበረ የእንግሊዙ ቴሌግራፍ ለፕሬዘደንትንት ተስፋ ማድረጋቸውን የሚገልጽ ዜና ይዞ የወጣው። ምርጫውን ተከትሎ ይፋ የሆነው ውጤት ግን ሳታ ኹለተኛ በመሆን መሸነፋቸውን የሚያሳይ ሆነ። ማይክል ሳታ ምርጫው መጭበርበሩንና አለመሸነፋቸውን በሰፊው በማስወራት ለማንገራገር ሞከሩ።

ብዙም ሳይቆዩ የሚደብቁት የልብ ድካማቸው በርትቶ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሄደው መታከም ግድ ሆነባቸው። ማይክል ሳታ በ2006 እና በ2008 ያቋቋሙትን ፓርቲአቸውን ወክለው ለፕሬዘደንትነት ተፎካክረው ሳይሳካላቸው ቀረ ማለት ነው።

ማይክል ሳታ በ2011 በተካሄደው ምርጫ አርበኞች ግንባርን ወክለው ለአራተኛ ጊዜ ተፎካክረው ተሳካላቸው። ቻይናን በሚመለከት የሚያራግቡት ጥላቻ በምዕራቡ የፕሮፓግንዳ ሥራ ሰፊ ቅብብሎሽ ቢያገኝም፣ የሳታን መምረጥ ተከትሎ ዛምቢያ ከውጭ የምታገኘው ኢንቨስትመንት መቀዛቀዙ አልረቀረም። ምክንያቱም የሳታ ጥላቻ በቻይና ኢንቨስትመንት ላይ ብቻ ተገድቦ እንደሚቀር ምንም ማረጋገጫ አልነበረም።

ሳታ ድኆችን አማልላለሁ ብለው የሚናገሩት ብዙው ነገራቸው የውጭ ኩባንያዎችንና በዛምቢያ በተለያዩ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ የውጭ ዜጎችን ሁሉ እንደ ቅኝ ገዥ፣ እንደ ዘራፊና ለዛምቢያ የድኅነት ምንጭ እንደሆኑ አድርገው የማየት ዝንባሌ እንዳለባቸው የሚያጋልጡ ነበሩ። የሳታ ተከታዮችም ቢሆኑ ተመሳሳይ አመለካከት ይዘው ታይተዋል።

ቴሌግራፍ የጠቀሰው ሬይ ዋሽ የተባለ የ40 ዓመት ዛምቢያዊ አባባል ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። ‹‹…እነሱም (ቻይናዎችም) እንደ አሜሪካና እንደ እንግሊዝ ናቸው። ይመጣሉ፣ ይሰርቃሉ፣ ይሄዳሉ… በገዛ ሀብታችን ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም…።››

ችምባ ዌባይ የተባለ የ25 ዓመት ዛምቢያዊ ደግሞ ‹… ብዙዎቹ የውጭ ሰዎች ለዚህች አገር ቋሚ ነገር አይሠሩም… ሀብት ይዘው ለመሄድ ብቻ ነው የሚመጡት… ቻይናዎች ደግሞ ከሁሉም የባሱ ናቸው…› በማለት ሐሳቡን ገልጿል። ማይክል ሳታ ለውጭ ባለጸጎች ጅምላ ጥላቻን አስፋፍተው ነበረ።

ከ2008 ጀምሮ ማይክል ሳታ በተሳተፉባቸው ምርጫዎች ከምርጫው ጋር በተያያዘ የሚሰራጩ ዜናዎች በአብዛኛው ‘በጸረ ቻይና አቋም’ የሚለውን አባባል እንደ ቅጥያ ወይም የሳታ ማንነት መግለጫ አድርጎ መጠቀም፣ ከዚህ ጋር በማያያዝም ጸረ-ቻይና ቅስቀሳዎችን ማካሄድ፣ ‹ጸረ ቻይና አቋም› ያላቸው መሪ ከተመረጡ በዛምቢያ የሚገኙ የቻይና ኩባንያዎች እንደሚዘጉና ቻይኖቹ እንደሚባረሩ በመተንበይ ቅስቀሳ ማካሄድ ወዘተ… የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኀን ዋና ሥራ ሆኖ ነበረ።
‹ቻይና ወደ አፍሪካ ምን ያህል ጠልቃ እንደገባች ለማወቅ የሚፈልግ ሰው ዛምቢያን ይጎብኝ› የሚል አባባል በመጠቀም ዘገባውን የጀመረ አንድ የቢቢሲ ጋዜጠኛ፣ ዛምቢያ በቻይና የተወረረች ቅኝ ግዛት አድርጎ የሚያሳይ ሰፊ ዘገባ ሠርቶ ነበረ። ቪኦኤ አማርኛ ፕሮግራምም የማይክል ሳታን ማሸነፍ የሚገልጽ ዜና የሠራው ‹በጸረ ቻይና አቋማቸው የሚታወቁት ተወዳዳሪ የዛምቢያ ፕሬዘደንትነትን አሸነፉ› ብሎ እንደነበረ የሚዘነጋ አይደለም።

ዴይሊ ሜል በግልጽ እንዳስቀመጠው ማይክል ሳታ በጩኸት በሚነገር ጸረ-ቻይና አቋማቸው ሕዝባዊ (populist) ለመሆን በቅተው ‘King Cobra’ ተብለው እስከ መጠራት ደርሰዋል። የማይክል ሳታ የሮበርት ሙጋቤ ቀንደኛ አድናቂ መሆንና ማይክል ሳታ ‹ዛምቢያ የውጭ ኢንቨስትመንት አያስፈልጋትም› የሚል አጠያያቂና ማስተዋል የጎደለው ሐሳባቸውን ማስተጋባታቸው፣ በአገር መሪዎችና በፖለቲከኞች ዘንድ ታይቶ በማይታወቅ መንገድ በሚያራምዱት ጸረ-ቻይና አቋማቸው ስለተከለለላቸው የምዕራባውያኑ መገናኛ ብዙኀን ትንሽም ሊተቿቸውና ሊገመግሟቸው አልፈቀዱም።

ሳታ ቻይናዎችን ከነ ኩባንያዎቻቸው አጥረግርጎ ማባረሩ እንደ ማውራቱ ቀላል አለመሆኑን በማየታቸው ባይተገብሩትም በቻይናዊ ኩባንያዎች ላይ ብቻ የሚሠራ ሕግ ለማውጣት አልሰነፉም። በማይክል ሳታ አቋም የተበረታቱት ዛምቢያዊ ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማዎች ከማድረግ ጀምሮ ከቻይናውያኑ አለቆቻቸው ጋር ግብግብ ለመግጠም እስከ መነሳት የደረሰ ችግር በተደጋጋሚ ስለሚፈጥሩ፣ የቻይናውያኑ ኩባንያዎች በተለይም የማዕድን ማውጫዎች ሥራ በጣም ተስተጓጉሎ ነበር።
መስከረም 23/2011 ፕሬዘደንት ይሆኑ ዘንድ የተመረጡት ማይክል ሳታ በሥልጣናቸው ላይ ብዙም ሳይቆዩ፣ የተመረጡለትን የሥልጣን ዘመንም ሳይጨርሱ ጥቅምት 28/2014 ይህችን ዓለምና ሥልጣናቸውን ተሰናብተዋል። በእግራቸው የተተኩት የዛምቢያ ፕሬዘደንት የመጀመሪያ ሥራ በማይክል ሳታ አማካኝነት የተበላሸውን የቻይናና የዛምቢያ ግንኙነት ማደስ ሆኖ ታይቷል።

የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙኀንን የማይክል ሳታን ዘመቻ ያህል ትኩረት አልሰጡትም እንጂ፣ አዲሱ የዛምቢያ ፕሬዘደንት ወደ ሥልጣን እንደ መጡ ቅድሚያ ሰጥተው ካደረጓቸው ነገሮች መካከል ወደ ቻይና አቅንተው የኹለቱን አገራት የሻከረ ግንኙነት ማደስና ግንኙነቱንም የጠለቀ ማድረግ ነው።

ማይክል ሳታ በሞት ቢለዩም በቻይናውያንና በኩባንያዎቻቸው ላይ እንዲፈጠሩ ያደረጓቸው ከመስመር የወጡ አካሄዶች እስከ አሁንም አልተቀረፉም። በቻይናዎችና በኩባንያዎቻቸው ላይ ችግሮችን መፍጠር መብት እንደሆነ አድርገው የሚቆጥሩ ዛምቢያውያን ጥቂቶች አይደሉም። የሥራ ማቆም አድማዎችና የድርድር ጥሪዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ከቻይናዎች ጋር ግብግብ ለመፍጠር መጋበዝም በተደጋጋሚ የሚታዩ ጉዳዮች ናቸው።

ይህን የማይክል ሳታን ግልጽ እና የጋዜጠኞችን የመሰለ ጸረ-ቻይና አቋም ማስታወስ የተፈለገው አፍሪካችን ሌላ የማይክል ሳታን የመሰለ አቋም ማሳየት ጀምረው የነበሩ አንድ መሪ ስላሏት ነው። እሳቸውም የኢትዮጵያችን ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መጥተው ብዙም ሳይቆዩ ወደ አስመራ ባደረጉት የመጀመሪያ ጉዞ፣ በአስመራ ቤተ-መንግሥት ውስጥ ባሰሙት ንግግር በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ሰላም መስፈኑን ለማሳየት ወደ ምሥራቅ መሣሪያ ፍለጋ መሄድ የለብንም፣ ሚሳኤል ለመግዛት ወደ ቻይናና ሩሲያ መሄድ የለብንም ወዘተ… የሚል ንግግር አሰምተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጦርነት አያስፈልግም ለማለት የአገር ሥም መጥራት አያስፈልጋቸውም ነበር። ነገር ግን እሳቸውም እንደ ማይክል ሳታ የምዕራባውያኑን ሌክቸር ያለ ቅጥ ስለተለማመዱት ጥንቃቄ በጎደለው መንገድ የአገራቱን ሥም በንግግራቸው ውስጥ ዶሉት። ከዚያም ከወታደራዊ ሥልጠና ከጦር መሣሪያ ጋር በተገናኘ ከእነ ፈረንሳይንና ከአረቦች ጋር ግንኙነት ማድረጋቸው ተሰማ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስመራ ላይ ያደረጉት ቻይናንና ሩሲያን ወዲያ እገፋለሁ የሚል ዓይነት ንግግር፣ የዓለምን ነባራዊ ሁኔታዎች ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያችን በተለያዩ ዘመናት በተለይም ወራሪዎች በመጡባት ቁጥር የገጠሟትን ፈተናዎች ግንዛቤ ውስጥ ያልጨመረ፣ በቅጡ ያልታሰበበት፣ በስሜታዊነት ብቻ የተመራ ነበረ ማለት ይቻላል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፈለጉትን ያህል ቢጥሩ፣ አየር መንገድንና ቴሌን እንኳ ያለ ጥንቃቄ ወደ ገበያ አውርደው መቸብቸቡ ቢሳካላቸው፣ በዚች አገር ምንም ዓይነት የመንግሥት ኩባንያና የንግድ ድርጅት እንዳይኖር አድርገው የነጸ ገበያ አፍቃሪ መሆናቸውን ቢያሳዩ፣ ቤቲንግ የተባለውን ቁማር ብቻ ሳይሆን ሌላውን የምዕራቡ ዓለም ‘ወጣት ገዳይ’ ገቢ መሰብሰቢያ ቢያስፋፉ ወዘተ…ወዘተ….ወዘተ…. የቱርክንና የሳዑዲ ዓረቢያን ያህል የምዕራባውያን በተለይም የአሜሪካ ወዳጅ መሆን አይችሉም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ራሳቸውን ሊጠይቁ የሚገባቸው አንድ ጉዳይ አለ። ቱርክና ሳዑዲ ዓረቢያ ባላቸው ከፍተኛ የጦር መሣሪያ ክምችት ሳይረኩ የሩሲያ የጦር መሣሪያ ይኖራቸው ዘንድ ከፍተኛ ፍላጎት ያደረባቸው ለምንድን ነው? ሳዑዲ ዓረቢያ ለዘብ ባለ ሁኔታ አቋሟን ግልጽ ስታደርግ ቱርክ ግን የመጣው ይምጣ የሚል ዓይነት አቋም ይዛ የሩሲያን የጦር መሣሪያ፣ በተለይም ኤስ-400 የተባሉትን ዘመናዊ አየር መቃወሚያና ሚሳይል ማክሸፊያ ሚሳይሎች እንዲኖሯት እየሠራች ነው።

ለምን?
ቱርክ የእስራኤል አየር ኃይል ያለው ዓይነት ዘመናዊ ተዋጊ ጀቶችን በሙሉ የታጠቀ አየር ኃይል አላት። ነገር ግን ስጋት እንዲያድርባት ያደረገ አንድ ነገር ስላለ ነው የዘመናዊ ጀቶችን ጥቃት መከላከል የሚችል ዘመናዊ ሚሳይል ያስፈለጋት። ለእነዚህ ዘመናዊ ጀቶች ከሚገጠሙላቸው ሶፍት ዌሮች መካከል አንደኛው ጀቶቹ በአየር ላይ እያሉ በርቀት ወይም በቅርበት ሌላ ጀት ራዳራቸው ውስጥ ቢገባ የወገን ወይም የጠላት መሆኑን ለይቶ ያሳውቃቸዋል።

ወታደራዊ ወሬዎችን የሚያነፈንፉ የመረጃ ምንጮች ቱርክ የአሜሪካው ኩባንያ ለጀቶቿ የገጠሙት ሶፍት ዌር የእስራኤል ጀቶች ራዳራቸው ውስጥ ሲገቡ፣ ሌሎች የቱርክ ጀቶች እንደሆኑ አድርጎ የሚያሳይና ለስህተት ወይም ለጥቃት የሚጋልጥ ስለሆነ ነው የሩሲን ዘመናዊ ሚሳይሎች ለመግዛት የፈለገችው ሲሉ ተሰምተዋል። በተመሳሳይ ሳዑዲ ዓረቢያም ጀቶቿ ብቻ ሳይሆኑ በሶፍት ዌር የሚሰሩ ማናቸውም ጦር መሳሪያወቿን እሷ በፈለገችው መንገድ እንዳትጠቀምባቸው እንዲያውም በርቀት ቁጥጥር የጦር መሣሪያዎቿን ከቁጥጥሯ ውጭ ሊሆኑ እንደሚችሉና፣ ራሷን የሚያወድሙ ጠላቶቿም ጭምር ሊያደርግባት የሚችል ቴክኖሎጂ ሊኖር እንደሚችል ጭምጭታ ስለሰማች ነው ሩሲያን ጨምሮ ከተለያዩ አገራት የጦር መሳሪያወችን ለመግዛት ፍላጎት ያሳደረችው ሲሉ መረጃ አነፍናፊወች ሹክ ብለዋል።

ኢትዮጵያችንስ ስለ ጦር መሣሪያዎች መገኛ ምንጭ እንዴት ትወስን? በዕውቀት ወይስ በስሜት? የአሜሪካ ጥብቅ ወዳጅ ከሆነችው ከግብጽ ጋር የተፈጠረው መፋጠጥ ወደ ቻይናና ሩሲያ እንሄድም የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሌላው ማይክል ሳታ ላለመሆን እንዲጠነቀቁ ትምህርት ይሰጥ ይሆን!
ጣሊያን የ40 ዓመታት ዝግጅቷን ጨርሶ ለወረራ ወደ ኢትዮጵያ በመጣችበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ጎረቤት ሶማሊያ ከ1950ዎቹ ጀምሮ ኢትዮጵያን ለመውረር ሰፊ ዝግጅት ስታደርግ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ምንም ዓይነት ጦርነት ዝግጅት እንዳላደረጉ የሚካድ አይደለም። ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን በተገቢው መጠንና ዓይነት አለማሰባሰብ ብቻ ሳይሆን የሠለጠነ ወታደራዊ ኃይልም በበቂ መጠን እንዲኖር አልተደረገም።

ኢትዮጵያውያን ጣሊያንን ጦርነት የገጠሙት በዘመነ ምኒልክ እንደተደረገው ከየቤታቸው ጥሪ ተቀብለው፣ ሥልጠና ሳያገኙ በቀጥታ ወደ ጦር ግንባር በመዝመት ነው። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ወደ ጦር ሜዳ የገባው ጦርና ጋሻ ጎራዴና ዱላውን ይዞ ነው። ዘመናዊ ይሁን ያልዘመነ ጠመንጃ የነበራቸወ በጣም ጥቂቶቹ ብቻ ነበሩ። አብዛኛው ሰው ከምርኮ የተገኘን ወይም የተሰዋ ወገኑን ጠመንጃ አንስቶ ለመዋጋት ተስፋ አድርጎ ነበረ የመዘተው። በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያ የነበራት የዘመናዊ ውትድርና ሥልጠና የወሰደ ወታደር በጣም ጥቂት የነበረ ሲሆን፣ ይህም ቤተ-መንግሥቱንና አካባቢውን ከመጠበቅ የዘለለ ሽፋን የማይሰጥ ነበረ።

የጣልያንን እንተወውና የዚያድ ባሬዋ ሶማሊያ በርካታ የሰው ኃይል አሰልፋ አዳዲስ ክፍለ ጦሮችን፣ ዘመናዊ ከባድ መሣሪያዎችንና ታንኮችን የታጠቁ ሜካናይዝድ የጦር ክፍሎችን፣ በርካታ ዘመናዊ የውጊያ ጀቶችን ያሰለፈ አየር ኃይል ወዘተ…. ስትገነባ ኢትዮጵያ፣ በሰው ኃይል ብዛት ያልደረጀ ወታደራዊ ክምችት፣ ጥቂት ብቻ ሳይሆን አስተማማኝ ያልሆኑ ከባድ መሣሪያዎችን የታጠቀ ምድር ጦር፣ ዕድሜ ጠገብ የሆኑ ጥቂት ተዋጊ ጀቶችን ብቻ የሚጠቀም አየር ኃይል ብቻ ነበረ የነበራት።
ጃንሆይና የኢትዮጵያ ወዳጅ የሚባሉት አነ አሜሪካ የሶማሊያን የዓመታት መጠነ ሰፊ የጦርነት ዝግጅት በሚገባ የሚያውቁ ቢሆኑም አንዳችም ያደረጉት ነገር አልነበረም። አዎ! ነገሩን በስለላ ከመከታተል ጀምሮ የአጸፋ ዝግጅት እስከ ማድረግ ኃላፊነት የነበረባቸው ንጉሡ ነበሩ፤ ይህን አላደረጉም።

የአጋጣሚ ነገር ሆኖ ንጉሥ ከሥልጣናቸው ተወግደው ደርግ ሥልጣን ሲይዝ፣ የዚያድ ባሬ መንግሥትም ‘ታላቋን ሶማሊያ መመስረቻ ጊዜው አሁን ነው’ ብሎ ወረራ ሲያካሂድ ኢትዮጵያ ከልጆቿ ወኔና ለአገራቸው ለመሰዋት ካላቸው ዝግጁነት ውጭ ሌላ አስተማማኝ ነገር አልነበራትም።

ጎረቤት ሶማሊያ በምሥራቅ ግንባር እስከ 700 ኪሎ ሜትሮችን፣ በደቡብ እስከ 300 ኪሎ ሜትሮችን ዘልቃ ለመግባት ችላ ነበረ። የደርግ መንግሥት በዚህ በወረራ ውስጥ ሆኖ ወደ 300 ሺሕ ተዋጊ የሰው ኃይል አሠልጥናኖ፣ ለምድር ጦሩና ለአየር ኃይል የሚሆኑ ዘመናዊ የጦር መሣሪያወችን እዚህና እዚያ ተሯሩጦ አሰባስቦ ወረራውን መቀልበሱም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

አሁንም ኢትዮጵያችንን ወዳጅም ሆነ አጋር ፍለጋ ወደ ሰሜን ይሁን ወደ ደቡብ፣ ወደ ምሥራቅ ይሁን ወደ ምዕራብ የሚወስዳት የመሪዎቿ ስሜትና ፍላጎት ሳይሆን ጥቅሟን ለማስከበርና ራሷን ላለማስደፈር የሚበጃት የየወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ ብቻ ነው። በኢኮኖሚ አውታሮች ውስጥ፣ በወታደራዊ መዋቅሮች ውስጥ፣ በምርጫ ቦርድና በሌሎችም የአገሪቱንና የሕዝቦቿን መጻዒ ዕድል በሚወስኑ ቦታዎች ሁሉ እጃቸውን እንዲከቱ የሚፈቀድላቸው የውጭ ኃይሎችና የውጭ ዜግነት የወሰዱ ግለሰቦች አካሄድ ከአገሪቱ ደኅንነትና ጥቅም አንጻር እየተቃኙ ሊገመገሙ ይገባል።

አሁን ደግሞ በአሜሪካ ዕርዳታ ግብጽን እንረታለን ብለን ማሰብ ወንዝን በተራራ ላይ ሽቅብ የማፍሰስ ያህል አዳጋች ሊሆንብን እንደሚችል ማሰብ ተገቢ ነው። እናም ለጥቅማችን የሚበጀንን እንጂ ለግል ስሜታችን የሚጥመንን መመኘት አይገባንም።
ግዛቸው አበበ / gizachewabe@gmail.com

ቅጽ 2 ቁጥር 77 ሚያዝያ 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here